ጠ/ሚ ዓብይ መቀሌ ሄደው ለጦር መሪዎቹ ካደረጉት ንግግር ….!!!
ጌታቸው ሽፈራው
“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ልክ እንደ አባቶቹ በሀገሩ ሉዓላዊነት የማይደራደር የተሰጠውን ሀገራዊና ሕጋዊ ሚሽን በብቃት የመፈፀም፣ ጠንካራ ቁመና ያለው ለሀገር ኩራት የሆነ፣ ለልጆቻችን በደስታ መናገር የሚያስችል ተቋም መሆኑን በተግባር አሳይታችኋል።
የኢትዮያ መንግስት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእናንተ ከፍተኛ ኩራት እና ክብር የተሰማው መሆኑን እዚሁ መቀሌ ላይ ብገልፅላችሁ ብዬ ነው የመጣሁት።
በአፍሪካ ዘመናዊ የሚባል “ሲቹዌሽን ሩም” ገንብተን ውጊያውን በዓይናችን እያየን ነው የመራነው።
ጀነራል ብርሃኑ ጁላ እና ቲማቸው ላበረከቱት የላቀ አመራርና ላሳዩት ቁርጠኝነት ከፍ ያለ ምስጋና ይገባቸዋል። በተጨማሪም የሁላችሁንም ስም ዳግም ባልጠራም ሶስት ሜካናይዝድ ክ/ጦር ያዳናችሁ ሶስቱ ጀነራሎች ኢትዮጵያ ለዘላለም የምታከብረው ገድል ሰርታችኋል። የሰራችሁትን ገድል በቀላሉ የምናየው አይሆንም። ስለዚህ እናንተ ከፍተኛ ክብርና ምስጋና ይገባችኋል።
በዚህ ጦርንት ወታደራዊ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂካል ቋንቋ መናገር የሚችሉ ኮማንዶዎችም ተፈጥረዋል።ይህ ሰራዊት የብልፅግና ሰራዊት አይደለም። ይህ ሰራዊት የዓብይ ሰራዊት አይደለም። የኢትዮጵያ መከታና ኩራት የሆነ ሰራዊት ነው። ኢትዮጵያ ከብልፅግና በላይ ናት። ከፓርቲም በላይ ናት። ስለዚህ እናንተ ትልቋን ሀገር የመታደግ ኋላፊነት ተጥሎባችኋል።
ፖለቲካው የተበላሸ ነው። የማያውቀውን የደም ስር፣ የደም ሐረግ እየፈለገ የሚቧደን ነው። እናንተ ግን ጀግኖች ብቻ ሳትሆኑ ንፁህ ኢትዮጵያዊያን ናችሁ። በየአንዳንዱ ጦር ግንባር ኦሮሞው አማራውን ለማዳን፣ አማራ ወላይታውን ለማዳን፣ ወላይታው ሲዳማውን፥ ሱማሌውን ለማዳን ያሳያችሁት ጀግንነት እንኳን መሪ ሊያስፈልጋችሁ ለመላው ኢትዮጵያውያንና ፖለቲከኛ አርዓያ የሚሆን ስራ ሰርታችኋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሚናገር ብቻ ሳይሆን የሚተገብር መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። እናንተ ጀግኖች የምለምናችሁ አንድ ነገር ነው። ጀግና አይፎክርም፣ እንዳትፎክሩ። ጁንታውን ጉድ የሰራው በምላስ ኃይል ማሸነፍ የሚቻል መስሎት ነው። ጀግና አስቀድሞ ከፎከረ ነገር ይበላሻል። ዋናው ተገባር ነው።
አነ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ በ24 ሰዓት ውስጥ የ2 ሳምንት ኦፕሬሽን ፕላን ማዘጋጀት የሚያስችል አቅምና ጦርነት የሚመራበትን ብቃት አሳይተዋል። እነ አበባው ዕቅዶቻችንን በየሁኔታው፣ በየመድረኩ ከምልክዓ ምድሩ ጋር ማናበብና መቀያየር የሚያስችል ብቃት አሳይተዋል። እነ ዓለምሸት የተኩስ ጥበብ ለእኛም ለጠላትም አስተምረዋል። የተኩስና የሞቢሊቲ አቅም አሳይተዋል። እነ ባጫ በነበሩበት መድረክ ቀን፣ ቀን የተሰጠውን የማደራጀት ስራ እየሰራ ማታ ማታ በየአንዳንዱ ቀን የናንተን ድል ይከታተል ነበር።
ወታደር በመሆኔ በጣም ኮርቻለሁ። በእናንተ ውስጥ በማደጌ በጣም ኮርቻለሁ። ባጠገባችሁም ያለፈ ይኮራል እንኳን በእናንተ ያለፈና በጣም ደስታ የተሰማኝ መሆኑን እየገለፅኩ፤ ተባብረን ሀገራችንን እናሳድጋት እንጠብቃት፣ በርቱ ለማለት ነው በጣም አመሰግናለሁ።”