>
9:00 pm - Tuesday June 6, 2023

የትግራይ ክ/ሃገር ጉዳይ - ድኅረ ጦርነት (ከይኄይስ እውነቱ)

የትግራይ ክ/ሃገር ጉዳይ – ድኅረ ጦርነት

ከይኄይስ እውነቱ


በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛት የሚኖሩ የትግራይ ወገኖቻችን የቅርብ ቤተሰብ፣ ቤተዘመድና ወዳጆች ጦርነቱ በተካሄደበት የትግራይ ክ/ሀገር የሚገኙ በመሆናቸው ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ በበለጠ ሕማሙ እንደሚሰማቸው፣ እንደሚረበሹና እንደሚጨነቁ ማሰብ ተፈጥሮአዊና ርግጥ ነው፡፡ ሰብአዊነት የሚሰማውና ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ይህንን በሚገባ ይረዳዋል፡፡

እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው በትግራይም ይሁን በሌላ የኢትዮጵያ ግዛት በወገኖቻችን ላይ የሚፈጸምን ግፍ ሊያቃልል አይችልም፡፡ የኢትዮጵያዊነት መለኪያ ትናንት የተነሱና ውስጣቸው በጐሠኛነት ካባ የተለበጡ የፖለቲካ ማኅበራት ወይም ቡድኖች ወይም ግለሰቦች አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ ብርሃን ከጨለማ ጋር እንደማይተባበር ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊነት ከጐሠኛነት ጋር ኅብረት የለውም፡፡ ከጐሠኛነት ጋር በንጽጽር የሚቀርብ ሃሳብም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ልዕለ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን መሬት የረገጠ እውነታ ነው፡፡ ደብዝዞ ሊሆን ይችላል፡፡ ነውረኛ ‹ትውልድ› አቧራ አልብሶት ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እንደ አዲስ የምንፈጥረው ማንነት አይደለም፡፡ ስለሆነም ልምድ ሆኖብን እንደምንናገረው በጎራ አንክፈለው፡፡ ጎራ ካለ ጊዜ አመጣሹ ጐሠኛነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብሉየ መዋዕል (ዘመን የጠገበ) ሲሆን፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ከትግሬ ምድር የፈለቀው ፋሺስቱ ወያኔ/ሕወሓት የአገራችንን ህልውና መያዣ አድርጎ እኔ በሥልጣን ከሌለሁ ኢትዮጵያን አፈርሳታለሁ/እበትናታለሁ በሚል ማስፈራሪያ የማይፈልጋትን አገር እና የማይወደውን ሕዝብ ጭንቅ ጥብብ አድርጎ በጀግንነቱ ሳይሆን በጥላቻና በጭካኔው እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ከገዛ በኋላ ለተረኞችና ከሱ ለከፉ አፅራረ ኢትዮጵያውያን አሳልፎ በመስጠት ዛሬም ኢትዮጵያና ሕዝቧ መቼ እንደሚገላገሉት በማያውቁት ረጅም ምጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ እግዚአብሔር ደግ ነውና ወያኔን ብትንትኑን አወጣልን፡፡ ርዝራዦችም ካሉ ለኢትዮጵያ ህልውና ስንል የገቡበት ገብተን አንለቃቸውም፡፡ በወያኔ መንገድ የሚሄድ ሁሉ – የጊዜ ጉዳይ እንጂ – ዕጣ ፈንታው ዕድል ተርታው ይኸው ነው፡፡ 

በቅርቡ አገዛዙ ‹ጁንታ› ከሚለው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ወያኔ/ሕወሓት ከሚለውና ደመኛ ጠላቱ ከሆነው ቡድን ጋር የተካሄደው ጦርነት ከተገባደደ (መገባደድ ወደ መጨረሻ መዳረስ እንጂ ብዙዎች በስህተት እንደሚያስቡት መጠናቀቅ ማለት አይደለም) በኋላ  አስደንጋጭ መረጃዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ጦርነቱ ባስከተለው መዘዝና የኤርትራ (ሻእቢያ) ወታደሮች በፈጸሙት የበቀል ወረራ ምክንያት የትግራይ ሕዝባችን በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ዕለት ዕለት እየሰማን ነው፡፡ እንኳን በጦርነቱ መገባደድ ማግስት አሁንም በክፍለ ሀገሩ የመገናኛ መስመር አልተስተካከለም፡፡ በመሆኑም የሚወጡት መረጃዎች ድብልቅልቅ ያሉ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ የቊጥሩን ነገር ለጊዜው እንተወውና ሕዝባችን ከፍተኛ የሆነ የረሃብ፣ የበሽታ፣ የመናፈቀል፣ የመሰደድ መከራ ውስጥ ይገኛል፡፡ በተለይም በሻእቢያ ወታደሮች የግድያና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየተፈጸመበት ይገኛል፡፡ የዐቢይ አገዛዝ የሻእቢያ ወታደር ጦርነቱን ምክንያት አድርጎ ወደ ትግራይ ምድር በገዛ ፈቃዱ መዝለቁን ቢያምንም ቢያንስ በባዕድ ኃይል/በሻእቢያ በኩል ሕዝባችን የሚደርስበትን ግፍ ለማስቆም ስለወሰደው ርምጃ አልሰማንም፡፡ ፍላጎቱም ያለው ስለመሆኑ በርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ ሲደሰኩር ከነበረው በተቃራኒ የትግራይ ሕዝብንና ሕወሓትን አንድ አድርጎ ማየት ይመስላል፡፡ ሕወሓት ሕዝባዊ መሠረቴ ነው በሚለው የትግራይ ምድር ቊጥራቸው ቀላል የማይባል ደጋፊዎችና በዘረጋው የዝርፊያ ሥርዓት ተጠቃሚዎች እንዳሉት ሁሉ አብዛኛው ደሀ የትግራይ ሕዝባችን እንደተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕወሓት ከፍተኛ ግፍና በደል የደረሰበት እንዲሁም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ 

የወያኔ አገዛዝ በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስምና ሀብት ዝርፊያ ከምዕራብና ከምሥራቁ ዓለም ወዳጆችን መግዛቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በዓለም አቀፉ መድረክ ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎች አፍርቶ ጦርነቱ በተጀመረ ማግስት ሲጮኹለት እንደነበረና አሁንም እንደቀጠሉ የሚታወቅ ነው፡፡ በውጩ ዓለም የሚገኙ አባላቱና ሕወሓት ቀለብ ሲሰፍርላቸው የነበሩ ዲጂታል ወያኔዎች ከፍተኛ መፍጨርጨር እያደረጉ እንደሚገኙ፣ በመረጃ ረገድ ውዥንብር እየፈጠሩ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ምድር ላይ ያለውን እውነታ ተረድቶ የትግራይ ሕዝባችን የሚያስፈልገውን አስቸኳይ የምግብ፣ የመድኃኒት ዕርዳታ፣ መልሶ የማቋቋሙን ሥራ ከሰላምና መረጋጋቱ ጎን ለጎን ማስኬድ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባጠቃላይ ጥሪዬን እያደረግኹ፣ አገዛዙም (ሌላ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ከሌለው) ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በማስተባበር አስቸኳይ ርዳታ ማሰባሰብና ያለምንም እንቅፋት ርዳታ የሚያስፈልገው ሕዝባችን ጋር እንዲደርስ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ወገን በረሃብ እያለቀ ተራ የሥልጣን ፖለቲካ እንጫወታለን ማለት በምድርም ሆነ በሰማይ የሚያስጠይቅ ነውር ነው፡፡ 

