ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ካልቻልን አለን ማለት እንችላለን?
ከይኄይስ እውነቱ
ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ተቃውሞ ማድረግ ማንም ከማይሰጠንና ከማይቀማን ተፈጥሯዊ የሰው ልጆች መብቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ መብት የመንግሥትን ቡራኬ የማይሻ፣ ጣልቃም ገብቶ የማይከለክለው መብት መሆኑ እየታወቀ፣ በ‹ሪፓብሊክ› ስም የንግሥና ዙፋን ላይ የተቀመጡና ዘውድ የጫኑ የእኛዎቹ ጨካኝ አምባገነኖች ለራሳቸው መወደሻና ድጋፍ መፈክር ጽፈው ሰጥተው፣ ሎሌዎቻቸውን አሰማርተው ሕዝብን አስገድደው በትእዛዝ ሲያስወጡ፤ ሕዝብ በገዛ ፈቃዱ ብሶቴን ምሬቴን በሰላማዊ ተቃውሞ ለመግለጽ እወጣለሁ ሲል ብረታቸውንና የሕዝብ ያልሆነ ዘረኛ ኃይላቸውን ተመክተው ደጋግመው ሲከለክሉ ተስተውሏል፡፡ ተረኛ የኦሮሞ ጐሠኞች አይነካብን የሚሉት የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› እንኳን ይህንን መብት ለይስሙላ አካትቷል፡፡ ታዲያ የሕዝቡን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ለምን ፈሩት? ከሕዝብ የተጣሉበትን ክፉ ሥራቸውን በሚገባ ያውቁታል፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ፡፡ እውነቱን ለመናገር (አገዛዙ በጥቅም የገዛቸው ካልሆኑ በቀር) ነፃ ቢሆን ኢትዮጵያዊው የኦሮሞ ሕዝብ በተረኞቹ ላይ በተቃውሞ እንደሚወጣ አልጠራጠርም፡፡
እንደ ባልደራስ ያለ እውነተኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበር አገዛዙ ከሕግ በላይ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን እንደሚከለክል እያወቀ ለምን ለሕዝብ ጥሪ ያደርጋል? ለታሪክ ለማስመዝገብና አገዛዙን ለማጋለጥ? ለዚህ ዓላማ አንድ ተሞክሮ በቂ ይመስለኛል፡፡ በሕግ የበላይነት የሚያምን ቢሆንማ ከመነሻውም እነ እስክንድር ባልታሠሩ ነበር፡፡
የኢትዮጵያም ሆነ ወካይ ማሳያው የሆነው የአዲስ አበባ ሕዝብ የአገዛዙን ጠባይ በሚገባ ያውቀዋል፡፡ አሁን ያለንበት ምርጫ እኮ ሰው ሆኖ በነፃነት መኖር/መሞት ወይም ከሰው በታች ተዋርዶ ባርነትን ተቀብሎ መዝለቅ ነው፡፡ አገዛዙ የሚያደርገውን ወይም ሊያደርግ የሚፈልገውን አጥተነው እኮ አይደለም፡፡ ሕፃናትን፣ ነፍሰ ጡር እናቶችንና አረጋውያንን ያለምንም ርህራሄ በማንነታቸውና በእምነታቸው በጅምላ የሚያርድ እንደሆነ አሳምረን እናውቃለን፡፡ ታዲያ ነፃነት በልመና በብላሽ ይገኛል እንዴ? ይህ ጀብደኝነት አይደለም፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞ የምናደርገው እኮ ያለምንም ምክንያት በግፍ የታሠሩ እነ እስክንድርና ጓዶቹን ለማስፈታት ብቻ ሳይሆን በመላው አገራችን አገዛዙ እየፈጸመና እያስፈጸመ ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል እያለቁ ያሉ ወገኖቻችንን ለመታደግ፣ የዜጎች ከትውልድ ስፍራቸውና ከቤት ንብረታቸው መፈናቀልን፣ ባጠቃላይ የጐሣ መድልዎ (አፓርታይድ) አገዛዝን ወዘተ. ለማስቆም እንጂ፡፡
