>

አልነጃሽ መስጅድ ጥቃትን በተመለከተ ከአብን የተሰጠ መግለጫ

አልነጃሽ መስጅድ ጥቃትን በተመለከተ ከአብን የተሰጠ መግለጫ


የአገራችንም ይሁን የዓለማችን የእምነትና ስልጣኔ ግንባር ቀደም ምልክቶች ከሆኑት መካከል የኢትዬጵያዊው አልነጃሽ መስጅድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑት ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል።
አልነጃሽ መስጅድ የሙስሊሙ ኢትዬጵያዊ ወገናችን፣ አጠቃላይ የኢትዬጵያ ሕዝብና የመላው ዓለም የታሪክ አካል ነው። በኢስላም ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሂጅራ የተደረገበት እስከመባል የደረሰ ጉልህ ቦታ ያለው የታሪክና የእምነት አካል ነው።
ትህነግ በቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት አገራችን በሕይወት፣ ንብረትና ቅርስ ረገድ ዘግናኝ ጥፋቶችን እንዳስተናገደች ይታወቃል። ትህነግ ለታሪክና እምነት ዋጋ የማይሰጥ ድርጅት መሆኑ ከውልደቱ ጀምሮ የሚታወቅ ባህሪው ነው። የእምነት ተቋማትን ለማጥቃትም ይሁን በምሽግነት ለመጠቀም የማያመነታ ኃይል እንደሆነ እንገነዘባለን። ነገር ግን አልነጃሽ ላይ የተፈፀመው ጉዳይ ከጥቅል ፖለቲካ ግምት ያለፈ እንደሆነ አብን ይገነዘባል።
ስለሆነም አልነጃሽ መስጅድ ላይ የደረሰው ጥቃት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በገለልተኛ መልኩ በጥልቀት መመርመር ያለበት እንደሆነ ድርጅታችን ያምናል። ሕዝበ ሙስሊሙ እንዲሁም መላው የኢትዬጵያ ሕዝብ በመስጅዱና መቃብር ቦታዎቹ ላይ የደረሰውን ጥቃት፣ መጠኑንና የፈፀመውን አካል በግልፅ ማወቅ እንደሚፈልግ እንረዳለን። የተዘረፉ ቅርሶች እንዳሉ እየተነገረ ያለውን ጉዳይም በአግባቡ መመርመርና ማጣራት ያስፈልጋል።
በተገቢው ሁኔታ ከተጣራም በኋላ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እየጠየቅን ጎንለጎን አፋጣኝ የመልሶ ግንባታና የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድ ለመንግስትና ለመላው የኢትዬጵያ ሕዝብ ለማሳሰብ እንወዳለን።
አልነጃሽ የመላ የሀገራችን ህዝብ ቅርስ መሆኑ እየታወቀ የአንድ ወገን ጉዳይ ብቻ እንደሆነ በማድረግ የተለመደ ሆኖም ያልተገባ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ከማንም ወገን የሚደረግ እንቅስቃሴ ተገቢነት የሌለውና በአፋጣኝ ሊቆም እንደሚገባ ለማሳሰብ እንወዳለን።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በአልነጃሽ መስጅድ ላይ በደረሰው ጥቃት እጅጉን ማዘኑን እየገለፀ በተለይ ለሕዝበ ሙስሊሙ ወገናችን አጋርነቱን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆኑን ለመግለፅ ይወዳል።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
ታኅሣሥ 24 ቀን 2013 ዓ.ም
ሸዋ ፥ አዲስ አበባ ፥ ኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic