ስድብ ለተዛቡ ጽሁፎች መልስ ሊሆን አይችልም
አበጋዝ ወንድሙ
የህወሃት አመራር የዛሬ ሰባት ሳምንት ባልተጠበቀና ባልታሰበ የሀገር ክህደት እርምጃ የሰሜን እዝ ላይ ባካሄደው ወታደራዊ ጥቃት የተነሳ፣ የፌደራል መንግስት ሁኔታውን ለመቀልበስ ወታደራዊ ዘመቻ እንዳካሄደ ይታወቃል።
የፌደራል መንግስት በወሰደውም እርምጃ መንግስት እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ ክልሉ ወደተረጋጋ ሁኔታ ጉዞ ጀምሯል።
የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠነ ሰፊ ስለነበርም ፣ በማናቸውም የጦርነት ወቅት የሚገጥም የሰላማዊ ህዝብ የመቁሰል አደጋ፣ የመሞት፣ መፈናቀልና መሰደድ የትግራይ ክልል ህዝብ እጣ ፈንታ ሆኗል። በነዚህ ባለፉት ሰባት ሳምንታት፣ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የስልክ፣ የበይነ መረብ፣የመብራትና ውሃ መቋረጥ ጦርነት ከሚያስከትለው ችግር በላይም የህዝብ የቀን ተቀን ኑሮ ላይ ተጨማሪ እጥረትና እንግልት እንደሚያስከትል የታወቀ ነው፣ መሬት ላይ የነበረው ሁኔታም ይሄንን አንጸባርቋል።
የህወሃት አመራር የወሰደውን የክህደት እርምጃና የፌደራል መንግስት ያካሄደውን ግብረ መልስ አስመልክቶ ፣ ከዋና ተዋንያኑና ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም ከውጭ ሀገር መንግሥታት በተጨማሪ፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ተመራማሪዎች አስተያየታችውን ሲሰጡ ከርመዋል፣ አሁንም በመስጠት ላይ ናቸው።
ሁሉም ወገን የሚደግፈውን ወገን ትክክለኛነት ለማሳየት የሚያካሂደው የፕሮፓጋንዳ እሰጥ አገባ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ሁሉም ወገን ግን የተቃራኒውን ስህተት ነቅሶ በማውጣት የሚደርሱበትን ድምዳሜ ትክክለኛ አለመሆን ከማሳየት ይልቅ ወደ ስድብና ዘለፋ መዝቀጥ የሚጠቅመው ነገር ካለመኖሩም በላይ ዘለቄታዊ ችግር ሊፈጥር ይችላል።
ሰዎች በማናቸውም የጽሑፍ ወይንም የመገናኛ አውታሮች የሚያቀርቧቸው አስተያየቶችም ሆነ ዘገባዎች በእውነት ላይ የተመሰረቱ ፣ ህዝብን የሚያቃቅርና የሚያለያይ ሳይሆን ልዩነቶችን የሚያጠቡ፣ፍቅርን የሚያጎለብቱና አንድነትን የሚያጠናክሩ ፣የህዝብ ሰላምና አብሮነት ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ ትልቅ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል።
በነዚህ በጎ እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ አስተያየቶች የተለያየ አመለካከት ያላቸውንም ሰዎች በሰከነ ውይይት፣ የተሳሳተ አስተያየትም ሆነ ግንዛቤ ካላቸው ለማስተካከል ሰፊ ዕድል ከፋች ሲሆን ፣ ስድብና ዘለፋ ግን እንደሚያራርቁና ጥላቻን እንደሚያነግሱ ከበቂ ባላይ ተመክሮ አለን።
ለኔ ፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ፣ የተለየ ዘገባ ወይንም አስተያየት የሚጽፉ ጋዜጠኞችም ሆነ ተመራማሪዎች ፣ የነሱንም አስተያየት በትዊተር ወይንም በሌላ ማህበራዊ ሚዲያ ያሰራጨም ሰው ጭምር ለስድብና ለዘለፋ የተጋለጡ መሆናቸው አሳሳቢ መስሎ የሚታየኝ ፣ ስህተት ከመሆኑ አንጻር ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር የገጠመንን ችግር ያባብሰዋል የሚል ፍራቻ ስላለኝም ጭምር ነው።
እርስ በርስ የምናደርገው መናቆር ሳያንስ ፣በሚልዮን የሚቆጠር አንባብያን ያላቸው የንውዮርክ ታይምስ ወይንም የቢቢሲ መገናኛ ወይንም ሌላ ድርጅቶች ላይ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ላይ የሚካሄደው የስድብና የማጥላላት ዘመቻ፣ ሰዎቹ ላይ በግል ሊያደርስ የሚችለው የረባ ችግር ባይኖርም፣ ለዘለቄታው ግን እንደግፈዋለን የምንለው ወገን ላይ ዜና አውታሮቹ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ይበጃል ባይ ነኝ ።
እርግጥ ነው በነዚህ ጋዜጦች ላይ ሚዛናዊ ያልሆኑ አንዳንዴም ትንሽ እውነት ላይ የተመሰረቱ ሆኖም ከተጨባጭ ሁኔታው የራቁ ዘገባዎች ቀርበዋል። የእነዚህን ዘገባዎች ሚዛናዊ አለመሆን ወይንም ከእውነት የራቁ የምንላቸውን ዘገባዎች ግን መሞገት የሚገባን፣ እውነተኛና ሚዛናዊ የሆነ የመልስ ምት በጽሁፍ በማቅረብ እንጂ፣ ከቶውም በዘለፋና በስድብ ሊሆን አይችልም።
እነዚህ የዜና አውታሮችና ጋዜጦች በመላው ዓለም ሰፊ ተነባቢነት ስላላቸው ፣የሚያቀርቡትን የተዛባ የምንለውን መረጃ ፣እውነተኛውን መረጃ በማቅረብ በቅጡ መሞገት ካቃተንና ወደ ዘለፋ ከወረድን፣ የተዛባ የምንለው የነሱ መረጃ ገዢ አስተያየት እንዲሆን አበርክቶት እያደረግን እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።