>

ስግብግብ ጁንታችንን አልገደልንም...  !!! (አብርሃም አለህኝ )

ስግብግብ ጁንታችንን አልገደልንም…  !!!

አብርሃም አለህኝ 

* …እየተገደሉ የሚኖሩ ፣ እየሞቱ የሚቀብሩ፣ እልፍ ወራሽ ያላቸው ጁንታዎች ተገደሉ የሚለው ዜና ለኢትዮጵያ መልካም የምስራች የሚሆነው እንዴት ነው ? ትህነጋውያኑን የተፀየፍናቸው በቋንቋቸው ወይም በደማቸው እኮ አይደለም። ቋንቋቸውም የቋንቋችን ዘር ነው። ደማቸውም  የደማችን ሸጥ ነው። አምባቸውም መኖርያችን ነው። የእነሱ መገደል ዜናም ያሳዝነናል እንጂ አያስደስተንም። 
“ሙት ይዞ ይሞታል” እንደሚባለው በሞታቸው የሚገድሉን፣ ከመቃብራቸው በላይ የሚቀብሩን እነዚህ የሀገር ጠላቶች እውነትም አልተገደሉም። ጁንታዎች ተገድለዋል በሚለው የምስራች ነጋሪ ቃል ውስጥ በየቀኑ የሚገደሉ ንጹሀን እልፍ ናቸው። ገዳዮቻችን ሳይገደሉ ያውም ደጋግመው እየገደሉን ጁንታዎች ተገድለዋል የሚለው ዜና የጁንታዎችን ከመቃብር በላይ መኖር ያረጋግጣል። እመኑኝ ጁንታዎቻችን  አልተገደሉም።
ኢትዮጵያ የወዳጆቿን መብዛት ያህል ጠላቶቿ እልፍ አእላፋት ናቸው። ደጋግመው የሚሳሳቱ ፣ በመሳሳት ልክፍት ውስጥ የተዘፈቁ አፍቃሪ ወያኔዎች ጥቂት አይደሉም። የወያኔ ሞት  ህመማቸው የሆነ ከስህተታቸው ከመማር ይልቅ ለሌላ ስህተት የተዘጋጁ የስሁት ታሪክ ቁሞ ቀሮች ብዙ ናቸው። እነዚህ የስሁት ታሪክ ቁሞ ቀሮች የስግብግብ ጁንታዎች ትንሳኤ ሙታን የምስራች ቃል ነጋሪ ናቸው። እነዚህ የስሁት ታሪክ ቁሞ ቀሮች የትህነግ የሃምሳ  አመታት የጥፋት እቅድ ፍሬዎች ናቸው። ትንሳኤ ትህነግ  ጸረ ኢትዮጵያ ሀሳዊ ነብይ ናቸው።
መተከልን አኬል ዳማ ለማድረግ ትጥቅና ስንቅ የሚቋጥሩ የጥላቻ ደቀመዝሙሮች  ምድርን በሞሉባት ኢትዮጵያ ስግብግብ ጁንታዎች ተገደሉ የሚለው ዜና እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል ? የአረመኔ ትህነጋውያን ጁንታዎች አሻራ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጤንነታችንን እያወከ ነፁህና ሰላማዊ አየር እንዳንስብ ሁለንተናችንን እየበከለ ፣ አብሮነታችንንና በመተባበርና በመደራደር ፍትሀዊ አማራጭ የመኖር ህልውናችንን እየተጋፋ ባለበት በዚህ ሰአት የጁንታዎች ተገደሉ ዜና ከስላቅ በላይ ነው።
በአንድ ወገን ስግብግብ ጁንታ እየገደሉ በሌላ ወገን ስግብግብ ጁንታ እየፈለፈሉ የደህንነት አዙሪት በሚፈታተናት አገር ውስጥ መኖራችን መቸ ያበቃል ?
