>
5:21 pm - Monday July 21, 3513

ጥቂት ገጾች ከጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዳያሪ . . . ! (አሰፋ ሀይሉ)

ጥቂት ገጾች ከጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዳያሪ . . . !

አሰፋ ሀይሉ

 

The Diary of Colonel Mengistu Hailemariam! 
ይህ ምሥጢራዊ መዝገብ ጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የጊዜያዊ ወታደረራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበርነቱን ወንበር ሙሉ በሙሉ በእጃቸው እስኪጨብጡ ድረስ ያለፉትን ፈተና፣ የሥልጣን ጉዞና አይረሴ ታሪክ የያዘ ጥብቅ የግል ማስታወሻ ነው፡፡ የሚጀምረው ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ የጦር መኮንኖች በንጉሡ ሥልጣን ጉዳይ ለመወያየት በተሰበሰቡበት ዕለት ማለትም በረቡዕ ሚያዝያ 1966 ዓመተ ምህረት ሲሆን፣ የሚጠናቀቀው ደግሞ የኮሎኔል አጥናፉ አባተ ክስ በተሰማባት በዕለተ ቅዳሜ ህዳር 3 ቀን 1970 ዓ.ም. ላይ ነው! በማስታወሻው በቀውጢ ጊዜ የተከናወኑ ብዙ ቁምነገሮች ባጭር ባጭሩ ተካተዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
Ω ዕለተ ረቡዕ፤ ሚያዝያ 16 ቀን 1966 ዓ/ም፡-
‹‹ ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡ የቀኃሥ የበታች መኮንኖች የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም በአዲስ አበባ አራተኛ ክፍለጦር ተሰብስበዋል፡፡ ሻለቃ አጥናፉ አባተ ስብሰባውን እየመራ ነው፡፡ ከ3ኛ ክፍለጦር መንግስቱ ኃ/ማርያም ‹‹የተቀናበረና ስሜት ቀስቃሽ›› ንግግሩን አሠማ፤ ለሚቋቋመው የጋራ ኮሚቴም በምሥጢር ድምፅ ተሰጥቶ ሊቀመንበሩ አሁኑኑ ይመረጥ አለ፤ አጥናፉ አባተ ግን ይህን በፅኑ ተቃወመው፤ ተሰብሳቢው ግን የሻለቃ መንግስቱን ሃሳብ ተቀበለ፤ የምሥጢር ድምፁም ተሰጠ፤ መንግስቱ ኃ/ማርያምም የልቡ ሰምሮለት በሊቀመንበርነት ተመረጠ፤ አጥናፉ አባተ ደግሞ ምክትል፡፡
Ω ዕለተ ዓርብ፤ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ/ም፡-
‹‹ 120 (በትክክል 109) አባላት ያሉት ከየጦሩ የተውጣጣው የበታች ወታደሮች ኮሚቴ ‹‹ደርግ›› በሚል አጭር ስያሜ ተቋቋመ ተባለ፡፡
Ω ዕለተ ሐሙስ፤ መስከረም 02 ቀን 1967 ዓ/ም፡-
‹‹ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀኃሥ በደርግ ውሣኔ ከመንበራቸው ወርደው ዓይን በማትገባ ክሬም ‹ኩምቢ-ቮልስ› ተጭነው ወደ እስር ገቡ፡፡
Ω ዕለተ እሁድ፤ መስከረም 05 ቀን 1967 ዓ/ም፡-
