>

የመተከሉ ፍጅት ዋናው ተጠያቂ የኦሮሙማ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስፈጻሚው ዐቢይ አሕመድ ነው! (አቻምየለህ ታምሩ)

የመተከሉ ፍጅት ዋናው ተጠያቂ የኦሮሙማ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስፈጻሚው ዐቢይ አሕመድ ነው!

አቻምየለህ ታምሩ

ዐቢይ አሕመድ በሚገዛት ኢትዮጵያ ጎጃም በነበረው መተከል  አማራ እና አገው «አገራችሁ አይደለም» ተብለው እንደ ፋሲካ ዶሮ በየዕለቱ በጭካኔ ይታረዳሉ፤ ለመስማትም ለማየትም በሚዘገንን መልኩ የእርጉዝ ሴት ማሕጽን ተቀዶ ጽንሱ ሜዳ ላይ ይጣላል፤  ገበሬዎች በማሳቸው ላይ እንዳሉ፣ እናቶችና ሕጻናት ቤታቸው በተቀመጡበት በዐይናቸው፣ በአፍንጫቸውና በጀርባቸው ላይ በመርዝ በተነከረ ክርክር ያለው ቀስት እየተቀደዱ በምድር ላይ ተፈጽሞ የማያውቅ የጅምላ ፍጅት በየሰርኩ እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ።
ከአንድ ሁለት ዓመታት በላይ የቀጠለው የመተከሉ ዘግናኝ የአማራ እና አገው እልቂት ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያን ይወዳሉ በሚባሉ ነገዶች ላይ እየተካሄደ ያለው ጭፍጨፋ ዋና መንስዔ አማራውን፣ አገውንና አገር ወዳዱን ኢትዮጵያዊ ሁሉ አዳክሞና አጥፍቶ ምድሩንም ሰማዩንም ኦሮሞ  አድርጎ  ኦሮሞን በሌላው ላይ የበላይ የማድረግ ፤ የኢትዮጵያውያን የጋራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛን አዳክሞና አጥፍቶ ኦሮሞኛን በአማርኛ ላይ የበላይ አድርጎ አማርኛ የማይነገርባትን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ በኦሮምያቸው  አምሳያ፣ ቅርጽ፡ ወርድና ስፋት የማበጀትና የመስራት አላማ ይዞ  የተነሳው ኦሮሙማ ፕሮጀክት ነው። የፕሮጀክቱ  ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ ቆማሪ፣ መሪና ኮማንደር በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየመው ዐቢይ አሕመድ ነው።
ዐቢይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚገዛት ኢትዮጵያ ንጹሐን በማንነታቸው እየተጨፈጨፉ በጅምላ የሚቀበሩባት ምድር ናት። የኦሮሙማን ፕሮጀክት እስካልነካ ድረስ ኢትዮጵያ የንጹሐን መታረጃ ቄራና የድኆች የጅምላ መቃብር ብትሆን ዐቢይ አሕመድ ደንታው አይደለም። የኦሮሙማን ፕሮጀክት የሚነካ አንዳች ነገር ቢፈጠር ትናንት የሾመውን ባለሥልጣን በብርሀን ፍጥነት ለመሻርና የሚፈልገውን ሰው ለመሾም፤ ተዋጊ ጀት ለማስነሳት፣ በድሮን ለመደብደብና ሚሳኤል ለማስወንጨፍ ጊዜ አይወስድበትም። አንድም ቀን “እኔ በማስተዳድራት ኢትዮጵያ ድኆች በማንነታቸው እየተጨፈጨፉ በግሬደር እየተዛቁ በጅምላ የሚቀበሩባት አገር አትሆንም” ሲል ሰምተነው አናውቅም።
የኦሮሙማ ፕሮጀክቱን ስኬን ለመጎብኘት መተከል በሄደበትና ገዳዮችን አናግሮ በተመለሰበት እለት ንጹሐን በተኙበት ተጨፍጭፈው እንደ ቆሻሻ ተዝቀው በጅምላ ሲቀበሩ “እኔ በማስተዳድራት ኢትዮጵያ ይህ ሊፈጽም አይችልም” ብሎ  የማጭበርበሪያ መግለጫ እንኳን  መስጠት አልፈለገም። የኦሮሙማ ፕሮጀክት እስከተገበረ ድረስ ለምን ይሰጣል? የማይመለከተውን! ፍጅቱ አካባቢውን ኦሮማይ ለማድረግ የኦሮሙማ ፕሮጀክት አካል ስለሆነ ውስጡ እንደ ሰው አያዝንማ! ሌሎች ደንገጡሮቹም በኢትዮጵያ ባሕል ንጽሑን በግሬደር ተዝቀው እንደ ቆሻሻ በጅምላ አይቀበሩም ብለው አምበላቸው ስላልተነፈሰ ምን ቤት ነን ብለው ትንፍሽ ሳይሉ ቀሩ።
