>

ቅጥቅጥ!  በላባ ትራስ...!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ቅጥቅጥ!  በላባ ትራስ…!!!

(በእውቀቱ ስዩም)

ብልፅግና ፓርቲን ለመደገፍ በተካሄደው ሰልፍ ላይ ወዳጄ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሲወገዝ አይቼ ገረመኝ !  “ብልጥግናን  እንደግፋለን ዳንኤል  ክብረትን እናወግዛለን” ማለትኮ “ ለኢትዮጵያ  ብሄራዊ ቡድን እንሞታለን  በረኛውን ግን እንገድለዋለን “ እንደማለት ነው ፤   ዳኒ  አንደበቱ የማይደነቃቀፍ ተናጋሪ ብእሩም የማይደክም ፀሀፊ ነው፤  በተሰጥኦው  ወፍራም እንጀራም ሆነ ሜዳልያ ማግኘት የሚያቀተው ሰው አይደለም ፤   እንግዲህ  እሳቱ በማያንቀላፋው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የተጣደ አገር እጠቅም ብሎ መሆን አለበት   !
 አንባቢ ሆይ! ይሄን አንብበህ ምን ያኮማትርሃል?   እያንዳንድህ በዚች አገር ልማትም ሆነ ጥፋት  ላይ እጅህም እግርህም አለበት !
ዳንኤልን የማውቀው  ገና በካምፓስ ፍሬሽ ሳለሁ ነው  ፤  ያኔ የሱን ስብከት ለመታደም እማይጋፋ አልነበረም  ፤ በነገራችን እያዝናኑ  መስበክን ወደ ኢትዮጵያ ያስገባው  ዳንኤል ይመስለኛል ፤ ፓስተር ዳዊትሳ  ትይኝ ይሆናል ? እሱ ከስብከቱ በላይ የህይወት ውጣ ውረዱ ያዝናናኛል  ፤ በነገራችን ታች ፥ ፓስተር ዳዊት ድሮ   ምስኪን ቦክሰኛ ነበር ፤  የሰውነቱ ቅጥነት  ብታዩት  እንኩዋን ለቦክስ ለቼዝ ግጥሚያ እንኩዋ እሚመች  አልነበረም ፤ ክንዱ እጅግ የመነመነ  ከመሆኑ የተነሳ ሴኮ ሰአቱን እሚያስረው  አንገቱ ላይ ነበር !  ለሰይፉ ሲነግረው እንደሰማሁት  ለመጀመርያም ለመጨረሻም በተሳተፈበት ግጥሚያ ላይ”   በዝረራ ነው የተሸነፈው”  !  ተጋጣሚው እንዴት ጨክኖ  ቡጢ ሰነዘረበት  ? ! የጉዋንቱ ክብደት ራሱ ስቦ  በግንባሩ ይደፋዋል!
ወደ ዳኒ እንመለስ!  እና በሚሰብክበት ጊዜ  በየደቂቃው ምእመኑ በሳቅ ይደክማል፤አንድ ቀን እንዲህ አለ፤
“ መንግስተ ሰማያት ኬኔዲ ላይበራሪ አይደለም! የፀደቀ ጉዋደኛህን ወንበር ይዘህ ጠብቀኝ ልትለው አትችልም! “
ዳንኤል ክብረት ስለ ፍትህ ርትእ  እንደምትሰራ ተስፋ አለኝ  ! ከዚያ ወለም ዘለም ካልህ አለቅህም!  በጨዋ ደንብ አርምሀለሁ!  በላባ በተሞላ ትራስ እቀጠቅጥሀለሁ !  በነገራችን ላይ በጨዋ ደንብ መተቸት ሲባል አያቴ ናት ትዝ እምትለኝ፤
 ልጅ እያለሁ ከለታት ባንዱ ቀን  ካያቴ እማሆይ ዘውዴ ጋር ገበያ ሄድን፤አንዱ ባላገር ቁጭ ብሎ የሆነ ነገር ይሸጣል፤ በሰፊ ቁምጣ   ውስጥ ቆ..ጦቹ   የተነፈሰ የላስቲክ ኩዋስ መስለው ይታያሉ፤ እና አያቴ እንዲህ አለችው፤
“ አንቱ ሰውየ!  እስቲ ብድግ ብለው ይቀመጡ”
ያው አቀማመጡን ሲያስተካክል ነገርየው ይሸፈናል ብላ ነው፤
Filed in: Amharic