>

‹‹ራስ ባጫ...!!!››  (አሳዬ ደርቤ ) 

‹‹ራስ ባጫ…!!!›› 

(አሳዬ ደርቤ ) 

ተስፋዬ ገብረ አብ ከሰው የሰማውን አንድ ገጽ አሉባልታ በእራሱ ፈጠራ አሳድጎ የታሪክ መጽሐፍ ሊያደርገው ይችላል፡፡
የነገር ጭራ ካስያዙት ጭራቁን እራሱ ይፈጥረዋል፡፡
ስለሆነም ተስፍሽ በግሉ ከወደደህ ከመጻጉነት ተራ አንስቶ ከእነ ጎሊያድ ተርታ ሊያሰልፍህ ይችላል፡፡ ከዞረብህ ደግሞ ሕዝብም ሆንክ ግለሰብ ግድ አይሰጠውም፡፡ ከወተት የነጣ ማንነት ኖረህም አልኖረህም በቀለም ፈንታ ጥላሸት የምትተፋ ብዕሩን አንስቶ ሊበክልህ ይችላል፡፡
ይህቺ የተስፋዬ ብዕር ታዲያ ከዘመተችባቸው ሰዎች አንዱ ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ቢሆኑም፣ እንዲያም ሆኖ ግን ደፋር ሰው መሆናቸውን መካድ አልተቻላትም፡፡ ጀግንነታውን በሚያንጸባርቅ መልኩ በአደባባይ ያደረጉትን ንግግር በጓዳ አሉባልታ ሊበክልባቸው ቢሞክርም ማንንም የማይፈሩ ደፋር ጄኔራል መሆናቸውን ግን መካድ አልቻለም፡፡
ለምሳሌ ያህል፡-
➛የመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ያሉ ቁልፍ ቁልፍ ተግባራት በትሕነግ ሰዎች ቁጥጥር ስር በዋሉበት ዘመን ወቅቱን መስለው ከመኖር ይልቅ ‹‹ባለኝ የጄኔራልነት ማዕረግ አገሬን ማገልገል ሲገባኝ ለይስሙላ አስቀምጣችሁ የኦሮሞን ሕዝብ ትኩሳት ማብረጃ አድርጋችሁኛል›› እያሉ ይሞግቱ ነበር፡፡
➛ሲቀጥል ደግሞ በዚያን ዘመን ማንም ሊናገረው የማይችለውን እውነት እንደ ወረደ በመዘርገፍ ‹‹ኢትዮጵያ በመላ ሀገሪቱ በመቶ ዓመት ያልገነባችውን መቀሌ በአሥር ዓመት ገንብታ ፋብሪካ በፋብሪካ ሆናለች፡፡ ይሄ ፍትሐዊ አይደለም›› ብለው ህውሓቶች በተሰበሰቡበት መድረክ ላይ እውነቱን የዘረገፉት እኒሁ ጄኔራል ነበሩ፡፡
.
➛በሌላ ጊዜ ደግሞ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በሚመራው መድረክ ላይ ‹‹ጄኔራል፣ ኮሎኔል እየተባልን በባዕዳን ቋንቋ ከምንጠራ የሀገራችንን የቀድሞ ባሕል መሠረት ባደረገ ማዕረግ ለምን አንጠራም?›› በሚል ጥያቄ የአጼውን ሥርዓት ናፋቂ መሆናቸውን በመግለጻቸው የትሕነጎች መንጋጋ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈም ‹‹ራስ ባጫ›› የሚል ቅጽል ሥም አውጥተውላቸው ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ ግን ተስፋዬ ጄኔራሉ በድፍረት የሚናገሯቸው ንግግሮች ከህውሓቶች ወጥመድ ውስጥ እንዳስገባቸው ገልጾ በጓዳ አሉባልታ ሊታደጋቸው ቢሞክርም…. በበኩሌ ግን በዚያን ዘመን ለሞትና ለስደት የሚዳርጉ አደገኛ ጥያቄዎችን በማንሳት ‹‹አገሬን ማገልገል አልቻልኩም፣ የመቀሌን ያህል ኢትዮጵያ አልተጠቀመችም፣ በሀገራችን ማዕረግ ለምን አንጠራም›› ብለው መናገራቸው አስደንቆኝ ነበር፡፡
ከረዥም ጊዜ በኋላ ታዲያ እኒህን ጄኔራል ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋቸው ከጄኔራል አበባው ጋር በቲቪ ቀርበው ሰፊ ትንታኔ ሲሰጡ ነበር፡፡ በማስከተል ደግሞ ሰሜን እዝ ላይ በደረሰው ጥቃት ዙሪያ ገለጻ ሲያደርጉ አየኋቸው፡፡ እናም በወቅቱ የአንደበታቸው ትባት፣ የፊታቸው አስፈሪነት፣ ለአገራቸው ያላቸው ተቆርቋሪነት እና የመሳሰሉትን ስታዘብ በባጫ አካል ውስጥ ማንን ባስተውል ጥሩ ነው?
‹‹መንጌን››
ባሁኑ ሰዓት ታዲያ ሌ/ጄ/ባጫ ደበሌ ከወንድማቸው ከሌ/ጄ አበባው ታደሰ ጋር ወደ ትግራይ ዘምተው ከሚወዱት ሠራዊትና ከተፈጠሩበት መክሊት ነጥሎ ያለ ጊዜያቸው ያሰናበታቸውን ከሃድ ቡድን ባላሰበው ጊዜ ድባቅ እየመቱት ይገኛሉ፡፡ ትሕነግ የሚኮራበትን ጦርና ምሽግ በቅጽበት ውስጥ እያወደሙ ‹‹ማይ ማይ እና ዋይ ዋይ›› ያስብሉት ይዘዋል፡፡
ስለሆነም  ‹‹የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች›› የሆኑት እኒህ ወንድማማቾች ገና ብዙ ተልዕኮ የሚጠብቃቸው እንደ መሆኑ መጠን ያለምንም ጭረት ከሃዲውን ቡድን ደምስሰው በሰላም ይመለሱ ዘንድ እመኛለሁ፡፡
Filed in: Amharic