>
5:18 pm - Thursday June 15, 6519

ህጋዊ መፍትሔ አሁኑኑ! (አሰፋ ሀይሉ)

ህጋዊ መፍትሔ አሁኑኑ!

አሰፋ ሀይሉ

 

“ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በእርጥቡ” — የኢትዮጵያውያን ምሣሌ!
ማንም ሀገሩን የሚያውቅ – እና ጤነኛ አዕምሮ ያለው – ዜጋ ከተከዜ ወዲህ ያለው የወልቃይት-ፀገዴ-ሑመራ-ፀለምት አካባቢ በጎንደር ሥር ሲተዳደር የኖረ፣ እና በወያኔ ናዚ ሽማግሌዎች እብሪት በጉልበት፣ ያለህግ፣ ያለጠያቂ በጠራራ ፀሐይ ተነጥቆ ‹‹ምዕራባዊ ትግራይ›› የሚል የዳቦ ስም የወጣለት፣ እና ለትግራይ ሠፋሪዎች የተከፋፈለ አካባቢ መሆኑ አይጠፋውም! ይህ በቅርቡ (የዛሬ 15ና 20 ዓመት) የተከናወነ ፀሐይ-የሞቀው (ያደባባይ) ንጥቂያ ስለሆነ ለጥያቄ የሚቀርብም፣ የሚያጨቃጭቅም፣ የሚያነጋግርም ጉዳይ አይደለም!
ጥያቄው አካባቢዎቹ በጎንደር ሥር የሚተዳደሩ መሆናቸው ወይም አለመሆናቸው አይደለም አሁን፡፡ ጥያቄው አሁን ሥልጣን ላይ ባለው የአብይ አህመድ አስተዳደር ውዝምዝም አቋም አንፃር – ይህ በወያኔ ናዚ ሽማግሌዎች በአደባባይ የተዘረፈ አካባቢ በህጋዊ መንገድ ወደነበረበት የጎንደር አስተዳደር ህጋዊ ርክክብ ተፈጽሞለት እንዲመለስ ይደረጋል ወይስ አይደረግም? የሚለው ነው፡፡
ለመሆኑ መቼ ነው ይህ ህጋዊ አስተዳደራዊ ርክክብ የሚደረገው? የአብይ አህመድ ፓርላማ በዚህ ጉዳይ ተሰብስቦ ይወስንበታል? መቼ? የፌዴሬሽን ምክርቤት ተብዬውስ ይህን ግልጽ ጉዳይ ያለአንዳች ውዝብዝብ ወደገደለው ገብቶ አስተዳደራዊ ርክክቡ በአስቸኳይ እንዲፈጸም ይወስናል? ወይስ አይወስንም?
የአብይ አህመድ ኦህዴድ መራሹ ካቢኔስ ከሻዕቢያና ከአማራው ኃይል ጋር ተባብሮ የሥልጣንና ወታደራዊ ተቀናቃኝ ሆነው የጎን ውጋት የሆኑትን የወያኔ ሽማግሌዎች ቀብር ለማፋጠን የሮጠውን ያህል፣ ይሄን የተቀበሩት የወያኔ ሽማግሌዎች የነጠቁትን የጎንደር አካባቢ የአስተዳደር ወሰንስ ለአማራው (‹‹ለሰሜን ጎንደሩ››) አስተዳደር በፍጥነት የሚመልሰው መቼ ነው? ይሄ በእውኑ ይደረጋልስ ወይ? መቼ?
አሁን ጥያቄው ይህን ሁሉ ነገር ያለ ጦርነትና የአማራውም የሌላውም ኢትዮጵያዊ ደም ሳይፈስ መከወን አይቻልም ነበር ወይ? በግልጽና በቀጥታ ቋንቋ ለእውነቱ የቆመ መንግሥታዊ አቋም ይዞ ይህን ጉዳይ ቀድሞውኑስ ቢያንስ በህግና በፖለቲካዊ መንገድ ገፍቶ ዳር ማድረስና ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተደራድሮ ያለአንዳች ማንገራገር በሠላም መፍታት ይቻል አልረነበረም ወይ? የሚለውን ጥያቄ አሁን አናነሳም፡፡ ይሄ ጊዜው አይደለም አሁን፡፡ ይሄ ጥያቄና አማራጭማ በተለመደው ኢህአዴጋዊ የበለው-ምታው መንገድ መልስ ያገኘ ስለሆነ፣ ለታሪክ አጥኚዎችና ተመራማሪዎች ብንተወው ይሻላል፡፡ አሁን ስላለፈ ዕድልና አማራጭ አንስቶ ለመነጋገርም ለመወቃቀስም ጊዜው አልፎበታል! ስለመከነው ዕድል መቆጨት ዋጋ የለውም! አሁን በእጅ ላይ ስላለው ስላልመከነው ዕድልና አማራጭ የምንጠይቅበት ጊዜ ነው!