አለመታደል ሆኖ ጐሠኛነት በነገሠበት ዘመን ላይ ስለምንገኝ የትግራይን ጉዳይ በሚመለከት ከተለያየ አቅጣጫ የሚሰማው ወሬ፣ጽሑፍ እንኪያ ስላንቲያ በዘረኝነት የተቃኘ ይመስላል፡፡ ወያኔ በዘረጋው አፋኝ መዋቅርና ሳያቋርጥ በነዛው ፕሮፓጋንዳ አብዛኛውን የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊ እሤቶች ያፋታው ይመስላል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በጠላትነት የሚያየው መሆኑ እስኪታክት የተነገረው ይመስላል፡፡ ስለዚህ ከራሱ ጐሣ ውጪ ያለውን በጥርጣሬ ማየቱ አሁን አሁን እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ ይህ ሁናቴ በመላው ኢትዮጵያ የሚታይ የወያኔ አገዛዝ የተከለውና አሁን ወራሹ የሆነው የዐቢይ የጐሣ አፓርታይድ አገዛዝ ያስቀጠለው የጥላቻና ሐሰት ትርክት መራር ፍሬ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለትግራይ ሕዝባችን ለማስተላለፍ የምፈልገው መልእክት እንደ ሕዝብ ሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ እንጂ ጠላቱ አለመሆኑን፣ ኦሮሙማ በሚባለው ፕሮጅክት አማካይነት ኢትዮጵያን ለማጥፋት፣ አማራውን ሕዝብ ከትግሬው በማጣላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሌት ተቀን የሚሠራውን፣ ባጠቃላይ የሰሜኑ ሕዝብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ተሳታፊ ሊሆን አይገባውም የሚል አቋም ይዞ የተነሳውን የዐቢይ አገዛዝ ልናውቅበት ይገባል፡፡ በኦሕዴድ/ኦነግ የበላይነት የሚመራው የኦሮሙማ ኃይል ይህንን ነውረኛ የሴራ ‹ፖለቲካ› ለማስፈጸም እንደ ግብር አባቱ ወያኔ የመንግሥትን መዋቅር ተጠቅሞ ያሰማራቸው ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች በደምም፣ በሥነ ልቦናም፣ በታሪክም በመልክዐ ምድርም በእጅጉ የሚቀራረበውን፣ በደስታም በመከራም ያልተለያየውን የትግራይና የአማራ ሕዝብ በጠላትነት እንዲተያይ 24/7 እየሠሩ መሆኑን ሊረዳ ይገባል፡፡ አንዳንድ ባለጌዎች የሚናገሩትና የሚጽፉት ሊያስቀይመንና ቅሬታ ሊፈጥርብን ቢችልም በበርካታ መከራዎችና ችግሮች ተፈትኖ ያለፈው የትግራይ ሕዝባችን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር አሁንም የተጋረጠበትን ፈተና እንደሚያልፈው አልጠራጠርም፡፡ ልዩነት የመጠን ካልሆነ በቀር ዛሬ ጐሠኞች የሐሰት ትርክት ላይ ተመሥርተው በፈጠሩት የጐሣ ፖለቲካና የአገዛዝ ሥርዓት ምክንያት በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዝናት ያልተገፋ ያልተበደለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የለም፡፡ ምሬት መገፋት ብዙ ሊያናግር ይችላል፡፡ የትግራይ ሕዝባችን ሆይ! የአማራው ወገንህ ካንተ ጋር ጠላትነት የለውም፡፡ ልብህንና ኅሊናህን ብትፈትሸው እውነቱን አንተው ታውቀዋለህ፡፡ ሕወሓትና ወራሹ የኦሮሙማ ፕሮጅክት አስፈጻሚ የዐቢይ አገዛዝ ግን ህልውናውን ለማጥፋት የተነሱ ደመኛ ጠላቱ በመሆናቸው እስከ መጨረሻው ይታገላቸዋል፡፡ ሕወሓትን ለመደምሰስ በተደረገው ትግል መሥዋዕትነት የከፈለው የዐቢይ አገዛዝን ወዶ እንዳልሆነ አንተም በሚገባ ታውቀዋለህ፡፡ በመሆኑም ከውስጥህ ሆነው ጥላቻ ለሚያራግቡ የሕወሓት እና የኦሮሙማ ኃይሎች ጆሮህን ሳትሰጥ ከወንድምህ የአማራ ሕዝብ ጋር አንድነትህን የበለጠ አጠንክረህ ኢትዮጵያ አገርህን የሕወሓት ወራሾች ከሆኑ ኃይሎች ልትታደግ ይገባል፡፡ 

በትግራይ ክ/ሃገር ከጦርነቱ ጋር በተያየዘ ተፈጽመዋል የሚባሉ ዋና ዋና ጉዳዮችን አንስቼ የሚሰማኝን አስተያየት ከመስጠቴ በፊት እንደ አንድ የየትኛውም ክ/ሃገር ተወላጅ ነኝ የማይልና ሁሉም ክፍላተ ሀገራት ግዛቴ፣ በየክፍላተ ሀገሩም የሚኖረው ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ነው ብሎ እንደሚያስብና አዲስ አበባ ተወልዶ እንዳደገና እንደሚኖር ኢትዮጵያዊ ጥቂት መርሆ ነክ ነጦቦችን ወይም ልዕለ ሃሳቦችን በቅድሚያ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡

  • በየትኛውም ስፍራ ባንድ ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ላይ የሚፈጸሙ ማናቸውም ኢሰብአዊ ድርጊቶች በሰዎች ልጆች ሁሉ ላይ የተፈጸሙ ኢሰብአዊ ድርጊቶች መሆናቸውን መቀበል፤
  • ኢትዮጵያውያን (ለጊዜው የሕጉን መሥፈርት ትተን) ኢትዮጵያ በምትባል ጥንታዊትና ታሪካዊት ነፃ ምድር በቅለው የአገሩ ባለቤት /በዓለ ሀገር/ የሆኑትን እና ለአስተዳደር ሲባል በተዋቀሩ መላ የኢትዮጵያ ግዛቶች እና በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተበትነው የሚኖሩ (ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባህል ያላቸውን) ማኅበረሰቦችን ወይም ሰዎችን መመልከቱን፤
  • ኢትዮጵያዊነት ብዙ ነገዶች/ጐሣዎች በታወቀ መልክዐ ምድር የሚኖሩበት ነገር ግን ነገድ/ጐሣ ዘለል የሆነ የአንድ ሀገር ሕዝብ የወል መታወቂያ/ማንነት መሆኑን፤
  • አሁንም የሕጉ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊነትን የተወሰነ ቡድን ወይም ግለሰብ ለሌላው በችሮታ የሚያድለው ማንነት አለመሆኑን፤ ለተለየ የፖለቲካ ቡድን ወይም ላንድ ማኅበረሰብ ተለይቶ የሚሰጥና በቡድኑ ወይም በማኅበረሰቡ ብቻ ጥብቅና የሚቆምለት ማንነት አለመሆኑን፤
  • ኢትዮጵያዊነት ሲከፋን/ሲመረን የምንጥለው/የማንፈልገው፣ ሲመቸን/ሲደላን ብቻ የምንቀበለው ማንነት አለመሆኑን፤
  • ኢትዮጵያውያን የየትኛውም ነገድ/ጐሣ አባላት ይሁኑ ወይም የትኛውንም ሃይማኖት ይከተሉ ወይም የትኛውንም ዓይነት ቋንቋ ይናገሩ ባገር ባለቤትነት ረገድ እኩል መሆናቸውን፤ በመሆኑም እንደ አንድ ሕዝብ በመከራውም በሐዘኑም እኩል ተካፋይ መሆናቸውን መቀበል፤
  • የነገድ/ጐሣ መቀያየር ቢኖርም የሕዝብንና የአገርን ሉዐላዊነት በሚክድ፣ ሕዝብን በጐሣ፣ በቋንቋና በሃይማኖት ከፋፍሎ አንድነትን በሚያጠፋ፣ የጋራ ታሪክና እሤቶችን በማጥፋት ዘመን የጠገበ ሀገረ መንግሥትነትን በፈጠራና ጥላቻ ላይ በተመሠረተ ትርክት ‹ሀ› ብሎ ለመጀመር ከሚፈልጉና የአገር ህልውናን አደጋ ላይ በሚጥሉ የጐሠኞች አገዛዝ ሥርዓት መካከል ልዩነትን አለመኖሩን መቀበል፤
  • ባንድ አገር ውስጥ በሚደረግ ጦርነት (የአገርን ህልውናና ሉዐላዊነት የሚፈታተን የውስጥ ጠላት ቢሆንም) የውጭ ኃይል በራሱ አነሳሽነትም ሆነ ተፈቅዶለት የሚገባና የሚሳተፍ ከሆነ ድርጊቱ ወረራ ከመሆኑም በተጨማሪ ሥልጣን ላይ ባለው አገዛዝ ተጋብዞ የገባ መሆኑ ከተረጋገጠ በከፍተኛ ወንጀል የሚያስጠይቅ ስለመሆኑ፤
  • አንድን እኩይ ድርጊት በነገድ/ጐሣ መርጦ ማውገዝ፣ መርጦ መንቀፍ ወዘተ.፤ መከራ የደረሰበት ወገናችንን በነገድ/ጐሣ መርጦ መርዳት፣ መርጦ ማዘን ወዘተ. ከሰብአዊነት የሚያወጣ የነውረኝነት ጥግ መሆኑን፤ 

የወያኔን ፈለግ በተከተለው፣ በተረኞችና የኦሮሞ የዘር ፖለቲከኞች (ኦሕዴዳውያን/ኦነጋውያን) በሚመራው፣ የአመራር ብቃትና ቈራጥነት በተለየው ልፍስፍስ የዐቢይ አገዛዝ ምክንያት በማለዳው ማስቀረት የሚቻል ጦርነት ተካሂዶ በብዙ መሥዋዕትነትና አገራዊ ሀብት ውድመት ጦርነቱ መገባደዱንና ወያኔ መደምሰሱን ሰምተናል፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያ ጠንቅ የሆነና ከምድረ ገጽ መጥፋት ያለበት የአጋንንት ስብስብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀዳሚ ጠላት ነው፡፡ የጦርነት በጎ የለምና ምንም ዓይነት ጥንቃቄ ቢደረግም ጦርነቱ በተካሄደበት የትግራይ ግዛት የሚገኘውን ከሕወሓት ወታደራዊ ኃይል ውጭ ያለውን ወገናችንን በሕይወትም ሆነ በንብረት በእጅጉ መጉዳቱ የማይቀር ነው፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛት የሚኖሩ የትግራይ ወገኖቻችን የቅርብ ቤተሰብ፣ ቤተዘመድና ወዳጆች ጦርነቱ በተካሄደበት የትግራይ ክ/ሀገር የሚገኙ በመሆናቸው ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ በበለጠ ሕማሙ እንደሚሰማቸው፣ እንደሚረበሹና እንደሚጨነቁ ማሰብ ተፈጥሮአዊና ርግጥ ነው፡፡ ሰብአዊነት የሚሰማውና ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ይህንን በሚገባ ይረዳዋል፡፡

  • እንደሚታወቀው ጦርነቱ በሚካሄድበት ሰሞን የመገናኛ መስመሮች ሁሉ በመቋረጣቸው ምክንያት ከግምትና ተባራሪ ወሬ ባለፈ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አይቻልም ነበር፡፡ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ከሆኑት ከሁለቱም ወገን ምን ያህል ሰው እንደሞተ፣ ምን ያህል እንደቆሰለ፣ ምን ያህል እንደተፈናቀለ፣ ምን ያህል የንብረት ውድመት እንደደረሰ ወዘተ. አሁንም ድረስ በውል አይታወቅም፡፡ በሌላ በኩል በተራው/ወታደር ባልሆነው የትግራይ ሕዝብ ላይ በሞት፣ በመቁሰልና በንብረት ውድመት የደረሰ አደጋ እንዳለ ቢገመትም አሁንም ትክክለኛ መረጃ የለም፡፡ ሁሉም ከቆመለትና ከቆመበት ዓላማ አንጻር ያሻውን ሲናገር ይሰማል፡፡ እውነቱን ለመናገር ጥቂት የማይባሉ የትግራይ ተወላጆች ጦርነቱን ተከትሎ ትግራይ ውስጥ ስለተፈጠረው ሁናቴ ዋና የመረጃ ምንጫቸው የነበሩት የፈጠራ ትርክት በማዘጋጀትና በሌላ አገር የተፈጸሙ ወንጀሎችን በኮምፒውተር ቴክኒክ አቀነባብረው ምስሎችን እያዘጋጁ በመልቀቅ ከሚታወቁት ዲጂታል ወያኔ ከሚባለው ቡድንና በውጭ በሚገኙ የወያኔ አባላት  መሆኑ አይካድም፡፡ ለደረሰው ሰብአዊ ቀውስና ጥፋት በዋነኛነት ተጠያቂ የሆኑት የውስጥና የውጭ የጠላት ኃይሎች (ሕወሓትና ሻእቢያ) መሆኑን መገናኛ በተወሰነ ደረጃ ክፍት ከሆነ በኋላ፣ በአገዛዙ የጦር መኮንኖች፣ ትግራይ ነዋሪ ከሆኑ ግለሰቦችና የውጭ ሜዲያዎችና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ተቋማት የተወሰኑ መረጃዎች (አንዳንዶቹ ሐቅ፣ ሌሎቹ ደግሞ ያልተጣሩ) ለማግኘት ተችሏል፡፡  

እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ታዛቢ የወያኔም ሆነ አሁን ያለው የኦሕዴድ/ኦነጋውያን አገዛዝ መሠረትና ጉልላቱ ውሸት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ እምነቴም እውነት እንደሆነ የአገዛዙ አለቃ በትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ባደባባይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ደጋግሞ ሲቀጥፍ ሰምተናል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ባልሆነው ደነዝ ‹ምክር ቤት› ጭምር፡፡ ከበቂ በላይ ማስረጃዎችም አሉ፡፡ ለአብነት ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ሦስት ቅጥፈቶችን ብቻ ላንሳ፤ 1ኛ/ ወታደር ባልሆነው አንድም የትግራይ ተራ ሕዝብ (ሲቪሎች) ላይ ጉዳት አልደረሰም፡፡ 2ኛ/ ጉዳት የደረሰባቸው ሃይማኖታዊም ሆኑ ታሪካዊ ቅርሶች የሉም፤ 3/ የድሮን ቴክኖሎጂ በተባለው የሕወሓት ዋና አመራሮች ያሉበትን ዐውቀናል ግን ከሕፃናትና ከሚሽቶቻቸው ጋር ስለሆኑ ርምጃ አልወሰደንም ባለ በማግስቱ የሕወሓት ዋና አመራሮች ያሉበትን ቦታ ለሚጠቁም የ10 ሚሊዮን ብር ወሮታ እንደሚከፍል ማሳወቁን ልብ እንላለን፡፡ በመሆኑም የአገዛዙ ሜዲያዎች በጭራሽ የሚታመኑ አይደሉም፡፡ የ27 ዓመታቱ የተመዘገበ ታሪካቸውም (track record) ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ለበለጠ ምክንያት ሕወሓት ለዓላማው ማስፈጸሚያ ያሠማራቸው መደበኛም ሆኑ ማኅበራዊ ሜዲያዎች የጠላት መሣሪያ በመሆናቸው ጥብቅናቸው ግልጽ ነው፡፡ ቊጥሩ ቀላል የማይባል የትግራይ ተወላጅ ግን (የሕውሓት አባላት ናቸው ካላልን በስተቀር) ሰምቶ የሚያስተጋባ መሆኑን ታዝበናል፡፡ 

አሁን በቅርቡ አንዳንድ መረጃዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በአገዛዙ ሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ከታመኑት ብንጀምር (ቊጥሩ ርግጠኛ ባለመሆኑ በደፈናው እገልጸዋለሁ)፣

1ኛ/ በጦርነቱ ምክንያት በሚሊዮን የሚቈጠሩ የትግራይ ወገኖቻችን በከፍተኛ ረሃብ ላይ የሚገኙና አስቸኳይ ርዳታ የሚሹ መሆናቸው፤

2ኛ/ በሺዎች የሚቈጠሩ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው እንዲሁም ሸሽተው በስደት ሱዳን እንደሚገኙ፤

3ኛ/ የኤርትራ አገዛዝ ወታደራዊ ኃይል ወደ አገራችን ዘልቆ በመግባት በትግራይ ወገኖቻችን (መጠኑ ባይገለጽም) በሕይወት፣ በአካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ በማድረስ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸሙን በዐቢይ አገዛዝ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊ በተባለው ባለሥልጣን በኩል መታመኑ ታውቋል፡፡ ወገኖቻችን በረሃብ መሞታቸውንም በጊዜያዊ አስተዳደሩ የማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ በኩል ተነግሯል፡፡

ከ3ኛው ልጀምር፤ የዐቢይ አገዛዝ በባለሥልጣናቱ በኩል የኤርትራ/ሻእቢያ ወታደራዊ ኃይል ጦርነቱን አስታኮ ወዳገራችን በመግባት በትግራይ ወገኖቻችን ላይ ጥቃት መሰንዘሩን በዚህም በወገኖቻችን ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ቢያምንም ይህ ባዕድ ኃይል በገዛ ፈቃዱ ድንበር ጥሶ እንደገባ ተናግሯል፡፡ ይሁን እንጂ የሌላ አገር ወታደራዊ ኃይል ባገራችን በመግባቱ ወረራ ፈጽሟል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ መንግሥትነት በተሰየመው አገዛዝ ሊጠየቅና ከትግራይ ምድርም ባስቸኳይ እንዲወጣ መደረግ ይኖርበታል፡፡ በግሌ በወያኔና በወራሹ የዐቢይ አገዛዝ ኢትዮጵያዊ የመከላከያ ኃይል አለ ከተባለ ሥራው ዜጎችን ከጠላት ኃይል መታደግና ሉዐላዊ ግዛታችንን መጠበቅ በመሆኑ የትግራይ ወገኖቻችንን ከጠላት ወራሪ መታደግ ግዴታው ይሆናል፡፡ ሕወሓት በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ያደረሰው አስነዋሪ የጦር ወንጀል ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ያስቆጣ ቢሆንም ለኤርትራ ሠራዊት መግባት ግን እንደ ምክንያት ሊቀርብ አይችልም፡፡ ቢያንስ ከአገዛዙ ፈቃድ ውጭ ገብተው ከሆነ ባስቸኳይ ማስወጣት ይኖርበታል፡፡ 

በጦርነቱ ምክንያት ሸሽተው ወደ ሱዳን የገቡ የትግራይ ወገኖቻችንን በሚመለከት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲደረግ ግን ትግራይን ለዘመናት ሲጠብቅ በኖረው የሰሜን ዕዝ የጦር አባላት ላይ የጦር ወንጀል፣ በጎንደር ማይካድራ ደግሞ በንጹሐን ዜጎች ላይ የዘር ፍጅት የፈጸሙ የሕወሓት ልዩ ኃይልና ‹ሳምሪ› የተባለው አሸባሪ የወጣቶች ቡድን ከተራው ሕዝብ ጋር ተቀላቅለው እንደሸሹ ስለሚነገር በሚገባና በጥንቀቄ ተጣርቶ እነዚህ አሰቃቂ ወንጀል የፈጸሙ የጠላት ኃይሎችን በሕግ ቊጥጥር ሥር ማዋል ያስፈልጋል፡፡

ሌላው ለረሃብ የተጋለጡ የትግራይ ወገኖቻችንን በሚመለከት መንግሥት ባለው አቅም፣ የቀረውን ደግሞ ከአገር ውስጥና ከውጭ ርዳታ በማስተባበር አስቸኳይ ርዳታ እንዲያገኙና በዘለቄታው መልሶ ማቋቋም ይኖርበታል፡፡ 

ባጠቃላይ በጦርነቱ ምክንያት በተራው የትግራይ ሕዝብ ላይ በኤርትራ ወታደራዊ ኃይል የደረሰው በደል በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለውና የሚወገዝ ነው፡፡ በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት በሚኖር ኢትዮጵያዊ ላይ የተፈጸመ ጥቃት አድርጌ ነው የማየው፡፡

