መንግስት የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ሊጠብቅ ይገባል
ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ
ታህሳስ 13/2013ዓ.ም. ማታ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች በመተከል በግፍ እንደተገደሉ ሰማን፡፡ ቀልዱን ወደ ጎን ትቶ መንግስት የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ሊጠብቅ ይገባል፡፡ በመግለጫዎችና በጫጫታዎች ዜጎችን ማምታታት አይቻልም፡፡ ያለንበት ዘመን እና የማሕበረሰቡ ንቃተ-ህሌና የባለስልጣናትን ማጭበርበሪያ ለማስተናገድ በቂ መደላድል የለውም፡፡ በቃላት ጋጋታ ወይም በወሬ ዜጎችን የምናታልልበት ዘመን በብዙ ምዕራፎች ርቀነው ሂደናል፡፡ ቃል እና ተግባር ተዋህደው፣ በእውነት ላይ የተመሰረተ ማንነትን መገንባት የአንድ መሪ ትልቁ የሰብዕና መለኪያ ነው፡፡ በቃሉ ያልፀና በተግባር ያልተፈተነ መሪ ግን የአስተማሪነት ባህሪ አይኖረውም፡፡
በኦህዴድ የፖለተካ ሊህቃን ዘንድ የህወሀት የሀሰት ትርክት የእውነትን የግዛት ስፍራ ስላስለቀቀ የፖለቲካ ስርዓቱ መሰረታዊ ዳራ በሌለው የበዳይ-ተበዳይ ትርክት በመቃኘቱ ይኸው ለማያባራ ቀውስ ዳርጎናል፡፡ በተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ያለውን ታሪካዊ አንድነት ወደ ጎን ከመተው ይልቅ፣ የህወሀት ዘረኛ ቡድን የጫነውን የሀሰት ትርክት በአውንታዊ ስነ-ልቦና ከመቃኘት ይልቅ፣ በጠራ የአስተሳሰብ መንፈስ የአብሮነት ጉዞው ቢቃና መልካም ነው፡፡ ልዩነትን በኪሳራነት ከመቃኘት ይልቅ ልዩነት ውበት እና ተፈጥሮዓዊ እንደሆነ ማሰብ ድንቅ ነው፡፡
በሰዎች ስቃይ ስሜት አልባ ከሆናችሁ እንኳን ጊዜው የሰጣችሁን የፖለቲካ ሉዓላዊነት በአግባቡ በመጠቀም እና ለፈጣሪ በሚኖራችሁ ፍራቻ(ምናልባት ካላችሁ) ይህን የግፍ ስራችሁን ለከት ብታበጁለት መልካም ነው፡፡ የግፍ ታሪክ ግፍን ይወልዳልና እንጠንቀቅ፡፡