‹‹ የወታደሮቹ ኮሚቴ ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ›› የሚል ኦፊሴላዊ ስያሜ በይፋ ተሠጠው፤ ደርጉ የመንግስትን ሥልጣነ-መንበር መረከቡም በይፋ ተነገረ፤ ቀኃሥ ከዙፋናቸው እንደወረዱና በውጭ ሃገር በህክምና ላይ የሚገኙት የቀኃሥ ልጅ ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን (አምኃ ሥላሴ) ርዕሰ-ብሔር ተደርገው መተካታቸው፤ እና ልዑሉ እስከሚመለሱ ሌተና ጄነራል አማን አንዶም (ብሔረ-ኤርትራው) በተጠባባቂ ርዕሰብሔርነት እና በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበርነት መሾማቸው በይፋ ተነገረ፡፡
Ω ዕለተ ቅዳሜ፤ ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ/ም፡-
‹‹ በእስር ላይ ከሚገኙት በንጉሠነገሥቱ ዘመን ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ከነበሩ 200 የፖለቲካ ታሳሪዎች ውስጥ ሁለቱን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች (ጠ/ሚ አክሊሉ ሃብተወልድን እና ጠ/ሚ እንዳልካቸው መኮንንን) ጨምሮ 29 የሲቪል እና 31 ወታደራዊ.. በድምሩ 60 የሃገሪቱ ባለሥልጣናት በደርግ አንድ በአንድ ሥማቸው እየተጠራ ድምፅ እየተሰጠባቸው ‹‹በሙሉ ድምፅ›› በጅምላ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ በትናንት ዕለት (ህዳር 13/1967 ዓ/ም) በተወሰነባቸው መሠረት ዕኩለ ሌሊት ላይ ተወስደው አብዮታዊ እርምጃ (የጅምላ ግድያ/ ‹‹ርሸና››) ተፈጸመባቸው፡፡
‹‹ በኤርትራ ጉዳይ እና በባለሥልጣናቱ ግድያ ሃሳቦች ላይ ከደርጉ አባላት ጋር ሽንጣቸውን ገትረው ሲሟገቱ የነበሩት (ለሁለት ወራት የደርጉ ሊቀመንበርና ተጠባባቂ ርዕሰ-ብሔር ሆነው የቆዩት) ሌተና ጄነራል አማን አንዶምም ተይዘው ከባለስልጣናቱ ጋር ተቀላቅለው እንዲገደሉ በማለት ደርጉ ቢወስንባቸውም ‹‹እጅ አልሰጥም ብለው›› በታዘዙባቸው ወታደሮች ‹‹አብዮታዊ እርምጃ ተወሰደባቸው›› (በበታቾቻቸው ተገደሉ!)፡፡ ይህ ዕለት ‹‹ጥቁሩ ቅዳሜ›› (‹‹Black Saturday›› ወይም ‹‹Bloody Saturday››) እየተባለም ይጠራል፡፡
Ω ዕለተ ሐሙስ፤ ህዳር 19 ቀን 1967 ዓ/ም፡-
‹‹ በአስመራ የጦር አዛዥ የነበሩት ብርጋዴየር ጄነራል ተፈሪ በንቲ የጊዜ/ወታ/አስ/ደርግ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው በይፋ ተነገረ፤ ሻለቃ መንግስቱ ኃ/ማርያም እና ሻለቃ አጥናፉ አባተ ደግሞ ሁለቱም የሌተና ኮሎኔልነት የማዕረግ ተሰጥቷቸው ሁለቱም የደርግ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መሾማቸው፤ የርዕሰብሔር ሥልጣን ማክተሙና የሃገሪቱም መንግስት የሚመራበት ርዕዮተ-ዓለም ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም እንደሆነ በይፋ ተነገረ፡፡
Ω ዕለተ ማክሰኞ፤ የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ/ም፡-
‹‹ የሃገሪቱ መሬቶች ከግለሰቦች ላይ ተወርሰው ለአርሶ አደሮች እንዲሰጥ የደነገገ አዲስ ባለ ‹‹ሥርነቀል ለውጥ››… የግለሰብ የመሬት ባለቤትነትን ያስቀረ ‹‹የመሬት ላራሹ አዋጅ›› በደርጉ በይፋ ታወጀ፤ ወዲያውም ሠላማዊ ሰልፍ ተጠራ፤ በርካታ ተማሪዎችም ሌ/ኮ መንግስቱ ኃይለማርያምን ነጥለው ‹‹የለውጡ ሃዋርያ›› እያሉ ባደባባይ ሲጠመጠሙባቸው ታዩ፡፡
Ω ዕለተ ቅዳሜ፤ ጥር 01 ቀን 1968 ዓ/ም፡-
‹‹ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ በአዲሳባ ከተገኙት የኡጋንዳው አምባገነን መሪ ከኢዲአሚን ዳዳ ጋር በመሆን… ብ/ጄ ተፈሪ በንቲ፣ ሌ/ኮ መንግስቱ ኃ/ማርያም እና ሌ/ኮ አጥናፉ አባተ የመታሰቢያ ፎቶ ተነሡ፡፡
Ω ዕለተ ሐሙስ፤ ጥር 26 ቀን 1969 ዓ/ም፡-
‹‹ የደርጉ ሊቀመንበር ብርጋዲዬር ጄነራል ተፈሪ በንቲ ከሌሎች 5 የደርግ አባላት ጋር ስብሰባ ተቀምጠዋል፤ በደርጉ ምክትል ሊቀመንበር በሌ/ኮ መንግስቱ ኃይለማርያም እና በታማኝ ታዛዡ በሌ/ኮ ዳንኤል አስፋው በህቡዕ የተጠራ የደርጉ ስብሰባ ደግሞ ከጎን እየተካሄደ ነው፡፡ የእነ መንግስቱ ተሰብሳቢዎች ቡድን የእነ ተፈሪን ተሰብሳቢዎች ከደርጉ ቀንደኛ ጠላት ከኢህአፓ ጋር የአብዮቱን አቅጣጫ ለመቀልበስ አሲረዋል የሚል አጀንዳ ይዞ ወደማያዳግም ውሳኔው እየገሠገሠ ነው፡፡ ውሣኔውም ተላለፈ፡፡ ውሳኔው በኮ/ል ዳንኤል በሚመሩ ድምፅ አልባ መሣሪያዎችን በታጠቁ ወታደሮች ተይዘው ሊቀመንበሩ ብ/ጄ ተፈሪ በንቲ እና አብረዋቸው የተሰበሰቡት ህዳጣን በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ነበር፡፡ አንደኛው የደርጉ ምክትል ሌ/ኮ አጥናፉ አባተ ለአብዮታዊ ጦር ባንዲራ ሊሸልሙ ሄደዋል በሚል በድምፅ አሠጣጥ አልተገኙም፡፡
‹‹ በውሳኔውም መሠረት እነ ተፈሪ በንቲ ከስብሰባቸው ላይ ተይዘው በአንድ የጓሮ ጭለማ ጋራዥ ታጎሩ፡፡ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስም በስህተት ከሟቾቹ ጋር ጋራዥ መግባታቸው እና ስህተቱ ሲታወቅ ደግሞ የደርጉ ሌ/ኮሎኔል ዳንኤል (‹እንደ መልአክ ድንገት ደርሶ›) ከሞት መንጋ መንጭቆ አወጣቸውም የሚል ወሬ ተሰማ፡፡ ታጋቾቹም ባሉበት በድምፅ-አልባ ተኩስ፣ በጥይት ተደብድበው ተገደሉ ተባለ፡፡
