ብቸኛው ፖለቲከኛ… !!!
.አሳዬ ደርቤ
ከንቲባ በነበረበት ዘመን ‹‹ከህውሓት ጋር አብሮ የማይሄድ ስብዕና ገነባህ›› ተብሎ ከመድረኩ ገሸሽ ተደረገ፡፡
እናም የትግል ጓዶቹ ለሐብቱና ለሹመቱ ሲራኮቱ እሱ ትምህርቱ ላይ በረታ፡፡
የሥልጣን ሽግግሩ ሲካሄድም ከተባረሩት ጋራ አልተባረረም፡፡ ከተሾሙት ጋር አልተሾመም፡፡
ህውሓት ከብልጽግና ጋር ፍቺ ስትፈጽም እነ ሥዬ አብርሐ እስራታቸውን እረስተው ድርጅታቸውን አስታወሱ፡፡
እናም ‹‹ይቅር ለእናት ድርጅቴ›› ብለው ትሕነግ ጋር ተኸነጉ፡፡ አንዳንዶቹም በለጸጉ፡፡
ይህ ሰው ግን ከሁለቱም ጎራ ሲያረበርብ አልታየም፡፡
.
ጦርነቱ ሊጀመር ሰሞን ህውሓት በፌደራል ለሚገኙ አመራሮቿ ጥሪ ስታቀርብ እነ ወ/ሮ ኬሪያ ወደ መቀሌ በሚያደርስ መኪና ከርቸሌ ገቡ፡፡
ከዘመቻው በኋላም አንዳንዶቹ ተርፈው ሲታሰሩ፣ እንደ ሴኮ ቱሬ ያሉት ደግሞ ቅጽበታዊ እርምጃ በወሰዱ ማግስት ተቀበሩ፡፡
አብዛኞቹ ሲደመሰሱ…
የተወሰኑት መነኮሱ…
ይህ ሰው ግን የድርጅታቸውን ጥሪ አክብረው ወደ መቀሌ ከሄዱትም ሆነ፣ ብልጽግናን ከመረጡት መሃከል አልታየም፡፡
ይልቅስ ‹‹ዝም አይነቅዝም›› ብሎ እራሱን ሆነ፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› በሚል ታርጋ የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር መሆን የቻለው ዶክተር ቴወድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ ግብዓተ መሬት ላይ የህውሓትን ቀጣይነት ሊያረጋግጥ ደፋ ቀና ሲል ታዬ፡፡ ሕልሙ አልሳካ ሲለውም ከኮሮና ክስተት እኩል የህውሓት ሽንፈት እንደሚያስጨንቀው ሲቀባጥር ተሰማ፡፡
ይህ ሰው ግን እንደ እሳት የሚጎንፈውን የፖለቲካ ረመጥ እንደ በረዶ በቀዘቀዘ ስብዕና ተሻገረው፡፡
ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
በዚህ ዘመን እዚህች አገር ላይ ከባዱ ነገር ስብሐት ነጋን ወይንም ደግሞ ዶክተር ሙሉ ነጋን ሆኖ መገኘት አይመስለኝም፡፡
ዶክተር አርከበን መሆን እንጂ…❗️