>
6:58 pm - Tuesday June 6, 2023

የዘር ማጥፋቱ ወንጀል ሴራ ከየት እስከ የት የሚዘረጋ ሰንሰለት እንዳለው ያመላከተ እውነታ...!!! (መስከረም አበራ)

የዘር ማጥፋቱ ወንጀል ሴራ ከየት እስከ የት የሚዘረጋ ሰንሰለት እንዳለው ያመላከተ እውነታ…!!!

መስከረም አበራ

እንቆቅልሹ መተከል?
የመተከል ጉዳይ መነሳት ከጀመረ፣ ዓመታት አልፎታል። ላነሳው አስብና ቁስሉ በጣም ስለሚያመኝ እተወዋለሁ። ብዙ ዘግናኝ ድርጊቶችን አይተናል። ከሰማናቸው ያልሰማናቸው ይበልጣሉ። ወደ 60 ሺ የሚጠጉ አገዎችና አማራዎች በማንነታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ወድቀዋል። ከቀስትና ስናይፐር የተረፉት፣ በበሽታና በረሃብ ማለቃቸው አይቀርም። ስለ ማይካድራና በሱዳን ስላሉ የኢትዮጵያ ስደተኞች በየቀኑ የሚያደርቁን ሚዲያዎች ስለ መተከል ፀጥ ብለዋል (ከአማራ ቲቪ በስተቀር)
በየከተሞች ከሚደረግላቸው ድጋፍ ውጭ፣ የፌደራል መንግስቱ ድጋፍ ያደረገ አይመስለኝም። ወይም አልሰማሁም።
 ከሳምንታት በፊት ጉዳዩን የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት “የአንድ ሳምንት ጊዜ” የሚል ቀጭን ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ አውቃለሁ። አቶ ደመቀም ለአሻድሌ ቀጠን ያለች ማስጠንቀቂያ እንደሰጡ ጭምር።
 ያው “ጌታዋን የተማመነች በግ…” እንዲሉ አሻድሌ የሚሉት ሰው ጣጣው አይደለም። ኬኩን እየዞረ እየቆረሰ ነው። ባለፈው የመተከል መዋቅር ሙሉ በሙሉ Hijacked ሆኗል ብዬ ነበር። የሰሜኑ ጁንታ ኃይል እየሸሸ ሲሄድ፣ ፊቱን ወደ ደቡብ አዙሮ የስልጣን ኮርቻውን ለማሰንበት “አቤት ምን ልታዘዝ” እያለ ነው። ጆሮ የሰጠው የለም እንጂ፣ አልፎ አልፎ  አክሰንታቸውን ሸምድዶ እንደወረደ መናገር ጀምሮ ነበር።
(ወደዚህ ጉዳይ በዝርዝር አልገባም። ጊዜው ሲደርስ እንመጣበታለን። በንቃት መከታተል ግን ይጠይቃል)
የአማራ ፖሊስ ኮሚሽነር፣ ፉከራ የሚመስል ነገር ዛሬ በሚዲያ ወጠው ተናግረዋል። “በዓለም ላይ እንደ መተከል ዘግናኝ ነገር የተፈፀመበት ቦታ የለም” ብለዋል። አውቃለሁ፣ የአማራ ልዩ ኃይል አካባቢውን ለማፅዳት ቀናት አይደለም፣ ረፋድ አይፈጅበትም።
ነገር ግን እስከመቼ ነው ንፁሃን የሚረግፉት?
ስንት ነፍሰጡሮች፣ ህፃናት እስኪሞቱ ነው የሚጠበቀው? ወደ ትግራይ ተወርውሮ እንዲገባ የተደረገው ልዩ ኃይል፣ ላለፉት አምስት ወራት “ወደ መተከል አትገባም” ተብሎ ድንበር ላይ የሚታመሰው እስከመቼ ነው? መልስ አላችሁ?