‹‹ አመሻሹ ላይ እነ ሌ/ኮ ዳንኤል ‹የኢህአፓ አባል ሆኗል› ያሉትን ሻለቃ ዮሐንስ ትኩን ከዚያው ግቢ ‹‹በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ተንቀሳቀሱ››፡፡ አሻፈረኝ ብሎ ቀደማቸው የሚል ወሬም ተናፈሰ፡፡ እንደተባለውም ሻለቃ ዮሐንስ ሌ/ኮ ዳንኤል አስፋውን ጨምሮ ብዙዎችን ሊይዙት ወይም ሊያጠፉት የተላኩበትን መለዮ ለባሾች ገደላቸው ተባለ፡፡ ከተኩሱ ልውውጥ መኃል የተገኘው… የቴኳንዶው ባለጥቁር ቀበቶ… የመዔሶኑ ዶ/ር ሰናይ ልኬም አብሮ ተታኩሶ አብሮ ተገዳደለ ተባለ፡፡ ሕይወቱ አለፈች፡፡ ገዳይ የተባለው ሻለቃ ዮሐንስ ትኩ እራሱ ደግሞ አብሮ ተገደለ ተባለ፡፡
‹‹ ማታ ላይ በ‹‹ሬዲዮ-ኢትዮጵያ›› ሌ/ኮ መንግስቱ ኃ/ማርያም ‹ከሟቹ ሊቀመንበር ከብ/ጄነራል ተፈሪ ባንቲ እጅ ከኢህአፓ ጋር የዶለቱትን ሴራ ቁልጭና ቅልብጭ አድርጎ የያዘ ባለ 47 ገፅ የ‹ተፈሪ-ኢህአፓ› ምስጢራዊ ዐቅድ ሰነድ በእጄ ገብቷል፤ አብዮቱም ከውስጥና ከውጪ አሻጥረኞች ተርፏል..!› የሚል ስሜታዊ የምሽት ዲስኩር አሰሙ፡፡ ዕለቱንም ራሳቸው ተፈሪ በንቲን በመተካት የደርጉ ጊዜያዊ ሊቀመንበር ተደርገው መመረጣቸውን በይፋ አወጁ፡፡
Ω ዕለተ ቅዳሜ፤ ህዳር 03 ቀን 1970 ዓ/ም፡-
‹‹ የደርግ ምክትል ሊቀመንበርነታቸውን እንደያዙ ሌ/ኮ መንግስቱ ቢሮ በገቡ ቁጥር ትጥቅ እየፈቱ በጥብቅ መፈተሹ፣ የሥልጣን ሽኩቻው፣ መላቅጥ የሌለው ትርምስና በየቀኑ ‹‹የሚፈጠረው›› የጠላቱ ብዛት፣ አፈናና ግድያው፣ በተለይ በተለይ ይሄ ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም የሚሉት ርዕዮተ-ዓለም… ብቻ ሁሉ ነገር ‹‹ምነው ያኔ በቀረብኝ!›› አስብሎ ያስመረራቸው ሌ/ኮ አጥናፉ አባተ፤ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገው የህዝብ ሚሊሺያ ጦር ዋና አደራጅ መኮንን በመሆን በወታደራዊ ግልጋሎት ከደርግ ቢሮ ራሳቸውን ገሸሽ ካደረጉ ዘጠኝ ወር ሞልቷቸዋል፡፡ ግን ውስጥ ውስጡን የኮሚኒስቱን አብዮት ለመቀልበስ መፈንቅለ-መንግስት ለማካሄድ እያሴሩ ነው በሚል በጥርጣሬ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዚህች ዕለት ደርጉ ሌ/ኮ መንግስቱ ኃይለማርያም ባልተገኙበት ስለ ሌ/ኮ አጥናፉ ዕጣ ፈንታ የሚወስንበት ስብሰባ አካሄደ፡፡
‹‹ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከልም… ከስራ በኋላ ከአድኃሪያንና ባለከፍተኛ ማዕረግ ወታደሮች ጋር ይታያሉ፤ በመስክ ጉዞ ወቅት ለጭሰኛው ትምክህት አሳይተዋል፤ ሀገሪቱ ለሶሻሊዝም ግንባታ ርብርብ እያደረገች በምትገኝበት ቀውጢ ወቅት ላይ እሳቸው ግን በተደጋጋሚ በስብሰባዎች ላይ ‹‹ከርዕዮተ-ዓለም ይልቅ የሃገር ጥቅም ይቅደም›› በማለት የሶሻሊዝምን ርዕዮተዓለም የሚፃረር ዝንባሌያቸውን አንፀባርቀዋል፤.. ‹‹ከኢምፔሪያሊስት ተላላኪዎች›› (‹‹ከሲአይኤ ወኪሎች››) ጋር ታይተዋል፤ ወዘተ ወዘተ. የሚሉ የበዙት ነጥቦች በአሉ አሉ አሉባልታዎች የተሞላ ባለ6 ገፅ አቋማቸውን የሚኮንን ሰነድ ቀረበ፡፡ ሌ/ኮ አጥናፉ ፈጽመዋቸዋል የተባሉ 12 ፀረ-አብዮት ወንጀሎች፣ እና አንጸባርቀዋቸዋል የተባሉ 5 የአድኃሪ አቋሞች በዝርዝር ሃተታ መልክ ቀረበባቸው፡፡
