የድህረ ህወሓቱ ህወሓት ….!!!
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ከርሴሞ
“ህወሓት እንደ ድርጅት ሞተ፤ ተቀበረ” ከሚሉ ወዳጆቼ ጋር አልስማማም። ህወሓት ለዓመታት አደራጅቶ ያስቀመጣቸው መዋቅሮች በመንግስት ውስጥና ከመንግስት ውጭ ከዚያም አልፎ በምዕራባዊያን አገራት ተቋማትም ውስጥ ጭምር እንዳሉት እገምታለሁ። ጠላትን አቅልሎ ማየት ምን ያህል ለጉዳት እንደሚዳርግ ያየነው ይመስለኛል። የሚሻለው ለ worst case scenario መዘጋጀት ነው።
እንደኔ ግምት በአደባባይ የምናውቃቸው የህወሓት መሪዎች ቢያዙ ወይም አመራር መስጠት በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ቢደረጉ እንኳን የህወሓት ጉዳይ የተዘጋ አጀንዳ አይሆንም። ስሙን ይዞ አልያም ቀይሮ መቀጠሉ አይቀርም። ከዛሬው ህወሓት፣ ሳልሳይ ወያኔ፣ ባይቶና … ወዘተ የተውጣጡ ወጣት መሪዎች አመራሩን ይይዙና በአዲስ መልክ – Lord’s Resistance Army, ISIS እና Boko Haramን በሚያስንቅ ጭካኔ – የጅምላ ሽብር ጥቃት ወደሚፈጽም በዓይነቱ ለየት ወደአለ የሽብር ድርጅትነት ይቀየራል። እርግጥ ነው የድሮው ዓይነት ሽምቅ ውጊያ አያዋጣም፤ እነሱም ይህንን የሚያውቁ ይመስለኛል። በተበታተኑ ጥቃቅን አሀዶች አማካይነት አውዳሚ የሽብር ጥቃቶች ሊያካሄዱ እንደሚችሉ እገምታለሁ። የሽምቅ ውጊያ እና ሽብርተኝነት ተዛማጅ ቢሆኑም አንድ አለመሆናቸውን ማጤን ይጠቅማል።
ከተሞች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የመሠረተ ልማት ተቋማት የዚህ ድርጅት የጥቃት ዒላማዎች ይሆናሉ። የምዕራባዊያን እና የህወሓት ፍቅር ነፋስ እስኪገባው ድረስ የሚዲያና ሌላም ርዳታዎችን ማግኘታቸውን ይቀጥላሉ።
ስለሆነም
1. ከሁሉ በፊት መሪዎቹን አሳዶ መያዝና ለፍርድ ማቅረብ ተቀዳሚ ተግባር ነው።
2. ትግራይን መልሶ ማቋቋም እና የትግራይን ሕዝብ ከህወሓት ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ማላቀቅ እጅግ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
3. የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ለ worst case scenario መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ዜጎችን፣ ከተሞቻችንና መሠረተልማቶችን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል የሚሠሩ ሥራዎች በጣም መጠናከር ይገባቸዋል።
4. ህወሓትን በሽብርተኝነት መፈረጅ፤ የጎረቤት አገራትም በሽብርተኝነት እንዲፈርጁት ማሳመን፤ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የህወሓትን እውነተኛ ገጽታ ለሩቅ ወዳጆቹ ማሳየት ይገባል። ህወሓት የደቀነው አደጋ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃ ቀንድ አገራት በሙሉ መሆኑ በሚገባ በመተንተን የጎረቤት አገራት ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ማግባባት እጅግ አስፈላጊ ነው፤ የሩቆቹም ለህወሓት ያላቸውን ተቋርቋሪነት ምንጭ ማጥናትና እውነታውን ማስረዳት ይገባል።
5. ቀስ በቀስ ሆኖም እምነት በሚያሳድር ፍጥነት ፓለቲካችንን ከዘር ለማላቀቅ እንትጋ። በየጊዜው በሚነሱ ስሜት ቀስቃሽ የጎንዮሽ ንግግሮች ላይ ጊዜዓችንን አናባክን።
6. የሰላም ሚኒስትር እጅግ ብዙ ኃላፊነቶችን ደራርቦ ይዞዓልና እንደገና ይፈተሽ፤ አቅሙ ይጠናከር፤ የእርቀሰላም እና የድንበርና ማንነት ኮሚሽኞች ሥራቸውን ይስሩ።
7. የድል ዘፈኖችና ሽለላዎች አይብዙ።