>

ጽንፍ የረገጠ ነውጠኝነትና ሰብዓዊ ደህንነት በአፍሪካ - ክፍል ሁለት (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

ጽንፍ የረገጠ ነውጠኝነትና ሰብዓዊ ደህንነት በአፍሪካ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

Tilahungesses@gmail.com


ክፍል ሁለት

ሰለፊዝም ( ውሃቢዝም) እና ግጭቶች በአፍሪካ  (Salafism (Wahhabism) and Conflicts in Africa  )

እንደ የአፍሪካ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኞች ጥናት ውጤት ከሆነ፣ ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት ለተከሰቱ ግጭቶች ወይም አፍሪካ ለገጠማት አስቸጋሪ ሁኔታዎች መሰረታዊ ምንጩ ( ምክንያቱ) አክራሪዎች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የአክራሪዎች ጥቃት በአለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋት የጀመረው ከ2011 ዱ ( እ.ኤ.አ.) የኒውዮርክ ከተማ ጥቃት እና ከአረቡ የጸደይ አብዮት በኋላ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደ አንዳንድ የአፍሪካ የፖለቲካ አዋቂዎች ጥናትና ምርምር ውጤት ከሆነ በአፍሪካም ሆነ በአረቡ አለም የሚነቀሳቀሱት እና የታወቁት አክራሪ ቡድኖች ( ድርጅቶች) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከውሃቢዝም ( ሰለፊዝም) ፍልስፍና ተከታይ ከሆኑ ቡድኖች ወይም መንግስታት ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በአፍሪካ የግጭት መንስኤና መፍትሔዎች ላይ ጥልቅ ጥናት ያደረጉት ዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ካቀረቡት ጽሁፍ ላይ እጠቅሳለሁ፡፡

There are no major extremist organizations operating in the Arab World  or in Africa that do not have direct or indirect support and inspiration from the  

Wahhabi /Salafist government of Saudi Arabia ( Dr.Dawit W Giorgis )

የሰለፊዝምን አስተምህሮ ከውሃቢዝም አስተምሮ መለየት አስቸጋሪ እንደሆነ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ በአጭሩ ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ በተለይም የአረቡ ባህረ ሰላጤ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ ፣ ቅኝ ገዢ እንግሊዝ ከአብዱል ወሃብ Abdul Wahhab  እና ከሳኡዲ ቤተሰቦች ( the Saudi family ) ጋር ባደረገችው ስምምነት መሰረት ሳኡዲአረቢያ ተብላ የምትታወቅ ሀገር መመስረታቸውን የቅኝ ግዛት ታሪክ ያስተምረናል፡፡ የአረቡ ባህረ ሰላጤ በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ስር ስለነበር፣ እንዲሁም ታላቋ ብሪታኒያ ከአብዱል ወሃብ እና ከሰኡዲ ቤተሰቦች ጋር በደረሰችበት ስምምነት መሰረት ይህቺ ሀገር እውን ለመሆን ችላለች፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ሰላፊ እና ወሃቢ ቃላቶች እየተለዋወጡ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ብዙ ሰዎች ሁለቱን ቃላቶች ለመለየት ይቸገራሉ፡፡ ግራ ይገባቸዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ሁለቱን ቃላት አንድ አይነት ትርጉም አላቸው ብለው ያምናሉ፡፡ በአጭሩ ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ውሃቢስ ራሳቸውን እንደ ሰላፊስ ይቆጥራሉ፡፡ እንደ አንዳንድ አዋቂዎች ጥናት ከሆነ ወሃቢስ ሰላፊስ ናቸው፡፡ሆኖም ግን ሰላፊሶች ራሳቸውን እንደ ወሃቢስ አይቆጥሩም፡፡ እንድ አዋቂዎች ጥናት ከሆነ ወሃቢስ እራሳቸውን እንደ ሰላፊስ አድርገው መቁጠር የጀመሩት በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡

በነገራችን ላይ ወሃቢዝም ለሳኡዲ ንጉሳዊ አገዛዝ እንደ ማእዘን የሚቆጠር ነው፡፡ ይህ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በትምህርት ቤቶች፣ ዩንቨርስቲዎች፣ መስጂዶች፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ በአለም አቀፍ ድርጅቶች፣ እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ያለው ተጽእኖ እጅጉን ሰፊ ነው፡፡

ሳኡዲአረቢያ የውሃቢዝምን አስተምህሮ ከሀገሯ ወደ ውጪው አለም መስበክ የጀመረችው በግብጽ ምድር ነበር፡፡ የግብጽ መሪ የነበሩት ናስር የጸረ ኢምፔሪያሊስት አቋም አራማጅ ስለነበሩ ሳኡዲ በሙስሊም አለም የሃይማኖት ግስጋሴ እንድታደረግ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላት ነበር፡፡

በነገራችን ላይ የውሃቢ ዋነኛ ስትራቴጂ የነበረው የቀድሞዋን ሶቬዬት ህብረት ለመዋጋት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል በአፍጋኒስታን የሙጃሂዲን እንቅስቃሴ ጉልህ ማሳያ እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ሙጃሂዲን ሃይማኖታዊ ንቅናቄ እንደነበር የሚሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአረቡ አለም የቀድሞዋን ሶቪዬት እንቅስቃሴ ለመግታት በሚል ስሌት ምእራባውያን ሃይማኖታዊ ተልእኮ ላላቸው ቡድኖች ወታደራዊ ስልጠና ይሰጡ እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የምእራባውያን ወታደራዊ ስልጠና የተሳካ እንዲሆን የፓኪስታን ሚና ጉልህ ነበር፡፡ በተለይ ምእራባውያን በአፍጋኒስታን ለሙጃሂዳን ወታደራዊ ስልጠና እውን የሆነው በአፍጋኒስታን ተባባሪነት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ፓኪስታን የምእራባውያን ሁነኛ ሸሪክ በመሆኗ ምክንያት በሀገሯ ምድር አክራሪ ሃይማኖተኞች እንዲበቅሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም ብቻ አልነበረም የቀድሞዋን ሶቪዬት ህብረት በመጀመሪያ፣ኋላ የተባበረችው አሜሪካ ራስ ምታት የነበረው ኦሳማ ቢንላደን የራሱን አክራሪ እስላማዊ ቡድን ለመፍጠር አስችሎት ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1979 ከተካሄደው የኢራኑ አብዮት በኋላ ክብር ያገኘው ሺያ ወይም ሺያዬዚም ከውሃቢዝም አስተምህሮ ጋር ተቃርኖ እንዳላቸው አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ውሃቢዝም ከሺያዬዝም አስተምህሮ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ ዘዴዎች ገቢራዊ ሆነዋል፡፡ እዚህ ላይ ኢራን እና ሳኡዲ ከሚያደርጉትን መቆራቆስ ጀርባ ያሉት መሰረታዊ ምክንያቶች ሲመረመሩ ዋነኞቹ በውሃቢዝም እና ሺያዪዝም መሃከል ያለው ልዩነቶች ነው፡፡ 

Wahhabism  is now being used to combat Shiism  (Shia), which has gained in  prestige and power since the Islamic Revolution in Iran in 1979.

