የተክለ ሚካኤል አበበ ነገር
አቻምየለህ ታምሩ
የካናዳው ተክለሚካኤል አበበ «ጎንደር» በሚለው የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ዘፈን እንደሚናደድ ከአቶ ክንፉ አሰፋ ጋር በሲያትል ባደረገውና በዘሐበሻ የዩቱብ ገጽ ላይ በተለቀቀው ቃለ ምልልሱ ተናግሯል። ተክለሚካኤል በቴዎድሮስ ካሳሁን የጎንደር ዘፈን የተናደደበትን ምክንያት ሲያብራራ አንድም «ዘፈኑ የትግሬና የኦሮሞ ፖለቲከኞች የዓፄ ቴዎድሮሷ ኢትዮጵያ ተጭና፣ ጨፍልቃና ማንነታችንን ያጠፋች ኢትዮጵያ ናት ስለሚሉ መስማት የማይፈልጓትን ኢትዮጵያ ስለሚያጎላ» ሁለትም «ጎንደር ጎንደር ፣ የኢትዮጵያ አንድነት ዋልታና ማገር» የሚለው በጣም የሚያናድደው ወይንም በተክለ ሚካኤል አገላለጽ “annoy” የሚያደርግ ግጥም በዘፈኑ ውስጥ በመካተቱ» መሆኑን ገልጧል።
በመጀመሪያው አመክንዮው ተክለ ሚካኤል አበበ የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች ከኢትዮጵያና ከአማራ አንጻር የቀፈቀፉትን የውሸት ታሪክ ሁሉ እንዳለ የሰለቀጠውና ሳያላምጥ የዋጠው ይመስላል። እስቲ የትኛው ብሔርተኛ ፖለቲከኛ ነው በጭካኔ ዔፄ ቴዎድሮስ ፈጽሞብናል እያለ ከሚያቀርበው የተሻለ ሩህሩህ አባት ነበረኝ የሚለው? እስቲ ጎላ ብለው የሚሰሙትን የትግሬና የኦሮሞ ብሔርተኞች «የኛ ናቸው» የሚሏቸው የዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ዘመን «አባቶቻቸው» ምን አይነት ገዢዎች እንደነበሩ እንይ።
«የዓፄ ቴዎድሮሷ ኢትዮጵያ ተጭና፣ ጨፍልቃና ማንነታችንን ያጠፋች ኢትዮጵያ ናት» የሚሉት የትግራይ ብሔርተኞች ትግሬ ናቸው ብለስ ስለሚያስቡ ብቻ ከመጠን በላይ የሚያደንቋቸው ዐፄ ዮሐንስና ራስ አሉላ ዋናዎቹ ናቸው። የኦሮሞ ብሔርተኞች ደግሞ «ዐፄያዊ ሥርዓት» የሚሉትን አንድ የአካባቢ የገበዝ አለቃ እስከገበረ ድረስ የውስጥ ግዛት ነጻነቱና የተለየ ማንነት መያዙ ጉዳይ የማይሆንበትን የአስተዳደር ዘይቤ እየኮነኑ “የኛ” የሚሉት ከሀያ ስምነት በላይ የኢትዮጵያ ነገዶች የጠፉበትንና አንድ ሶስተኛው ለምለሙ የኢትዮጵያ ክፍል በወረራ የተያዘበትን የዘመቻ ሥርዓት «ለአለም ሳይቀር ዲሞክራሲን ያስተማርንበት ሥርዓት ነው» አድርገው በማቅረብ የኦነግ ዶክተሮችንና ፕሮፌሰሮችን ሁሉ የሚደነቁበት የገዳ ሥርዓት ቀዳሚው ነው። እስቲ ሁለቱ ብሔርተኞች ከመጠን በላይ የሚያስጮሁት ታሪክ ምን እንደሚመስል ዶሴው ይውጣና ይመርመር።
የትግሬው በዝብዝብ ካሳይ ወይንም ዓፄ ዮሐንስ ጎጃምን ቤት እየዘጉ ያቃጠሉ፤ ሠራዊታቸውን ወንዱን ብልቱን፣ ሴቱን ጡቱን ቁረጥ ብለው ያሰማሩ፣ ለምለሙን ምድር ድምጥማጡን ያጠፉ መሆናቸውን ጸሐፌ ትዕዛዛቸው ሊቀ መርዓዊ ጽፈዋል። ዐፄ ዮሐንስ ራቸውን ጎጃምን እንዳጠፉት ለራስ ዳጌ በጻፉት ደብዳቤያቸው ምስክርነታቸው ሰጥተዋል።
ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ጎጃምን ለማጥፋት ሁለት ጊዜ በዘመቱበት ወቅት «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን አይተርፈኝም» ብለው አዋጅ በማስነገር ነበር። ሰማኒያ ሺ የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት ጎጃም የተሰማራው ይህንን ንጉሣዊ ትዕዛዝ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ነበር። የዐፄ ዮሐንስ ዜና መዋዕል ጸሐፊም ይህን አልደበቁም። ዜና መዋዕል ጸሐፊያቸው ሊቀ መርዓዊ የዐፄ ዮሐንስን የጎጃም ዘመቻ ሲገልጹ «ወሖረ ሀገረ በላዕተ ሰብእ እምብሔረ ጎጃም» ሲሉ ነበር የጻፉት። ይህን የዐፄ ዮሐንስ የዘር ማጥፋት ዘመቻና አላማው ወደ አማርኛ ሲመለስ «[ጃንሆይ] ወደ ሰው በላው [ቡዳው] አገር ወደ ጎጃም ዘመተ» ማለት ነው።
ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን ከዳር እስከ ዳር ቤተ ክርስቲያን ሳይቀር እያቃጠሉ፣ ታቦቱን እያወጡ እየጣሉ ካባይ እስከ አባይ ድረስ ያጠፉት በመጀመሪያ ሕዝቡን «ቡዳ» በማለት demonize አድርገው ሠራዊታቸው ሰው ሳይሆን ቡዳ እየጨፈጨፈ እንደሆነ እንዲሰማው በማድረግ ነበር። የሴቱን ጡት፣ የወንዱን ብልት ቁረጥ ተብሎ በጎጃም ላይ የዘመተው የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት ጎጃምን ያን ያህል ጥፋት ያደረሰውና ካባይ እስከ አባይ የሬሳ ክምር ያደረገው «ወሖር ሀገረ በላዕተ ሰብእ እምብሔረ ጎጃም» ተብሎ ሰው ሳይሆን ጎጃምን በሙሉ ቡዳ ነውና መደዳውን ጨፍጭፍ ተብሎ በንጉሠ ነገሥታት ዮሐንስ ንጉሠ ፅዮን ዘ ኢትዮጵያ አዋጅ ስለተነገረው ነበር። ይህ የንጉሡ ታሪከ ነገሥት ጸሐፊ የተመዘገቡት ታሪክ እንጂ።
ከታሪከ ነገሥት ጸሐፊው በተጨማሪ በግፉዓኑ ማኅበረሰብ ዘንድም ዐፄ ዮሐንስ በጎጃም ያካሄዱት ሁለት ዙር ጭፍጨፋ በስነ ቃል ሲወሳ ኖሯል። ጭፍጨፋውን በዐይኑ ያየውና በተዓምር የተረፈው ቦጋለ አይናበባ የሚባል የጎጃም አሰላሳይ [የአባቴ የቅርብ ዘመድ] ያንን የጎጃም የመከራ ዘመን እንዲህ ሲል ገልጾት ነበር፤
ዮሐንስ ነው ብለው ስንሰማ ባዋጅ፣
ዮሐንስ አይደለም ሳጥናኤል ነው እንጂ፤
ዮሐንስ አጠፋው አደረገው ዱር፣
ጎጃምን የሚያህል ያን ለምለም ምድር፤
በትግሬ ተዘርፈን እንጀራ ፍለጋ ወንዙን ሳንሻገር፣
ድሮ ባገራችን ቡቃያው በጓሮ በጎታ እህል ነበር፤
በላይኛው ጌታ በባልንጀራዎ፣
በቅዱስ ሚካኤል በጋሻ ጃግሬወ፣
በጽላተ-ሙሴ በነጭ አበዛወ፣
ጎጃምን ይማሩት ፈሪም አንልወ፤