ለምሣሌ በወያኔ ሽማግሌዎች በተነጠቁት የጎንደር አካባቢዎች ላይ ወያኔ በእቅድ ፕሮግራም ይዞ በተከታታይ ባካሄዳቸው ህገወጥ ሰፈራዎች በሀገሩ ላይ የሚኖሩት በብዛት ከትግራይ የተጋዙ ዜጎች፣ ቤተሰቦችና ባለሀብቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አሁን ጥያቄው የእነዚህ ዜጎች አኗኗር፣ የሀገር ሀብት ድልድል፣ አያያዝና አጠቃቀምን በተመለከተ – የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ባከበረና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን አካሎች ባሳተፈ መልኩ – ሠላማዊና ዘላቂ የሆነ ህጋዊ አሠራርና አስተዳደራዊ ሽግግር መዘርጋት የሚቻለው በእንዴት ያለ መልኩ ነው? ይህን በህጋዊ መንገድና በግልጽ መከወን ይቻላል? ወይስ አይቻልም? ነው ጥያቄው!
በአሁኑ ሰዓት ዓይኖቹን በጨው አጥቦ ወልቃይት-ፀገዴ-ሑመራ-ፀለምት የትግራይ ክልል ነው የሚል ጊዜው-ያለፈበትና የተበላበት የድርቅና አታሞ በአደባባይ ለመጎሰም የሚደፍር ዘላባጅ ካለ – በእውነቱ እንዲያ ዓይነቱ ሰው ከናዚዎቹ የወያኔ ሽማግሎች ተለይቶ የማይታይ የፀረ-እውነት፣ የፀረ-ፍትህ፣ የፀረ-ሥርዓትና የፀረ-ሠላም አቀንቃኝ ብቻ ነው! ስናውቅ – ወደ ትፋቱ የሚመለስ ውሻ ብቻ ነው፡፡ የሚያስብ አዕምሮ ያለው የሰው ልጅ፣ ይሉኝታንና ሰው-ምን-ይለኝን ዋጥ አድርጎ ዓይኑን ድርቅ አድርጎ ዳግመኛ ወደ አሳፋሪ ጥፋቱ አይመለስም፡፡ እንዲያ ዓይነቱ ሰው ካለ – በትክክልም የቀማኞች አጋፋሪ ብቻ ነው! አሊያ ደግሞ ወፉ-ዛፉ ሁሉ የወያኔን ሙሾ በሚያፏጭበት ምድረ በዳ መድረክ ላይ- ወያኔን ተመስሎ ለመተወን የሚፍጨረጨር – አማተር የፖለቲካ ተዋናይ ብቻ ነው!
እስከዛሬ በሠላም አልኖርንም፡፡ ተነጥቀን፣ ተቀጥቅጠን፣ ተዘርፈን፣ ተንቀጥቅጠን ነው የኖርነው፡፡ ሠላም የራቀን ግዞተኛ ሕዝቦች ነን፡፡ አሁንም ግዞታችን አላበቃም፡፡ ሠላም የሚመጣው ንጥቂያን በማበረታታትና መጪ የህዝቦች ግጭት የሚከሰትበትን ሰበብ በመጠንሰስና፣ የቁርሾ ፈንጂ በመቅበር አይደለም! ሠላም የሚመጣው ጠብመንጃ ተኩሶ የተኮሰን በመግደል ብቻ አይደለም! ሠላም የሚመጣው ነጣቂን በንጥቂያውን እንዲቀጥል የፖለቲካ ቡራኬ በመስጠት አይደለም! የዓለም ታሪክ፣ የራሳችን ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ አሳይቶናል፡፡ ፍትህ ያልጎበኘው ሠላም አይዘልቅም! ለነገ አይተርፍም!