በነገራችን ላይ በየመን ምድር የተከሰተው አስፈሪና አሰቃቂ ጦርነት ከመጋረጀው ጀርባ የሚዘወረው በኢራንና ሳኡዲ አረቢያ ነው፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ ማሳዘን ብቻ አይደለም ህሊናን ያደማል፡፡ ልብን ያቆስላል፡፡ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡

መቀመጫውን ታላቋ ብሪታኒያ ፣መዲና ለንደን ያደረገው  ሊይፍ ዌናር ኪነግ ኮሌጅ Leif Wenar  of King’s College London states  የተባለ የአዋቂዎች ማህበር በአደረገው ጥናት መሰረት አብዛኞቹ አሸባሪ ቡድኖች ወይም አክራሪ የሙስሊም ቡድኖች የተወለዱት በሳኡዲ አረቢያ ሳላፊዝም እና ዋሃቢዝም አስተምህሮ ተከታዮች ነው፡፡ ባለፉት አስር አመታት ከተከሰቱት አራት የአሸባሪ ቡድኖች ጥቃቶች መሃከል፣ ሶስቱ የአሸባሪ ጥቃቶች የተፈጸሙት በሳላፊዝም አስተምህሮ ልባቸው በሸፈተ አክራሪ ወይም ሽብረተኛ ቡድኖች ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአለም ላይ የሣላፊዝም አስተምህሮ እንዲሰራጭ ዋነኛዋ ተዋናይ ሳኡዲ አረቢያ ከመሆኗ ባሻግር በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ረብጣ ዶላር በማፍሰስ መስጊዶች ማስገንባቷ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ለመድራሳዎች እና ለሃይማኖቱ ሰባኪዎች ገንዘብ እና ባጀት ትመድባለች፡፡ አክራሪ እስልምና ተከታዮችን ለማፍራት ነጻ የትምህርት እድል ትሰጣለች፡፡ በአጭሩ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ርእዮት አለምን ለማሰራጨት መጠነ ሰፊ ዶላር የፈሰሰበት እንደሆነ የሚያሳዩ ጥናታዊ ጽሁፎች በበርካታ አዋቂዎች ቀርበዋል፡፡

በአለም ላይ ለሚፈጸሙ የአሸባሪ ጥቃቶች ተጠያቂዋ ሰኡዲ አረቢያ ብቻ አይደለችም፡፡ ሆኖም ገን ይሁንና ላለፉት 50 አመታት አክራሪ እና ጽንፈኛ የሃይማኖት ሰባኪዎችን የሚያበቅሉ ትምህርት ቤቶችና መስጊዶችን ለማሰራት ይህች ሀገር በገንዘብ እረድታለች፡፡ ( ዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ)

ፎሪያን ፖሊሲ የተሰኘ  ሜጋዚን (Foreign  Policy ) በሰፊው እንደሄደበት ከሆነ ጽንፈኛ የእስልምና አክራሪ ቡድኖችን የሚፈጥሩትን ችግሮች ለማምከን እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ከኒውዮርክ የመስከረም 2011  የአሸባሪዎች ጥቃት ከደረሰ ሃያ አመት አለፈው፡፡ ይሄን ተከትሎ የተባበረችው አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት አሸባሪዎችን ለማጥፋት መጠነ ሰፊ ዘመቻ ቢከፍቱም፣ አሸባሪዎች እና አክራሪ ጽንፈኞች ዛሬም የአለም ስጋት ሆነዋል፡፡

እስቲ በመሬት ላይ ከሚታዩ መራር እውነቶች መሃከል የሚከተለውን እንቃኝ ምንም እንኳን የእስልምና ካሊፌት መንግስት  በኢራቅና ሶሪያ ለመመስረት ሲታገሉ የነበሩ አክራሪዎች ቢፈረካከሱም ፣ከመስከረም 11ዱ 2011 ( እ.ኤ.አ.) የኒውዮርኩ ጥቃት በበለጠ አሁን ባለንበት ዘመን በብዙ ሀገራት አክራሪ ጽንፈኞች ወይም ወንጀለኞች ውጊያ ከፍተው ከፍተኛ የሰብዓዊ ጥሰት ፈጽመዋል፡፡ ግጭቶች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበረችው አሜሪካ አክራሪዎችንና ጽንፈኞችን በጦር ሜዳ ላይ አሸንፋ እንደ መስከረም 11ዱ የኒውዮርኩ የአሸባሪዎችን ጥቃት አይነት ዳግም እንዳይፈጸም ለመከላከል ብትችልም፣ የእስልምና አክራሪዎች የሚፈጽሙት ጥቃት ሊቀንስ አልቻለም፡፡ ጥቃታቸው አድማሱን አስፍቶ ይገኛል፡፡በተቃራኒው ቁጥራቸው ቀላል ባልሆኑ የአለም ክፍሎች ደግሞ የኑሮ ስጋት ሆነዋል፡፡

