>

ፓርላማው እና አራቱ የግምገማ ነጥቦች...!!! (ሙሉአለም ገብረመድህን)

ፓርላማው እና አራቱ የግምገማ ነጥቦች…!!!

ሙሉአለም ገብረመድህን

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ ብዙ የሚያስብል ቢሆንም አራት ጉዳዮች ላይ  ግላዊ እይታዎቼን መግለጽ ወድጃለሁ። አራቱም ጉዳዮች ከሙገሳ ይልቅ በትችት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።
፩.የትህነግ የሽብርና ቀውስ አከፋፋይነት ሚና ማቅለል?
ከለውጡ መባቻ ጀምሮ ትህነግ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን ለማፈን ብዙ ርቀት ተጉዟል። በእኛ ያልተመራች ኢትዮጵያ ትፈረካከስ ባዩ ትህነግ በዙሪያው የሰበሰባቸውን የፖለቲካ፣ ወታደራዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋምና ልሂቃኑን ሙሉ አቅም ተጠቅሟል። ይህ ጥረቱ ዐቢይ አህመድን ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት፣ ከስኬታማው የ 90 ቀናት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድሎች አላገደውም። “ራሴን እና ቤተሰቤን መጠበቅ የማልችልበት ሁኔታ ነበር” የሚለው የጠቅላይ ሚንስትሩ አገላለጽ ትህነግ በኢትዮጵያ ተቋማት ግንባታ ላይ የፈፀመውን ውድመት የሚያመላክት ነው። ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ የትግረኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች  መረዳጃ ዕድር እንጅ ለአገር ግንባታ እርሾ የሚሆኑ ተቋማትን አልፈጠረም ነበር። የደህንነት መስሪያ ቤቱ በአፍሪቃ አቻ የለሽ የሚል ሙገሳና ምስባክ ቢዘንብለትም ሙያው በተግባር ሲገለጥ ብልት ላይ ኮዳ ከማንጠልጠል የማይሻገር የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች የጭካኔ መለማመጃ ማህበር ነበር።
ይህ ኃይል ነው የፖለቲካ አመራሩን ተቆጣጥሮ (የሃሳብ ምንጭ ሆኖ) አገር ሲያምስ የነበረው። ከለውጡ ወዲህ 113 ግጭቶችና የሽብር ተግባራት ሲፈጠሩ ትህነግ ከጀርባ ስለመኖሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ይህን ሁሉ ጥፋት የፈፀመን ድርጅት በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ምክር ቤቱን ሳይጠይቁ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።በርግጥ አንድን የፖለቲካ ድርጅት፣ የፋይናንስ፣ የሚዲያ፣ …ወዘተ ተቋም በፓላማው በአሸባሪነት ለመፈረጅ  በሕግና የፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኩል ከአዋጁ አንፃር ጥናቶች መሰራት አለባቸው፣ ጥያቄው የሚቀርበውም በፓርላማ የመንግሥት ቋሚ ተጠሪ በሆነው ሰው በኩል ነው። ይህ የሕግ ፕሮሲጀር ትህነግ ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ ከፈጠራቸው 113 ግጭቶችና የሽብር ተግባራት አንፃር ቢሮክራሲው/ፕሮሲጀሩ ከፍላጎት ማጣት በመነጨ የተንዛዛ ሆኖ ይታያል።
በአጭሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር፦ ትህነግ በሽብርተኝነት የሚያስፈርጁት በቂ አገራዊና ቀጣናዊ ውድመቶችን ያደረሰ እንደሆነ ቢያውቅም የድርጅቱ ታሪክ ላይ የመጨከን ፍላጎት የለም። ቢያንስ ግለሰቦችን በስም ለይቶ አሸባሪ በሚል የመሰየም የፖለቲካ ስራ መስራት አልተፈለገም። ይህ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ ተከፍቶ የከረመውን የሽብር ጥቃት የማቅለል፣ ሰለባዎቹን ደመ ከልብ የማድረግ አዝማሚያ ነው። ይህ ለሀገር ልዖላዊነት እና ለመለዬው ክብር እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊት ያለማክበር ምልክት ነው።
. የትህነግ ‘የአልጋ ጀኔራሎች’ ክህደትና ገመና
ሌላኛው በጠቅላዪ ማብራሪያ የተሰጠው ከለውጡ በፊት ስለነበረው የመከላከያ ሰራዊት ተቋማዊ ይዞታ ነው። የመከላከያው ጉድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጠቀሷቸው አህዛዊ መረጃዎችም በላይ ነው። አገሩ ኢትዮጵያ ሆኖ ጠንካራ ተዋጊ አለን እንጅ እንደ ትህነግ ጀኔራሎች ጠባብ ብሄርተኝነት እና ማህበራዊ ስንፍናቸው ኢትዮጵያ በውጭ ኃይሎች በየሰዓቱ ተገዳ የምትደፈር ጋለሞታ በሆነች ነበር።
ጀኔራሎቹ የሰው ሚስት መቀማት፣ አርቲስት እያደኑ መተኛት፣ ሩቅ ምስራቅ ድረስ ቪያግራ ተሸክሞ መዝመት የተልዕኳቸው አካል አድርገውት ኑረዋል። በተለዬ ሁኔታ ከመለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ ባለው ጊዜ የነበረው ብልግና እንኳንስ ለነሱ እኛ እንደ ጠላት ለምናያቸውም ዜግነታችን መጋራታቸው አልፎም በመለዮቸው ኢትዮጵያን መወከላቸው ያሳፍረን ነበር። ውሽማ መነጣጠቅን እንደ ገድል በየባንኮኒው ጠረጴዛ ላይ የሚተርኩ ጉድ ፍጠረቶች ነበሩ። በቴሊቪዥን ያዬትን አርቲስት ለመተኛት የወሲብ ዕቅድ የሚያወጡ ቅንዝራሞች ነበሩ ሠራዊቱን የሚመሩት። አገሩ ኢትዮጵያ ሆነና ይሄው ለዚህ በቃን እንጅ እንደሰዎቹ ማህበራዊ ስንፍና ከፊት ብታሰልፋቸው ጦርነቱ በኮንደም ይሁንልን የሚሉ የውርደት ምልክቶች ነበሩ። የአልጋ ጀኔራሎች!
በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመከላከያ ጀኔራሎች የብሔር ተዋጽዖ ቁጥሩን እንጅ  ስብዕና እንዲነግሩን አይጠበቅም፤ አገሪቱን እንዴት ሲቀብሯት እንደኖሩ ግን መንገር ይጠበቅባቸው ነበር። አልሸባብን እዋጋለሁ ብሎ ሠላም አስከባሪ የሚልክ አመራር በጎን ለአልሸባብ የጦር መሳሪያ ሽያጭ/ዝውውር ከኢራን እስከ ሶማሊያ ቀይባህር ዳርቻ ድረስ ሲሰራ እንደነበር የሚያውቅ ያውቃል። የሰሜን ዕዝ ላይ እነሱ ጨክነው ምላጭ ሳቡ እንጅ ሠራዊቱን ሠላም አስከባሪ በሚል በማዝመት በጎን በሚሰሩት የጦር መሳሪያ ዝውውር ሲያስወጉት ነው የኖሩት። ይህ በትህነግ ኮር አመራር እንደተፈፀመ  መገለጽ ነበረበት። የአፍሪቃ ቀንድ የቀውስ ምንጭ ይህ ኃይል መሆኑ ለምክር ቤቱ ከማሳያዎች ጋር መቅረብ ነበረበት።
የጀኔራሎቹ ፕሮፋይል ግንባታ (በመሪ ደረጃ?)
