>

ጠላታችን ቀስቱ አልያም ጥይቱ ሳይሆን ተኳሹ ነው፤ እሱም ብልጽግና ፓርቲ ነው...!!! (ክርስቲያን ታደለ)

ጠላታችን ቀስቱ አልያም ጥይቱ ሳይሆን ተኳሹ ነው፤ እሱም ብልጽግና ፓርቲ ነው…!!!

ክርስቲያን ታደለ

የመተከል ችግር ዋነኛ ተጠያቂዎች መንግስትና ገዥው የብልጽግና ፓርቲ ናቸው። ዜጎችን ከዘር ፍጅት መታደግ የማይችል…ባስ ሲልም የሾማቸው አመራሮች በዘር ፍጅት በቀጥታ እጃቸውን አስገብተው በደም የተበሻቀጡበት የፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነት ይዞ እንዲቀጥል መደረጉ ትልቅ ስህተት ይሆናል። ብልጽግና ፓርቲ የዘር ፍጅት የፈፀመና ያስፈፀመ ፓርቲ ነው።
ይህ በዘር ፍጅት ወንጀል በደም የተጨማለቀ ፓርቲ በምን የሞራል መነሻ ነው በቀጣይ አገርና ሕዝብ ለማስተዳደር ለምርጫስ የሚቀርበው? የሾማቸው ግለሰቦች በዘር ፍጅት ወንጀል ሲሰማሩ መጠየቅ ያልቻለ ፓርቲ፣ ከሕግም ከሞራልም ባፈነገጠ መንገድ ዜጎች በአማራ ማንነታቸው ተለይተው ሲጨፈጨፉና እንደቆሻሻ ሲጣሉ በዝምታ የተባበረ ፓርቲ አገር እንዲመራ ስለምን ይፈቀድለታል?
ወንጀለኛ አመራሮች ምን ያድርጉ? ስምሪት የሰጣቸው ፓርቲያቸው ነው!  የትሕነግ የጭቆና እርሾ ካልተደፋ በስተቀር ሕዝባችን እረፍትን አያገኝም። ጭቆና ከነሰንኮፉ ካልተነቀለ በስተቀር አገር ሰላም አትሆንም።  የመተከል የዘር ፍጅት ያንገበገባችሁ ወገኖች ትኩረታችሁን በሙሉ በብልጽግና ፓርቲ ላይ አድርጉ። ፓርቲው ለራሱ ኅልውና ሲል የዘር ፍጅቱን አስቁሞ ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅለት አቅጣጫ ያስቀምጣል ወይንም የትሕነግ እጣፈንታን ጊዜ ያስጎነጨዋል። በአሁኑ ወቅት ዋነኛ የአማራ ሕዝብ ጠላት ብልጽግና ፓርቲ ነው። ይኸው ፓርቲ የመደባቸው አመራሮች በወንጀል በመሳተፍና ወንጀሉን በበቂ ትኩረት ባለመከላከል በሕዝባችን ላይ የማያባራ የዘር ፍጅት ፈጽመዋል።
Filed in: Amharic