ከዚህ በመቀጠል የማነሳው ብዙ ኢትዮጵያውያን ቊጥራቸው በቀላሉ የማይገመት የትግራይ ወገኖቻችን (የሕወሓት አባል ያልሆኑ) የሚሸሹትን በምድር ላይ የሚታይ ጽድቅ፣በልባችን የያዝነውን እና በይሉኝታ የማንናገረውን እውነታ ይመለከታል፡፡ የማነሳቸው እኔ በመጀመሪያ ደረጃ ምስክር የሆንኩባቸውና የዐደባባይ ምሥጢር የሆኑ ተሐዝቦቶች (observations) ናቸው፡፡ ሃሳቡ የሚያስከፋቸው ወገኖች እንዳሉ ባምንም አሁን ላይ ፍርጥርጥ ተደርገው መነገር አለባቸው፡፡ ተሐዝቦቴን በጥላቻና በክፋት የሚመነዝሩም እንዳሉ አልጠራጠርም፡፡ ልብ ያሰበውን ኵላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ አንድ እግዚአብሔር በመሆኑ ብዙም አልጨነቅም፡፡ 

በቅድሚያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የምትታወቀውን አንድ ኢትዮጵያዊት አነሳለሁ፡፡ ባነሳሁት ርእስ ረገድ ታናሽ እህቴ የምትሆነው መምህርት መስከረም አበራ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ከማናቸውም የኢትዮጵያ ክፍልና ከማንኛውም ሕዝብ በተለየ ሁናቴ በሕወሓት ተጽእኖ ሥር ለረጅም ጊዜ በመኖሩና ስለተቀረውም ኢትዮጵያዊ ሲሰበክለት የኖረውን ውሸት በመቀበል ወዶም ሆነ ተገዶ ከሕወሓት ጋር ትስስር መፍጠሩንና ደጋፊም መሆኑን፤ በዚህም ምክንያት ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል ሰፊ ሥራ እንደሚጠብቀንና እውነታውን በሂደት በማስረዳት ግንዛቤውን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ በጥቅሉ አንስተዋለች፡፡ ቃል በቃል ባይሆንም ሃሳቧ ይህ ይመስለኛል፤ አዛብቼው ከሆነ ከይቅርታ ጋር ለማረም ዝግጁ ነኝ፡፡ የተጠቀሰው ሃሳብ እንዳለ ሆኖ የኔ ተሐዝቦቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ምልከታዎች በየትኛውም ሁናቴ በትግራይ ክ/ሀገር ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ሰብአዊ ቀውስ፣ ሴት እህቶቻችንን በመድፈር የተፈጸሙ ነውሮች እና እንግልት የሚያቀሉ ተደርገው መወሰድ የለባቸውም፡፡ በፍጹም! አመለካከቱን የሚያንፀባርቁ የትግራይ ተወላጆች ለአብሮነት ሕይወት ራስን ለመመርመር እንዲያግዛቸው ያለሙ እንጂ፡፡

1ኛ/ ሕወሓት የጐሠኝነት አገዛዝን በሕግ፣ በመዋቅርና በሥርዓት ደረጃ ሲተክል የትግራይ ሕዝብ ቀድሞ የሚታወቅበትን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ባጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ተጋፍቶ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመነጠልና ቢያንስ በስብከት ደረጃ የትግራይን የበላይነት በሚያሳይና በተወሰነም መልኩ በሚያረጋግጥ ሁናቴ ነበር፡፡ ‹ከዚህ ወርቅ ሕዝብ በመውጣቴ…› የሚለው የዘረኛው መለስ አነጋገር እና ከዚያም በፊትም ሆነ በኋላ ለትግራይ ቅድሚያ የሚሰጡ ፕሮፓጋንዳዎች ሕወሓትን ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ሕዝብ (ከድርጅቱ ውጭ ያለውም- ባሉት የፓርቲው መዋቅሮች የተጠረነፈ በመሆኑ) የቀረው ኢትዮጵያዊ አለቃ ሆኖ እንዲሰማው አድርጓል፡፡ ይህ በሌሎች ዜጎች የፈጠረውን እጅግ የመከፋትና የመገለል ስሜት የትግራይ ሕዝብ እንዴት ዓይቶታል? ወይስ በራስ ሲደርስ ብቻ ነው ሕማሙ የሚሰማው፣ ጩኸቱ የሚበዛው?

2ኛ/ የጐሣ ፖለቲካ አንዱ መሠረት የተበዳይነት መንፈስ በመሆኑ ተበድሏል በሚል በሁሉም መስክ ለትግራይ ተወላጆች (ቅድሚያው በየደረጃው ላሉ የሕወሓት አመራሮች፣ ከዚያም ለአባላቱ) ጐሣን መሠረት ያደረገ መድልዎ ሲደረግ ቈይቷል፡፡ በመከላከያው፣ በፖሊስ፣በደኅንነቱ፣ በዲፕሎማሲው፣ በሲቪል ሰርቪስ (የጽዳት ሠራተኞች፣ ተላላኪዎችና ጥበቃዎች ሳይቀሩ ሌላውን ከፍ ዝቅ አድርገው ሲያዩና ሲያሽቆጠቁጡ አይደል እንዴ የኖሩት)፣ በትምሕርት ሥርዓቱ፣ በፍትሕ ተቋማት (በወህኒ ቤት ስቃይ ፈጻሚነት/ገራፊነት ሳይቀር)፣ በልማት ድርጅቶች፣ በብሔራዊ ባንክ፣ በንግድ ባንክ፣ በልማት ባንክ፣ በአየር መንገድ፣ በቴሌኮም፣ በኢንቨስትመንትና ንግድ በተለይ÷ ባጠቃላይ በኢኮኖሚው ወዘተ. አንደኛ ደረጃ ዜጎች ነበሩ፡፡  ተጠቃሚ ያልሆነ የትግራይ ተወላጅ አለ ወይ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ አዎን ሞልቷል ነው፡፡ በተለይ በገጠር ነዋሪው ደሀው የትግራይ ሕዝብ፡፡ ግን ይህ እውነታውን እንድንክድ አያደርገንም፡፡ ይህ ሁናቴ በጐሣው ማንነት ምክንያት በሕይወቱና በአካሉ ኢሰብአዊ ድርጊቶች የተፈጸሙበት፣ ሥራ እንዲያጣ የተደረገው፣ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለው፣ የበዪ ተመልካች የሆነው፣ የተሰደደው፣ ባገሩ ባይተዋር የተደረው፣ ባጠቃላይ ሲገፋ የኖረው የተቀረው ኢትዮጵያዊ የሚሰማውን ሥር የሰደደ የመገፋት ስሜት/ቅሬታ (resentment) የትግሬ ሰው ለአፍታ ቆም ብሎ አስተውሎታል? ወይስ በራስ ሲደርስ ብቻ ነው ሕማሙ የሚሰማው፣ ጩኸቱ የሚበዛው?

