>

*የቤት እመቤት በመሆን ውስጥ እመቤትነት አለ ? (ህይወት እምሻው)

የቤት እመቤት በመሆን ውስጥ እመቤትነት አለ ?

ህይወት እምሻው

በአንድ ወቅት፤ ያገኘኋቸውን ወንዶች በሙሉ አንድ ጥያቄ ስጠይቅ ነበር ፤ “የቤት እመቤት ማለት ምን ማለት ነው ?”
ከአንድ ወይም ሁለት መልሶች ዉጪ የተሰጡኝ ፍቺዎች በሚከተሉት ሐረጎች ሊጠቃለል ይችላል ።
“የማትሰራ ሴት”
“ስራ የሌላት ሴት”
“ገቢ የሌላት ሴት”
“ሥራ አጥ ሴት”
“ሥራ ፈት ሴት”
እነዚህን መልሶች የሰጡኝን ወንዶች መልሼ ይሄንን ጥያቄ ጠየኳቸው።
ነጋ ጠባ አልጋ ማነጠፍ ፣ ቆሻሻ ልብስ ማጠብ ፣ የታጠበ ልብስ በየቦታው ማስቀመጥ ፣ ከሻይ ማንኪያ እስከ በርሜል ሙልጭ አድርጎ ማጠብ ፣ ከሻይ ማንኪያ እስከ በርሜል ሙልጭ አድርጎ የታጠበ እቃን ማድረቅ ፣ ከሻይ ማንኪያ እስከ በርሜል ሙልጭ ተደርጎ የታጠበና የደረቀ እቃን በየቦታው ማስቀመጥ ፤ ስራ አይደለም ?
በየቀኑ ከኩሽና እስከ ሳሎን ፣ ከሽንት ቤት እስከ ግቢ መጥረግና መወልወል፤
ከሳሎን ጠረጴዛ እስከ ቁምሣጥን ጀርባ እና አልጋ ሥር ድረስ መጥረግ እና መወልወል፤
የቤቱን ሁሉ የተጠረገና የተወለወለ ቆሻሻን ሰብስቦ መጣልስ፣ ሥራ አይደለም ?
ቀን ቆጥሮ አንሶላ ፣ ትራስ ልብስና አልጋ ልብስ መቀየር ፣ጊዜን አስልቶ የኩሽና እቃ ግልብጥ አድርጎ አዉጥቶ ማፅዳት ፣ ጊዜን ወስኖ የመስኮትና የበር መስታወትን በጋዜጣ ሲያፀዱ እና ሲያስውቡ መዋል ፣ የአደፈ መጋረጃን መለወጥ ፣ ሥራ አይደለም ?
“ምን አለቀ ?” ብሎ ቀለብ መሸመት ፣ የተሸመተውን አመጣጥኖ ማዘጋጀት ፣ የተዘጋጀውን ማቅረብና ቤተሰብ መመገብ ፣ ሥራ አይደለም ? ደግሞ ከሁሉ በላይ
ልጅ ማርገዝ፤
ልጅ አምጦ መዉለድ፤
ልጅ አጥብቶ ማሳደግ፤
ልጅ ማነፅ፤
ልጅን ለወግ ማብቃት ፤ ሥራ አይደለም ?
እናም ወንድሞቼ…..
አገልግሎትና ምርታማነትን በጥሬ ገንዘብ በሚተምን የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ በመኖራችን ብቻ ፤
በቀጥታ የገንዘብ ክፍያ የማያስገኝ ሥራ እንደ ሥራ በማይቆጠርበት ዓለም በመኖራችን ብቻ ፤ ይሄንና ሌላም ልዘረዝረው ብል መፅሐፍ የማይበቃዉን ሥራ ሁሉ የምትሠራን ሴት “ሥራ የላትም” አትበሉኝ ።
ይልቅስ ፣ በእኛ ሀገር የቤት እመቤት መሆን ፤ ከእመቤትነቱ ሸክሙ ይበልጣልና ፤ ሚዛናችሁን አስተካክላችሁ የቤት እመቤት ማለት ፤ “በዓለም ላይ ከባዱን ፣ ግን ክፍያ የሌለውን ሥራ የምትሠራ ሴት ማለት ናት” በሉኝ።
Filed in: Amharic