እየተገደሉ የሚኖሩ ፣ እየሞቱ የሚቀብሩ፣ እልፍ ወራሽ ያላቸው ጁንታዎች ተገደሉ የሚለው ዜና ለኢትዮጵያ መልካም የምስራች የሚሆነው እንዴት ነው ? ትህነጋውያኑን የተፀየፍናቸው በቋንቋቸው ወይም በደማቸው እኮ አይደለም። ቋንቋቸውም የቋንቋችን ዘር ነው። ደማቸውም  የደማችን ሸጥ ነው። አምባቸውም መኖርያችን ነው። የእነሱ መገደል ዜናም ያሳዝነናል እንጂ አያስደስተንም። ይሰቀጥጠናል እንጂ ጮቤ አያስረግጠንም። ይሁን እንጂ በመረጡትና በተለሙት መንገድ መጓዝን የመረጡት ራሳቸው ናቸው። የያዙት መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ደጋግመን አሳስበናቸዋል። ከማሳሰብም አልፈን በወገናዊነት ስሜት ከአንጀታችን ተማጽነናቸዋል። የተማጽኗችን ክታብ ቤተመዛግብታችንን ሞልቶታል። በችርቻሮ ሳይሆን በጅምላ ደርዘን ምስክር ማቅረብ እንችላለን። አልተገደሉም የምንለው ስላልተገደሉ አይደለም። ቢገደሉም አለመገደላቸውን የሚተርክ የስሁት ትርክታቸው አልጋ ወራሽ በመቃብራቸው ጥግ ቁሞ መቃብራችንን እየቆፈረ ስለምናየው ነው። የስግብግብ ጁንታዎች የመቃብር ዘብ መተከል ላይ በህይወት አለ። በየቀኑ ብዙ ንጹሀንን ይገድላል። በየክልሉ ሰርጎ እየገባ ለህጻናት ለአረጋውያን፣ ለአባዎራዎችና  ለመበለቶች የሙት መንፈስ ያድላል። ብሄር መርጦ የሚበላው የኦነግ ሽኔ ክንፍ፣ የትህነግ ቅራሪ የሆነው  የጉሙዝ አማፂ ቡድን ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የፈጸሙት ህገወጥ ጋብቻ የትህነጋውያኑ የሙት መንፈስ ወራሾች መሆናቸው አያጠራጥርም። እነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች መገደላቸው አይቀርም። የእነሱ መገደል ብቻውን ለኢትዮጵያ ሰላምና ለዜጎች ሰብአዊና ህሊናዊ ጤንነት አልፋና ኦሜጋ አይደለም። ስግብግብ ጁንታው ተገደለ አልተገደለ ፣ ኦነግ ሸኔ ተገደለ አልተገደለ ፣ የጉሙዝ አማጺ ተገደለ አልተገደለ ፣ የሱዳን ክፉ መንፈስ ተገደለ አልተገደለ ፣ የግብጽ ፈርኦናዊ መናፍስት ተገደለ አልተገደለ ኢትዮጵያን ነጻ አያወጣትም።
የመረጡት መንገድ ነውና ሁሉም ይገደሉ ሸጋ ነው። በዚህ ረገድ የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን እየፈጸመው ያለ ጀብዱና ኢትዮጵያዊ ተጋድሎ ታላቅ ክብር የሚሰጠውና በወርቅ ቀለም የሚጻፍ ነው። ኢትዮጵያን ነጻ የሚያወጣት ግን የስሁት ትርክት ቁሞ ቀርነት ሙሉ ለሙሉ ሲደመሰስ ነው። እዚህ ላይ ፖለቲከኞች ፣ ምሁራን ፣ የሚዲያ ሰዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ነፍስ ያወቅን ሁሉ መረባረብ ይኖርብናል። የስግብግብ ጁንታወች አካላዊ መገደል ሀሳባዊ ኑባሬያቸውን ካላከሰመው ነገም የሚቀጥል ችግር አለ ማለት ነው። ታሪክን በታሪክ መሞገት እየተቻለ ታሪክን ማጭበርበርም ሆነ በታሪክ ላይ የውንብድና ወንጀል ደጋግሞ መፈጸም ካለፈው ስህተት ባለመማር ለዳግም የመናቆር ቅርቃር መዘጋጀት ነው።
ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ችግር ያለባት አገር ብትሆንም ባለፉት አምስት አስርተ አመታት የተደረተባት ችግር ግን በቀላሉ የሚፈታ አይደለም። አሁን በምንገኝበት የታሪክ መድረክ ሳይቀር እየተፈጸሙ ያሉ ኢሰብአዊና ዘግናኝ ድርጊቶችን  ሊያጭበረብር የሚፈልግ ስሁት ብዕርና ቀሳጢ አንደበት የነገሰባት ምድር ናት ኢትዮጵያ ።
በዘመናችን የተቆረጡ እጆች ፣ የተተለተሉ ሰውነቶች ፣ በግፍ የተቀሉ አንገቶች ፣ በጭካኔ የተበለቱ ልቦች፣ ጉበቶችና ኩላሊቶች ፣ ያለርህራሄ የተነቀሉ የሴት ልጅ ጡቶችና የወንድ ልጅ ሙርጦች፣ በታንክና በስካቫተር የተጨፈለቁ በድነ ስጋዎች፣ ለአእምሮ በሚዘገንን ሁኔታ በጭካኔ በትር ፣ በድንጋይ ፣ በቀስት ፣ በገጀራ ፣ በቢላዋ ፣ በተተኳሽና በተቀጣጣይ አውዳሚ መሳርያዎች የተለበለቡ የንጹሀን ዜጎች፣ እንደዝንጀሮ ናዳ ወደገደል ተወርውረው  እልቂት የተፈጸመባቸው የሀገር ልጆች የምናስታውሳቸው በምንድን ነው ?
የበደኖ አዙሪት ለጉራ ፈርዳ ፣ የጉራ ፈርዳ አዙሪት ለጉሊሶ ፣ የጉሊሶ አዙሪት ለቡለን ፣ የቡለን አዙሪት ለማይካድራ፣ የማይካድራ አዙሪት ለድባጤ፣ የድባጤ አዙሪት…..ነገ ለማን እንደሆነ በማይታወቅበት ነባራዊ ሁኔታ ምን ብናደርግላቸው ነው የምናስታውሳቸው። በቁጥርስ በአይነትስ  ስንት የሰማዕታት ሀውልት ያስፈልጋቸዋል። ኦ ጉራ ፈርዳ ብለን ሳናበቃ፣ ኦ ጉሊሶ ይተካል። ኦ ጉሊሶ ብለን ሳንጨርስ ኦ ማይካድራ ይተካል። ኦ ማይካድራ ብለን ሳንጽናና ኦ ቡለን ፣ ድባጤ እያለ ይቀጥላል። ይህንንም አይን ያወጣ የታሪክ ሀቅ ሊያድበሰብስ ፣ ሊያፈራርስ ፣ ሊያጭበረበር የሚፈልገው ስግብግብ ጁንታ ብዙ ነው። ህሊና ላለው ሰው፣ አእምሮ ላለው ፍጡር እንዲህ አይነት ቁማር መፍቀድ በእውነት ከስግብግብ ጁንታነት በላይ ነው። እርግጥ ነው የአምስት አስርተ አመታት እርስ በእርስ የመተላለቅ ውጥን አሁናዊ ድርጊት በቅጡ በቅጡ ካላደረግነው የነግ በኔ (ነገ በእኔ) ትንቢታዊ ሀቅ እንደወንዝ ሙላት ከተፍ ማለቱ አይቀርም። እስከአሁን የሆነው ሁሉ ሆነ ። ሀውልት አቁመን ቂምና ጥላቻን የማውረስ ቅንጣት ታህል ፍላጎት ባይኖረንም ቀለም በጥብጠን ፣ ብራና ፍቀን፣ ብዕር ቀርጸን በደብተራነት (የዘመኑ ዶክተር ፣ ፕሮፌሰር ፣ ተመራማሪ ፣ አማካሪ እንደማለት ነው) ጥበብ እንከትበዋለን። ቂምና ጥላቻ ፣ ፖለቲካዊ ደባና  ርዕዮተዓለማዊ ሸፍጥ ለትውልድ አይተላለፍም ስንል በሰላም ፣ በይቅርታና በፍቅር ማህተም እንዘጋዋለን። እንዲህ ነበሩ አሉን ፣ እንዲህም አደረጉን እንዲህ ግን መሆንም ማድረግም አንፈልግም ስንል አገር በሚያሻግር የታላቅነት ምስጢር ክርችም አድርገን እንዘጋዋለን። መፍትሄው የጥላቻንና የስሁት ትርክት መናፍስታዊ ልክፍትን ጥርቅም አድርጎ መዝጋት ብቻ ነው።
ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትቀጥላለች !!!!