የተባበረችው አሜሪካ ላለፉት 18 አመታት እጅግ መጠነ ሰፊ የጦርነት ዘመቻ ብትከፍትም፣ በብዙ መቶ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ብታፈስም፣ ቀላል የማይባል የሰው ህይወት ብትገብርም፣ ወደ አክራሪ የእስልምና ቡድን ውስጥ በመሄድ የሚመዘገቡ አክራሪ የእስልምና ተከታይ ወጣቶችን ቁጥር መቀነስ አልተቻላትም፡፡ ከዚህ ባሻግር የአሜሪካ የፖሊሲ አርቃቂዎች የአክራሪ እስልምና መሪዎች የሚሏቸውን እያደኑ መግደል የአሸናፊነት አክሊል መድፋት አላስቻላቸውም፡፡

በነገራችን ላይ አክራሪ የእስልምና ቡድኖች ጥቃት አድማሱን የማስፋት ሁኔታ፣አንዲሁም የአክራሪ ጽንፈኛ ሙስሊም ቡድኖች አባላት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ የመምጣቱ ጉዳይ እንደው ዝም ብሎ ሳይሆን በዘይት ሀብት የበለጸጉ ሀገራት በተለይም ሳኡዲአረቢያ በሚረጩት የፔትሮል ዶላር አማሃኝነት የአክራሪ እስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ የሚሰጥባቸው ዩነቨርስቲዎች መስፋፋት እንደሆነ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የመዲና እስልምና ዩንቨርስቲ (The Islamic University of Medina )፣የኡማአልቋራ መካ ዩንቨርስቲ (the Umm Al-Qura University in Mecca )፣ የኢማም መሃመድ ዩንቨርስቲ (Imam Muhammad in Saud Islamic University in Riyadh ) ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የወሃቢ አስተምህሮን በህጻናት ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር ይረዳ ዘንድ ትምህርት ቤቶች፣የባህል ማእከላት፣መስጂዶች፣ እና የርዳታ ድርጅቶች ሌሎች  ማእከላት ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2013 ሳኡዲአረቢያ በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ስም የውሃቢዝምን አስተምህሮ ለማስፋፋት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስክሳለች፡፡ አንዳኖዶቹ ከአክራሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው፡፡ በብዙ ሚሊዮን  የሚቆጠር ዶላር ወደ አፍሪካ ተልኳል፡፡ ለአብነት ያህል በንጉስ ፋይስል ስም የተመሰረቱ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ካቀዱት 197 ፕሮጄክቶች መሃከል 43ቱ ያነጣጠሩት በአፍሪካ ምድር ላይ ነው፡፡  ሚስተር ኡጊ  የተባሉ ምሁር በእንግሊዝኛ ያቀረቡትን ጽሁፍ በአስረጂነት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

The Wahhabi influence has also been increasing through schools for children,  cultural centers, mosques, and charities.   In a 2013 report Saudi Arabia provided  as much as 10 billion dollars to promote Wahhabism through charities, some  with ties to terrorists (Palazzo).  Millions of dollars from charities goes to Africa,  for example, the King Faisal Foundation has 197 projects, 43 of them target  Africa (Auge).

