>
5:18 pm - Thursday June 15, 3420

የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ ተመራጭ እና ፀሐፊ ተውኔት.. !!! (አብርሐም ፈንታው)

የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ ተመራጭ እና ፀሐፊ ተውኔት.. !!!

አብርሐም ፈንታው

*…. ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ላበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሣባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ዘመን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል
 
የክብር ዶክተር ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ይባላሉ ጥር 6 ቀን 1908ዓ.ም ነው በሸዋ ክፍለ ሐገር በመናገሻ አውራጃ በአዲስ አለም ከተማ ነው የተወለዱት። አባታቸውም ታዋቂው ዲፕሎማት፣ የመጀመርያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የመጀመርያው የጎንደር ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት የ #ከንቲባ_ገብሩ ልጅ ናት።
ስንዱ እድሜዋ ለትምህርት በደረሰበት ወቅት እቤታቸው አስተማሪ
ተቀጥሮላቸው የ አማርኛ ን ትምህረት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም በቤታቸው ተማሩ። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሄደው በ
ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል።
ከንቲባ ገብሩ ወጣቷን ስንዱ ገብሩን እያስከተሉ ወደ ቤተ መንግሥትም ሆነሌላ ሥፍራዎች ይወስዷቸው እንደነበረና ከጊዜው አልጋ ወራሽ ተፈሪመኮንንም ጋር እንዳስተዋዋቋቸው ተዘግቧል። አልጋ ወራሹም የወጣቷንብልህነትና ትጋት በማድነቅ ወደ ፈረንጅ አገር ተልከው ትምህርታቸውንእንዲከታተሉ ባዘዙት መሠረት ወይዘሮ ስንዱ በ 1921 ዓ/ም ወደ ስዊስ ለትምህርት ቢሄዱም ኑሮውስላልተመቻቸውና ትምህርትይሰጥበት የነበረውን የ ጀርመንኛ ቋንቋስላልወደዱት ወደ ፈረንሳይ አቅንተው ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም
በ ስዊስ እና በ ፈረንሳይ ሁለት ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር በዲፕሎማተመረቁ። እዛው የሕግ ትምህርት ለመቀጠል ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ፍላጎታቸው ወደ ሥነ-ጽሑፍ በማዘንበሉ በአጠቃላይ
ለአምስት ዓመታትእዛው ተምረው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
የፋሺስት ኢጣልያ ወረራ ዘመናት
ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደእንግሊዝ ሀገር ሲሰደዱ ብላታ ሎሬንሶ ታዕዛዝ ም አብረው ከጃንሆይ ጋር ሄዱ። ወይዘሮ ስንዱ ግን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እና ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ ወደ መቶ የሚጠጉ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችን ለመፋለም ወደ ቦሬ ሄዱ። እዚያም የመትረየስ አተኳኮስ ትምህርት ተማሩ። ወደ ነቀምት በመሄድም ሕዝብን እየሰበሰቡ ስለ ነፃነት ማስተማሩን ተያያዙት። በዚህ ወቅት በባንዳዎች ጠቋሚነት በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት አምልጠው ጎሬ ላይ ከ ልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ። ከዚያም በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ለማቋቋም መፈለጋቸውን ለራስ
እምሩ አማክረው በተሰጣቸው 5 መቶ ብር አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ። ወዲያው ግን እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲመታ በ ጣልያን ሠራዊት እጅ ተማርከው በእስር ወደ አዲስ አበባ አመጧቸውና የቁም እስረኛ ሆኑ።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ/ም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው ሙከራ
ወንድማቸው መሸሻ ገብሩ አሉበት በመባል ይታሰሱ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሞክሩ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ። በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ፣ ከዚያ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋ ወደብ ሦስት መቶ ወንዶችና ስምንት ሴቶች (እማሆይ ጽጌ ማርያምን ጭምር) ሆነው በመርከብ “አዚናራ” ወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤት ተወስደው ዘጠኝ ወራት
ታሰሩ።
ከእስር በኋላም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ
እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ ማስፈራሪያው
ሳይበግራቸው አርበኞችን በግጥም፣ በወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት፣ መረጃ በማቀበል፣ መሣሪያ በማዳረስ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።
ከድል በኃላ
ከድል በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው የ ወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን፣ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰውም የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ መምህር ሆነው አገልግለዋል። በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በነበሩበት ወቅት፤ “ኮከብ ያለው ያበራል ገና”፣ “የየካቲት ቀኖች”፣ “የኑሮ ስህተት” የሚሉ
ትያትሮችን ሠርተው አቅርበዋል።
ከ 1948 ዓ/ም እስከ 1952 ዓ/ም ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የሕግ
መምሪያ ምክር ቤት አባልና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው አገልግለዋል። በዚህ ምክር ቤት አባል በነበሩበት ጊዜ ብቸኛዋ ሴት ከመሆናቸውም ባሻገር የሴቶች እኩልነት በማይከበርበት ጊዜ እና “የወንድ ዓለም” በገነነበት የታሪክ ምዕራፍ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና እኩልነትን በሕግ ለማስተማመን ብዙ የታገሉ ሴት ነበሩ።
ስንዱ ገብሩ ካበረከቷቸው አስተዋጾወች:- 
· የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዝዳንት
• የሕዝባዊ ኑሮእድገት ዋና ፀሐፊነትና አስተዳዳሪነት
• በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመትየትምህርት አታሼ በመሆን አገልግለዋል።
የክብር ዶክተር ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ የፃፏቸው መፅሐፎች
*
– ኮከብህ ያውና ያበራል ገና
– በግራዚያኒ ጊዜ የየካቲት ቀኖች (1947 ዓ/ም)
– የታደለች ህልም (1948 ዓ/ም)
– ርእስ የሌለው ትዳር (1948 ዓ/ም)
– የኔሮ ስህተት (1948  ዓ/ም)
– ከማይጨው መልስ (1949 ዓ/ም)
– ፊታውራሪ ረታ አዳሙ (1949 ዓ/ም) ናቸው።
የመጀመሪያዋ የሴት ፓርላማ አባል፣ የሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣
ጀግናና ፀረ-ፋሺስት አርበኛ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣የመጽሐፍ ደራሲ፣ እና
የመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት ስንዱ ገብሩ (የክቡር ዶክተር) ሰኞ ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ/ም በተወለዱ በ 93 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፎ በ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተቀብረዋል።
ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ላበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሣባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ዘመን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት
ተሰጥቷቸዋል።
ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ
Filed in: Amharic