 ለንጹሀን ወገኖቻችን እልቂት መሠረቱ በታሪካችን ላይ  የተፈጸመ ስሁት ትርክት ከፍ ያለ ተጠያቂነት ይይዛል። በዚህ ሁሉ እልቂት የሚደሰቱ ለኢትዮጵያ መበላሸትና መበሻቀጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ትህነግና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና ቅዠት አቀንቃኞች ናቸው። እነዚህ የስሁት ትርክት ቁሞ ቀሮች በየሚዲያዉ በሚንደላቀቁባት አገርና ባፈተተው እንዲጓዙ በተፈቀደበት የፖለቲካ ምህዳር  ውስጥ ስግብግብ ጁንታዎች ተገደሉ የሚለው ዜና በእውነት ስላቅ ነው።
አገር ለማፍረስ ያሴሩ ጁንታዎች ተገደሉ ብለን የምስራች ቃል በምናውጅበት የቴሌቪዥን መስኮቶች፣ ጋዜጦች ፣ መጽሄቶች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ የማህበራዊ ድረገጽ ትስስር የግንኙነት መረቦች፣ የባለስልጣናት መግለጫዎችና ቃለመጠይቆች ስግብግብ ጁንታዎች ያወረሱንን ትሩፋት የሚያቀነቅኑ ከሆነ በእርግጥም ጁንታዎች አልተገደሉም።
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን መተከልን ጨምሮ በሁሉም የጦር አውድ ላይ እየከፈለው ያለውን ክቡር መስዋዕትነት የሚያግዝ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስራ መጀመር ይኖርብናል። በዚህ አውድ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጨምሮ ሁሉም መሪዎች የተጫወቱትን ሚና አለማድነቅ ንፉግነት ከመሆኑም በላይ ፍርደገምድልነት ነው። የመላው ህዝብ የደጀንነት ተሳትፎም ማለፍያ ነው። ጠቅለል ሲል ያሸነፈው ኢትዮጵያዊነት ነው። ነገር ግን ጁንታዎቻችን አልተገደሉም።
እንደሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ሁሉ በፖለቲካችን፣ በመዋቅራችን፣ በጽሁፋችን፣ በመንፈሳዊና በምድራዊ አስተምህሯችን፣ በየተሰማራንበት የስራ መስክ ሁሉ፣ በምናረጋግጠው አመራር ጭምር በውስጣችን የሚንከላወሱ  ስግብግብ ጁንታዎቻችንን ማደን አለብን። በየቀኑ የሚገድለንንና የሚያስገድለንን ሁሉአቀፍ ያልተገራ መስተጋብራችንን ፈጥነን እናርም። ለስግብግብ ጁንታዎች አቅምና ጉልበት ፣ ስንቅና ትጥቅ እየሆነ የሚገኘውን ውስጣዊ ስህተቶቻችንን እንግደል። ፖለቲካው በውስጡ ያለውን ስግብግብ ጁንታ መግደል ይጀምር። ሁሉም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ መዋቅር በውስጡ ያለውን ስግብግብ ጁንታ መግደሉን ያረጋግጥ።
እኛ ነፍስ ያወቅን ኢትዮጵያውያን ሁላችንም በውስጣችን ያልታገልነው የጥላቻ ፣ የእርስ በእርስ መፈራረጅ ፣ የጥራዝ ነጠቅነት፣ የጭካኔና የስግብግብነት ሰንኮፍ ቀፍድዶ ይዞናል።
