>
5:13 pm - Saturday April 20, 8774

የነዳጅ ጭማሪው ወቅቱን የጠበቀ ነው! (ይነጋል በላቸው)

የነዳጅ ጭማሪው ወቅቱን የጠበቀ ነው!

ይነጋል በላቸው


“ካልደፈረሰ አይጠራም” እንዲሉ ነውና የሰሞኑ የችርቻሮ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ወቅቱን የጠበቀ እንደሆነ መግለጽ ወደድኩ፡፡ ከጥር ወር 2013 መባቻ ጀምሮ በአንድ ሊትር ቤንዚን ቀድሞ ከነበረው ዋጋ ላይ ሁለት ብር ገደማ ተጨምሯል፡፡ ግዴላችሁም ይሄ ጎደሎ ዓመት ብዙ ክስተት ሳያሳየን አይቀርም፡፡ (ሄኖክ አለማየሁ ይህችን ጽሑፍ ካየህልኝ ላንተ አንድ ወንድማዊ መልእክት አለኝ፤ የዩቲዩብ ዜናህን በፍቅርና በጉጉት ከሚከታተሉ አንዱ ነኝ፡፡ በዜናህ መጨረሻ የምትጠቅሳት የ13 ቁጥር ጉዳይ ግን ሁሌም ያስደነግጠኛል፡፡ ቁጥሯን ከመውደድህ የተነሣ እንጂ ግጥምጥሞሽ አይመስለኝም፡፡ እባክህን ከዚህች ነገረኛ ቁጥር የምትወጣበትን ብልኃት ፈልግና አስደስተኝ፡፡ ሌላ መስመር ስላጣሁ ነው ብሶቴን በዚህች አጋጣሚ መተንፈሴ፡፡ “ዜናውን ከማጠቃለሌ በፊት 13 አጫጭር መረጃዎችን አስደምጣችኋለሁ” በምትለው “ምርቃት”ህ ላይ ያለችው ከዜናህ መቼም የማትለያት 13 ቁጥር፡፡)

ይህ በሁሉም የነዳጅ ውጤቶች ላይ የተጨመረው ዋጋ የበላችው እያስገሳት በላይ በላዩ ለሚያጎርሷት ሀገራችን ለይቶላት መፈንዳት ወይም ወደ ችግሮቿ መፍትሔ መቃረብ የራሱን አወንታዊ ሚና ሊጫወት እንደሚችል በበኩሌ ተገንዝቤያለሁ፤ እናም ጭማሪውን በይሁንታ ለመቀበል ራሴን አሳምኛለሁ፡፡ ለነገሩ ምርጫስ ሲኖረኝ አይደል!

በመሠረቱ የሰውኛ ስሜት ያለው መንግሥት የለንም እንጂ ቢኖረን ኖሮ አንድ ጭማሪ ሲደረግ አካባቢያዊና ወቅታዊ ሁኔታዎች መጤን ነበረባቸው፡፡ አለበለዚያ የሚኖራቸው አሉታዊ ጎን ሊበዛና ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ይህ ጭማሪ የሚያስከትለውን ቀውስ ቀስ ብለን የምናየው ቢሆንም በነበረው የኑሮ ውድነትና ዱሮውንም ሕዝብን ያንገፈግፍ የነበረ የዕቃዎች ዋጋ ላይ ለየት ያለ የዋጋ መሰቀልን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ያኔ የለየለት ኳስ አበደች ውስጥ እንገባለን፡፡ ይህን መሰሉን አስቀያሚ ትዕይንት የሚፈልጉ የውስጥም ሆኑ የውጭ ጠላቶች እንዲሁም የአቢይን መንግሥት በቶሎ መውደቅ የሚሹ ኃይሎች ጮቤ የሚረግጡበት ጊዜ ደጃፋችን ላይ ቆሟል፡፡ ማን ያውቃል – ጭማሬው የአምስተኛ ረድፈኞች ሤራም ሊሆን ይችላል፡፡ እንጂ አሁን ኢኮኖሚውን እንደምንም ማረጋጋት ሲገባ ይህን የማይም ሥራ መሥራት ማንን እንደሚጠቅምና ማንንስ እንደሚጎዳ ጠፍቷቸው አይደለም – ዋጋ ተማኝ ባለሥልጣናቱን፡፡ በቃ – ሤራ ነው፤ ትልቅ ሤራ፡፡  

የኑሮ ውድነቱና የኦሮሙማ ዘመቻ ሰንገው የያዟት ሀገራችን በቅርብ ስትፈነዳ ልናይ ወይንም በተቃራኒው ሁሉም የሀገራችን ራስ ምታቶች አንድ በአንድ ግን ቀስ እያሉ እንደወያኔው እንደጤዛ ሊረግፉና እንደጉም ሊበኑ ይችሉ ይሆናል፡፡ መጥፎ አጋጣሚ ሁሌም አይጠላም፡፡ መፈጠርን ከሚያስጠላና ከሚያስረግምም ምጥ በኋላ የሚወለድ እምቦቀቅላ ትዳርን በፍቅር እንደሚያጸና፣ የወላጆችን ሕይወት እንደሚለውጥና ልዩ ደስታን እንደሚያላብስ የሚያውቅ ያውቃል፡፡ …

ሦስት ኮሮናዎች አሉብን፡፡ ኮቪድ 19፣ ኮቪድ 18 (ኦነግ/ኦህዲድ) እና ሕወሓት ሠራሹ ኮቪድ 91 ያስከተለው የኑሮ ውድነት፡፡ ኮቪድ 67/75ን (ወያኔን) እያየነው በምንገኘው ትያትር መሰል የእግዜር ሥራ ብንገላገልም ለ46 ዓመታት የተዘራው ዘር እስከቤተ መንግሥታችን ዘልቆ ሥር በመስደዱ ለጥቂት ጊዜ መቸገራችን አይቀርም፡፡ ሽመልስንና አቢይን የወለደ ኮቪድ 67/75 አሁን ምን እየሠራ እንደሆነ እናውቃለንና የእምዬ ኢትዮጵያ ነጻነት እንዲህ በቀላሉ እንደማይመጣ እንረዳለን፡፡ 

እነዚህ ኮቪዶች በጥምረት ሀገራችንን እንጦርጦስ እየከተቷት በመሆናቸው አንድዬ የጀመረውን ድንቅ ተዓምር ቀጥሎበተ አንድ ነገር በቅርብ እንደሚያሳየን የብዙዎቻችን እምነት ነው፡፡ ስለዚህ “ኃጢኣተኛ ስለሆንኩ እግዜር የኔን ጸሎት አይሰማም” ማለትን ትተን ጸሎታችንን በያለንበት እንቀጥል፡፡

ኦሮሙማ ኢትዮጵያን በብርሃን ፍጥነት እየተቆጣጠራት ነው፡፡ የአቢይ አህመድ የዓላማ ወንድም ኦቦ ሽመልስ አብዲሣ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ አማራውን ከያለበት እያሳረደና እያፈናቀለ በመጠለያ ጣቢያዎችም በመቶ ሽዎች በማጎር እህልና መድኃኒት እንዳይገባላቸው እየከለከለ በርሀብና በበሽታ እየፈጃቸው ነው – ይህ ድርጊት እኔን ከማስገረም አልፎ በሰው ልጅ ድንቁርና እንድስቅ እያስገደደኝ ነው፡፡ “አቦይ” ስብሃትንና ጀሌውን እንዲህ እያጃጃለ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ የሚመስለው ካለ በቶሎ ወደ ሐኪም ቤት ይሂድ፤ መከላከያው ምክንያት እንጂ ገፊ ኃይል አይደለም፡፡ ከዚህ የማይማር ደንቆሮ ሁላ ነገ ምን እንደሚደርስበት ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ መጽሐፉ “በዘሰፈርክሙ ይሰፈርለክሙ” ይላል አሉ፡፡ መተከልና ወለጋ እንዲሁም ባሌና ሐረር በነሽመልስ ላይ የሚያመጡት መብረቃዊ መቅሰፍት ወደር አይገኝለትም – ከወያኔና ከፊተኛው የደርግ ውድቀት እንዲማሩ የተሰጣቸውን ወርቃማ ዕድል አባክነው በፈጣሪ ምሕረትና ትዕግሥት አላግጠዋልና በነሱ ላይ የሚወርደው ቅጣት ከወያኔው የከፋ ይሆናል፡፡ (ይህን ስል እነሱ ይሰሙኛል ብዬ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ አንዴውን የታበየ ጭንቅላት ባለቤቱን መቃብር ካልከተተ ዕረፍት አንደሌለው አውቃለሁ፡፡ ከኔ ይውጣ በሚል ነው እንደልማዴ የምጮኀው፡፡ በተለይ በዘር ልክፍት የሚሰቃይን ሰው እግዜሩም ወደራሱ ከመውሰድ ባለፈ ሊፈውሰው ወይም ሊመልሰው አይችልም፡፡ ሀሰቴን ከሆነ አንድ የየትም ሀገር ምሣሌ ስጡኝ፡፡)