እንደ አፍሪካዊ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ጥናት ከሆነ ሳኡዲአረቢያ ፖሊሲ ቀርጻ በዲፕሎማሲ፣ በእርዳታ ሥም፣ የእስልምና ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር በማሳለጥ ( ወይም በመደበላለቅ) በአፍሪካ አህጉር በተለያዩ ክፍሎች ተጽእኖ ትፈጥራለች፡፡ ምንም እንኳን ህልሟና አቅዷ ሁልጊዜ ( በአቀደችው መሰረት) ባይሳካላትም በሳህልና በአፍሪካው ቀንድ ሁነኛ ወዳጆችን አፍርታለች፣ጥልቅ ግንኙነት ለመፍጠር ችላለች፡፡ በነገራችን ላይ ሪያድ በአፍሪካ ያሰማራችው ሀይል በቀጥታ ከመንግስታት ጋር ግንኙነት በመፍጠር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፍሪካ ምድር ለአክራሪ ጽንፈኞች መስፋፋት በዋነኝነት ተጠያቂው አይሲሲ ተብሎ የሚታወቅ አለም አቀፍ የአሸባሪዎች ቡድን ሳይሆን ሳኡዲ ሰራሽ የሆነው የውሃቢዘም ጽንፈኞች አስተምህሮ እና የገልፍ ሀገሮች አንቅስቃሴ እንደሆነ የሚያሳዩ ጥናታዊ ጽፎች በአፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪዎች የሄዱበት መራር እውነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ለአፍሪካ የጽንፈኞች መስፋፋት ስጋት አይሲሲ ሳይሆን የውሃቢዝም አስተምህሮ ነው፡፡ እነኚሁ በፔትሮል ዶላር የሰከሩ ሀገራት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በመርጨት፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን አይምሮ በመመረዝ የጽንፈኛ አስተሳሰብ ተሸካሚ እንዲሆኑ ማድረጋቸው የአደባባ ሚስጥር ነው፡፡ ለአብነት ያህል በጣም አደገኛዎቹ የጽንፈኛ አሸባሪ ቡድኖች ቡክሃራም እና አልሻባብ ይጠቀሳሉ፡፡ የቡክሃራም መሪ የሆነው አቡበከር ሼካኡ በራሱ አንደበት እንደተናገረው ስልጠና የወሰደው በሳኡዲአረቢያ ነበር፡፡ አልሸባብ ስልጣን በሃይል ለመጨበጥ የሚሞክረው አልሸባብ የውሃቢዝምን አስተምህሮ የሚሰብክ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ሶማሊዎች የሡፊ (Sufis.)አስተምህሮ ተከታዮች እንደሆኑ የታወቀ ነው፡፡

ዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ይሄንኑ እውነት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጥናት ወረቀታቸው ላይ ዳሰውታል፡፡ እጠቅሰዋለሁ፡፡

The most dominant and influential extremist ideology in Africa has never been  ISIS but its derivative and source the ultra-conservative ‘Arab-infused Wahhabi  model of Islam’ that is being spread by Saudi Arabia and the Gulf States. With the  enormous amount of wealth hey have and investment on mainstream and social  media globally they have been able to change mindsets of millions of vulnerable  Africans. The most dangerous violent extremist groups, Boko Haram and al Shabab were created re ISIS. The leader of Boko Haram, Abubakar Shekau, in his  own words, was trained n Saudi Arabia.  Al-Shabab advocates taking political  power by force and practices Saudi inspired Wahabism while most of Somalis  are Sufis.  ( Doctor Dawite wledgiYoregis )

በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች የሚገኙ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድኖች በአሁኑ ግዜ ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ መንግስት ለመመስረት የሚደርጉት ሴራ ሲታሰብ የአፍሪካን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ከዚሁ ባሻር እነኚሁ እኩይ ቡድኖች በብዙ የአፍሪካ ክፍሎች ለእድገትና ልማት ደንቃራ ሆነዋል፡፡ በህዝብ መሃከል ግጭቶች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆነዋል፡፡