ፍጅቱ የኦሮሙማ ፕሮጀክት አካል መሆኑ ከተገለጠባቸው ማሳያዎች አንዱ ፍጅቱ ሳምንት ሳይሆነው በዐቢይ ልዩ ኃይል የሚጠበቀው ኦነግ በጅምላ በተቀበሩ ንጹሐን ቤት የመተከል ጽሕፈት ቤቱን መክፈቱ ነው። የአዲስ አበባው ኦነግ እነ ዐቢይ በቀጥታ ቢንፈጽመው  ጭንብላችንን ይገልጥብናል ብለው የሚያስቡትን የኦሮሙማ ፕሮጀክት የሚያስፈጽሙበት ኃይል ነው። ጋሞ፣ ጌዲዮ፣ ከሚሴ፣ አማሮ፣ ኮንሶ፣ መተከል ወዘተ…በኦነግ ስም የኦሮሙማ ፕሮጀክት ከተሰራ በኋላ በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኦሮምያ ብልጽግና ተብዮው ይገባና የኦሮሙማን መዋቅር በኦፊሴል ይዘረጋል፣ ካሪኩለም ያዘጋጅና ገዳንና ኦሮምኛን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ያካትታል። ድኆች በጅምላ እየተጨፈጨፉ  ባሉባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ እየተደረገ ያለው ይህ ነው።
ወያኔ መተከልን ከጎጃም ቆርሶ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ሲል የፈጠረው ክልል አካል ያደረገው ባጭር ጊዜ ለትግራይ  ባለሀብቶች የተንጣለለ መሬት በነጻ ለማደልና በረጅም ጊዜ ደግሞ አካባቢውን ከትግራይ አልፎ ተከዜን በመሻገር በሱዳንና በጎንደር-ወለጋ መካከል እየተዋሰነ ቤንሻንጉል የሚባለውን ክልል ጠቅልሎ ጋምቤላን በማቀፍ ከመረብ እስከ ባሮ ለመዘርጋት ላሰባት የታላቋ ትግራይ ሪፑብሊክ አካል ለማድረግ ነበር። ለዚህ አላማ ተፈጻሚነት ያላደረጉት ነገር አልነበረም።
አገሪቷ የእነሱ ስለነበረች ባላገሮቹን አማሮችና አገዎችን  አፈናቅለው ያሻቸውን ሰፊ መሬት ከልማት ባንክ ባገኙት ገንዘብ የገዟቸውን ትራክተሮች ይዘው  መተከል ለገቡ የትግራይ ባለሀብቶች አድለዋል። መተከል በሙሉ ትራክተር ይዘው በገቡ የትግራይ ባለሀብቶች ተወሮ ነበር።  መቀሌና መተከልን መለየት አይቻልም ነበር። ከትንሽ እስከ ትልቅ ምግብ ቤቶች የሚወራው ትግርኛ ነበር። በወያኔ ዘመን የመጨረሻ ዓመታት ጋምቤላ ሲዝቁ የከረሙት የትግራይ ጄኔራሎችና ዘመዶቻቸው ጭምር ጠቅልለው ትራክተሮቻቸውን ይዘው መተከል ዘምተው ነበር። መተከል አማራውንና አገውን  አፈናቅለው ለሙን  የጎጃም መሬት ለማረስ  ካፍ እስከ ደገፉ ትራክተር ይዘው በገቡ የትግራይ ጀኔራሎች ጢም ብላ ነበር።
ወያኔን የተኩት እነ ዐቢይ አሕመድም መተከልን የድኆች መታረጃ ቄራ ያደረጉት መተከል በኦሮሙማ አስተሳሰብ ለመሰልቀጥና ኢትዮጵያን የምታህለዋን  ኦሮምያቸውን ለመፍጠር ባላቸው ህልም ነው።
በመተከል የቀጠለውን የአማራና አገው እልቂት ለማስቆምና ድኆችን ለመታደግ መተከል ይገቡ ዘንድ የፌዴራል መንግሥት ተብዮው ተጠይቆ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አማራ ክልል የሚባለው ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከወር በፊት በቴሌቭዥን ሲናገር ሰምተነዋል። አማራ ክልል የሚባለው አካል እስካሁን ድረስ  የጸጥታ ኃይል ወደ መተከል ልኮ የንጹሐን አማራና አገው ተወላጆችን ሕይዎት መታደግ ያልቻለው ዐቢይ አሕመድ ስላልፈቀደ ነው። የአማራና የአፋር ልዩ ኃይል በስልጣኑ የመጡበትን ወያኔዎች ትግራይ ክልል ድረስ ገብተው ስለወጉ ያመሰገነው “ፌዴራሊስቱ” ዐቢይ አሕመድ የአማራ ልዩ ኃይል የጎጃም ክፍል በነበረው መተከል ገብቶ ሊቆም ያልቻለውን የአማራና አገው ተወላጆች እልቂት ይቆም ዘንድ ለተጠቀው ሕይዎት አድን ጥሪ ፊዴራሊዝም የሚሉትን አሳቦ  ፍቃድ መስጠት ያልፈለገው የኦሮሙማው ፕሮጀክት እንዳይደናቀፍበት ነው።
ዐቢይ የመተከሉ እልቂት ለአፍታ እንኳን እንዲቆም ቢፈልጎ ኖሮ  ድኆች አድኑን እያሉ እየጮሁ የቀረበለትን የሕይዎት አድን ላለመቀበል አያመነታም ነበር። እልቂቱን ማስቆምና ንጹሐን መታደግ የሚችለውን የአማራ ልዩ ኃይል እንዳይገባ ፍቃድ ከልክሉ እልቂት አስቀጣዮችን እነ ጀኔራል አስራት ደኔሮና አዲስ አበባን በኦሮሙማ ያሰለቀጡትን ደሕዴኖችን እነ ተስፋዬ በልጅጌን ላከ። በሌላ አነጋገር በመተከል የአማራና አገው ድኆች እየተፈጁ ያሉት በዐቢይ አሕመድ ፍቃድ ነው። ለዚህም ነው የመተከሉ ፍጅት ዋናው ተጠያቂ የኦሮሙማ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስፈጻሚው ዐቢይ አሕመድ ነው ያልሁት!
Filed in: Amharic