‹‹ በመጨረሻም በእነዚህ 17 ወንጀሎችም ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ደርጉ በምክትል ሊቀመንበሩ በሌ/ኮ አጥናፉ አባተ ላይ አብዮታዊ እርምጃ ይወሰድባቸው (ይገደሉ!) ብሎ በመወሰን በታዛዥ ወታደሮች በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ሆነ፡፡ ሌ/ኮ መንግስቱ ኃይለማርያም ግን በስብሰባው አልተገኙም፡፡ ድምፅም አልሰጡምም፡፡ እንዲያውም ቀደም ብለው አጥናፉን ለማዳን ተሟግተውላቸውም ነበር ተባለ፡፡ ብዙዎች የቅርብ ታዛቢዎች እንደሚሉት – ከዚህች የቀዳሚት ሰንበት ዕለት ጀምሮ – ሌ/ኮ መንግስቱ ኃይለማርያም – ከንጉሠነገሥቱ ከራሳቸው አንስቶ በሥልጣን መንገዳቸው ሊመጡ የሚችሉባቸውን ሁሉንም ከፍተኛ የደርግ ጓዶቻቸውን ‹ሲያስወግዱ› ቆይተው – እነሆ በመጨረሻ ደግሞ – የቀራቸውን አንድ የቅርብ ጓደኛቸውን – ሌ/ኮ አጥናፉ አባተን – በደርጉ ውሳኔ አማካይነት ‹የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድበት በማስደረግ› – ከዚህች ቀን ጀምሮ – ያለ አንድም የሥልጣን ተቀናቃኝ – ብቸኛው ባለሙሉ ሥልጣን የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርጉ ሊቀመንበር መሆናቸውን አረጋገጠዋል፡፡
Ω መደምደሚያ፡-
‹‹ በእውነት ሌ/ኮ መንግስቱ ኃይለማርያም ብዙ ውጣውረድ አሣልፈዋል፡፡ ‹ትግላችን መራራ፤ ግባችን ሩቅ› ያሉበትንም ምክንያት ከልብ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሌተና ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ስለ ሥልጣን ጉዟቸው እና በዚያ ሁሉ ውስጥ በህይወት ስለመትረፋቸው በመደመም… እንዴት እንደተረፉ በአንድ ወቅት ለጠየቃቸው ጋዜጠኛ… በራሳቸው አንደበት እንዲህ ብለው መልሰውለታል፡-
‹‹ለምሣ ያሰቡንን፤ ለቁርስ እየበላን፤ እዚህ ደርሰናል!››፤
‹‹ የገዛ ጓዶቻቸውን እንዴት እርምጃ ሲወሰድባቸው ዓይናቸው እያየ ዝም ብለው እንደመተለከቱ ሲጠየቁ ደግሞ ከሌሎች የዘመናቸው አብዮተኞች በተዋሷት አባባል እንዲህ ነበር ያሉት፡-
‹‹ምን ማድረግ ይቻላል? በየትኛውም የዓለም ጫፍ አንዳንዴ ልታስቆመው የማትችለው ሂደት አለ! አብዮት ልጆቿን ትበላለች! ማለት የምችለው ያንን ነው!›› ነበር ያሉት ቆራጡ አብዮተኛ መሪ፤ ሌተና ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፡፡››
አይ አብዮት…! አብዮት ምንም አይቀራትም በቃ! አብዮት… ድመት ናት! የገዛ ልጆቿን ቅርጥፍ አድርጋ የምትበላ ድመት! – ከፍቅሯ የተነሣ ነው ግን!! መልካም ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic