ከየት እንጀምር …???
ዳንኤል ክብረት
.
ወዳጄ ሆይ ለምን ከሌለህ ነገር ትጅምራለህ? በሰው ላይ ኀዘን የሚጨምረው፣ ተስፋ መቁረጥም የሚያደርሰው፣ የበታችነትንም የሚያመጣው፣ ቅዠትንም የሚያባብሰው ከሌለ ነገር መጀመር ነው፡፡ እስኪ ራስህን አስበው? ስላላገኘሃቸውና ስላልደረስክባቸው፤ ስላመለጡህና ስላልተደረጉልህ ነገሮች ከማሰብ በእጅህ ስላለውና ስለደረስክበት ነገር ለምን አታስብም፡፡
በአንተ እጅ ያለው ነገር በአንተ እጅ ከሌለው ነገር ይበልጣል ወይስ ያንሳል? በእጄ ያለው ትንሽ ነገር ነው፣ በእጄ የሌለው ግን ዓለም በሙሉ ነው፤ ታድያ እንዴት በእጄ ያለው በእጄ ከሌለው ነገር ሊበልጥ ይችላል? እንደምትል አይጠረጠርም፡፡ ሲገመትም እንደዚያው ነው፡፡
እንደ እውነቱ ግን በእጅህ ያለው ነገር በእጅህ ከሌለው ነገር ይበልጣል፡፡ እንዴት? አልክ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በእጅህ ያለው ነገር ያንተ ነው፡፡ በእጅህ የሌለው ግን ገና ያንተ አይደለም፡፡ ያንተ የሆነው ያንተ ካልሆነው ነገር ይበልጣል፡፡ ምክንያቱም ያንተ በሆነው ነገር መጠቀም ትችላለህ ያንተ ባልሆነው ነገር ግን ልትጠቀም አትችልም፡፡ ያንተ በሆነው ነገር ልታዝዝ ትችላለህ፤ ያንተ ባልሆነው ነገር ግን ልታዝ አትችልም፡፡ ያንተ የሆነውን ነገር ማግኘትህን ርግጠኛ ሆነሃል፡፡ ያንተ ያልሆነውን ማግኘትህን ግን ርግጠኛ መሆን አትችልም፡፡ ያንተ በሆነው ነገር ልትወስንበት ትችላለህ፤ ያንተ ባልሆነው ነገር ግን ልትወስን አትችልም፡፡ ያንተ የሆነውን ነገር ለሌላው መስጠት ትችላለህ፤ ያንተ ያልሆነውን ግን መስጠት አትችልም፡፡ ካለህ ነገር ላይ ቆመህ የሌለህን ማየት ትችላለህ፤ ከሌለህ ነገር ላይ ቆመህ ግን ያለሀን ነገር ማየት አትችልም፡፡
እናም ወዳጄ ስትቆጥር ካገኘኸውና ከሆነልህ ነገር ጀምረህ ቁጠር፡፡ ባላገኘኸው ነገር ከምትበሳጭ ባገኘኸው ነገር ተደሰት፡፡ ባልሆንከው ነገር ከምታዝን በሆንከው ነገር ሐሴት አድርግ፡፡ ባልያዝከው ነገር ከመበሳጨት በያዝከው ነገር ሥራበት፡፡ ባልሆንከው ማንነት ከመቃዠት በሆንከው ማንነት መኖር ጀምር፡፡
ይህ ማለት ምን ይመስልሃል?
ስትጓዝ እያረጋገጠክ ተጓዝ፡፡ መጀመርያ ያለህን ዕወቀው፣ ከዚያም ባለህ ነገር ምን ያህል እንደ ተጠቀምክበት ርግጠኛ ሁን፡፡ ላለህ ነገር ዋጋ ስጠው፡፡ ያንተ የሆነውን ነገር አክብረው፡፡ ያን ጊዜ የሌለህን ታገኘዋለህ፡፡ የሌላውን ሰው ትዳር አይተህ፣ እርሱን ተመኝተህ፣ እንደዚያ በሆንኩ እያልክ በሌለህ ነገር ከማዘን፤ እስኪ በአንተ ትዳር ውስጥ ምን መልካም ነገሮች አሉ? የትኞቹን ተጠቅመህባቸዋል? የትኞቹን አድንቀሃቸዋል? ለየትኞቹስ ዋጋ ሰጥተሃቸዋል፡፡ የሌለህን ብቻ የምታይ ከሆነ ያለህን ማወቅ አትችልም፡፡ ስለ ሌለህ ነገር ብቻ የምታስብ ከሆነ ባለህ ነገር መጠቀም አትችልም፡፡ አሁን የምትሠ ራበትን ሞያ ወይም ቢሮ ወይንም መስክ በሚገባ ተጠቅመህበታል? ሠርተህበታል? ከዚያስ ማግኘት ያለብህን አግኝተሃል? ወይስ ሌላ ሞያ የምትፈልገው፣ ሌላ ቦታ መቀጠርም የምትመኘው፣ ሌላስ መስክ ላይ መዋል የምትጓጓው ሰዎች አደረግነው ሲሉ ስለሰማህ ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ታች ከፍል በተማሩት ምንም ሳይሠሩበት ወደ ላይ ይወጣሉ፡፡ በመጀመርያ ዲግሪያቸው አንዳች ሳይፈይዱ ሁለተኛና ሦስተኛ ይይዛሉ፡፡ አኗኗራቸውንና አስተሳሰባቸውን ስታየው ግን ታች ክፍል ናቸው፡፡ ለምን ይመስልሃል? መጀመርያ በያዙት ነገር ሳይረኩና ሳይጠቀሙ፣ የያዙትን ነገር ፈጽመው ማወቃቸውን ሳያረጋግጡ ሰው ስላደረገው ብቻ ሌላውን አደረጉ፡፡
በቤታችን ውስጥ ይህኮ የለንም ብለን የገዛናቸው የማንጠቀምባቸው አያሌ ዕቃዎች አሉ፡፡ በየቁም ሳጥናችን ውስጥ ስለሌለን ብቻ የገዛናቸው የማንለብሳቸው ብዙ ልብሶች አሉ፡፡ ምናልባት ግን እነርሱን ከመግዛታችን በፊት ምን እንዳለን ብናስብ ኖሮ እነርሱን የሚተካ ወይንም የሚያስከነዳ ነገር በቤታችን ነበረ፡፡ እስኪ ሰዎችን ስማቸው፡፡ እዚህ መሥሪያ ቤት የተቀጠሩ የሚሠሩበትን እያማረሩ ያኛውን መሥሪያ ቤት ያደንቃሉ፡፡ እዚያ ያሉት ደግሞ ያሉበትን እየረገሙ እዚህ ያለውን ያመሰግናሉ፡፡ ለምን? ሁሉም ሌላ ያያሉ እንጂ ያላቸውን አያዩም፡፡
የት እንደምትሄድ ሳታውቅ አትሂድ፡፡ የት እንደምትሄድ ለመወሰን ደግሞ ከየት እንደተነሳህ ማወቅ የግድ ነው፡፡ ምናልባትምኮ አለመሄዱ ከመሄዱ የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዴት መሄድ ብቻውን ዓላማህ ይሆናል? ለአንዳንዶች መማር ብቻ ዓላማቸው ነው፡፡ ለአንዳንዶች ደግሞ ማግባት፡፡ለአንዳንዶች መነገድ፡፡ ለአንዳንዶች ውጭ ሀገር መሄድ፡፡ ለአንዳንዶች ቤተ ክርስቲያን መሄድ፤ እነዚህ መንገዶች እንጂ መድ ረሻዎች አይደሉም፡፡
ሰውዬው መንገድ ሲሄድ አንድ ሽማግሌ ያገኛል፡፡
«አባቴ ይኼ መንገድ ይወስዳል?» ይላቸዋል፡፡
«የት ለመሄድ ፈልገህ ነው» አሉት ሽማግሌው፡፡
«የምሄድበትን አላውቀውም» አላቸው፡፡
«የምትሄድበትን ካላወቅከውማ የትኛውም መንገድ ይወስድሃልኮ» አሉት ይባላል፡፡