>
5:21 pm - Monday July 21, 7777

ዘጋቢ ፊልሙ እና አውዳሚው ትርክት... እስከመቼ ?  (ቹቹ አለባቸው)

ዘጋቢ ፊልሙ እና አውዳሚው ትርክት… እስከመቼ ? 

ቹቹ አለባቸው

 

እንደመግቢያ፦ ተጠየቅ
*
በትላንትናው ምሽት “ሞት በማንነት_ማይካድራ” በሚል ርዕስ በፋና ቲቪ የተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ለወዳጅም ሆነ ለጠላት አንድ መራር እውነት አስተላልፏል። አማራነት ወንጀል ሆኖ የአማራ ልጆች በማንነታቸው ብቻ ‘ይሙት በቃ’ ፖለቲካዊ ብያኔ ተፈርዶባቸው በየአቅጣጫው በጅምላ ይገደሉ እንደነበር ዘጋቢ ፊልሙ ላይ ተመልክቷል። ለሦስት አስርት ዓመታት አማራ በተለያዩ አካባቢዎች ዘሩን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ሲፈጸሙበት ጥቃቱ መዋቅራዊና በፖሊሲ የተደገፈ ነበር፡፡
በበኩሌ  በትላንቱ ዘጋቢ ፊልም ይዘት ላይ ብደሰትም፤ ግን ደግሞ አቀራረቡ ላይ ጥያቄ አለኝ፡፡ ለአማራው በደል ትህነግ መነሻ ቢሆንም የእርሱን አስተሳሰብ የተሸከሙት እነ ኦነግ ሸኔና መሰሎቹ ዛሬም አማራውን ማረድና ማሳደድ ቀጥለውበታል። ከዚህ ጸረ-አማራ አመለካከት የተጣቡ በመንግሥት መዋቅሩ ላይ የሚገኙ አንዳንድ አመራሮችም አማራ ሲቀነስ የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት አደገኛ ዝንባሌ እንዳላቸው እየተመለከትን ነው። ዛሬም የአማራው የጅምላ ሞት ከትራፊክ አደጋ እንኳ ያነሰ ትኩረት የማይሰጠው ስለመሆኑ በኦሮሚያ የወለጋ ዞኖችና በመተከል የሚሰሙ ዕለታዊ መርዶዎች አስረጅ ምሳሌ ናቸው።
ዛሬ ላይ ደርሶ አማራው በማንነቱ ዘሩ ተለይቶ ሲጠቃ መኖሩን በመንግስት (ፋናን በመሳሰሉት) ሚዲያዎች ሳይቀር ማመን ያስፈለገበት ምክንያት ምን ይሆን? ስል ራሴን ጠይቄያለሁ፡፡ ለአማራው የዘመናት መታረድ ብቸኛ ተጠያቂስ ትህነግ ብቻ ነው? ዘጋቢ ፊልሙ ማይካድራን ዐቢይ ማሳያ ያደረገ ቢሆንም የበደኖ፣ ወተር፣ አርባ ጉጉ፣ ጉራፈርዳ፣ ጉሊሶ፣ መተከል እልቂቶች ዋቢ ሆነው ቀርበዋልና ሌሎች የትህነግ አስተሳሰብ ተሸካሚዎችስ ስለምን ተጠያቂ አልተደረጉም?
የፋሽዝም ወላጅና ውላጆችን መነጠል አይቻልም!
