>

በመተከል፣ በወለጋ፣ በሰገን አካባቢ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት አጥብቀን እናወግዛለን!!!  (ከባልደራስ-መኢአድ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ)

በመተከል፣ በወለጋ፣ በሰገን አካባቢ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት አጥብቀን እናወግዛለን!!! 

ከባልደራስ-መኢአድ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

 

በዓለም ላይ ማንነትን መሠረት አድርጎ የሚፈፀም ግፍ እየጠፋ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት እየተገደሉ ነው፡፡ ግልፅ የሆነ የዘር ፍጅት ወንጀል እየተፈፀመ ነው፡፡ በታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ከ207 በላይ የአማራ ተወላጆች በመተከል አካባቢ ተገድለዋል፡፡ ባልደራስ-መኢአድ የተሰማውን መሪር ሐዘን ይገልፃል፡፡ ከዚህ በፊት በቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢ በተደጋጋሚ አንድን ዘር መሠረት ያደረገ ተመሳሳይ ግድያ መፈፀሙን አለም ያውቃል፡፡ የአማራ ተወላጆች በወለጋ፣ በጉራፈርዳ፣ በቤንሻንጉልና በሌሎች አካባቢዎች በማንነታቸው ብቻ ለዘር ፍጅት እየተዳረጉ ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ሌላው የዘር ፍጅት የሚካሄድበት አካባቢ ደግሞ በሰገን ሕዝብ አካባቢ ነው፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ የጉማይዴ ነዋሪዎችና የኩስሜ ብሔረሰብ አባላት አካባቢ ወገኖቻችንን እያለቁ ነው፡፡ የኩስሜ ብሔረሰብ በቁጥሩ አነስተኛ ሲሆን 40‚000 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ያሉት ነው፡፡ የኩስሜ ዜጎች በአነሷቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ የንፁህ ውሃ አገልግሎት ጥያቄዎች ለእልቂት ተዳርገዋል፡፡የኩስሜ ብሔረሰብ አስተዳደር ካሉት 9 አስተዳደር ቀጣናዎች መካከል በ7ቱ ቀጣናዎች ከፍተኛ የሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የደረሰ ሲሆን በተለይ ቀጣና 1 ሙሉ በሙሉ ወድሞ የኩስሜ ብሔር አባላት ተሰደዋል፡፡ በተመሳሳይ በአሁን ሰዓት በምስራቅ ወለጋ ጌዳ ወረዳ፣በምዕራብ ወለጋ ሳምቦ ወረዳ፣ በሆሮ-ጉድሩ ዞን እየተፈፀመ ያለው ታሪክ ይቅር የማይለው የግፍ ጭፍጨፋ ሊቆም አልቻም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆንና ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሲፈፀም ፌደራል መንግስትም ሆነ የክልሉ መንግስት ትኩረት አልሰጡትም፡፡ ዛሬ በኩስሜ ብሔር አካባቢ የትምህርት ተቋማት፣ ጤና ጥበቃ ተቋማት፣ ግብርና ወዘተ የመሳሰሉት ተቋማት ፈርሰዋል ሕዝቡ በስደትና በስጋት ቁም ስቅሉን እያየ ነው፡፡ በዚሁ በሰገን ሕዝቦች አካባቢ የጉማይዴ ሕዝብ የማያባራ የዘር ፍጅት ወንጀል እየተፈፀመበት ነው፡፡ ዛሬ ጉማይዴ ውስጥ በሰላም ውሎ በሰላም መግባት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በ10000 ሺህ የሚቆጠሩ የጉማይዴ ነዋሪዎች ተሰደዋል፡፡ ይህ ሕዝብ በማንነቱ ጥቃት ሲደርስበት የሚከላከልለት ከማጣቱም በላይ በተሰደደባቸው አካባቢዎች የዕለት ደራሽ እርዳታ ማግኘትም አልቻለም፡፡ መንግስት ለዚህ ሕዝብ ሰላምና ፀጥታ መከታ መሆን አለመቻሉም ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን የጎዳው በጥቃቱ የመንግስት ባለሥልጣናት ቀጥተኛ እጅ መኖሩ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ የሚደርስበት ግፍ የማያባራው ጥቃቱ በመንግስት የተደራጀ ኃይል እየተፈፀመ በመሆኑ ነው፡፡
በሀገራችን ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ማንነት ተኮር የሆነ የዘር ፍጅት ሕዝባችን ለእልቂት ከመዳረጉም በላይ በየጊዜው የሚያልቁ ወገኖቻችን አስከሬናቸው እንኳን በወጉ አያርፍም፡፡ በታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም በመተከል የተጨፈጨፉት ከ207 በላይ ወገኖቻችንን መንግስት በግሪደር አንድ ጉድጓድ ውስጥ እንዲቀበሩ አድርጓል፡፡ በዓለም አቀፍ የዘር ፍጅት ጥናት ውስጥ የዘር ፍጅት አንዱ መገለጫ በጅምላ መግደልና በጅምላ መቅበር ነው፡፡ በጅምላ መቅበር አንዱ የዘር ፍጅት የመደምደሚያው ወንጀል ነው፡፡ መንግስት ይህንን ወንጀል በገሀድ ፈፅሞታል፡፡ ይህ ጉዳይ የሀገራችንን ባህል፣ ኃይማኖትና የቀብር ሥርዓት የጣሰ እና ያላገጠ ሲሆን ሥነ-ልቦናቸውንም ጎድቷል፡፡ በመሆኑም መንግስት ሊጠየቅበት ይገባል፡፡ በአጠቃላይ በሀገራችን ውስጥ የዘር ፍጅት ወንጀል በየጊዜው እየተፈመ ሲሆን ፌደራል መንግስትም ሆነ የክልል መንግስት ይህንን ወንጀል ለመመከት አልቻሉም ተጠያቂም ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ የዘር ፍጅት ወንጀል ክስ ወቅት በየትም ሀገር የዘር ፍጅት ሲፈፀም ተጠያቂው ራሱ መንግስት ነው፡፡
በመሆኑም ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚከተሉትን አስቸኳይ ጥሪዎች እናቀርባለን፡- 1ኛ. የዘር ፍጅት ምልክቶች የሚታዩባቸው አካባቢዎች በፍጥነት ሠራዊታችን በቂ ኃይል እንዲያሰፍር፣ 2ኛ. መላው የሀገራችን ሕዝብ የዘር ፍጅትን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነቅቶና ተግቶ እንዲቃወም፣ 3ኛ. ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን ክፉ ወንጀል በመቃወም በአንድነት እንዲቆም 4ኛ. በሀገር ውስጥና በውጪ ያላችሁ የኢትዮጵያ ምሁራን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት ወንጀል ወደ ሕግ እንድታቀርቡ፣ 5ኛ. በኢትዮጵያ ውስጥ የምትገኙ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ሰብዓዊ መብት ተቋማት በሙሉ ይህንን ወንጀል እንድትቃወሙ እና ወንጀል የፈፀሙት ኃይሎች ወደ ሕግ እንዲቀርቡ እንድትታገሉ፣ 6ኛ. የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ወዳጅ ሀገራት በሙሉ የዘር ፍጅት ወንጀልን እንድታወግዙና በመንግስት ላይ ተገቢውን የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ በማሳደር ወንጀሉ እንዲቆም እና ወንጀለኞች ለፍትህ እንዲቀርቡ እንድታደርጉ፣ 7ኛ. መላው የሀገራችን ሕዝብ በዘር፣ በኃይማኖት፣ በብሔር ሳንከፋፈል ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ፀንተን እንድንቆምና የዘር ፍጅት እንድንከላከልና የተባበረችውን ኢትዮጵያችንን በጋራ እንድንገነባ በትህትና እንጠይቃለን፡፡
የተባበረችውን ኢትዮጵያን እንገነባለን !
“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር”!!
ታህሳስ 20 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ
Filed in: Amharic