ቀንደኛ የፖለቲካም ሆነ ወታደራዊ ተቀናቃኝ ሆነው የታሰቡትን ጊዜ ያለፈባቸውን የወያኔ ናዚ ሽማግሌዎች (ከነምዕመኖቻቸው) በባሩድ ኃይል ገፍቶ የጣለው የወቅቱ የአብይ አህመድ አስተዳደር፣ የሽማግሌዎቹን ዓይን-ያወጣ እርኩሰትና ቅሚያ ግን እንዳለ መተዉ – ለነገ ጦርነትና ግጭት እፍ ብሎ እሳት አጋግሎ፣ ረመጡን ቀጣጥሎ እንደመሄድ ይቆጠርበታል! መቆጠር ብቻ ሳይሆን ነውም! አንድም ለታለመ የፖለቲካ ትርፍ የወደፊት ግጭት መጠንሰስ፣ አሊያ ደግሞ የተለመደው እስስትነት ያልተለየው የፖለቲካ አቋም መዋዠቅ ብቻ ነው!
ይህ እውነተኛ የሰላም መንገድ አይደለም! ይህ የከሸፈበት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች፣ የአረመኔዎቹ የወያኔ ሽማግሌዎች፣ እና የመሰሎቻቸው የእባብ መንገድ ነው፡፡ ይህ የክፋትና የሤራ፣ አንዱን ካንዱ የማጋጨትና የማላኮስ፣ አንዱ ካንዱ ጋር የሚቆራቆዝበትንና የሚናከስበትን ነገር እያስቀመጡ የመሄድ፣ እና እርስበርስ የማባላት መንገድ – ከእንግዲህ እንደማያዋጣ፣ ከእንግዲህ በሀገራችን ቦታ እንደማይኖረው – አክ እንትፍ ተብለው ተተፍተው ብቻቸውን የቀሩትን፣ በቁማቸው የተንጋፈፉትንና የተቀበሩትን የወያኔ ናዚ ሽማግሌዎች አይቶ ትምህርት የማይወስድ ካለ – ከትልቅ ይቅርታ ጋር – እርሱ ደንቁሮ የቀረ ብቻ ነው በእውነቱ!
ስለ አሁኑ ደፍረን ካልተነጋገርን፣ የነገ ግጭትን የሚያስቀሩ መፍትሄዎችንና ዕድሎችን ሳንጠቀምባቸው አለባብሰን እናልፋለን፡፡ አሁን በወያኔ ናዚ ሽማግሌዎች ከጎንደር አስተዳደር በተነጠቁት የወልቃይት-ፀገዴ-ሑመራ-ፀለምት አካባቢዎች ላይ በወያኔ በሸፍጥ የተከናወኑ ቁጥራቸው የበዛ የሠፈራ ፕሮጀክቶች አማካይነት ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች መጥተው እንዲሠፍሩ የተደረጉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ወያኔን እንደ ግል አዳኛቸው ተቀብለው የተሻረኩ – እና አጠቃላዩን የወልቃይት-ፀገዴ-ሑመራ-ፀለምት የሰሊጥና የጥጥ ማሳዎች ከተራው ህዝብ ጉሮሮ ነጥቀው የሠፈሩበት – መሬቱን እንደ ቅርጫ ሥጋ እርስበርስ ተከፋፍለው ለዓመታት ሲግጡት የኖሩት የወያኔ ታማኝ ጭፍሮችና የጥቅም ቱሩፋት ተቋዳሾችም አሉ በአካባቢው ላይ፡፡
እና አሁን ዛሬ ላይ በግልጽ ማንሳትና ምላሽ መስጠት ያለብን ጥያቄ የእነዚህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሥርዓቱ በሀብት ፀጋ ቀብቶ በንጥቂያው ማዕድ ላይ ያሰማራቸው የወያኔ ባለሀብቶች ወቅታዊና የወደፊት ዕጣ ፈንታስ ምንድነው የሚሆነው? የሚለውን ነው፡፡ እነዚህ ባሉበት የአካባቢውን ቱሩፋት እየጋጡ ይቀጥላሉ? ወይስ የሀብትና የዕድል ክፍፍሉ ክለሳና እርምት ይወሰድበታል? የእነዚህን አካባቢዎች ተፈጥሯዊና ሰው-ሠራሽ ሀብቶች እንዴት አድርጎ ነው ዳግም መሥራት ለሚችሉና ለሚገባቸው የሀገሪቱ ዜጎች ዝግጁ አድርጎና አደራጅቶ – ሁሉም የጋራ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ፍትሃዊ የልማት አጀንዳ ነድፎ በሥራ ላይ ማዋል የሚቻለው?