በሁላችንም ስነልቦና ውስጥ ትህነግ ሰራሽ ማንነት አለ። በአይናችን ከምናየው የሰቆቃ ድርጊት ይልቅ የሰማነውና እድሜ ዘመናችንን እያልመዘመዘ እንደብል የበላንን ስሁት ትርክት አግዝፈን ማነብነብ እንመርጣለን። ክፉ ክፉውን በመዘገብ ለትውልድ የሚያስተላልፍ ጨለምተኛ የታሪክ ቤርሙዳችንን እናስተካክለው። በጀርመናዊው ቢዝማርክና  በኢጣልያዊው ጋሪባልዲ ፍቅር ተነድፈን ስናበቃ ኢትዮጵያ ላይ ስንደርስ እንደጓያ እህል ወገባችንን የሚሰብረው ፍልስፍና መዳኒት ይፈልጋል። የማህተመ ጋንዲሂንና የኔልሰን ማንዴላን የሞራል ልዕልና ስናሞካሽ አርጅተን ኢትዮጵያን ሾተላይ ማድረግ ለማንም አይጠቅምም። እነእገሌ የኦስካር ተሸላሚ ሆኑ ብለን ጣቶቻችን እስኪነቀሉ እንዳላጨበጨብን ኖቬል ጉበናችን ላይ ሲደርስ በነቀፌታ መውረግረግ የስግብግብ ጁንታነት ልክፍት ነው።
ቫቲካን ላይ ቁመን ያመሰገንነው ቅድስት ስላሴ ኢትዮጵያ ስንደርስ ያንዘፈዝፈናል።  በርሊን አደባባይ ላይ የተማጸንነው ጌታ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልጋይ ሊሆን አይችልም። መካመዲና ላለው ቤተጸሎት ተንበርክከን አክብሮት ሰጥተን ስናበቃ ሀረር ወይም መርካቶ ላይ ያለውን ቤተሙስሊም (መስጂድ) የምንነቅፍበት አመክንዮ የዜሮ ድምር ጨዋታ ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ስንዱ እመቤት ፣ መሶበ ወርቅ ናት። ችግሩ በውስጣችን ካለው የጁንታ መንፈስ ነው።
መውጫ መንገድ
===========
1. ነፃ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው በመረጡት የጥፋት መንገድ እየተለቃቀሙ ከሚገደሉት ስግብግብ ጁንታዎች የተሻልን ሆነን ካልተገኘን መተከልን በሌላ መተከል እንቀይረው ካልሆነ በስተቀር ለውጥ አናመጣም። በስንፍናችን ምክንያት እርስ በእርስ የመጠፋፋት ታሪካችን ይቀጥላል። ስለሆነም በውስጣችን የሚንከላወሰውን ስግብግብ ጁንታ በመግደል ራሳችንን ነጻ እናውጣ።
2. ዛሬ ላይ እየሆነ ያለው የእኛነታችን እውነተኛ ኑባሬ ነው። ልዩነቱ የቅደም ተከተል ጉዳይ ነው።  ትላንት አብዲ ኢሌ የሰራውን ስህተት ገና በማለዳው ደብረጽዮን የደገመው። ነገስ ብለን እንጠይቅ ። ከዚህ የስህተት አዙሪት የምንላቀቀው በእርግጥም ከቀደሙ ስህተቶቻችን ስንላቀቅና ደግመን ደጋግመን ስህተት ከመስራት ስንቆጠብ ነው። በለውጥ ዘመናችን ብቻ የሁለት ክልሎች የተገንጣይነትና  የአፈንጋጭነት ፊትአውራሪዎችን አስተናግደናል። ምስጢሩ የአምስት አስርተ አመታት የግፈኞች እቅድ ውጤት ቢሆንም ቅሉ ዛሬ ላይ ተምረን ነገን የተሻለ ነገ ማድረግ አለብን። እንደአገር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማድረግ ብንችልም ሰላማዊና ተወዳዳሪ አገር መፍጠር ግን አልቻልንም። እንደአገር የኖቤል ፈርጥ ሽልማት እድለኞች ብንሆንም ስህተትን ደጋግሞ ላለመስራት መወሰን አለመቻላችን በታሪክ ሀዲድ ላይ የቆምን ደካማ ቋጠሮ ሁነናል። ስለሆነም ደጋግሞ ስህተት ከመስራት እንታቀብ።
3. የውጤቱ መንስኤ ላይ እንረባረብ።የዛሬ ድካማችን የትላንትና ስንፍናችን ውጤት ነው። የዛሬ ሞታችን የትላንትና ቅድመ ወንጀል ዝግጅታችን ነው። እንደአገር መሰረት እያጸናንና እያጠበቅን አልመጣንም። የቀደመውን መሰረታችንን እያፈረስንና እየደረመስን እንጂ። ከትላንት የምንማር ብልሆች እንሁን። መሰረታችንን እናፅና ፣ በጸናው መሰረት ላይ ቁመን ስህተቶቻችንን እናርም። አድዋ፣ ማይጨው፣ ኢትዮ ሶማልያና ኢትዮ ኤርትራ ላይ ተገኝተን ሜዳልያ ለመውሰድ የምንደፍረውን ያህል የችግሩም ተካፋይ እንሁን። የድልን እፍታ እየጨለፉ ለማጣጣም የምንሽቀዳደመውን ያህል የኪሳራ ታሪኮቻችንንም በድፍረት መጋራት አለብን።
የብሽሽቅ ፖለቲካ ለማናችንም አይጠቅመንም። የሰው ዘር ውሀ ልኮች እኛ ነን የሚል ጫፍ ረገጥ ጨፍላቂ አስተሳሰብም ሆነ ቅኝ ተገዝተናል ታሪክ አፋሽና ሀቅ  ደምሳሽ ብያኔ ለህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያ እርባና ቢስ የተረኝነት ቅዠት ነው። እንዲህ አይነቱን በሽታ ሁላችንንም አይጠቅመንም። አገር ስንሆን አብረን ነበርን። ፡ሁላችንም በታሪክ ስህተት ውስጥ አልፈናል። በጀግንነትም ተዋድቀናል። በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ የታሪክ አላባዎች የፈጠሩብንን ቅዠት በትብብርና በአብሮነት ስሜት፣ በእኩልነትና በአንድነት መንፈስ እናርም። በትላንት ስሁት ትርክት ተቸክለን እንደአበደ ውሻ እርስ በእርስ አንነካከስ። በታሪክ መግባባት ካልቻልን አለመግባባታችንን በትምህርትነት ወስደን ዛሬን ለመኖር ነገን ለማሳመር እንትጋ። በህግ መከልከል ያለበትን በህግ እንከልክል። የዜጎች ግድያና እልቂት ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ህመማችንን በዘላቂነት አይፈውሰውም። ግድያና እልቂት የሚሰፍሩ ሚዛኖችን መግደል እንጀምር።
እስከአሁን ድረስ የሚያልቁ ወገኖቻችን ደም ወደላይ፣ ወደሰማይ ፣ ወደሰማያ ሰማያት ይጮሀል። ይኸ የኛም የቀጣዩም ትውልድ የተከማቸ እዳ ነው። ለዚህ ሁሉ ጥፋት ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን።
መንግስት ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የሚዲያና የሃይማኖት ተቋማት፣ ገብቶንም ሳይገባንም የምንሞነጫጭር ዘባተሎ ብዕረኞች፣ በእውቀት ፈለግና በጥልቅ የታሪክ ምርምር የደረሱበትን ሳይሆን ባለፉት ሃምሳ አመታት በወፍ በረር የቃረሙትን ስሁት ትርክት እንደገደል ማሚቶ የሚያስተጋቡ ተረፈ ትህነጎች ሁሉ ለዚህ አገር ብልሽት ኃላፊነት መውሰድ አለብን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ለዘለአለም  ይጠብቅ !!!
Filed in: Amharic