አሁን ውጊያውን እየመሩ ስላሉት ጀኔራሎች Profile ግንባታው ከመጠን በላይ የጮኸ ይመስለኛል። በመሪ ደረጃ ተቀምጦ ጀኔራሎቹን እንዲህ መስቀሉ ነገ የማይጠበቅ ድርጊት ቢፈጠር ቀዳዳው ከወደየት ነው ለሚለው ጥያቄ የዛሬው መድረክ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል። በግማሽ ክፍለ ዘመኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ተላምዶ ወታደር ለመፈንቅለ መንግሥት የሚሆን ኮዝ ያገኘ ቀን ወደ ኋላ ይላል ብዬ ለማሰብ እቸገራለሁ። የ 2011ዱ የእብደት ዘመን አማራ ክልል ላይ የሆነው ነገር ሊያስተምረን ካልቻለ ለነገ ተጨማሪ ዕዳ እያመጣን ነው ማለት ነው። በመሪ ደረጃ የሚገለጽ ሁሉም ነገር በልኩ ሊሆን ይገባል።
በሌላ በኩል Situation Room ያዋጉትን ጀኔራሎች ያሞገሱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ዳንሻ ላይ ለሦስት ቀናት በከበባ ውስጥ ሆኖ ሲያዋጋ የሰነበተውን ኋላም የባዕከርና የሁመራን ፍልሚያ የመራውን ብርጋዴየር ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱን መዝለላቸው ባጋጣሚ ነው ካላልን በስተቀር ነገርየው ‘ነውር’ ነው። የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመስዋዕትነቱ ከሕዝብ ጋር የሚታረቅበት ጥሩ ዕድል ተፈጥሯል። እንደኔ ግምገማ በትህነግ የአልጋ ጀኔራሎች የአመራር ጉድለት ተፈጥሮ የነበረው የቀደመው ከሕዝብ ጋር መቃቃር ተሽሯል። ይህ ትልቅ ለተቋሙ ግንባታና የሀገረ መንግሥቱ ዘብ ለማድረግ ትልቅ አገራዊ ዕድል ነው። ይህን ዕድል ካፒታል አድርጎ መስራቱ ነው የሚያዋጣው። ያኔ ነበልባልም ግስላም ተቋም ተገንብቶ እናያለን። የተቋሙ ክብር የጀኔራሎቹም ይሆናል። ሰው ያልፋል ተቋሙ ግን በትውልድ ቅብብል ይቀጥላል።
“የድል ሽሚያ ውስጥ አንግባ” ሲባል ?
በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜው ስላልሆነ ብዙ ማለት አልፈልግም። ነገር ግን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ከከበባ ያወጣው የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ/የአርሶ አደሩ ጦር ነው።  እኛ ይህን ኃይል የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (The Amhara Popular Force) እንለዋለን። የዚህ ኃይል ገድልና ጀብዱ በቅጡ አልተተረከለትም። ገና ወደ ፊት በኪናዊ ዘርፎች ይተነተናል ትርክትም ይፈጠርለታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የመጨረሻዎቹ ዓርፍተ ነገሮች ውስጥ “የድል ሽሚያ ውስጥ አንግባ” ያሉት መልዕክታቸው ለማን እንደሆነ ግልጽ ነው።  አጠቃላይ የጦርነቱን ሂደት እንደተከታተለ ሰው ትርጉም ያለው መስዋዕትነት የከፈለው የአማራ ሕዝባዊ ኃይል ገድሉና ጀብዱ በሚናው ልክ መጻፍ፣ መተረክ አለበት ባይ ነኝ። ምናልባትም በትህነግ መቃብር ላይ የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች በማዕከላዊ  መንግሥቱ ስር ተጠቃለው Command and Control ሊበጅላቸው ይችላል። ይህን ለማየት ከአስር ወር በታች መታገስ በቂ ነው የመስከረም 2014 ሰው ይበለን።
የአደረጃጀት ለውጥ መጣም አልመጣም የአማራ ልዩ ኃይል ተጋድሎ ለታሪክ ሊቀመጥ ይገባል። ይህ የድል ሽሚያ ሳይሆን በሚናችን ልክ ገድላችን ለመጭው ትውልድ ማውረስ ነው። የዛሬ ፖለቲካ የነገ ታሪክ መሆኑን ኢትዮጵያ ደጋግማ አስተምራናለች። እንደ እውነቱ ከሆነ ይሄ ድል የትህነጎች ሆኖ ቢሆን ኑሮ በሚዲያ አይደለም በየቤታችን ከበሮ ይዘው ይመጡ ነበር:: ለማንኛውም ድል ብርቃችን ስላልሆነ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ምክር አልሞቀንም አልበረደንም።
Filed in: Amharic