**
በትሕነግ ፋሽታዊ ግብር የጅምላ ፍጅት የተፈፀመበትን የአማራን በደል ለሕዝብ ማድረስ አንድ ቁምነገር ሆኖ፤ ተጠያቂነቱን ለአንድ ቡድን ማሸከም ትክክል አይደለም። ትሕነግ የፋሽዝም ወላጅ አባት ቢሆንም፤ ታዳጊዎቹ ኦነግ፣ ቤጉነንና መሰሎቻቸው የፋሽዝም ውርስ አስቀጣዮቹ ናቸው። በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ግን ትሕነግ ብቻ ነበር ተጠያቂ የተደረገው ውላጆቹ ተዘንግተዋል። ይሁንና ዘጋቢ ፊልሙ ላይ የግልገል ፋሽቶች ስም አልተካተተም ማለት በሕዝብ ውስጥ ያለውን መራር እውነት መሻር ማለት አይደለም። ሕዝብ ገጀራ አቀባዮቹንም ሆነ አራጆቹን ጠንቅቆ ያውቃል። ዛሬ የፋሽስም ወላጅ አባታቸው ትህነግ በመንግሥታዊ ሚዲያዎች በአደባባይ ተጠያቂ እንደሆነው ሁሉ ውላጆቹ ግልገል ፋሽስቶችም  በታሪክ ፊት መጠየቃቸው አይቀርም።
የዘጋቢ ፊልሙ ጉድለት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የአማራ ህዝብ ላለፉት 30 ዓመታት በማንነቱ ምክንያት እየተጠቃ ነው በማለት ሲቀርቡ የኖሩትን አቤቱታዎች እንኳን መደመጥ መብት ተነፍጎት በኖረበት፤ እውነታው ተዳፍኖ በተቃራኒው ሲዘገብ በኖረበት ሚዲያ በደሉ መደመጡ ይበል የሚያሰኝ ነው። ቀሪውን በትግላችን እውን እናደርገዋለን፡፡
የትርክቱ ወራሾችና ትርክቱ!
***
በፋና ቲቪ እንደቀረበው በአማራ ህዝብ ላይ ማንነትነ መሰረት ያደረገ ጥቃት ሲደርስበት የመክረሙ መነሻ ትህነግ ባሰራጨው የተሳሳተ ትርክት ነው፡፡ ፋና ለዚህ አባባሉ አስረጅ አድርጎ ያቀረበው የትህነግን ማኒፌስቶ እና ባለፉት 30 አመታ ምድር ላይ የተከሰተውን እውነታ በማመሳከር ነው፡፡ በዚህ በኩል ምንም አነጋገሪ ነገር ያለው አልመሰለኝም፡፡ ትህነግ በማኒፌስቶዋ በግልጽ እንዳስቀመጠችው “አማራ ቀንደኛ ጠላት፤ የሁሉም ብሄርና ብሄረሰቦች ጨቋኝ” አድርጋ ነው፡፡ ስለሆነም “ማህበራዊ እረፍት የማይገባው ማህበረሰብ ነው” ብላ በማኒፌስቶ ደረጃ ተንቀሳቅሳለች ፤ ተሳክቶላታልም፡፡
እውነት ነው አማራ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በዚሁ የትህነግ የተዛባ ትርክት “ፍሬ” አፍርቶ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች እረፍት ያጣ ማህበረሰብ ሁኗል፡፡ ትርክቱ የአማራ ሕዝብ በሀገረ-መንግሥቱ ምስረታ ላይ የነበረውን የመሪነት ሚና በአሉታዊ ጎኑ በመሳል ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በጋራ ባቆማት ኢትዮጵያ ባይተዋር ሆኖ እንዲኖር የመነጠያና የመምቻ በትር ሆኗል። ከትህነግ ማኒፌስቶ በሚቀዳው ፍረጃ አማራውን ‹ነፍጠኛ›፣ ‹ትምክህተኛ›፣ ‹ጨቋኝ›፣ ‹ተስፋፊ›፣ ‹መጤ›፣ ‹ወራሪ›፣ ‹ቅኝ-ገዢ›፣ ‹የድሮ ሥርዐት ናፋቂ›… በሚሉ ፍረጃዎች አንገቱን ለማስደፋት በመዋቅር ደረጃ ተሰርቶበታል፡፡ የትርክቱ ማጠንጠኛም ይሄው ነው፤ አጋር አልባ በማስቀረት ነጥሎ መምታት!!