እኔ በግሌ በአገራችን ላይ መአት ለሚያመጣና ከወዲሁ የተበላ ዕቁብ ለሆነ የውሸት ወይም ‹ኢሕአዴጋዊ› ምርጫ አሳስቦኝ አይደለም እነ እስክንድር እንዲፈቱ የምፈልገው፡፡ በጭራሽ! አላግባብ በመታሠራቸው እንጂ፡፡ ቢወጡ ሕዝብን የማስተባበርና የአገዛዙን ሸፍጥ እግር በእግር እየተከታተሉ የማጋለጥ አቅማቸውን ስለማውቅ ነው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ ምድር ላይ የምናየው ጽድቅ የሚነግረን አሁን ሊደረግ የታሰበው ‹ምርጫ› ተጨማሪ ትርምስ ውስጥ ከሚያስገባን በቀር የትኛውንም ችግራችንን አይፈታልንም፡፡ ምርጫውን የሚፈልገው ሕዝብን በኃይል አፍኖ ሕውሓታዊውን የአገዛዝ ሥርዓት በማስቀጠል የኦሮሙማ ፕሮጀክቱን በተሟላ ሁናቴ ለማስፈጸም አሰፍስፎ የሚገኘው የዐቢይ አገዛዝ ነው፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል የሥልጣን ፍርፋሪ ፈላጊና በድርጎ አዳሪ ሐሳውያን ተቃዋሚዎች እንደሚፈልጉት አልጠራጠርም፡፡
ወደ ሰላማዊ ተቃውሞው ስመለስ፣ በርግጥ ሕዝብ የሚያስተባብረው ኃይል ያስፈልገዋል፡፡ ለሕዝብ ደኅንነት ከመጨነቅ የመነጨም ቢሆን ኃላፊነትን በመፍራት ማፈግፈጉ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ሕገ ወጡ እኮ ሰላማዊ ሰልፉን የሚከለክለው አገዛዝ እንጂ እናንተ አይደላችሁም፡፡ በመሆኑም በሕገ አራዊት ካልሆነ በቀር እናንተን በኃላፊነት ለመጠየቅ የሚችልበት የሕግም ሆነ የሞራል ምክንያት የለውም፡፡ በመተከል፣ በወለጋና በኮንሶ ሕፃናትና እናቶች በእምነታቸውና በማንነታቸው ከከፈሉት ያነሰ መክፈል የሚያቅተን ይመስላችኋል? ይህ ዋሾና ፈሪ አገዛዝ የሐሰት ምክንያት ፈጥሮ ለመፍጀት ወደ ኋላ እንደማይል እያወቅን በተቀደሰ ዓላማና በእውነተኛ ምክንያት የምናደርገው ሰላማዊ ትግል የሚያስከፍለን መሥዋዕትነት ካለ ከንቱ እንደማይሆን እምነቴ የጸና ነው፡፡ በተጨማሪም ሌሎች የሰላማዊ ትግል አማራጮችንም ጊዜ ሳትወስዱ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁናቴ የሰላማዊ ሰልፉን ያህል ይሠራሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ገና ለገና ዐቢይ ሽመልስ ‹ያሠለጠናቸውን› የጐሣ ሕገ ወጥ ኃይል ያሰማራል በሚል ሥጋት ሕዝብ ያለውን ውጤታማ አማራጭ መዝጋት ትክክል አይመስለኝም፡፡ የአገዛዞቹ አውሬነት መጠን ቢለያይም እንኳን እኛ ባለንበት የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ውስጥ ባሉ ሀገራት ሰላማዊ ሰልፎች ይካሄዳሉ፡፡ ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርምና በሚገባ እናስብበት፡፡
በትግራይ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ በኮንሶና በሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ባስቸኳይ ይቁሙ!!! በሁሉም አካባቢ አደጋ የደረሰባቸው ወገኖቻችንን ፈጥነን እንርዳ!!!
እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!!
ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡
ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡ (የምርጫ ቦርድ የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነትን መሠረዙ አንድ የሚያበረታታ ጉዳይ ሆኖ፣ በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባዋል፤ ትጥቅ ይዞ አገርንና ሕዝብን እያሸበረ ያለው ኦነግም ላይ ባስቸኳይ ሕጋዊ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡)