>

የጋፋትን አፈር አቅልጦ ቀጥቅጦ መድፍ ያሰራው የመይሳውና የዙፊል ወንዝ...!!! (ሔቨን ዮሐንስ)

የጋፋትን አፈር አቅልጦ ቀጥቅጦ መድፍ ያሰራው የመይሳውና የዙፊል ወንዝ…!!!
ሔቨን ዮሐንስ
ይለያል መይሳው ካሳ
የቋራው ፀሀይ የኢትዮጵያ አንበሳ
ስለ መይሳው ካሳ (አጤ ቴዎድሮስ) ብዙ ተብሏል፤ እኔም ብዙ ለማውራት ሳይሆን ዛሬ ላይ ሆኘ ትናንትን በሃሳብ መነፀር ሳየው የአጤ ቴዎድሮስ ድካም ውልብ ይልብኛል እጅግ ያሳዝነኛል! የሚያሳዝነኝ ያለ ዘመኑ ብቅ ያለ ብሩህ አዕምሮ ያለው፣ ስልጣኔን የሚወድ፣ ለቴክኖሎጂ ትልቅ ቦታ የነበረው ስለነበር ህዝቡን እንደ ልቡ ፍላጎት ለማስተካከል ሲል ብዙ ውጣ ውረድን ሲቃትት እንደነበር ይሰማኛል፤ እናም በጣሙን ያሳዝነኛል!
እኛ እንደሆን ዳተኞች ነን ቶሎ አንረዳም በዚህም የተነሳ መይሳው ካሳ አልረዳው ሲሉ ይቀጣቸው ነበር! ንጉስ ሆኖ አንድ ሰው ቀጥቶ ገድሎ ለሞተው ሰው የሚያለቅስ እና የሚያዝን ደግሞ የሚያስቀብር ታላቅ ብቸኛ ንጉስ ነው! አጤ ቴዎድሮስ ትልቅ ንጉስ ለአገርና ለህዝብ አሳቢ መሆኑን ማወቅ የሚቻለው በአለም ላይ የማይደረግ መሪ የመፍጠር ስራ፣ ተጠኪውን ምኒልክን እንደት እንዳሳደገው ማወቅ ብቻ በቂ ነው። ይህንን መሳጭ ታሪክ እመለስበታለሁ
ዛሬ ግን አጤ ቴዎድሮስ ለእንግሊዙ ጀነራል የፃፋትን መልክት ላጋራችሁ ፈለግሁ። ይህ የአጤ ቴዎድሮስ ደብዳቤ እኔ ስመነዝረው በጣም ያስለቅሰኛል! እስኪ እናንተም በገባችሁ ልክ ተረዱት
“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ በሦስትነት በአንድነቱ በክርስቶስ ያመነው ካሳ መቼም ያገሬ ሰዎች በእግዚአብሔር ኃይል እኔ ካልወረድኩላችሁ ሽሽታችሁን አትተውም። ክርስቲያኑን ሁሉ ጉልበት አለኝ መስሎኝ ካረመኔ አገር አግብቼው ወንድ የሌላት ቆንጆ አለች፣ ወንድ የነበራት ቆንጆ ነበረች፣ ትላንትናም የሞተባት ትኖራለች ሽማግሌ ልጅ የሌለው ባልቴት ልጅ የሌላት፣ እኔ የምጦራቸው ብዙ በከተማየ አሉ። እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ፍቀዷቸው። ያረመኔ አገር ነውና ያገሬ ሰው ገብር ስርዓት ግባ ብየው ብለው እንቢ ብሎ ተጣላኝ። እናንተ ግን በስርዓት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ። እኔን ወደውኝ የተከተሉኝ ሰዎች አንድ እርሳስ ፈርተው ጥለውኝ ሸሹ፣ ልትቀጧቸው ከሮጡት ሰዎች ጋር አልነበርኩም፣ ጌታ ነኝ መስሎኝ ባልሰላ መድፍ ስታገል ውየ ነው። ያገሬ ሰው የፈረንጅ ሀይማኖት ይዟል እያለ አስሩን ምክንያት የሰጠኝ ነበር። እኔ ከከፋሁበት እግዚአብሔር መልካም ይስጠው። እንደወደደ ይሁን እግዚአብሔር ቢሰጠኝ ሁሉን ልገዛ ሀሳብ ነበረኝ። እግዚአብሔር ቢነሳኝ ልሞት ሀሳቤ ይህ ነበር። ከተወለድሁም እስከ አሁን ወንድ እጄን ጨብጦት አያውቅም ነበር፤ ሰዎች ሲሸሹኝ ተነስቼ ማረጋጋት ልማድ ነበረኝ፣ ጨለማ ከለከለኝ። እንደ እኔ አያድርጋችሁ። እንኳንስ የሀበሻ ጠላት የኢየሩሳሌም ዘምቼ ቱርኮችን አስለቅቃለሁ መስሎኝ ነበር። ወንድ ያቀፈ ወንድ ተመልሶ አይታቀፍም። “
ይህ ደብዳቤ ምንኛ ልብ እንደሚነኳ በእግዚአብሔር! የአገሬ ሰው ገብር ስርዓት ግባ ብየ ብለው ተጣላኝ። እናንተ በሥርዓት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ።” የምትለውማ ውስጠ ወይራ ናት፤ ዛሬም ድረስ የምታገለግል ይመስለኛል። ልብ አድርጉ መይሳው ያለው ህዝቤ ቢሰለጥንልኝ፣ አንድ ቢሆንልኝ እና በሥርዓት ገብሮልኝ ስለ አገሩ ቢያስብልኝ አታሸንፉኝም ነበር። አሁንም ያሸነፋችሁኝ እናንተ የሰለጠ እና ታዛዥ አጋዥ ህዝብ ስላላችሁ ነው። ብሎ የፈለጉትን እሱን ይዞ የኢትዮጵያ ህዝብ አንገት ማስደፋት ነበርና ህልማቸው እውን እንዳይሆን ሞቶ ጠበቃቸው! ስለክብር መሞትን አሳያቸው! ያኔ ለመይሳው ካሳ ህልም ህዝብ ከረዳው በላይ አንድ ተፈጥሮ ውለታ የዋለለት አለ? እሱ ማነው ወደሚለው ልውሰዳችሁ
ዙፊል የወንዝ ስም ነው! በፋርጣ አውራጃ ሕሩይ ጊዮርጊስን፣ ጃንሜዳን እና የጋፋት ጉብታን አሳብሮ በጋ ከክረምት ይፈሳል። የአባ ታጠቅ (የአጤ ቴዎድሮስ) መድፍ የሴባስቶፓል ልደት ያለ ዙፊል እውን አይሆንም ነበር። የጋፋትን አፈር አቅልጦ ቀጥቅጦና ቅርጽ ሰጥቶ የመይሳውን ተስፋ ለማለምለም በእርግጥም የዙፊል ወንዝ አስፈልጓል። በነገራችን ላይ በ1987ዓ/ም በዙፊል ስም መጽሔት ይታተም ነበር። መጠሪያ ስሙንም የሰየሙበት ምክንያት የመይሳው ካሳ ህልም መሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ ያባረከተ ወንዝ ስለሆነ ለውለታው ሲሉ እንደሰየሙትም ተናግረዋል!
ወገኔ ዛሬም መነሻችን ጋርዮሽ ይሁን! ለክብር መኖር እንውደድ! ለክብራቸው የኖሩ ልጆች ነንና
Filed in: Amharic