3ኛ/ እላይ በተራ ቊ. 2 ከተመለከተው ጋር በተያያዘ ወያኔ ኤፈርት በሚል ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፋቸው ሀብቶች የተቋቋሙ የፓርቲ ንግድ ድርጅቶች በዋናነት ተጠቃሚዎቹ የወያኔ አመራሮች ቢሆኑም በነዚህ ድርጅቶች ተቀጥሮ የመሥራት ዕድል ያገኘው ማነው? በየክፍላተ ሀገራቱ በሚደረገው የበጀት ድልድል በተለየ ሁናቴ ተጠቃሚው ትግራይ አልነበረም? ትግራይ ከሌሎች ክፍላተ ሀገራት ጋር ሲነፃፅር በተለይም በመሠረተ ልማት ረገድ ገጠሩን ጨምሮ (ከሌሎች በዝርፊያ ጭምር በተወሰደ ሀብትና ንብረት) ተመጣጣኝ ባልሆነና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ትግራይ አልለማም? ጥያቄው ለምን ተጠቀመ የሚል ተራ የቅናት ጉዳይ አይደለም፡፡ የፍትሕና የእኩል ተጠቃሚነት እንጂ፡፡ ዛሬ አንዳንድ የትግሬ ሰዎች ያዙኝ ልቀቁኝ እንደምትሉት ሳይሆን የቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወገናችን ነው ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ፣ በተወለደበት ቦታ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ፣ እንዳይሠራ ተደርጎ፣ ጦሙን አድሮ እያለ፣ ከትግራይ የመጣ ወገኑ (የሕወሓት አባልም ሳይሆን) በአንድ ጀምበር በአድልዎ ቱጃር ሲሆን÷ የቤት ንብረት ባለቤት ሲሆን ምን ይሰማው? እናስተውል! የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ ይታዘባል፡፡ ወይስ በራስ ሲደርስ ብቻ ነው ሕማሙ የሚሰማው፣ ጩኸቱ የሚበዛው?

4ኛ/ የ27 ዓመታቱን ግፍና ሰቈቃ ትተን የወያኔ ወራሽ የሆነው ዘረኛው የዐቢይ አፓርታይዳዊ አገዛዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዓመጻ ነጥቆ በጉልበት ሥልጣን ከያዘ በኋላ በመላው የአገራችን ግዛቶች በተለይም በአማራው ማኅበረሰብ እና በኦርቶዶክሳውያን ላይ (በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣ ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ በፈጠረው የሰው ቄራ ግዛት/በሽመልስና ጀዋር ቄሮዎች/፣ በቡራዩ፣ በአ.አ.፣ በሻሸመኔ፣ በአርሲ፣ በዝዋይ፣ በድሬደዋ፣ በጅጅጋ፣ በመተከል፣ በኮንሶ፣ በወለጋ ወዘተ) በዓለም ተሰምቶ የማይታወቅ ግፍ ሲፈጸም አንድ ሁለት ብለን በጣት ከምንቈጥራቸው ትግራውያን በስተቀር እንደ ሕዝብ ሌላው ቢቀር ለማውገዝ የደፈረ፣ ወገኔ ነው ብሎ የጮኸ ትግሬ አለ? የትግራይ ሕዝብ እኮ ታፍኗል የሚለው ምክንያት የትም አያደርሰንም፡፡ ሌላው በከፋ ሁናቴ አልታፈነም እንዴ? ወይስ በራስ ሲደርስ ብቻ ነው ሕማሙ የሚሰማው፣ ጩኸቱ የሚበዛው? ኧረ ይሉኝታ የሚባል ነገር አለ!

5ኛ/ ወያኔ ‹ሕገ መንግሥቴ› ብሎ ያፀደቀው የደደቢት መግለጫውን/ፕሮግራሙን ሥራ ላይ ከማዋሉ በፊት – በመገንጠል ዓላማ – የዘር ፍጅት በመፈጸም ከጎንደርና ከወሎ የወሰዳቸውን የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ሁመራ እና የራያ ግዛቶችን በሚመለከት የትግራይ ግዛቶች አይደሉም የሚል (ቀደም ብለው ምስክርነታቸውን ከሰጡት ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ዮሐንስ እና አንዳንድ የቀደሙ ባለሥልጣናት በስተቀር) የትግራይ ሰው ማግኘት ይቻላል? ዋናው መፍትሄ የወያኔን የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› እስከነ መዋቅሩ በማስወገድ በሳይንሳዊ ጥናት የታገዘ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመረጠው ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብቱን የሚያስጠብቅ የአስተዳደር መዋቅር ማዘጋጀት መሆኑ ቢታመንበትም ይህ እውን እስኪሆን ባለው ጊዜ ግዛቶቹን ማን ያስተዳድራቸው የሚለውን ጥያቄ በሚመለከት የዘር ፍጅት ፈጽሞ፣ ሆን ብሎ የሕዝብ ስብጥር ቀይሮ ነዋሪውን ያፈናቀለው የኢትዮጵያ ጠላት ሕወሓት በተከለው መዋቅር ይተዳደር ማለት በሕግ፣ በሞራል እንዲሁም በሕገ ልቦና ሚዛን ስናየው በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ በስርቆት የተገኘን ሀብት የራሴ ካልሆነ የሚል ማነው? የሌባው ግብረአበር ካልሆነ በስተቀር፡፡ 

6ኛ/ አንዳንድ ትግራውያን የወያኔ አመራሮችን አሳልፋችሁ መስጠት አለባችሁ፡፡ ሲባሉ ዐቢይ ማነውና ነው አሳልፈን የምንሰጠው? ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ዐቢይ የመለስ ደቀመዝሙር ነው፡፡ እሱና እመራዋለሁ የሚለው ድርጅት አመራርና በርካታ አባላት በወያኔ አገዛዝ ውስጥ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተሳታፊ መሆናቸውም የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ አሁን ያለውን ‹የፍትሕ ሥርዓት› ያደራጁት የወያኔ ወንጀለኞች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ የሚዳኙትም ባቋቋሙትና በመረጡት የዳኝነት ሥርዓት ነው፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ ወያኔ የኢትዮጵያ ጠላትና ግዙፍ የሆኑ ይቅርታ የሌላቸው ወንጀሎች የፈጸመ አሸባሪ ቡድን መሆኑን ታምናላችሁ/አታምኑም? የሚለው ይመስለኛል፡፡ ሕዝባዊ ሥርዓት መትከል ስንችል ወያኔ በእጁ ጠፍጥፎ በሠራቸው ሦስት ድርጅቶችና ‹አጋር› ባላቸው ድርጅቶች ውስጥ ያሉ አመራሮችና አባላት እንደ ተሳትፎአቸው መጠን በወንጀል የሚጠየቁበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ይሄ ወንጀለኛ ቡድን እኮ ለ27 ዓመታት ሥልጣን ላይ ባለበት ጊዜ (ከሌላውም ማኅበረሰብ በተለየ የኛ ነው ብላችሁ) እንደ መንግሥት ተቀብላችሁት አልነበረም? ወንጀለኞቹን የደርግ ባለሥልጣናትን የዳኘው እኮ አገርን በማስገንጠልና ወደብ አልባ በማድረግ በአገር ላይ ክህደት የፈጸመው የወያኔ አገዛዝ መሆኑን ትዘነጋላችሁ ልበል? በመለስም ሆነ በዐቢይ አገዛዝ ፍርድ የሚወጣው ከቤተመንግሥት አልነበርም/አይደለም እንዴ? የፍትሕ ሥርዓቱን የፖለቲካ ደንገጡር ያደረገው ወያኔ አይደለም እንዴ? ዐቢይ የመለስ ግርፍ መሆኑን መቼስ አጥታችሁት አይደለም፡፡ ከእኛ ጐሣ አልተገኘም ካላላችሁ በስተቀር፡፡ እውነቱን ለመናገር በወያኔ/ሕወሓት አገዛዝ እና የሱ ቅጥያ/ወራሽ በሆነው በዐቢይ አገዛዝ መካከል የተረኛ ጐሠኞች ለውጥ ካልሆነ በስተቀር መሠረታዊ ልዩነት አለ? መልሱን በሁለቱም አገዛዞች ቁም ስቅሉን ላየው እና አሁንም የአገዛዝ ቀንበር እጥፍ ድርብ ለጸናበት የኢትዮጵያ ሕዝብ እተወዋለሁ፡፡ እውን የዐቢይ ‹አባ ገዳዎች› እንርዳ ብለው የመጡት ነውረኛ የፖለቲካ ተልእኮ ይዘው (አማራውን ከትግሬው ብናናክሰው ለኦሮሙማ ፕሮጀክታችን ጠቃሚ ነው በሚል) እንጂ ለትግራይ ሕዝብ ከአማራው ቀርበውና አዝነው ይመስላችኋል? 