ጎጃም ተቃጠለ ዐባይ እስከ ዐባይ፣
ትግሬ ቅጠል ይዞ ሊያጠፋው ነወይ፤
ከሀበሻ ወዲህ ከሀበሻ ወዲያ፣
ሰውን ገረመው እኔንም ገረመኝ፤
ዮሐንስ እግዜርን ገድሎታል መሰለኝ፤
በእኔ ዘመንም ከዛሬ ሀያ ስድስት ዓመታት በፊት ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን በጨፈጨፉ ልክ በመቶ አመቱ የዐፄ ዮሐንስ የልጅ ልጆች ነን ያሉን ወያኔዎች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተቋቋመን የወባ ማጥፊያ ድርጅት ከፍኖተ ሰላም ከተማ ነቅለው ወደ ትግራይ ወስደው የአዲግራት መድሐኒት ፋብሪካ ሲያቋቋሙበት በመቶ ሺዎች እንደሚቆጠር የሚገመት የጎጃም ሕዝብ እንዲያልቅ አድርገው ነበር። በወቅቱ ከመቶ አመት በፊት ዐፄ ዮሐንስ በጎጃም ሕዝብ ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ ተመሳስሎ ከመቶ አመት በኋላ የልጅ ልጆቻቸው ነን ባሉ ወያኔዎች ዘግናኙ ታሪክ መልኩን ቀይሮ ራሱን በጎጃም ላይ ሲደግም የቦጋለ አይናበባ የልጅ ልጅ እንዲህ ብሎ ነበር፤
ጦማችን ባይሰምር ጸሎታችን ባይደርስ፣
በልጅ ልጅ መጡብ ዐፄ ዮሐንስ፤
ከጎጃም አልፈን ወደ ወሎ ስንገባ በዝብዝ ካሳ የጨፈጨፉትበን፤ የእኅታቸውን ባል የላስታና ዋግ ተወላጁን ንጉሠ ነገሥት የዐፄ ተክለጊዮርጊስን ዐይን ሳይቀር በጋለ ብረት አፍርጠው በዱልዱም ያረዱበትን፤ እጅና እግር የቆረጡበትን፤ ከንፈርና አንፍንጫ የፎነኑበትን፣ አመጸብኝ ያሉትን የራያ ሕዝብ አንድ ሳይተርፈኝ ፈጀሁት ብለው ደብዳቤ የጻፉበትን በራሳቸውና በታሪከ ነገሥታቸው የተመዘገበውን ታሪካቸውን እናገኛለን።
የትግሬ ብሔርተኞች የመጀመሪያው አፍሪካዊ ጀኔራል የሚሏቸውን ራስ አሉላንም ብንወስድ እ.ኤ.አ. በ1886 ዓ.ም. ባሕር ምድር [የዛሬው ኤርትራ] ባርካን አካባቢ ባካሄዱት ዘመቻ ሁለት ሦስተኛውን የኩናማና የናራ ሕዝብ መጨፍጨፋቸውን፤ የደጋማውን ባሕር ምድር ገበሬ አፈናቅለው መሬታቸውን በሙሉ መውረሳቸውን፤ በባሕር ምድር ደጋማው አካባቢ የሚኖሩት ባላገሮች ቤሳ ቢስቲ ሳያስቀሩ መዝረፋቸውን፣ ሁሉንም የባሕር ምድርተወላጆች በጠቅላይ ግዛታቸው አስተዳደር ባጠቃላይ ያገለሉና አስመራ ከተማን ሙሉ በሙሉ አቃጥለው እንዳጠፉ በታሪክ ተመዝግቧል።
የኦሮሞ ብሔርተኞች ስለሚያጸድቁት ወደ ገዳ ስርዓት ስንመጣ በ1800ዎቹ የነበረውን የኦሮሞ አባ ገዳ አባ ጉጂ ወስደን ምን አይነት ገዢ እንደነበሩ ማየት እንችላለን። አባ ገዳ ጉጂ በጭካኔ የሚዝናኑ sadist የነበሩ ሰው ናቸው። አባ ገዳ ጉጂ በምርኮ የያዟቸውን ሰዎች ዐይን እንደሙጀሌ እያወጡ ፤ ጭንቅላታቸውን እንደ ማገዶ እንጨት እያስፈለጡ የሚደሰቱ ጨካኝ እንደነበሩ የዐይን ምስክሩ እንግሊዛዊ ናትናኤል ፒርሰን ነግሮናል።
ዐፄ ቴዎድሮስና ብሔርተኞች!
ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን የሚያወፍዙት የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች ከላይ የተጠቀሱት የሚያደንቋቸው ሰዎች ከሰሩት የተለየ ጭካኔ እንደሰሩ የሚያሳይ ያቀረቡት ማስረጃ የለም። ታዲያ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ምን የከፋ ነገር ሰርተው ነው የጭካኔ ቁንጮ፤ ብሔርተኞችን የሚያስኮፉ ተደርገው የሚቆጠሩት? በእውነቱ በራሳቸው ዘመን መመዘን ያለባቸውን የዚያ ዘመን ሰዎች በዚህ ዘመን መለኪያ ሰፍሮ እንዲህ ነበሩ ማለት፡ የራስን ድንቁርና ከማወጅ በስተቀር አዋቂነትን የሚያሳይ ትርጉም ያለው ንጽጽር ሊሆን አይችልም።
የዛሬዎቹንና የቀድሞዎቹን [ነገሥታቱን] መሪዎች በዚህ ዘመን ሚዛን ማወዳደር ማለት፤ የዛሬዎቹን አለም በሰለጠነበት የኮምቲውተር ዘመን ገዢዎች አስተሳሰብና ዝንባሌ፡ ካለፉት የዘመኑ መንፈስ ውጤት ከሆኑት መሪዎች ጋር አንድ ረድፍ በማስቀመጥ፤ ነገሥታት መሪዎችን ከፍ ባለ መለኪያና ፍትሐዊ ባልሆነ ሚዛን እየሰፈሩ፥ የዛሬዎቹን ግን በጣም ዝቅ ባለ ልኬት በመመዘን፡ ትይዩ ሊሆኑ ወደማይችሉበት ሚዛን እንዲቀመጡ ማድረግ እንደማለት ነው። በተመሳሳይ መንገድ፡ የዛሬዎችንና የመጪዎችን መሪዎች ባንድ ረድፍ ወይም ባንድ መደብ ማስቀመጥ ማለት፡ ሚዛናዊ የማይሆንና መጪዎቹን ካሁኖቹ በጣም በማግዘፍ፤ ያሁኖቹ ከመጪዎች እንዳይመጣጠኑ አድርጎ ባንድ ሚዛን እንደማስቀመጥ ማለት ነው። ባጠቃላይ ያለዘመኑ በሌላ ዘመን መስፈርት መመዘን፣ መተቸትና መናቅ ቀርቶ ማሞገስም እንኳ ከፍተኛ ድንቁርና ነው።
በዚያ ላይ የንጉሥ አስተዳደር በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ዘንድ ይሰራበት የነበረ መሆኑ ተዘንግቶ ቴዎድሮስ ወይንም ምኒልክ እንዳመጡት አድረጎ ማስቀመጡ ትልቅ ስህተት ነው። ቴዎድሮስን ከዘመኑ የጎበዝ አለቆች የሚለየው የሌሎቹን እጥረት በመስበር ግራኝ ያፈረሳትን ሰፊ አገር እንደገና አንድ ለማድረግ የሰነቀው ራዕይ ነው። ይህ ከዘመኑ የላቅ ትልቅ ራዕይ ደግሞ በዘፈንም ሆነ በሌላ ጥበብ ቢነሳ ያንስበታል እንጂ የሚያናድድ ሊሆን አይችልም።
ሌላው ተክለሚካኤል «ጎንደር ጎንደር ፣ የኢትዮጵያ አንድነት ዋልታና ማገር» የሚለው ዘፈን በጣም “annoy” አደረገኝ ያለው ምናልባት ታሪካችንን ስላላወቀው ይመስለኛል። ታሪካችንን ለሚያውቅ ሰው «ጎንደር ጎንደር ፣ የኢትዮጵያ አንድነት ዋልታና ማገር» የሚለው አገላለጽ አናዳጅ ሳይሆን ገላጭ ሆኖ ነው የሚያገኘው። ማንም ስምንተኛ ክልፍ የደረሰ ተማሪ በየአካባቢው መሳፍንትና መኳንንት ተከፋፍላ የነበረችው ኢትዮጵያ እንደገና አንድነት የተጀመረው ጎንደር፤ ጀማሪውም ዓፄ ቴዎድሮስ መሆኑን ያውቃል። ርግጥ ነው በየ አካባቢውን የነበሩ መሳፍንትና መኳንንት ሁሉን ጠቅልለው የመግዛት ፍላጎትና ሕልም ነበራቸው። ሆኖሞ ግን እጥረት ስለነበራቸው መጠቅለል ስላልቻሉ የነበረውን እጥረት የሰበረው የሁሉንም የዘመኑን ባላልጋዎች ፍላጎት ማሳካት ቻለ። ከሱ በኋላ የነገሠት መሪዎች ሕዝቡ የተከተላቸው ቴዎድሮስ የጀመረውን መጠቅለልተረክበው ስላስቀጠሉ ነው። ስለዚህ ዋልትና ማገር ማለት ምን እንደሆነ የሚያውቅ የኢትዮጵያ ዳግም አንድነት የቆመበት ዋልታና የተጠቀለለበት ማገር ማዕከል የሆነችዋ ጎንደር ዋልታና ማገር መባሏ ለምን እንደሚያበሳጨው ሊገባኝ አይችልም።
ተክለሚካኤል አበበ የዓፄ ቴዎድሮስ ታሪክ መጉላቱ ብሔርተኞች የዓፄ ቴዎድሮሷን ኢትዮጵያ ሊጭኑብን ነው የሚለው ቅስቀሳቸው እንዲሰምርላቸው ያግዛቸዋል የሚለው ትርክቱ አስቂኝ ነው። ተክለሚካኤል እዚህ ላይ የዘነጋው ትልቁ ነገር ዓፄ ቴዎድሮስ ዛሬ ቢኖር ኖሮ ልክ በዘመኑ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ከተክለሚካኤልም ሆነ ብሔርተኛ ከሚላቸውም ፖለቲከኞች ሁሉ የላቀ ተራማጅና ባለራዕይ መሪ ሊሆን እንደሚችል አለመገመቱ ነው። አለም ባልሰለጠነበት ዘመን በያካባቢያችን ከነበሩት የጎበዝ አለቆች ሁሉ የላቀ ተራማጅና አርቆ አሳቢ የነበረው ቴዎድሮስ ዛሬ በዚህ ዘመን በድጋሚ የመፈጠር እድል ቢያገኝ ኖሮ ከተክለሚካኤልምን ሆነ ከተክሌ ብሔርተኞች አልያም በካድሬዎቹ «ታላቁ መሪ» እየተባለ ሲሞካሽ ከኖረው ከመለስ ዜናዊ ስንት እጥፍ የላቀ አስተሳሰብ የሚኖረው ተራማጅ ክስተት ነበር የሚሆነው።
ልጅ ተክሌ፡- ብሔርተኖች የምትላቸው ወዳጆችህን እስቲ ከሚያደንቁት ንጉሥ፣ የጦር መሪ ወይም አባ ገዳ ውስጥ በቴዎድሮስ ላይ ከሚያቀርቡት ክስ ያነሳ ጭካኔ ይፈጸም የነበረ ሰው ከነበራቸው ንገሩን በላቸው?! የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኞች እንደሚሉት ዓፄ ቴዎድሮስ ማንነታቸውን ተጭኖና ጨፍልቆ አጥፍቶት ከነበር እነሱ ከየት የተገኙ ክስተቶች እንደሆኑ እስቲ ጠይቃቸው? ቴዎድሮስ ማንነት አጥፊ ከነበር ለምን ማንነታቸው ጨርሶ ሳይጠፋ እነሱ ተረፉ? እስኪ ጠይቅልን?!
ከሶስት ዓመታት በፊት ካናዳዊው ጠበቃ ተክለ ሚካኤል አበበ በአንድ መድረክ ስለ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ያስተጋባውን ወቀሳ ተከትሎ ከታች የታተመውን አስተያየት ጽፌ ነበር! ለዳግማዊ ቴዎድሮስ 202ኛ ዓመት የልደት ቀን ማስታወሻ ትሆን ዘንድ እነሆ እንደገና አትመናታል!