>

ሁሉም በሀገር ነው. ..!!! (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

ሁሉም በሀገር ነው. ..!!!

ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን

ሳቅ ፈገግታ ደስታን ሁሌ የምናየው፣ሁሌ የምናየው፤
ሀገር በነፃነት ኮርታ ስትኖር ነው፣ ሁሉም የሚያምረው፤

 ፩

ከላይ ያነበባችሁት በጥላሁን ገሰሰ አንደበት የናኘ ዘመን አይሽሬ የዘፈን ግጥም ነው፡፡ ቢደመጥ፣ ቢደመጥ አይሰለችም፡፡ ሀገርን ያህል ነገር አቅፎ የያዘ የጥበብ ሥራ ነውና፡፡ የግጥሙ እና የዜማው ደራሲ ደግሞ አየለ ማሞ ነው፡፡
አየለ ማሞ፣ የማንዶሊን ንጉሥ፡፡
እንደ ሊድ ጊታር ያለ፣ ከሊድ ጊታር አነስ የምትል፣ እንደክራር ዓይነት ድምፅ የምታወጣ፣ ባለ አራት ገመድ የክር መሣሪያ፣ በአየለ ማሞ እጅ ላይ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አስቆጥራለች፡፡ ከአንጋፋዎቹ ድምፃውያን፣ እስከመሃከለኞቹ፣ ከነሱም አልፋ እስከአሁነኞቹ ድረስ በዚች ማንዶሊን የተሰናሰኑ ዜማዎችን ተጫውተዋል፡፡ እሱ ራሱ ከብዙነሽ በቀለ ጋር በሰርግ ዘፈን መድረክ ላይ ነግሶበታል፡፡

 ፪

አየለ፤ በያኔው አጠራር ሸዋ ክ/ሃገር ፍቼ ነው የተወለደው፡፡ በልጅነቱ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ዲያቆን ሆነ፡፡ የደብር አሜን ተክለኃይማኖት ቤተ ክርስትያን ዳቆን፡፡ ብዙም አልቆየ የቀድሞ የክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ውስጥ ተቀጠረ፤ በድምፅዊነት፡፡
ይህ የሆነው የዛሬ 64 ዓመት ነው፡፡ ወሩ ደግሞ ጥር፡፡ ከወሩም በመጀመሪያ ቀን 1949 ዓም ክብርዘበኛ ሙዚቃ ክፍልን የተቀላቀለው አየለ ማሞ በመጀመሪያ የተጫወተው” የእኔ ውብ ዓይናማ” የሚል ዘፈን ነበር፡፡ ከዚያም “ያለሰለሴ ባዬቲ” (ኦሮምኛ)፣ እና “እማማ ድንቡሎ” የተሰኘ ጉራጊኛ ዘፈን መድረክ ላይ ተጫውቷል፡፡ ይሁን እንጂ የበለጠ ዕውቅና ያተረፈው በማንዶሊኑ በተጫወተው “ወይ ካሊፕሶ” በተባለው ዘፈን ነበር፡፡
አየለ ማሞ ክቡር ዘበኛ ውስጥ ድምፃዊ ብቻ አልነበረም፡፡ ተወዛዋዥም ጭምር እንጂ፡፡ ከተወዛዋዥነትም አልፎ እስከ አሰልጣኝነት ዘልቋል፤ በርካታ ሙያተኞችንም አፍርቷል፡፡

 ፫

አየለ ማሞ ለመማር ፈጣን ነበር፡፡ የሙዚቃ መሳሪያ የተማረው እዚያው ክቡር ዘበኛ ነበር፡፡ ወዲያው ሊድ ጊታር መጫወት ጀመረ፡፡ ከዚያም ወደ ማንዶሊን ተሻገረ፡፡ ለዘመኑ ፈርጦች ለእነ ጥላሁን ገሰሰ ግጥምና ዜማ ማቀበልን ተያያዘ፡፡  ቀጠለ፤ ቀጠለ፡፡ ለጥላሁን ገሰሰ ብቻ ከ200 በላይ ግጥምና ዜማ ያቀበለ ነው፡- አየለ ማሞ፡፡
ብዙነሽ በቀለ ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ ያቀነቀነችውን “አሸብርቆ ደምቆ እንደፀሐይ” የሚለውን ዘፈን ያቀበላት አየለ ነው፡፡ ከመሐሙድ አህሙድ ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኖች ውስጥ የአየለ ማሞ ስራዎች አሉ፡፡ ውብሻው ስለሺ ፣መንበረ በየነ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ሐመልማል አባተ፣ ብፅአት ስዩም ወረታው ውበት፣ አስቴር ከበደ ፣ እያዩ ማንያዘዋል፣ ሻንበል በላይነህ፣ ደረጄ ደገፋው፣ ጌታቸው ጋዲሳ፣ ምንያህል ጥላሁን ገሰሰ፣ ትዕግስት ይልማ፣ ከበቡሽ ነጋሽ (ሚሚ)፣ ገነነ ኃይሌ፣ ፣ ሀብታሙ ገ/ፃዲቅ (ፈረንጁ) ሕብስት ጥሩነህ፣ ሔለን በርሄ፣ ዳዊት ፅጌ….ወዘተ የአየለ ማሞን የግጥምና የዜማ ሥራዎች ተቋደሱ፤ አቋደሱንም፡፡ እንደው ለነገሩ ነው እነዚህን ድምፃውያን የጠቀስነው፡፡ እንጂ አየለ ማሞ ለቁጥር ለሚታክቱ አርቲስቶች ነው የግጥምና ሥራዎችን የሰጠው፡፡

 ፬

አየለ ማሞ እና ወርሃ ጥር “ግጥም” ናቸው፡፡
ከላይ እንደነገርኳችሁ፤ ክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል  የተቀጠረው ጥር 1 ቀን 1949 ዓ.ም ነው፡፡ የተወለደው ደግሞ ጥር 12 ቀን ነው፤ 1934 ዓም፡፡ አየለ ዘንድሮ 80ኛ ዓመቱን ይደፍናል፡፡
እኛ (የፈረንሳይ ወጣቶች) ለ64 ዓመታት ላበረከተልን የጥበብ ስራዎች ለማመስገን እና 80ኛ ዓመት ልደቱን ለማክበር አቀድን፡፡ እኔ፣ ዓለምዬ፣ ኤፍሬም ሽጉጤ እና ሮቤል ምትኩ ሆነን እንቅስቃሴ ጀመርን፡- በዚህ ሳምንት፡፡ የሰፈሩ ወጣቶች የሙዚቃ መሳርያ በነፃ ሊሰጡን ቃል ገቡ፡፡ አርቲስት ታምሩ ንጉሴ በነፃ ሙዚቃ ሊሰራልን ቃል ገባልን፡፡ የሰፈሩን ዕድር አዳራሽ ለመከራየት ገንዘብ ለማዋጣት አቀድን፡፡ እናም ሌላ ፣ ሌላ ዝግጅት እያቀድን ሳለ እንቅስቃሴአችንን የሚገታ መረጃ ደረስን፡፡
አየለ ማሞ ታሞ አልጋ ላይ ውሏል የሚል፡፡
እናም ሃሳባችንን ገታ አድርገን ልንጠይቀው ወደ ቤቱ ሄድን፡፡
ሳሎን ውስጥ አንዲት እናት ቁጭ ብለው ቴሌቪዥን ያያሉ፡፡ “ቤቶች” እያልን ገባን፡፡ አየለ ከመኝታ ቤቱ ውስጥ ድምፁን አሰማን፡፡
“እግዜር ይማርህ”
“ከዓመታት በፊት ኩላሊቴ ላይ ትንሽ ዕጢ ወጥታብኝ በኦፕራሲዮን ወጥታልኝ ነበር” አለን በትንሽ ጣቱ ጫፍ የዕጢዋን ልክ እያሳየን፡፡
“….አሁን እዛው ቦታ ነው ችግር የተፈጠረው፡፡ ኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ሄጄ ሕክምና ተደርጎልኛል፤ ወደ ሃሌ ሉያ ክሊኒክ ለተጨማሪ ምርመራ (ሲቲ ስካን) ልከውኝ አሁን የምርመራውን ውጤት ነው እየተጠባበቅኩ ነው ያለሁት፡፡….” አለን ከተኛበት ቀና ብሎ እየተቀመጠ፡፡

 ፭

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ  80ኛ ዓመት ልደቱን ልናከብር እንቅስቃሴ ጀምረን እንደነበር ነገርነው፡፡ ትክዝ ብሎ ሰማን፡፡ ሰማንና እንዲህ አለ፡-
“…. የፈንሳይ ልጆች ልደቴን ስታከብሩልኝ የመጀመሪያችሁ አይደለም፤ ይኼ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፤ እንዴት ብዬ እንደማመሰግናችሁ አላውቅም፡፡  ….. ሰሞኑን በጣም አሞኝ ነበር፤ አሁን ነው ቀና ያልኩት፡፡ አሁን በተስፋ ጭምር ነው የማነጋግራችሁ፡፡ ….ሆኖም ዝግጅታችሁ ላይ መገኘት አልችልም፡፡ አሁን ከዚህ ተነስቼ ውጪ በር አስፋልት ድረስ መሄድ አልችልም፡፡ ብትችሉ ብትችሉ፣ ያቺን ቀን በማህበራዊ ሚዲያ መልካም ምኞታችሁን ብትገልፁልኝ ደስ ይለኛል፤ እሱ ይበቃኛል፤ እግዜር ያክብራችሁ፡፡”
ይኼኔ እኔ ጣልቃ ገባሁ፡፡
“… ጋሽ አየለ አንድ ጥያቄ መልስልኝ”
“እሺ”
“ እስከዛሬ ከሰራሃቸው በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዘፈኖች ሁሉ የምትወዳቸውን ሶስት ዘፈን ምረጥ ብትባል የትኞቹን ትመርጣለህ?”
ትንሽ አሰብ አደረገና
“አንደኛ – ‹ሁሉም በሀገር ነው”፡፡  ….እናንተ ራሳችሁ አሁን የኔን ልደት ለማክበር የመጣችሁት በሀገር ስላለችሁ አይደል?! ሀገራችን ደህና በመሆኗ ነው፡፡ ሀገር ባይኖር አይደለም ልደት ቀብራችን አያምርም፡፡
“ሁለተኛ፣
“ስደሰት ብከፋም ቢመጣም መከራ፣
ሕይወት ካንቺ አይበልጥም ኑሪልኝ አደራ” የሚለውን፡፡ ለዚያች ልጄ  ለሕይወት ነበር የፃፍኩት” አለ ፊትለፊቱ ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን የልጁን ፎቶ እያሳየ፡፡
ሶስተኛ …….
“ያቺን ማንዶሊን አምጪ እስቲ! እንዲሁማ አትሄዱም፤ በዚያው ማንዶሊን እየተጫወትኩ ጋብዤአችሁ ነው የምትሄዱት” አለ፡፡
 ዓለምዬ ማንዶሊን አቀበለው፡፡ አየለ አልጋው ላይ ተመቻችቶ ተቀመጠና ሶስተኛውን የሙዚቃ ምርጫውን ተጫወተልን፡፡
እኔም ግብዣውን ትጋበዙልን ዘንድ ወደድኩ፡፡
እነሆ፤
እግዜአብሄር ይማርህ ጋሽ አየለ!
Filed in: Amharic