ኦሮሙማ ሶማሌንና አፋርን፣ ጋምቤላንና ደቡብን፣ አማራንና ቤንሻጉል ጉሙዝን፣ ትግራይንና ከተቻለም ኤርትራን ጠቅልሎ ኦሮምያ በሚባል የህልም ዓለም ፍጡር የሆነ ኦነጋዊ ኢምፓየር በማስገባት በጋዳ ሥርዓት ለማስተዳደር ሩጫውን በማገባደድ ላይ ይገኛል፡፡ የሽመልስ ኅቡዕ ንግግር በተግባር ሊታይ አንድ ሐሙስ ብቻ እንደቀረው መገመት አይከብድም – ዙሩን አክርረውታል፡፡ አንደርባዊ ምትሃት የፈጠረው በሚመስል በሌላ አስገራሚ አቅጣጫ ደግሞ የራሴን ወንድሞች ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን “ለአቢይ ጊዜ እንስጠው፡፡ እሱ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አላሠራም ያሉት ከጎኑ ያሉት ናቸው፡፡ እንጂ እሱ ሩህሩህ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማዳን ከላይ የተላከ ‹መሢሕ› ነውና እንታገሰው” እያሉን ነው – የሦስት ዓመት ትግስት ቀላል ይመስል፡፡ እነዚህ ወገኖች ከላይ የተላክ ሁሉ መልካም ይመስላቸዋል – ሰይጣንም ጠቢብ ነው፤ የሚኖረውም ከታችም ከላይም ነው፡፡ እግዜር ቤት ውስጥ ካሉ ብዙ መሣሪያዎች መካከል ብዙዎቹ በሰይጣን ቤት ውስጥም እንዳሉ ማወቅ አለብን፡፡ ሰይጣን ተለዋዋጭ ነው፤ በምትወደው ገብቶ ከመንገድህ ያስወጣሃል፡፡ ተፈጥሯችንን ያውቃልና ከርሱ ጋር ያለብን ትግል እጅግ ከባድ ነው፡፡ ችግሩ አጠቃቀሙን ማወቅ ላይ ነው እንጂ ወሲብ፣ ገንዘብና ሥልጣን በሁሉም ግዛቶች ውስጥ አሉ ወንድሜ እንዲሁም እህቴ፡፡ በአደንዛዥ ንግግር እየተማረክህ ሀገርህን አትጣት!! እንደብሂሉ መጽሐፍን በሽፋኑ ማማር መዳኘት እንደማይቻል ሁሉ ሰውንም በንግግሩ ‹አስማጭነት›ና በማስመሰያ ተግባራቱ አትፍረድ፡፡ ሰው ከሁሉም እንስሳት የበለጠ ክፉ ነው፡፡ ለክፋቱ ማጀቢያ ደግሞ እየለዋወጠ እንደፈለገው የሚጠቀምባቸው ቋንቋ፣ ሣቅና የፊት ፈገግታ አሉት፡፡     

በነገራችን ላይ ወያኔ ካቆመውም ወልጋዳ ህገ መንግሥት በማፈንገጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኦሮሙማ አስተሳሰብ እየተነዳ ነው፡፡ ደረሰኞቹ ሁሉ በኦሮምኛ የላቲን ፊደላት እየተጻፉ በብዙ ባንኮቹ አገልግሎት እየሰጡ ነው – የ“ኬኛ ፖለቲካ”ን በዕብሪት ለማራመድ የተጓዙት ርቀት አስደማሚ ሆነ እንጂ ይህ በራሱ ክፋት የለውም፡፡ ነገ ደግሞ ሌላ ተረኛ ቢመጣ ባንኩም እንደ እስስት ሲለዋወጥ መኖሩ ነው፡፡ አስቡት – ኢትዮጵያን የሚመራው ጉራጌ ቢሆን፣ አገው ቢሆን፣ ሶማሌ ቢሆን፣ ደራሳ ቢሆን፣ ሃዲያ ቢሆን፣ ኣሪ ቢሆን፣ ከፊቾ ቢሆን … የባንኩ ደረሰኞችና ቫውቸሮች ሁሉ በ80 ቋንቋዎች ሊጥለቀለቁ ነው፡፡ ወንድሜ – ቀን ሰጠኝ ብለህ አደራህን ከሚገባህ በላይ እንዳትመኝ! የምኞት ባርያም ሆነህ አንዱንም ሳትጨብጥ መና ሆነህ እንዳትቀር ፈር የለቀቀ ፍላጎትህን ሰብሰብ አድርግ፡፡ ከሁሉም ደግሞ ሁሉም ነገር አላፊ መሆኑን እንዳትረሣ! እንደመጽሐፉ – ሰማይንና ምድርን ጨምሮ፡፡ የምፈራው ደግሞ ሮጠው ሳይጠግቡ ሥልጣን ይዘው እኛንም አላግባቡ ከሚያሯሩጡን ከነአቢይና ሽመልስ ልጓሙን የሚረከበው ኃይልም ከነዚህ ውርጋጦች የማይማር ሆኖ አበሳችን እንዳይቀጥል ነው፡፡ የዚህች አገር ነገር እኮ ሁሉም ነገር አስፈሪ እየሆነ ሕይወታችን መቅኖ አጣ፡፡ በሚገርም የታሪክ አንጓ ላይ እንገኛለን፡፡ ግን አይዞን!! እንዲህ እንደሆነ አይቀርም፡፡ ቀጣዩን ኦሮሙማዊ ምሣሌ እንይ፡፡

Filed in: Amharic