>

የድመትን ያህል ቁመና ሳይዙ የአንበሳን ያህል ማጓራት ትልቅነት አይደለም...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የድመትን ያህል ቁመና ሳይዙ የአንበሳን ያህል ማጓራት ትልቅነት አይደለም…!!!

አሰፋ ሀይሉ

ፖለቲካ ፓርቲ መሆን ማለት የወሬ ጋጋታ ማዝነብ፣ ገዢውን ኃይል በአፈቀላጤነት መካደም፣ ወይም ድንፋታና ቀረርቶ ማሰማት አይደለም! ከዚህ በጣም ይለያል! አሁን አብይ (ግራኝ) አህመድ ውል ብሎት የአብንን መሪዎች ጠራርጎ ወደለመደውና ወደለመዱት ከርቸሌ ቢያጉራቸውስ? ያንን የሚቀለብስ ህዝባዊ ኃይል አላቸው ወይ? ወይስ ወሬ ማውራትብቻ – የወረቀት ላይ ነብር ብቻ – ናቸው? ፖለቲካ ማለት ገዢውን የሚገዳደር ተክለሰውነት ይዞ መገኘት፣ ገዢውን ማስከንዳት፣ ገዢውን ማንበርከክና የሀገር መሪነትን መረከብ ማለት ነው። ወይም ለዚህ መሥራት ማለት ነው። የድመትን ያህል ቁመና ሳይዙ የአንበሳን ያህል ማጓራት ትልቅነት አይደለም። ከንቱ ነው። መጀመሪያ መሆን ይቀድማል። ሰው ሳይቀድመው መጮህ ለአውራ ዶሮም አልጠቀመው። ያን ግለሰቦችም ያደርጉታል። የፓርቲ ትልቅነት አኩኩሉው አይደለም። ሕዝብን ይዞ አይደፈሬ ሆኖ መገኘት ነው። ትልቅ ሆኖ በተገኙት ልክ ያወሩትን ሆኖ በመገኘት እኖጂ፣ ሚጢጢ ተሆኖ ትልቅ ስለተናገሩ ትልቅ አይኮንም። ትልቅ መስሎ ማናፋት ኋላ ላይ ግራኙ ጠራርጎ ሲያስር ማጣፊያው ያጥርና ያን ትልቅ ዲስኩር አምኖ የተከተለውን ሕዝብ አንገት ያስደፋል። መከበርን በከንፈር አንፈልግ። ትልቅነትን ቀደም ቀደም በማለት ለማግኘት አንሻ።  አለመለፍለፍ፣ ሆኖ መገኘት፣ ሲነካ በልበሙሉነት መነሳት ነው የሕዝባችን ባህል። እኛ ተቃራኒውን እየሆንን ሕዝብን በወሬ መምራት አንችልም። ይህ የክፋትም የቅናትም የቅዋሜም አስተያየት አይደለም። ወንድማዊ ምክር እና ሀቅ ብቻ ነው። ፈጣሪ ልቦናውን ይስጠን። ከመቅለብለብ ይሰውረን። ሆነን ለመገኘት፣ ሆነን ለመገኘት በቻልነው ልክ ቆመን ለመታየት ያብቃን። ብልህነትን ይግለፅልን። ጥበቡን ያመላክተን። ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን።

 

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር።

Filed in: Amharic