ሞዛምቢክ እንደ የግጭቶች ማሳያ

በደቡባዊት የአፍሪካ  በምትገኘው ሞዛምቢክ ሰሜናዊ ክፍል ካቦ ድልጋዶ ክፍለሀገር (northern province of Cabo Delgado, ) የእስልምና አክራሪዎች እንቅስቃሴ በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል፡፡ በዚች ሰሜናዊት የሞዛምቢክ ክፍለሀገር አክራሪ እና ጽንፈኛ የሙስሊም ተዋጊዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያ ይፈጽማሉ፣ሰዎችን እያፈኑ ወደ አልታወቁ ሥፍራዎች ይሸሽጋሉ፣መሰረተ ልማቶችን ያወድማ ወዘተ ወዘተ ይህ በደቡባዊት የአፍሪካ ክፍል በአልተጠበቀ ሁኔታ የተከሰተ የሰላም መደፍረስ እና የህዝብ ደህንነት ችግር እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች የሄሱት አቢይ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ አክራሪ እና ጽንፈኛ የሙስሊም ተዋጊዎች ይወለዳሉ ተብሎ በፍጹም የተጠበቀ ሁነት አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የታዋቂው የአፍሪካ ልጅ ሳሞራ ማሼል እናት በሆነችው ሞዛቢክ የበቀሉት አክራሪ የሙስሊም ጽንፈኛ ተዋጊዎች መሰረታቸው በሶሪያ እና ኢራቅ ምድር የእስልምና መንግስት ለመመስረት ሲታገሉ ከነበሩት የሙስሊም ጽንፈኛ ተዋጊዎች ጋር የሚመሳሰል እንደሆነ ምሁራን ከጻፉት የምርምር ውጤት ማየት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚዛምቢክ መንግስት ከሩሲያ ባገኘው ወታደራዊ እርዳታ በሰሜን ሞዛምቢክ የአክራሪ ሙስሊም ግስጋሴን መግታት ቢቻለውም ፣ እነኚህን ጽንፈኛ የሙስሊም ተዋጊዎችን ሙሉበሙሉ ማጥፋት አልተቻለውም፡፡ በአጭሩ ጽንፈኞቹ በሞዛምቢክ የጸጥታ ስጋት መሆናቸው ቀጥሏል፡፡ በሌላ በኩል በመካከለኛው አፍሪካ የሚንቀሳቀሱት አክራሪ የሙስሊም ጽንፈኛ ተዋጊዎች ለሞዛምቢክ ጸጥታ መደፍረስ አጋዦች ናቸው የሚሉ መረጃዎች ቢኖሩም፣ ስለጽንፈኞቹ ግንኙነት ( በሞዛምቢክና ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መሬት ላይ ስለሚገኙት ማለቴ ነው) ፍንትው ያሉ መረጃዎች ማግኘት እጅጉን አስቸጋሪ ነው፡፡ ወይም ሁለቱ ጽንፈኛ ቡድኖች ያላቸው ግንኙነት ግልጽ አይደለም፡፡

“The ongoing conflict in northern Mozambique has gathered pace over the past several months and shows little sign of abating, despite the Mozambican military and Russian private military contractor (PMC)Wagner’s security operations in the region. Islamic State Central Africa Province (IS-CAP) has claimed responsibility for attacks at an increasing rate over the past six months, but the dynamics between various militant cells in the region remain opaque. While the dynamic between local cells in Mozambique is still unclear, there have been mounting indications as to what IS-CAP’s overall structure will look like and the logic behind its geographic layout.”(Perkins)