የመተከል ጉዳይ፣ አንደ ወልቃይትና ራያ ተመሳሳይ የማንነት ጥያቄ ያለበት ቀጠና ነው። የመተከል ግድያዎችና ማፈናቀሎች በጁንታው ይሳበቡ እንጂ፣ ክፍል ሁለት የሪፐብሊክ ካርታ ከጀርባው አለመኖሩን ስንት ሰው ጠይቆ ይሆን? የህውሃትን እንቆቅልሽ የፈታ ህዝብ፣ ለዚች እንቆቅልሽ የህፃን አፍ በቂ ነው።  አንዳንዴ “በቃ” ማለት ጥሩ ነው። ልክ እንደ ህውሃት። የሚሻለው ነጭ ነጩን በአደባባይ ተነጋግሮ ፣ከመሸበት ማደር ነው።
በዓለም ላይ የተደረጉ አሰቃቂና ተራዛሚ ዘር ተኮር መተራረዶች በሙሉ በመንግስት መዋቅር የተመሩ ወይም የተደገፉ ናቸው። በመንግስት መዋቅር የማይደገፍ ዘር የማጥፋት እንቅስቃሴ ገቢራዊ አይሆንም።ምክንያቱም ከመንግስት የሚበልጥ ሃይል ያለው አካል ስለሌለ የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ የሚሞክረው አካል ብዙ ርቀት ሳይሄድ በመንግስት ጠንካራ ክንድ ተመቶ  በአጭር ይቀራል።
 ይህ የሚሆነው የመንግስት መዋቅር በዘር ማጥፋቱ ላይ ፍላጎት ከሌለው ነው።መንግስት በዘር ማጥፋቱ ላይ ፍላጎት ካለው ግን ወይ እንደ የጀርመኑ የናዚ መንግስት በግልፅ ዘር ማጥፋቱን ይመራል፨ ወይም እንደ ሩዋንዳው መንግስት “ነገሩ ተራ ግጭት ነው፣የእርስ በእርስ ጦርነቱ አካል ነው”  እያለ እያጭበረበረ ዘር ማጥፋቱን ያሳልጣል፨ አለያም በዝምታ ወይም እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ዘር ማጥፋቱን በስሙ እንኳን ሳይጠራ  “ነገሩን ለማስቆም እየሰራሁ ነው” እያለ በክቡሩ የሰው ልጅ ደም ያፌዛል፤ እንደ ቤኒሻንጉል ያለውን ዘር ማጥፋት የሚጧጧፍበትን ክልል የሚመራውን  ሰውዬ የክብር እንግዳ አድርጎ ኬክ ያስቆርሳል።
 ይህ የክብር እንግዳ ግብዣ  የዘር ማጥፋቱ ወንጀል ሴራ ከየት እስከ የት የሚዘረጋ ሰንሰለት እንዳለው ያስመሰክራል! ይሄ የሰው ገላ በመጥረቢያ የሚቆረስበትን  ክልል የሚመራ ሰውዬ ከስልጣኑ ወርዶ በህግ መጠየቅ ሲገባው ለብሄረሰቦች ቀን በዓል የክብር እንግዳ ተደርጎ ሲቀርብ ሃገሬ ሩዋንዳን ሩዋንዳን ሸተተችኝ!!!!  የንፁሃንን ደም ማፍሰስ እንደ ሰናይ ሥራ ኮራ ተብሎ በሬዲዮ የተሰበከባትን ሩዋንዳን…..
 
እየነካካችሁ አክቲቪስት አታድርጉን… ዝም እንዳንል የወገን ህመም ይጠዘጥዘናል። እንቅልፍ ይነሳናል። ለጌዶ የጮኸ ህዝብ፣ ለአገውና ለአማራ ሲጮህ ዘረኛ ይባላል። “ለወንድሙ፣ ለእናቱ፣ ለአባቱ ጥቃት መጮህ ዘረኛ ካሰኘ” አንክት! እንዲያውም ንግግሩ በሌላ ነበር። እሱን አመስግኑ።
Filed in: Amharic