>
5:26 pm - Saturday September 15, 3100

የሱዳን ጉዳይ ትልቅ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው! (ጌታቸው ሽፈራው)

የሱዳን ጉዳይ ትልቅ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው!

ጌታቸው ሽፈራው

… የማይካድራው ጨፍጫፊ ኃይል፣ ጨፍጫፊው ባለሀብት፣ የደሕንነት፣ የፀጥታና የልዩ ኃይል አባል ወደ ሱዳን ከሄደ በኋላ በስም ዘርዝረን፣ በፎቶ አስቀምጠን፣ ምን እየሰሩ፣ ምን እያቀዱ  እንደሆነ በተደጋጋሚ ተናግረናል። የሱዳን ባለሀብት የሚያዘው ሰራዊት፣ በትህነግ ባለሀብት፣ ካድሬና ደሕንነት ተፅዕኖ ስር እንደሆነ ተናግረናል።  በሀገር ቤቱ ፍልሚያ ሲሸነፉ የውጭ ጠላት ነው ይዘው የመጡት።
የትህነግ ሰዎች የኢትዮጵያን መሬት ቆርሰው ለሱዳን ለመስጠት ፍላጎት ነበራቸው። በአማራ ሕዝብ ፅናት ሳይሰጥ ቀርቷል። አሁን የድሮ ክህደታቸውን ነው የቀጠሉት። የሱዳን ባለሀብቶች የሚፈልጉትን አጀንዳ ነው ያመጡላቸው። የገፋፏቸው  ለዘመናት ሲያባብሏቸው በኖሩት ጉዳይ ነው።
የትህነግ ትርፍራፊዎች የሱዳንን ባለሀብቶችና ያኮረፉ የሱዳን ሰራዊት አመሮችን ደልለውና አባብለው እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑ  ለኢትዮጵያውያን ቀድመው የተናገሩት ሰላም የሚፈልጉ ሱዳናዊያን ባለሀብቶች ናቸው።
አንድ የትህነግ ሚሊሻ መሪ ቢሊዮን ብሮችን ይዞ ሱዳን ውስጥ ተይዞ በየሚዲያው ሰምተናል። ባንክ እየዘረፉ የከረሙት ሌሎች የትህነግ ገዳዮችና ባለሀብቶች ገንዘቡን በሰላም ሊበሉት ስለማይችሉ ኢትዮጵያን ለማስጠቃት ነው የተጠቀሙበት፣ መደለያ ነው ያደረጉት። ሀብታም በገንዘብ ለሚቀጥረው ሰራዊት ማማለያ ነው ያደረጉት!
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳን ሰራዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ፀብ ጭሮ መልስ ሲሰጥ በደቂቃዎች ውስጥ መልስ የሰጠችው ግብፅ ነች።  የረባ መጣራት ሳታደርግ ከሱዳን ጎን ነኝ ብላለች። ሱዳን በተነኮሰ እኛን አውግዛናለች። ሱዳን ውስጥ በመከላከያ ሰራዊቱና በሲቪሎቹ መካከል ያለው ልዩነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። በቅርቡ በተደረገው ሰልፍ ሰራዊቱ ከሰልፈኞቹ ጎን ለመምሰል ጥረት አድርጓል። ዋናው አላማው ፖለቲከኞችን ገለል አድርጎ ሰራዊቱ ስልጣኑን እንዲይዝ መደላድል መፍጠር ነው። ሰራዊቱ ኢትዮጵያን ወርሮ ሉአላዊነት የሚያስከብር ለመምሰል የጣረውም ባኮረፉት የሰራዊቱ አመራሮች ፍላጎት ነው። አብዛኛዎቹ በትህነግ ግብዧ  መቀሌ  የከረሙ ናቸው። ትህነግ ኢትዮጵያ እንድትጠቃ ይፈልጋል። ከዛም አልፎ የትጥቅ ትግሉን በሱዳን ጀምሮ ወደ ትግራይ ለማለፍ ህልም አለው። የሱዳን ሰራዊት አመራሮች ደግሞ በሀሰት ሉአላዊነት አስከበርን ብለው ለቀጣይ ስልጣን መቀስቀሻ ይዘዋል!
