>

"የሱዳን ኃይል የኢትዮጵያን ድንበር  በተጠና እና በተጠናከረ ሁኔታ ጥሶ እየገባ   ነው!!!" (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር)

“የሱዳን ኃይል የኢትዮጵያን ድንበር  በተጠና እና በተጠናከረ ሁኔታ ጥሶ እየገባ   ነው!!!”

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር


የሱዳን ኃይል በኢትዮጵያ በድንበር አካባቢ በተጠናከረ ሁኔታ ገፍቶ ወደ ኢትዮጵያ ውስጥ እየገባ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ። ይህ በተደጋጋሚ እንደማያዋጣ በኢትዮጵያ በኩል እየተገለፀ ነው የሚለው ሚኒስቴሩ አንድ መቶ ዓመት የቆየው የሁለቱ ሀገራት ድንበር እንደጎርጎሪያኑ በ1972 ይህንን ጉዳይ ለመፍታት ሦስት የድንበር ኮሚቴዎች ተቋቁመው በድንበሩ አካባቢ ያሉትን መንደሮች፣የሰፈራ እና የእርሻን ጉዳይ እንዲያጣሩ ፣ ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስም ድንበሩ ባለበት ሁኔታ እንዲቆይ ተደርጎ እንደነበር የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ በሰሜኑ ኢትዮጵያ የሕግ ማስከበር ሥራ ሲጀመር የሱዳን ወገን ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ በድንበር አካባቢ የሳሳ የመከላከያ እና የደኅንነት ኃይል አለ በሚል የኢትዮጵያን መሬት ወርሯል፣ አርሶ አደሩን ማጎሳቆል ጀምራል፣ አሁንም ይህንን ሁኔታ አላቆመም ብለዋል ቃል አቀባዩ በጽ/ ቤታቸው በሰጡት መግለጫ። ይህ ሕገ ወጥ ተግባር እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጥስ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና ድርጊቱ የሱዳንንም ሆነ የኢትዮጵያን ጥቅም እንደማያስጠብቅም ገልፀዋል። ድርጊቱም ማን እንደሆን ባይገልፁትም በላሌች ኃይሎች የሚገፋ ነው ብለዋል።
ግጭቱን ቀጣናዊ ማድረግ ባለመፈለጉ እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን ስለምታከብር ኢትዮጵያ ክስተቱን በትዕግስት እያለፈች ነውም ተብሏል። ይህ ግን ገደብ እንዳለውና እንደ ፍርሃትም እንደ መወላወልም ሊቆጠር የማይገባ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ነገሮች አሁንም በዲፕሎማሲያዊ ሁኔታ እንዲፈቱ ጥረት መደረጉ ይቀጥላል ያሉት ቃል አቀባዩ የሱዳን አካሄድ የሕዳሴ ግድብን በድንበሩ እንደመደራደሪያ የማየት አዝማሚያ ይሆን ወይ ተብለው ተጠይቀው መንግሥት እንደዚያ ያለ ግምገማ የለውም ብለዋል።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድርን በተመለከተ አሁን ድርድሩን በሚያከናውነው አካል መፍትሔ እንዳያገኝ እና አሰልች ሆኖ እንዲዘገይ በማድረግ አልያም ወደተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የመምራት ፍላጎት ስላለ ሊሆን ይችላል ሲሉ ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ግን አሁንም ድርድሩ የሦስቱንም ሀገራት ጥቅም ጠብቆ እንዲከናወን የማድረግ ፍላጎት ነው ያላት ብለዋል።
DW Amharic
ዘገባ፤ ሰለሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ
Filed in: Amharic