>

የአማራ ልዩ-ኃይል Vs የትግራይ ልዩ-ኃይል!! (ኤርሚያስ ለገሰ)

የአማራ ልዩ-ኃይል Vs የትግራይ ልዩ-ኃይል!!

ኤርሚያስ ለገሰ

ሰሞኑን የአማራ ልዩ-ኃይልና ሚሊሻ ለአመታት በሜካናይዝድ ክፍለ-ጦርና ብርጌድ ሲደራጅ የነበረውን የትግራይ ልዩ-ኃይልና ሚሊሻ የደቀነውን አገራዊ የህልውና አደጋ ማስቀረት ችሏል። ለዚህ ውለታው ክብርና ምስጋና ይገባዋል።
ለሁሉም ግልጽ እንደሆነው ከዘጠኝ ወር በፊት የኢትዮ-360 ባልደረቦች ይፋ እንዳደረግነው ህውሃት መጀመሪያ አካባቢ የሃይል አሰላለፍ ስትሰራ በመጀመሪያው ረድፍ የስጋት ምንጭ አድርጋ ያስቀመጠችው የአማራ ልዩ-ሃይልን ነበር። ሆኖም ከሰኔው ውስጥ የአማራ ክልል አመራሮች ግድያና የልዩ-ሃይል ስልጠና ከሁለት ዙር መቋረጥ ጋር ተያይዞ የአማራ ልዩ-ሃይልን ከዋነኛ የስጋት ምንጭነት አስወጥታው ነበር። በመሰረቱ ይሄ የትግራይ ነፃ አውጭ ግምገማ ስህተት እንደነበር የአማራ ልዩ-ሃይል በተግባር በማሳየት ኢትዮጵያውያንን አኩርቷል። ጀግንነቱንም በጦር አውድማ አስመስክሯል።
ይሄ የአማራ ልዩ-ሃይልና ሚሊሻ ዘንድ ተሻጋሪና አንፀባራቂ ድል እንዴት ሊመዘገብ ቻለ የሚለውን ደጋግሞ መጠየቅና ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል። ሩቅ ሳይኬድ ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጡን የቀድሞው የልዩ-ኃይሉ አዛዥ ብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ ናቸው። ጄኔራሉ በቅርብ ግዜ ከአባይ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሁለት ዙር ብቻ ተመልምሎ የሰለጠነው የአማራ ልዩ-ሃይልና ሚሊሻ የድል ምክንያት አስረድተዋል። ወደ ሚሊዬን ይጠጋል ተብሎ የተነገረለትን የትግራይ ጦር ድባቅ የመታበትን አመክንዬዎች አብራርተዋል።
ለጊዜው የማስታውሳቸው የሚከተሉት ናቸው፣
፩: የአማራ ልዩ-ሃይል ልምዱና ብቃቱ በተግባር የተፈተሸ ነው። በሌላ አነጋገር ልዩ-ሃይሉ ሲዋቀር በምልመላው እንዲሳተፉ የተደረጉት ለአመታት በትጥቅ ትግሉ ወቅት በኢህዴን ስር ታቅፈው የታገሉና ከሰራዊቱ ውስጥ በሴራና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ የተቀነሱ ብቃት ያላቸው ተዋጊዎች ናቸው። ለወታደር ዋነኛው የብቃት መለኪያው በጦርነት በመሳተፉ የሚያገኝው ልምድ ነው። በተቃራኒው የትግራይ ልዩ-ሃይል ልምድ የሌለው በጦር ሜዳ ያልተሳተፉ ወጣቶች ያሉበት ነው።
     ( የእናንተን ባላውቅም ከብቃት አንፃር የቁጥር መለኪያ ይቀመጥለት ቢባል እኔ ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ አንድ የአማራ ልዩ-ሃይል ለ25 የትግራይ ልዩ-ሃይል እመድባለሁ።)
፪: የአማራ ልዩ-ሃይል ከወታደራዊ ልምዱና ብቃቱ በተጨማሪ የሰለጠነበት ወታደራዊና ፖለቲካዊ የስልጠና ማንዋሎች(ዶክትሪን) አማራን መታደግና አገሩ ኢትዮጵያን መጠበቅ መሰረት ያደረገ ነው። የሰራዊቱ ተልዕኮም በግልፅ ነጥሮ የተቀመጠ ነበር። በነገራችን ላይ ይህን አገላለጥ ቃል በቃል ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ደግሞታል። በሌላ በኩል የትግራይ ልዩ-ኃይል ተልዕኮው የአንድ ፓለቲካዊ ሽንፈት አጋጥሞት መቀሌ የሸሸ “የበሰበሰ አስኳል” የትርምስ መሳሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ነው። የሰለጠነበት ማንዋልም ከላይ የተጠቀሰውን አላማ ለማሳካት ዘመን ያለፈበት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርሆዎችና እሳቤዎችን ማዕከል ያደረገ ነው። አሰልጣኞቹም ትላንት ህዝባቸውን ዞር ብለው ያላዩ ዘረኞች፣ ዘራፊዎች፣ ተስፋ የቆረጡ ሱሰኞችና ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች ናቸው።
     (የእናንተን ባላውቅም ከተልዕኮ ግልፀኝነትና የስልጠና ዶክትሪን አንፃር በዓሃዝ መለኪያ አስቀምጥ ብባል እኔ ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ አንድ የአማራ ልዩ-ሃይል ለ50 የትግራይ ልዩ-ሃይል እመድባለሁ።)
፫: የአማራ ልዩ ሃይል ሌሎቹን የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የሚመለከተው እንደ ስትራቴጂክ አሊያንስ እንጂ እንደ ተፃራሪ ኅይል አይደለም። በዚህም ምክንያት በቀላሉና በአጭር ጊዜ ከፌዴራል ፀጥታ ኃይሎች ጋር ተዋህዶና ተቀናጅቶ ለመስራት አልተቸገረም። በብርሃን ፍጥነት ሲነርጃይዝ አድርጐ ምትሐታዊ ድል የተጐናፀፈው በዚህ ምክንያት ነው። በተቃራኒው የትግራይ ልዩ-ሃይል የፌዴራል ፀጥታ ኃይሎችን የሚመለከተው እንደ ተፎካካሪ ባላንጣና ጠላት ነው። በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ሲጠብቀው የነበረውን የአገር መከላከያ ሰራዊት እንደ ቀበሮ አድብቶ ጨፈጨፈ። ጠላትነቱን በአደባባይ አስመሰከረ።
     ( የእናንተን ባላውቅም ከፌዴራል የፀጥታ ሃይሎች ጋር ያለን ግንኙነት እና መቀናጆ በቁጥር ይሰላ ቢባል እኔ ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ አንድ የአማራ ልዩ-ኃይል ለ25 የትግራይ ልዩ ሃይል እመድባለሁ።)
ማስታወሻ:- በቁጥር ሁለት መጣጥፌ የአማራ ልዩ-ኃይልን ከኦሮሚያ ልዩ-ኃይል ጋር አነፃፅራለሁ። በቁጥር ሶስት  የወደፊቱን በመተንበይ (አይፈርስም በሚል እና የወላይታ ክልል ይመሰረታል በሚል ታሳቢ ተወስዶ) የአማራ ልዩ-ሃይልና የወላይታ ልዩ-ሀይል አነፃፅራለሁ( ከወዲሁ ወደ ትክክል የተጠጋ ግምቴን ለማስቀመጥ ከላይ በተቀመጡት መመዘኛዎች የአማራ እና የወላይታ ልዩ-ኃይል እኩል ሚዛን ይመዝናሉ።)
Filed in: Amharic