የበርካታ አማራ ባለሀብቶች ንብረት እየተመረጠ ወድሟል። የትግራይ ባለሀብቶች ንብረት አልተዘረፈም፣ አልተቃጠለም። እንደአጋጣሚ ሆኖ አይደለም። ከሱዳን ጀርባ ያለው ማን እንደሆነ ግልፅ ስለሆነ ነው። የሱዳን ጦር በሌሊት ተዋግቶ አያውቅም። አሁን በሌሊት መዋጋት ጀምሯል።
የሱዳን ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉአላዊ መሬት ዘልቆ መግባት፣ የግብፅና  የትህነግ መኖርን መንግስት ያውቃል። ይሁን ዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡ ይህን አያውቅም። ዋነኛው የእኛም ድክመት ነው። ትህነግ የጡረታ መውጫ፣ የጃጀ ፖለቲከኛ ማሸሺያ አድርጎ ያለማመደው የዲፕሎማሲ ጉዳይ አሁንም በእንቅልፉ እንደቀጠለ ነው። በኢትዮጵያ ጉዳይ ውጭ ሄደው ሕይወት እንዲቀጩ የሚደረጉ የድሮ ፖለቲከኞች “ዲፕሎማት” ተብለው ምን እንደሚሰሩ የሚታወቅ ነገር የለም። ዞን በቅጡ ማስተዳደር የማይችሉ “አብዮታዊ ዲምክራሲያውያን” በዓለም መድረክ ምንም እንዲሰሩ ሊጠበቅ አይችልም።  ይህን ስል የእነዚህ ስራ ፈት ዲፕሎማቶች ጉዳይ እያበሸቃቸው የየፊናቸውን ሚና ለመወጣት እየሰሩ ያሉ ዲፕሎማቶች የሉም ለማለት አይደለም። ጥቂት ናቸው። ለኢትዮጵያ የሚመጥን ስራ ለመስራት የእነሱ ብርታት ብቻ በቂ አይደለም።
ብዙ ጉዳት ቢያደርስም የሱዳን  ጉዳይ መጀመርያ በውይይትና በዲፕሎማሲ መታየት አለበት። ወደማይቀረው ጦርነት የሚያስገባ ከሆነም መጀመርያ አማራጮቹ እስኪፈተሹ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የትህነግ ትርፍራፊ አማራውንም ሆነ ኢትዮጵያን ወደ ሌላ ግጭት ጎትቶ አስገብቶ ያገኙትን ድል ማስጣል ፈልጓል። ባለፈው ከኤርትራ ጋር ግጭት ፈልጎ ሳይሳካለት ቀርቷል። አሁን የእኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ጥንቃቄያችን ግን በዲፕሎማሲው በደንብ እየሰራን፣ ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርሱ እየተከላከልን መሆን አለበት። የትህነግ ቅሬቶችና ግብፅ ለአማራውም ለኢትዮጵያም ባላቸው ጥላቻ እንደ ዝምታ የሚያዩዋቸው ጉዳዮችም የበለጠ ዋጋ ሊያስከፍሉ ይችላሉ። ጥንቃቄ ይደረግ ስንል በተናጠል መከላከልም ሆነ በተናጠል ጩኸት አያስፈልግም ነው። ተመክሮበት፣ በአንድ ላይ አቋም ተይዞበት መደረግ ያለበት ጉዳይ ነው። በየግል የምናደርጋቸው ጩኸቶች ሕዝባችን ከመረበሽ አልፈው ለሌላም መጠቀሚያ ስለሚሆኑ መናበብን የመሰለ ነገር የለም።
Filed in: Amharic