ኢትዮጵያ አንድ ሉዐላዊት አገር ሆና ሳለ ‹‹ሕዝቦች›› የሚለው ከየት መጣ?
ከይኄይስ እውነቱ
ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ› መጽሐፋቸው ሕዝብ የሚለውን ቃል የሚከተለውን ፍች ሰጥተውታል፤
‹‹(ብ፡ሕዝብ፤ አሕዛብ)፤ በቁሙ፤ ወገን፣ ነገድ፤ የተሰበሰበ ብዙ ሰው፤ ጉባኤ፣ሸንጎ፤ ልቅሶኛ፣ ሰርገኛ፣ ገበያተኛ፡፡ ያንዲት አገር፣ ያንዲት ከተማ ወይም ያንድ ብሔር [አገር]፣ ያንድ መንግሥት ሰው፤ ቋንቋውና ሕጉ አንድ የኾነ፤ ባንድ ሕግ የሚኖር፡፡ ውስጠ ብዙነት ስላለውም ባንድም በብዙም በወንድም በሴትም ይነገራል፡፡››
አሕዛብ የሚለው ቃል በግእዙ የሕዝብ ብዙ ቊጥር ሲሆን፣ በሃይማኖት ዐውድ ጸያፍ አገባብም አለው፡፡
እዚህ ፍቺ ላይ ‹ቋንቋው አንድ የሆነ› ሲል ወልጋዳ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እንደሚሉት ነገዶች/ጐሣዎች በራሳቸው ቋንቋ አይጠቀሙ ማለት አይደለም፡፡ ይህንን መብት ማንም የሚፈቅድላቸውና የሚነፍጋቸው አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ነገሥታት የሚመሰገኑ እንጂ የሚወቀሱ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከ20 በላይ ነገዶች/ጐሣዎችን ቋንቋና ባህል ያጠፋው በ16ኛው ክ/ዘመን የተነሳው የገዳ የወረራ ሥርዓት ነው፡፡ ሊቁ ቋንቋው አንድ የሆነ ሕዝብ ያሉትን በኢትዮጵያ ዐውድ ስንወስደው ሁላችን ኢትዮጵያውያን በዘመናት ሂደት አዳብረነው የምንግባባበትን፣ የመንግሥት የሆነውን ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛን ለማለት ነው፡፡ ይህ ቋንቋ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር አዛምዷል፣ አስተሳስሯል፣ አዋሕዷል፣ የጋራ ሥነ ልቦና እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
የወያኔ የጐሣ መድልዎ አገዛዝ ሥርዓት ሆን ብሎ ከፈጠራቸውና ትውልዱንም ካበላሸበት ቃል አንዱ በማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ› ጭምር ዕውቅና እንዲያገኝ ያደረገው ‹ሕዝቦች› የሚል ላንድ አገር ዜጎች መጠቀም የማይገባን፣ በዚህም መልኩ ስንጠቀምበት ጸያፍ የሆነ ልዩ የፖለቲካ ‹ፍጥረት› ነው፡፡ አሁን በምንነጋርበት ዐውድ ግን ቃሉን ጸያፍ የምንለው ብቻ ሳይሆን መርዛማ መልእክት ያዘለ ነው፡፡ ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦች› ከሚላቸው ማደናገሪያ ቃላት ጋር ሰውነት እና ኢትዮጵያዊነት የሚሰጠውንና የሚያሰገኘውን መብትና ነፃነት ለመንፈግ የሰነቀራቸው ግዑዛን ፍጥረታት ናቸው፡፡ ዛሬ ጐሠኞች ብቻ ሳይሆኑ ሣር ቅጠሉ ሁሉ የአፉ ማሟሻ አድርጓቸዋል፡፡ የሚያሳዝነው በዚህ የጥፋት ጎርፍ የተወሰዱት የቈየው ትውልድና ዘረኝነትን የሚየጸየፉትም መሆናቸው በእጅጉ ቅር ያሰኛል፡፡
ይህንን ርእሰ ጉዳይ በአለፍ ገደም እኔም ሆንኩ ታላላቆቼ በተለያዩ ጊዜያት አንስተንዋል፡፡ አንድም ቋንቋን የመላጠንቀቅ*/የመራቀቅ ነገር በማድረግ፣ አንድም የጸጕር ስንጠቃ በማስመሰል፣ አንድም አገር ጭንቅ ጥብ ውስጥ ሆና ይህንን ማንሣት ሥራ ፈትነት አድርጎ በመቊጠር፣ ወዲህም አስተዋይ በመጥፋቱ ሁሉም ባፈተተው ቀጥሏል፡፡
