ዛሬ ንጋት ላይ በመተከል ዞን ጨለያ ቀበሌ 27 ሰዎች ተገደሉ…!!!
D.W
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ጨለያ ቀበሌ ዳሊቲ በተባለ ጎጥ በዛሬው ዕለት 27 ሰዎች መገደላቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።የዓይን እማኙ ግድያው ዛሬ ንጋት በግምት 11 ስዓት ላይ መፈጸሙን፣ጥቃት አድራሾቹ ግድያውን የፈፀሙት በቀስት መሆኑን ከግድያው አምልጠው ከመጡ ዘመዶቻቸው መስማታቸውን ገልጸዋል።
በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች አስከሬን በጨለያ ቀበሌ አስከሬናቸው መሰብሰቡንም ገልፀዋል። ከሟቾቹ በተጨማሪ በርካታ ቁስለኞች በአካባቢው በሚገኝ የጤና ተቋም ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።በርካታ ቁጥር ያላቸው የአጎራባች ቀበሌ ነዋሪዎችም ጥቃቱን በመፍራት ቀያቸውን ለቀው እየሸሹ ነው ብለዋል።
አስከሬናቸው ከተሰበሰቡ 27ቱ ሟቾች ውጭ በአሁኑ ጊዜ በየአካባቢው አስከሬን እየተፈለገ በመሰብሰብ ላይ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችልም አስረድተዋል።በአካባቢው እስካሁን የመከላከያ ሰራዊት አለመግባቱንም ጨምረው ገልፀዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ የአካባቢውን ባለስልጣናት ጨምሮ የኮማንድ ፖስቱን መሪ ሌትናል ጀነራል አስራት ደነሮን ለማግኘት የእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ምላሽ ባለማግኘታችን አስተያየታቸውን ልናካትት አልቻልንም።
በቤንሻንጉል ጉምዝ በመተከል ዞን ካለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ ጉባን ፣ወንበራ፣ ድባጤና ቡለን በተባሉ ወረዳዎች ያሸመቁ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢውን ነዋሪዎች ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።