7ኛ/ መለስና ኩባንያው ከሻእቢያ ጋር በጥቅም ግጭት ምክንያት በቀሰቀሱት ትርጕም አልባ ጦርነት ከሰባ ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ማጣታቸው በወቅቱ ተዘግቧል፡፡ ይህ ወያኔና/ሻእቢያ ወለድ ጦርነት በተነሳ ጊዜ የደርግ ነው ተብሎ እንደ ዕቃ የተወረወረው የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይ ወገኔ ሲጠቃ ከማይ ሞቴን እመርጣለሁ ብሎ ደምና አጥንቱን መገበሩ ለትግራይ ሕዝብ የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው? መሬቱን እንጂ ሕዝቡን አንፈልገውም ነው? ተዉ እናስተውል!

8ኛ/ ብዙዎች በትግራይ ስለተፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተለይም በኤርትራ ወታደራዊ ኃይል ስለተፈጸመው ወረራ ‹ገለልተኛ አጣሪ› እያሉ ሲናገሩ ይሰማል፡፡ እውነቱ ነጥሮ ይወጣ ዘንድ እኔም እስማማለሁ፡፡ ‹ገለልተኛ› ግን ማነው? ከኢትዮጵያ ውጭ የሚመጣ ኃይል ነው? ፈረንጅ ስለሆነ ብቻ ገለልተኛ እንደሆነ ይሰማናል? ባገሮች ጣልቃ እየገቡ ዓለምን የሚያምሱት የአፍሪቃንና ሦስተኛው ዓለም ብለው ስም ያወጡላቸውን አገራት መንግሥታት የሚሰቅሉትና የሚያወርዱት ምዕራባውያን መንግሥታት፣ የስለላ ድርጅቶቻቸውና ቅጥረኞቻቸው አይደሉም? የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ዓለም አቀፍ የሚባሉት ድርጅቶች የነሱ ገንዘቦች አይደሉም ወይ? ይህንን አሁን ርእሰ ጉዳያችን ለሆነውና በትግራይ ተፈጽሟል ተብሎ ስለተነገረን ጥፋት ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አገር የውስጥ ጉዳዮች ተፈጻሚነት ያለው እውነት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ይሠራሉ የሚባሉት ተቋማትስ እውን ከተመዘገቡባቸው አገራት መንግሥታት ፍላጎትና ጥቅም ነፃ ናቸው? ትላልቆቹ ሜዲያዎችስ? ዓለም አቀፉ ካፒታሊዝም የሚዘውረውና ዓለምን ለመሰልቀጥ የሚሠራው የሉላዊው ግዙፍ ግዛት (global empire) አካል አይደሉም ወይ? በአገዛዙ ሥር ያለውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ስለ ኮሚሽኑ እና ኃላፊው በቅርቡ ለጋዜጠኛ መዓዛ ሞሐመድ የሰጠው ቃለ መጠይቅን በሚመለከት የራሴ ተዐቅቦ አለኝ) የአቅም ውሱንነቱን አጠናክሮ የማይካድራውን የዘር ጭፍጨፋ እንዳጣራው ሁሉ አሁንም በትግራይ ሕዝብ ላይ ደርሷል ስለተባለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተሟላ ሁናቴ እንዲያጣራ ማድረግ አንድ አማራጭ ሲሆን (በነገራችን ላይ ኮሚሽኑ ከኅዳር ወር እስከ ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ድረስ በሑመራ፣ በዳንሻ እና በቢሶበር ሲቪል ሰዎች ላይ ስለደረሰ ጉዳት እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ማጣራት አድርጎ አጭር ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል፤ ከጥር 2/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በመቀሌ እና በሌሎች የትግራይ ክ/ሀገር አካባቢዎች የማጣራት ምርመራ ሥራውን እንደቀጠለና ሲጠናቀቅም የተሟላ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ባጭር ሪፖርቱ ተመልክቷል)፣ ተአማኒነት አይኖረውም ከተባለ ደግሞ መንግሥት ጣልቃ የማይገባበት ከሁሉም የኅብረተሰባችን ክፍል የተወጣጡ ኢትዮጵያውያን ስብስብ እንዲያጣሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህንን እንደ መፍትሄ ያቀረብኩበት ዋና ምክንያት የወያኔ እጅ ረጅም መሆኑን ስለተገነዘብኹ ነው፡፡ ወያኔ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ኃይሉን ተጠቅሞና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት ጭምር ከምዕራባውያን መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ከተባሉ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር – በኢትዮጵያ ስም ሕወሓት ቊልፍ በሚባሉ አገሮች በሚመድባቸው የራሱ ታማኝ አባላት (‹አምባሳደሮች›) እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፈው ሀብት አማካይነት – ተወዳጅቶበታል፡፡ ዛሬ እነዚህ ኃይሎች ከወያኔ ‹የተበደሩትን› የሚከፍሉበት ጊዜ ስላለመሆኑ ማን በርግጠኝነት መናገር ይችላል? ጦርነቱን ሕወሓት በጀመረ ማግስት አይደለም እንዴ ለወያኔ ወግነው መጮኽ የጀመሩት? ቀንደኞቹ ወያኔዎች እነ ቴዎድሮስ አድኃኖም እና ‹አምባሳደር› ብርሃነ ሥራቸው ይኸው አይደል? ወያኔ ጦርነቱ ዓለም አቀፍ አድማስ እንዲኖረው የሞከረው አልፎ ተርፎም የውጭ ኃይል አስገባለሁ እስከማለት የፎከረው ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ከውጭ ታሳድራለች እንደተባለው ምዕራባውያን አጋሮቹን ተማምኖ አይደለም?