የአብይ አህመድ አስተዳደር – እንደ ብዙዎቹ የሀገሪቱ መሠረታዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥያቄዎች ሁሉ – ለዚህም አንገብጋቢና ወሳኝ የወቅቱ ጥያቄ – ቁርጥ ያለ መልስ የሚመልስ ተክለሰብዕና ያለው አስተዳደር ነው ለመሆኑ? ወይስ… ረጋ-ሠራሽ፣ አንዴ በግራ አንዴ በቀኝ የሚዋልል፣ በቀደመው ኢህአዴጋዊ ክፉ ውርስ አንዱን ካንዱ እያጋጨ፣ ተቀናቃኙን እየዋጠ እየሰለቀጠ፣ ሆዱን አሳብጦ፣ ክንዱን አደንድኖ በሥልጣን ሃዲዱ ላይ ለመጓዝ የተመኘና የሚንገታገት የአምታታው-በከተማ፣ የአምታታው-በገጠር በልቶ-ሟቾች ስብስብ ነው?
በበኩሌ – ወደድንም ጠላን – እስካሁን ሀገሪቱ እንደተውሸለሸለች ከወያኔ ወለዱ የጎጥና የዘር ፖለቲካ ፈቀቅ ሳትል ባለችበት እያዘገመች ያለችው – በዚሁ አቋም-የለሽ፣ ራዕይ-የለሽ፣ እዚህም እዚያም ረጋጭ፣ እና ካለፈው ሥርዓት ክፉ ውርሶች ራሱን ያላላቀቀ ለወስዋሳ የሥልጣን ኃይል ምክንያት ነው፡፡ መረረንም፣ ጣፈጠንም – እውነቱ ይኸውና ይኸው ነው፡፡
በግልጽ የሚታይ እውነታም ቢሆን በዚህን ያህል ደረጃ አስረግጦ መናገር ትልቅ ድፍረት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ግን የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ እውነቱ ገዝፎ ተራራ አክሎ እየታየ ነውና ድምዳሜ ቢሰጥበት አይገርምም፡፡ ችግሩ አፍጥጦ የሚታየው የዛሬው የችግር ተራራ አይደለም፡፡ ዋናው ችግር ዛሬ በወቅቱ መፍትሄ ካልተሰጠው – ነገ ማለቂያ የሌለውን የዜጋ ደም የሚያፈሰው የችግሩ አለንጋ ነው፡፡ ነገ ድጋሚ ሌላ ጦርነት፣ ሌላ ሰዶ ማሳደድ፣ ሌላ ዶሮን በቆቅ መለወጥ፣ ሌላም ሌላም ሀገራዊ ጦስ እንዳይመጣብን ነው ካሁኑ – ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ – በዚህ ደረጃ አስረግጦ መናገር አስፈላጊ የሆነው!
ብዙ ሥልጣን አምላኪዎች በበዙበት፣ ብዙ የሥልጣን አወዳሾችና ካዳሚዎች ሚዲያውን ሁሉ ተቆጣጥረው በሚፈነጩበት፣ ብዙ ተተኪ የወንበር ወራሾችና ተስፈኞች የሀገሪቱን ርዕሰ መንበር ዙሪያ ከበው ጧት ማታ በሚያሸበሽቡበትና ታማኝነታቸውን በሚያረጋግጡበት በዚህ የወቅቱ ሀገራዊ የፖለቲካ ገበታና የፖለቲካ ድግስ መሐል – ይህን መሰሉ ፈጥኖ መመለስ ያለበት ወቅታዊ ጥያቄ፣ ወቅታዊ ማነቆ ሲነሳባቸው – ዛር እንደያዘው ባለውቃቢ የሚያንዘረዝራቸው ብዙ ናቸው፡፡
እውነት የምታንገፈግፋቸውና የምታስቆጣቸው – እንደ ተራራ ፊታቸው የቆመውን ጥያቄና እውነት የሚሸሹ – ምክርንና ትችትን የሚቀበል ልቦና ያልፈጠረባቸው – ለጥቅም፣ ለሥልጣን፣ ለአነብናቢነትና ለአለቅላቂነት ራሳቸውን ያስገዙ – እና ችግርንና መፍትሄን ቀድመው ለማየት የማይሹም – የማይታያቸውምም – ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን የአቸፍቻፊ መዓት የወያኔን ሽማግሌዎች እና ሀገርን ወደምን አዘቅት እንደከተታቸው ያየ፣ በዚያው የማቸፍቸፍ መንገድ የሚገኝ የተለየ መጨረሻ እንደሌላቸው ማወቅ አለባቸው፡፡
