>

ከድል በኋላ አገር የሚያፈርስ መከፋፈል የሚከሰተው በድል ስካር ሳይሆን ከጦርነቱ በፊት በነበሩ ለጠብ የሚያበቁ የአገር አንድነት ጠንቆች ነው!  (አቻሜለህ ታምሩ)

ከድል በኋላ አገር የሚያፈርስ መከፋፈል የሚከሰተው በድል ስካር ሳይሆን ከጦርነቱ በፊት በነበሩ ለጠብ የሚያበቁ የአገር አንድነት ጠንቆች ነው! 

አቻሜለህ ታምሩ

ዐቢይ አሕመድ መቀሌ ተጉዞ በጦር መሪዎች ፊት በሰጠው መግለጫ “ከድል በኋላ የሚመጣ መከፋፈል ለብዙ አገሮች መከፋፈል ምክንያት ሆኗል፤ በኢትዮጵያ ታሪክም መኢሶንና ደርግ የሱማሊያን ወረራ ለመቀልበስ አብረው ቢዘምቱም ከድሉ በኋላ ግን [በድል ስካር] አብረው መቀጠል አልቻሉም፤ [ከዚህ ተምራችሁ] በጦርነት የተገኘውን አንድነትና ወንድማማችነት ከድል በኋላ ማስቀጠል አለባችሁ” ሲል ተናግሯል።
ሲጀመር መኢሶንና ደርግ የሶማሊያን ወረራ ለመመከት አብረው አልዘመቱም። በደርግ ቋንቋ መኢሶን የፈረጠጠው፤ መኢሶኖች እንደሚሉት ደግሞ ስልታዊ ማፈግፈግ ያደረገው ኢትዮጵያ ወደ ጦርነቱ ሳትገባ በ1969 ዓ.ም. ነው። በሶማሊያ ወረራ ሠራዊት ላይ ኢትዮጵያ ዳግማዊ አድዋን የተቀዳጀችው የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም. ነው። በመሆኑም  ዐቢይ መኢሶንና ደርግ ከድሉ በኋላ ተጣሉ የሚለን መኢሶን ባልተገኘበት የጦርነው ውሎ ነው።
የሆነው ሆኖ ከድል በኋላ ተጣሉ የተባሉት ከጦርነቱ በፊት ችግር ስለነበር እንጂ ጦርነቱን ማሸነፋቸው የወለደው ስካር አይደለም። በዓድዋ ጦርነት  ኢትዮጵያውያን ታላቅ ጦርነት አሸንፈዋል። ይህ የዓድዋ ድል የወለደው ስካር ግን  ኢትዮጵያውያን እንዲጣሉና እንዲከፋፈሉ አላደረጋቸውም። ይህም ሊሆን ይቻለው  ከድሉ በፊት በኢትዮጵያውያን መካከል ለጠብ የሚያበቁ ቀዳዳዎች፤ በነገድ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ስላልነበረ ነው።
ስለዚህ ለጠብ የሚዳርጉትን እነዚህን የአገር አንድነት ጠንቆችን ሳያስወግዱ፣ ቀዳዳዎች ሳይደፍኑና ኢትዮጵያውያን በነገድ ተቧድነው እየተከሳከሱ ሞትን የሚያነግሡበትን የጠብ ደንብ በሕገ መንግሥትነት እያሰቡ  “በጦርነት የተገኘውን አንድነትና ወንድማማችነት ከድል በኋላ ማስቀጠል አለባችሁ” በሚል ስብከት ብቻ  አይደለም ዘላቂ ሰላም ጸጥታ እንኳን  ማስፈን  አይችልም።
ባጭሩ ኢትዮጵያውያን በቋንቋና በነገድ ተቧድነው እየተከሳከሱ ሞትን የሚያነግሡበት የጠብ ደንብ  ሕጋዊ ሆኖ ባለበት ሁኔታ “አትጣሉ” በሚል ስብከት ሰላም ማስፈንና ከታሪካዊ ችግሮቻችን እንድንገላገል ሊያደርገን አይችልም። ሰላም ማስፈን የሚቻለው፤ ከታሪካዊ ችግሮቻችን ልንገላገል የምንችለው የጠብ ምንጭ የሆኑት ሕወሓት መንግሥታዊ ያደረጋቸው የአፓርታይድ አስተሳሰቦች፣ ሕጋዊ ያደረጋቸው የአፓርታይድ ደንቦች፣ ኢትዮጵያን ያዋቀረበት ሕገ መንግሥት የሚባለው የወንጀል ሥነ ሥርዓትና መዋቅር የዘረጋላቸውን ሌሎች የአፓርታይድ አሰራሮች ሲሻሩና የአገር ጠንቆችን  በማስወገድ ብቻ ነው።
Filed in: Amharic