9ኛ/ በወያኔም ዘመን ሆነ አሁን የቀረው ኢትዮጵያዊ የትግራይ ጉዳይ ሲነሳ በእግር ጥፍሩ እንዲቆም የሚፈለገው ለምንድን ነው? ከትግራዮች ፊት ለመናገርና ለመከራከር የምንሰቀቀው ለምንድን ነው? ወያኔ ሥልጣን ላይ ለመቈየት የኢትዮጵያን አገራዊ ህልውና መያዣ እንዳደረገ ሁሉ÷አሁንም አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች የምትፈልጉት እኛን ሳይሆን መሬቱን፣ታሪክና ቅርሱን ብቻ ስለሆነ አብረን አንኖርም የሚል ዛቻ/ማስፈራሪያ ሲያሰሙ ይደመጣል፡፡ ትግራይ የኢትዮጵያ ታሪክ መሠረት ናት ብሎ መናገር በትእቢት ያሳብጥ ይሆን እንዴ? ሀገረ መንግሥቱን እኮ ሁሉ ተባብሮ የመሠረተው ነው፡፡ በገራ የተደረገውን የነፃነት ተጋድሎ ማስታወስ መልካም ነው፡፡ መቼ ነው ከድንፋታ ወጥተን፣ በእኩልነት ተያይተን በጨውነትና በሥርዓት መነጋገር የምንችለው? ይህን የመከራ ዘመን ለምን ተጋግዘን ለማሳለፍ አንጥርም? ለምን ዓመል እንደሌለው ልጅ እንሞላቀቃለን! ይልቁንስ ከአካባቢያው ስሜታዊነት ወጥተን ካስተዋልን ባንድ ሕዝብነት የሚያስተሳስሩን፣ የሚያግባቡን እጅግ ብዙ የጋራ ጉዳዮች አሉን፡፡ ሁላችን ነፃ እና እኩል ሆነን በጋራ ለመልማት በቅድሚያ ወያኔ ከተከለው እና ወራሹና ተረኛው ጐሠኛ የዐቢይ አገዛዝ ካስቀጠለው የጐሣ ፖለቲካ፣ የጐሣና ቋንቋ ፌዴራሊዝም፣ ይህንንም የጐሣ ሥርዓት ሕጋዊ መሠረት የሰጠውን አገር አፍራሽ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› እና ሕዝብን ርስ በርስ ከሚለያይና ከሚያጋጭ ሥርዓት ተላቅቀን ሁላችን እንደ አንድ አገር ዜጋ በእኩልነት የምንኖርበትን አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት በጋራ እንድንታገል ጥሪዬን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አቀርባለሁ፡፡ ወያኔን አነውሮ ሲያበቁ እሱ የተከለውን የጐሣ ሥርዓት ተቀብሎ መኖር ተረኛ ወያኔነት እንጂ ሌላ ስያሜ የለውም፡፡ ለምን ባርነትንና ጐሠኝነትን አንጠየፍም? በመንደርተኝነት መንፈስ የሚያቈስሉ መርዘኛ ቃላት ከመለዋወጥና ለርስ በርስ ፍልሚያ ከመዘጋጀት እውነተኛ ጠላታችን ላይ ለምን አናተኩርም? ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ጠባሳ ማስቀመጡ ይብቃን፡፡ የሠላሳ ዓመቱ አይበቃንም? በጦርነቱም ባገዛዙ የኦሮሙማ ፕሮጀክት ምክንያትም መከራ የደረሰባቸው ወገኖቻችንን መልሶ በማቋቋም ያለፈውን የጐሠኛነትና የመለያየት ምዕራፍ የምንዘጋበት የሽሽግግር ጊዜ – አገራዊ ጉባኤ፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ተደማምጠን ውይይት የምናደርግበት፣ ለብሔራዊ ሕማማችን ፈውስ የምንፈልግበት፣ በሚያግባቡን የጋራ ጉዳዮች ላይ ተስማምተን ለወደፊቱ አብሮነት ከጐሣ መንደር ወጥተን የጋራና የእኩልነት አገር ስለምንገነባበት ሁናቴ ወዘተ. መነጋገር – አስፈላጊ አይመስላችሁም? በእኔ ትሁት አስተያየት የተሻለው አማራጭ ይሄ ይመስለኛል፡፡ 

ባጭሩ አነጋገር ለብሶት ከሆነ (አገዛዞችና በጥቅም ተጋሪአቸው ካልሆኑ በቀር) ያልባሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ  አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡  ልዩነቱ የመጠን ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ረገድ የአማራው ሕዝብ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ አልጠራጠርም፡፡ ያም ሆኖ በመገፋት ብዛት፣ በዘር ፍጅቱ፣ በመፈናቀሉ፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ከኔ ጋር አልቆሙም በሚል ወዘተ. ምክንያት ኢትዮጵያዊነት ላይ ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጥ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው በትግራይም ይሁን በሌላ የኢትዮጵያ ግዛት በወገኖቻችን ላይ የሚፈጸምን ግፍ ሊያቃልል አይችልም፡፡ የኢትዮጵያዊነት መለኪያ ትናንት የተነሱና ውስጣቸው በጐሠኛነት ካባ የተለበጡ የፖለቲካ ማኅበራት ወይም ቡድኖች ወይም ግለሰቦች አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡ ብርሃን ከጨለማ ጋር እንደማይተባበር ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊነት ከጐሠኛነት ጋር ኅብረት የለውም፡፡ ከጐሠኛነት ጋር በንጽጽር የሚቀርብ ሃሳብም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ልዕለ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን መሬት የረገጠ እውነታ ነው፡፡ ደብዝዞ ሊሆን ይችላል፡፡ ነውረኛ ‹ትውልድ› አቧራ አልብሶት ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እንደ አዲስ የምንፈጥረው ማንነት አይደለም፡፡ ስለሆነም ልምድ ሆኖብን እንደምንናገረው በጎራ አንክፈለው፡፡ ጎራ ካለ ጊዜ አመጣሹ ጐሠኛነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብሉየ መዋዕል (ዘመን የጠገበ) ሲሆን፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ 

በትግራይ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ በኮንሶና በሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ባስቸኳይ ይቁሙ!!! በሁሉም አካባቢ አደጋ የደረሰባቸው ወገኖቻችንን ፈጥነን እንርዳ!!! 

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!! 

ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡

ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡

(የምርጫ ቦርድ የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነትን መሠረዙ አንድ የሚያበረታታ ጉዳይ ሆኖ፣ በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባዋል፤ ትጥቅ ይዞ አገርንና ሕዝብን እያሸበረ ያለው ኦነግም ላይ ባስቸኳይ ሕጋዊ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡)

Filed in: Amharic