እርግጥ ነው፤ ብዙ ውጊያዎች ከፊታችን አሉ!!!
ዶር በድሉ ዋቅጅራ
.
የህውሀትን አሸባሪ መሪዎች ከብቦ የሚገኘው ክፍለ ጦር አዛዥ፣ ‹‹ጦርነቱ አልቋል፤ የሚቀረው ትንንሽ ውጊያ ነው፤›› ብለዋል፤ ጦርነት ፖለቲካዊ መልክም እንዳለው በመግለጽ፡፡ እርግጥ ነው፤ ከህወሀት ጋር የሚደረገው ጦርነት አልቋል፡፡ ቢበዛ እንደ ሽፍታ ሊዋጋ እንጂ፣ ህዝብን እንደሚወክል መንግስት ጦርነት ሊገጥም አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ በመቃብሩም ላይ ሆነን ከመቃብር በላይ ትቷቸው ከሄደው የጥፋት ቡቃያዎች ጋር ከባድ (ምናልባትም ከህወሀት ጋር ካደረግነው ጦርነት የበለጠ ከባድና አስቸጋሪ) ውጊያ ይጠብቀናል፤ ቡቃያው አብቦ መርዝ እንዲያፈራ መፈቀድ አይኖርብንም፡፡
.
ከበርካታ ውጊያዎቻችን መካከል፣ የሚከተሉት ሁለቱ አንገብጋቢዎች ናቸው፡፡
.
· ብሄርንና ቋንቋን መሰረት ካደረገው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጋር ውጊያ ይጠብቀናል፡፡ ወያኔ ብሄርና ቋንቋ ብቸኛው የፌደራሊዝም ስርአት መንገድ እንደሆነ ሲሰብክ የኖረው እውን አምኖበት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል ለእድሜ ይፍታህ ስልጣኑ ሲያመቻች ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ከልማቱ ጥፋቱ እንደሚጎላ፣ ኖረን አይተነዋል፤ የብዙ ሀገራት ተሞክሮም ነው፡፡ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት አዎንታዊ የፌደራል ስርአት መቀየስ ያሻል፡፡ በመሆኑም ዜጎች ላይ ያደረሰው በህይወት የመኖር፣ ሰርቶ የማደር መብት ጥሰት፣ ሀገሪቱ ላይ ያሰፈነው የእርስ በርስ ግጭት የኖርነው ነውና የጎሳ ፖለቲካ በህግ ሊታገድ ያገባል፡፡
.
· ኢትዮጵያን በመከላከያ ሰራዊታችን ብቻ የምትጠበቅ ሀገር የማድረግ ውጊያ ይጠብቀናል፡፡ ዛሬ ክልሎች አንድን ትንሽ ሉአላዊ ሀገር የሚገዳደር ሰራዊት (ልዩ ሀይል) አደራጅተዋል፡፡ የጎሳ ፖለቲካው በክልሎች መካከል በፈጠረው የወሰን ሽኮቻ፣ የማንነት ስርቆት፣ የእርስ በርስ ጠላትነት፣ ወዘተ. በመሳሰሉ ስጋቶች ልዩ ሀይል ማደራጀታቸው አይደንቅም፤ አስፈላጊም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በክልሎችን መካከል ያለውን አለመግባባት በህግ በመፍታትና በክልሎች መካከል ወደ ግጭት የሚያመራ ችግር ቢፈጠር እንኳን፣ ጉዳዩን በዋናነት የፌደራሉ መንግስት ሀላፊነት በማድረግ፤ ክልሎች ለውስጥ ደህንነታቸው ጥበቃ ጠንካራ የፖሊስ ሀይል እንዲያደራጁ በማድረግ፣ አሁን ያለው ልዩ ሀይል በሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ እንዲጠቃለል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሀገሪቱን በሁለት መንገድ ይጠቅማል፤ ልዩ ሀይል የሰለጠነ በመሆኑ የመከላከያውን የስልጠና ወጪ ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪም የአዲስ ምልምሎችን እጥረት ይታደጋል (እዚህ ላይ በቀደም ጠ/ሚንስትሩ ለፓርላማ ባደረጉት ገለጻ የአዲስ ተመልማይ እጦት እንደገጠማቸው የተናገሩትን ልብ ይሏል)፡