የጐሣ አገዛዝ ሥርዓት መሐንዲስ የነበረው መለስ ደቀ መዝሙርና የአገር አጥፊ ሰነዱ ጠበቃ ነኝ የሚለው ዐቢይም ‹ሕዝቦች› የሚለው ቃል ከአንደበቱ የማይለይ መሆኑን ደጋግመን ሰምተናል፡፡ ያርመው እንደሆነ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ አገር እመራለሁ ከሚል ሰው የሚወጣ ንግግር ጥንቃቄ ያሸዋልና፡፡
ወያኔ ከፈበረካቸው የሐሰት ትርክቶች/ተረቶች አንዱ ኢትዮጵያ የምትባል ከጥንቱ ሥልጣኔ ተካፋይ የሆነች ታሪካዊትና ጥንታዊት አገርን በመቶ ዘመን በመወሰን፣ በታወቀ መልክዐ ምድሯ የሚኖሩና የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የተለያየ ባህል ያላቸው ማኅበረሰቦች ኢትዮጵያዊነት የሚባል የጋራ ብሔራዊ ማንነት ያልነበራቸው፣ የጋራ ብሔራዊ ቋንቋ የሌላቸው፣ የጋራ ብሔራዊ ዕሤቶችና ሥነልቦና ያላዳበሩ፣ ባንድ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሥር ያልተሰባሰቡ በግድ/በጭቆና ወይም ተረቱን እስከ ጥግ ከወሰድነው በቅኝ ግዛት ሥር የተያዙ የተለያዩ ‹አገሮች ሕዝቦች› ሲኖሩባት የነበረች አገር በማስመሰል፣ ወያኔ የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን በጉልበት ከተቈጣጠረ ወዲህ ‹ክልል› ባላቸውና በፈለጉ ጊዜ ተገንጥለው መሄድ የሚችሉ 9 አገር-አከል ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ‹ሕዝቦች› ተፈቃቅደው የሚኖሩባት አድርጎ ነው፡፡ በመሆኑም ወያኔ ታሳቢ ያደረገው የብዙ አገሮች ‹ሕዝቦችን› እንጂ የአንድ አገር ሕዝብን አይደለም፡፡ የቃሉ አጥፊ መልእክት ያለው እዚህ ጋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንዲት ሉዐላዊት አገር፣ ሕዝቧም አንድ ሉዐላዊ ሕዝብ ነው ብለን (ወያኔ አገራዊ አንድነትን ለማጥፋት የተከለውን ሰነድ ትተን ስንነጋገር) የምናምን ከሆነ፣ አንድ አገር የሚኖረው አንድ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ልዩ ልዩ ነገዶች/ጐሣዎች መኖር የሕዝቡን አንድነት ወይም የአንድ አገር ሰውነት የሚያስቀር አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ከኢትዮጵያ በላይ በርካታ ነገዶች/ጐሣዎች ያሉባቸው አገራት በሕግጋተ መንግሥታቸው የአንድ አገር ሕዝብነትን አጽንተው የሚናገሩት፡፡
- ይህ ቃል እውነተኛ አብሮነትን (federalism) አጥፍቶ የጐሣ መንደሮችን (ethnic enclaves) የፈጠረ ነው፤
- ይህ ቃል የዜግነት መሠረት የሆነውን የግለሰብ መብትና ነፃነትን የገፈፈ ነው፤
- ይህ ቃል ወያኔ አገር ለማጥፋት ባዘጋጀው ሰነድ ‹ክልል› በሚል ባዋቀረው የአትድረሱብኝ አጥር ዜጎችን/ኢትዮጵያውያንን ባገራቸው ባይተዋር/መጻተኛ ያደረገ ነው፤
- ይህ ቃል በዘመነ ወያኔ በተለይም ባለፉት 3 ዓመታት በተረኛ ጐሣ ፖለቲከኞችና ባሠማሯቸው ሽብርተኛ ኃይሎች ዜጎች ከገዛ አገራቸው በገፍ ለተፈናቀሉበት፣ ቤት ንብረታቸውን ላጡበት እና ማንነትን መሠረት ያደረጉ ዘግናኝ የዘር ፍጅቶች (ጄኖሳይድ) ለመፈጸሙ ምክንያት የሆነ ነው፡፡
ስለሆነም ወያኔና ተረፈ-ወያኔዎች (ጐሠኞች) ከጫኑብን ኮተቶች መካከል አንዱ ‹ሕዝቦች› የሚለው ቃል በመሆኑ ከአእምሮ ትውስታችን አውጥተን ልንጥለው (unlearn ልናደርገው) ይገባል፡፡
እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!!
ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡
ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