በአፍሪካ ምድር የሚርመሰመሱ ጽንፈኛ የሙስሊም አክራሪ ቡድኖች

እንደ ብዙ የአፍሪካ የፖለቲካ ጠበብቶች በአፍሪካ ምድር የመርመሰመሱ ወይም የፈሉ አክራሪ ነውጠኞች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. የሢናይ የእስልምና መንግስት The Islamic State in Sinai (Ansar Beit al-Maqdis),
  2. በግብጽ የእስልምና መንግስት ለመመስረት የሚታገል ጽንፈኛ ቡድን Islamic State in Egypt (IS-Misr),
  3. በአልጂሪያ ምድር የሚንቀሳቀስ አይስ ተብሎ የሚጠራ ጽንፈኛ ቡድን IS in Algeria  (ISAP),
  4. ቡኩሃራም በናይጄሪያ Boko Haram in Nigeria
  5. ቡኩሃራም በካሜሮን Boko Haram in Cameroon
  6. በማሊ የአዝዋድ ነጻ አውጪ ብሔራዊ እንቅስቃሴ National  Movement for the Liberation of Azawad (MNLA) in Mali
  7. በሶማሊያ የእስልምና መንግስት ለመመስረት የሚታገሉ የጽንፍኛ ቡድኖች ( ቡድን) በተለይ አልሻባብ ይጠቀሳል Islamic State in Somalia, al-Shabab,
  8. አይሲ በቱኒዚያ IS in  Tunisia
  9. በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የእስልምና መንግስት የሚታገለው ጽፈኛ ቡድን Islamic State in Central Africa Province (ISCAP)
  10. በሞዛምቢክ የእስልምና መንግስት ለመመስረት እምቡር እምቡር የሚል ጽንፈኛ ቡድን ፣ በዲሞክራቲክ  ሪፐብሊክ ኮንጎና ታንዛኒያ የሚንቀሳቀሱ የተደራጁ ወንበዴዎች  Mozambique, Democratic Republic of  Congo and Tanzania
  11. በኬኒያ፣ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ አንዳንድ ስፍራዎች የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ቡድኖች እና የተደራጁ ወንበዴዎች የአካባቢው የጸጥታ ችግሮች ናቸው Islamic State in  Kenya, Tanzania and Uganda
  12. በኢትዮጵያ የመንግስት የፕሬስ አታሺዎችንና ባለስልጣናትን ጠቅሰው መገናኛ ብዙሃንና የፕሬስ ውጤቶች ዘገባና ህትመት መሰረት ‹‹ የኦነግ ሸኔ ›› በመባል የሚጠራው ቡድን፣ የወደቀው የወያኔ ቡድን ለኢትዮጵያ የጸጥታ ችግሮች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ በተለይ በቤኒሻንጉል ክልል መተክል ዞን እና ምእራብ ወለጋ አንዳንድ አካባቢዎች በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ( ኢሰብዓዊ  ሆነ ሁኔታ የኢትዮጵያውያን ዜጎችን ህይወት የሚያጠፉ ታጣቂዎች ጉዳይ) ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንቅልፍ የሚነሳ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ጨካኞችንና ለጨካኞቹ አመራር የሚሰጡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባዮችን በእውነት፣ በሞራል እና በፍትህ መሰረት ላይ ሆኖ ለፍርድ እንዲያቀርባቸው እንማጸናለን፡፡ ይህ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት አስከባሪ መንግስታዊ ግዴታ መሆኑ የታወቀ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት ምንም አይነት  ውትወታ የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡
  13. በዩራኒየም ንጥረ ነገር በበለጸገችው ኒጀር ፣ ሆኖም ግን በችጋር በምትታወቀው ኒጀር ምእራባዊ ክፍል ከአልቃኢዳ አክራሪ ቡድን ጋር ንክኪ ያላቸው ጽንፈኞች፣ እንዲሁም ኒጀርን ከናይጄሪያ ጋር በሚያዋስነው የድንበር አቅጣጫ ቡክሃራም የተሰኘው አክራሪና ጽንፈኛ ቡድን የዚችን ደሃ ሀገር ሰላም ካናጉት አመታት ተቆጥረዋል፡፡

ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት፡

  1. የዶክተር ዳዊት ወልደጊዮርግስን ጥናታዊ ጽሁፍ
  2. the detail research to be found in www.africaisss.org)   

ታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም.

ክፍል ሶስት ይቀጥላል

Filed in: Amharic