ዛሬ ላይ ይህ የአብይ አህመድ አስተዳደር እንደ ቀደሙት የከሰሩ የወያኔ ሽማግሌዎች – ለፖለቲካ ቁማር አውለዋለሁ በሚል መንታ ልብ የወለደው እሳቤ የተነሳ – ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት አቅቶት እየተውሸለሸለ ያቆየው ይህ የወልቃይት-ፀገዴ-ሑመራ-ፀለምት ጥያቄ – ለራሱም ሲል – ከምንም ጉዳይ በፊት ትኩረት ተሰጥቶት – ግልጽና ቀላል ወቅታዊ ምላሽ ሊቸረው የሚገባ መሆኑን መረዳት የግድ ይላል፡፡
ውሎ ሲያድር ጦሱና መዘዙ፣ የሚያስነሳው እሳት – የቤተመንግሥቱ የቅርብና የሩቅ አጋፋሪዎች ከሚያልሙት በተቃራኒው – ዳሩን ብቻ ይዞ የሚነድ አይሆንም፡፡ መሐሉንም ጭምር ይዞ የሚጠፋ እጅግ አደገኛ የእሳት ጅረት እንደሚሆን ሁሉም መረዳት ያለበት፣ እና አሁንም ቢዘገይም ገና ያልረፈደበት ለመፍትሄ ክፍት የሆነ ወቅት ላይ መገኘታችንን ማስተዋል ያሻል፡፡ ይህ ጉዳይ አሳሳቢና ፈጣን ምላሽ የሚያሻው መሆኑን ዛሬ ያልተረዳ – እንደ ሁሌው ሁሉ – ነገ ከነገወዲያ ችግሩ ሥር ሰድዶ ባሩድ ሲጨስና ደም ሲረጭ ብቻ የሚታየው ይሆናል! ከዚያ የሚያተርፍ አይኖርም!
እንደ ቀደመው – እንደረፈደባቸው የወያኔ ናዚ ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ – አሁንም ከቀድሞዎቹ በተረፈው የጠብመንጃና የህግ ጉልበት የእነርሱን ከመሰለ መጪው ቀብር ለመትረፍ የሚንደፋደፈው የወያኔው ተራፊ ሥርዓትም ሆነ ተራፊ ሥልጣናቱ – ችግሮችን ወደፊት ተመልክተው ሳይደርሱና ሳይሆኑ መፍትሄያቸውን ከማበጀት ይልቅ – ደግመው ደጋግመው ለምን በስፖኪዮ (በኋላ መስታወት) እያዩ መጓዝን እንደሚመርጡ ሁላችንንም የማይገባ ነገር አለ! ምናልባት ይህም አንዱ ልንላቀቀው ያልቻልነው የተወራረሰ አጉል ልክፍታችን ሳይሆን አይቀርም!
ለምሳሌ ዛሬ ላይ መተከል ሰው ይጨፈጨፋል፡፡ ሲሆን ሲሆን – ሰው ጭፍጨፋ ላይ ሳይገባ የወደፊቱን ተመልክተህ ማስቀረት መቻል አለብህ፡፡ ካልሆነም አንድ ጭፍጨፋ ሲደረግ ያን አስቁመህ፣ ዳግመኛ እንዳይደገም ሄደህ ትሠራለህ፡፡ የኛ እኮ ነገር ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም ጭፍጨፋው ይቀጥላል፡፡ ወሬው፣ ዜናው፣ የወሬ ዘመቻው ይቀጥላል፡፡ ገፈቱ ግን አይቆምም፡፡ መቼ ይሆን በስፖኪዮ ከመንዳትና ከመነዳት የምንላቀቀው? – አላውቅም፡፡ ብቻ የፊቱን እያዩ መሄድ – ከተጋጩ በኋላ፣ ጉዳት ከደረሰብን በኋላ፣ ከዘገየ ከማየት ያስጥላልና – አሁን ጊዜውና ዕድሉ እያለን ወደፊት እያየን ብንጓዝ ብዙ አላስፈላጊ ግጭቶችን ማስቀረት እንችላለን፡፡
ምንም እንኳ በበቀቀንነት ባላምንም – አሁን ግን ወቅታዊ ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሾችን ይሻሉ እያልኩ ስንብቴን ሳሰላስል – አንድ ሰሞኑን እየተበቀቀነ ያለ ቃል ድንገት በጣቶቼ ጫፍ መጥቶ ተሰነቀረብኝ! አዎ፡፡ በትክክልም፡፡ ‹‹ጊዜው አሁን ነው››!
/በጽሑፉ ውስጥ ስለሚገኙ ማናቸውም ጠጣር መልዕክቶችና ኃይለ-ቃሎች በአንባቢው ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ!/
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ችግር ሰጥቶ፣ መፍትሔውን አይንሳን የኢትዮጵያ አምላክ!
መልካም ጊዜ! 
Filed in: Amharic