እውነት ነው ትህነግ ላለፉት 30 አመታት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በአማራ ህዝብ ላይ ለደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል ቀዳሚ ተጠያቂ ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ከዚህም በላይ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይሄውም ከትህነግ በተጨማሪ፤ በአማራ ህዝብ ላይ ለደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል አስተዋጽኦ ያደረጉ፤ በቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረጉ ሌሎች ድርጅቶች የሉም ወይ ?የሚለው ነገር በደንብ መፈተሸ አለበት። ለአብነት፦  የኢህዴን መስራች ታጋዮች ይሄንኑ  የተሳሳተ የትህነግን ትርክት ተቀብለው  አስፈጽመዋል፤ ዛሬ ላይ ግን ይቅርታ እንኳን ሲጠይቁ አልሰማንም፡፡ እንዲሁም ሌሎች ፅንፈኛ ድርጅቶች (ኦነግና መሰል ነጻ አውጭ ድርጅቶች) የአማራን ህዝብ በተመለከተ የሚከተሉት ትርክት ከትህነግ የተለየ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለአማራ ህዝብ እረፍት ማጣት የነዚህና መሰል አካላት ተሳትፎም መታየት አለበት፡፡ ምንም እንኳን ትህነግ ስለ አማራ የዘራው መርዝ ባንዴ በብርሀን ፍጥነት የሚከስምና በዚሁ ፍጥነት የአማራ ህዝብም ማህበራዊ እረፍት ያገኛል ብለን ባንጠብቅም፤ ነገሩን ሁሉ ከትህነግ የተዛባ ትርክት ጋር ብቻ እያያዙ ለመጓዝ ማሰብ ግን የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ላይ ትህነግ  የለችም፤ ስለሆነም ካሁን በኃላ በአማራ ህዝብ ላይ ለሚደርስ ጥቃት ዋነኛ ተጠያቂ ሌሎች (የአስተሳሰቡ ተሸካሚዎች)ን ማድረግ የግድ ይላል፡፡
የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ መልዕክት፤ በአማራ ህዝብ ላይ እስከዛሬ ለደረሰው፤ ዛሬም እየደረሰ ላለውና ለወደፊቱም ለሚደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል፤ በትህነግ ስም የሌሎች ወገኖች ወንጀል ተድበስብሶ ሊታለፍ አይገባም የሚል ነው፡፡ ትህነግ የጁን አግኝቷል!! ቀሪው ተረፈ ኃይሉም በወታደራዊ ኦፕሬሽኖች  ይደመሰሳል፡፡ የትህነግ አስኳል (Core Group) አከርካሪው በተመታበት ሁኔታ የትርክቱ ወራሾች በአማራ ህዝብ ላይ ዛሬም በደል ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። እናም በደል ፈጻሚዎቹን ለይቶ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ለነገ ሊባል የማይገባ የዛሬ የቤት ስራ ነው፤ ተጠያቂነትን ማሻገርም ሆነ ማድበስበስ አዙሪቱን ከማስቀጠል ውጭ አንዳች ፖለቲካዊ ትርፍ የለውም!
ለሁሉም ከፋና ቲቪ ዘጋቢ ፊልም የወደድኩት ዋና መልዕክት “ላለፉት 30 አመታ በአማራ ህዝብ ላይ የዘር መጥፋት ወንጀል ተፈፅሞበታል” የሚለውን ነው። ለዚህ ወንጀል ተጠያቂው ትህነግ ነው የሚለውለውን ገዥ ሀሳብ የምቀበለው ቢሆንም፤  ከትህነግ ትይዩ የጸረ-አማራ ትርክቱ ወራሾች እንደየሚናቸው ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል።
ፋና ቲቪ የዘለላቸው አንዳንድ እውነታዎች ቢኖሩም ቁልፉን ግን  አግኝቶታል፡፡ ይሄውም የትህነግ የተዛባ ትርክት የአማራን ህዝብ ከባድ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ አሁን ጥያቄው ብልፅግና እንደ ድርጅት፤ ዶ/ር ዐቢይ ደግሞ እንደ  ፓርቲና መንግስት መሪነታቸው፤ ይሄንን የተዛባና ፀረ-አማራ ትርክት ለመቀየር ተዘጋጅተዋል ወይ? የሚለው ነው።  በትህነግ መሪነት በውላጆቹ አስፈጻሚነት በፖሊሲ ደረጃ ሲሰራበት የኖረውን ፀረ-አማራ ትርክት ለማረም ጥረቱ ተጀምሯል ወይ? ስንል እንጠይቃለን!!
ከዚህም በላይ የወቅቱ የአማራ ብልፅግና መሪዎች፤ አማራን ረፍት የነሳውን ትርክት በተመለከተ የኢህዴን/ብአዴን ስህተት እንዳይደገም ነገሮችን ሁሉ በጥንቃቄ እየተመለከቷቸው ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንጠይቃለን። የከረመውን ፀረ-አማራ ትርክት ለማረም፤ ስራዎች በብቃት እየተሰሩ ነው ወይ?  የሚሉት ተጠይቆች ለከፍተኛ አመራሩ እየሰነዘርን፤
ከክልሉ ውጭ ያለውና በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠረው አማራ የፖለቲካ ውክልና አልቦ በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት እንዲቀጥል ያደረገው ትርክት ሊታረም ይገባል። ‘የመጤ’ ፣ ‘ሰፋሪ’፣ ‘ተስፋፊ’ ፣… የሚሉ ፍረጃዎች ኢትዮጵያን ይበትኗት ካልሆነ ለአማራው ብቻ የመከራ ምንጭ ሆነው ሊቀጥሉ አይችሉም። ኢትዮጵያን በአብሮነት ለማስቀጠል ነባሩና አውዳሚው ትርክት በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን በሚያሳድግ አዲስ ትርክት ሊቀየር ይገባል። ይህ ነው የወቅቱን ወጀብ መሻገሪያ ብቸኛው መንገድ!
በድኀረ-ትሕነግ የቆምንበት ፈተና እንደኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ላሉ አንዳንድ የብልጽግና አመራሮች መልዕክት ለማስተላለፍ የግድ ብሎናል። ኢትዮጵያን ‘አማራ ሲቀነስ’ በሆነ ስሌት መምራትም ሆነ መገንባት እንደማይቻል ሊያውቁት ይገባል።
በመሠረቱ ከሆነ የሕዝቦች አብሮነትና ሀገራዊ አንድነት የሚረጋገጠው የአንዱ ጉዳት ለሌላው ህመም ሆኖ ሲሰማው፤ የአንዱ ልማት ለሌላው ፀጋው ሲሆን ነው። እንደሀገር የጋራ ዕጣ ፈንታ እንጅ የተናጠል መዳረሻ የለንም! ስለሆነም የሚያኗኑር ትርክት ማበጀት ለነገ የማይባል የቤት ስራችን ሊሆን ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ሊቀድም ይገባል።
በመጨረሻም፤
አኔ እንደ አንድ አማራ፤ የአማራ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚረጋገጠው በህብረ-ብሄራዊት ኢትዮጵያ ጥላ ስር ነው ብለው ከሚያምኑት ሰዎቸ መካል አንዱ ነኝ፡፡ ስለሆነም የአማራ ህዝብ በብልጽግና ዘመን ከአጭር ጊዜ አኳያ ቢያንስ ማንነቱን መሰረት አድርጎ የሚደረስበት ጥቃት ሊያስቆምለት ይገባል፡፡ በትህነግ ዘመን የከረመው ጥቃት አይነት በብልፅግና ዘመንም ካልቆመ፤ ነገሩ ሁሉ “እነዘጭ እምቦጭ” ከመሆን አያልፍም፡፡ በዝህች ሀገር የተተከለው አውዳሚ ትርክት የሚያጠፋፋ እንጅ የሚያኗኑር አይደለም። ያለፈው የጥፋት ዘመን አዙሪቱ እንዲቆም ኢትዮጵያም እንደ ሀገር እንድትቀጥል  አዎንታዊና ወንድማማችነትን የሚያሳድግ ትርክት ከሌሎች ጋር በመመካከር ማነበሩ የአማራ ብልፅግና አመራር ግንባር ቀደም ሚና ሊሆን ይገባል።
አንድ ጠንካራ የሆነ የብልፅግና ማህበረሰብ ለመገንባት፤ ከሁሉ በፊት የከረመውን ፀረ-አማራ ትረክት ስሁትነት ላይ መግባበትና ለማስተካከል ቁርጠኛ ሆኖ መገኘት የብልፅግና አመራርና አባላት ሊወስኑበት የሚገባ ቅድመ ሁኔታ ነው።
የተዛባውን ትርክት በሀቀኛ ትርክት መተካት የነገ ሳይሆን የዛሬ የቤት ስራ ነው!
Filed in: Amharic