>

የአማራ ልዩ ሃይል "ስጋት ነው" ሲባል አሜን ብለው ወገባቸውን የሰበሩ ብአዴኖች ዛሬ በምናቸው ቀና ይበሉ ....?!? (መስከረም አበራ)

የአማራ ልዩ ሃይል “ስጋት ነው” ሲባል አሜን ብለው ወገባቸውን የሰበሩ ብአዴኖች ዛሬ በምናቸው ቀና ይበሉ ….?!?

መስከረም አበራ

የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መተከል ገብቶ ነፍሳትን የሚታደግ ልዩ ሃይል የማይልከው ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳል። በሌላ በኩል የአማራ ልዩ ሃይል መተከል የመግባት መብት የለውም የሚሉ አሉ። እነዚህ የአማራው ሞት መቀጠል ብቻ ስልጣን መያዛቸውን የሚያስረግጥላቸው  እነ ባለ ጊዜ ናቸው።
 የሆነ ሆኖ የአማራ ልዩ ሃይል ቀርቶ ከኢትዮጵያ ድንበር ውጭ ያለ አካልም የዘር ማጥፋትን ለማስቆም መንቀሳቀስ እንደሚችል ነው አለማቀፉ ህግና ፍርድቤት የሚያዘው።(ከታች ያያዝኩትን የUN ዶክመንት ተመልከቱ)
ከሆነ የአማራ ልዩ ሃይል ወደ መተከል የማይገባው ለምንድን ነው መባሉ አይቀርም። የዚህ ምክንያቱ የአማራ ልዩ ሃይል ቁጥር መሳሳት ነው። በርግጠኝነት የአማራ ልዩ ሃይል ቤኒሻንጉል ቢገባ የአብይ መንግስት በ30 ደቂቃ ውስጥ የአማራ ክልል ባለስልጣናትን አንጠልጥሎ ቃሊቲ ያወርዳል ፣”በጉምዝ ህዝብ ላይ ጭፍጨፋ ያወጁ ሌሎቹ ጁንታዎች ተያዙ” ሲል ፕሮፖጋንዳ ይደልቃል።
 ይህ እንዳይሆን መንግስትን ሁለቴ እንዲያስብ የሚያደርግ የአማራ ክልልን የሚያስከብር ልዩ ሃይል የለም!ያለው ወደ ቤኒሻንጉል ሲላክ ደግሞ አብይ መከላከያ ሰራዊት ቀርቶ  ሪፐብሊካን ጋርድ ሳይቀር ልኮ ያስፈጀዋል።
 የዚህ ሁሉ ስር መሰረቱ የዛሬ ስንት አመት የአብይ መንግስት “በሃገሪቱ ያሉ ልዩ ሃይሎች ሁሉ ለኢትዮጵያ መልካም ሲሆኑ የአማራ ልዩ ሃይል ግን ለኢትዮጵያ ስጋት ነው” ሲል በሚሊተሪ ካውንስል አስወስኖ አማራ ክልል ብቻ ልዩ ሃይል እንዳያሰለጥን ሲወስን የአማራ ብልፅግና መሪዎች (ያኔ አዴፓዎች) “አሜን ፣ይሁን ጌቶች” ብለው መቀበላቸው ነው።
 ብአዴኖች ከወያኔ መሄድ በኋላ ከሰሩት ትልቅ የፖለቲካ መነሁለል ይህን የሚስተካከል ነገር ያለ አይመስለኝም። ልዩ ሃይል አይሰልጥን ከተባለ ሁሉም ጋ መሆን ሲገባው የአማራ ልዩሃይል እንጅ ሌላው ስጋት አይደለም ሲባል ይሁን ብሎ ተስማምቶ ነሁልሎ የሚቀመጥ የፖለቲካ ሃይል በምድር ላይ ይገኛል??????? ያን ጊዜ የሰሩት ስህተት ፣ያኔ ለንጉስ ያጎነበሱበት ማጎንበስ ዛሬ ወገባቸው ቀጥ እንዳይል ጨምድዶ ይዟቸዋል።
Filed in: Amharic