>

አሳረኛዋ ጎንደር... (ሙሉነህ ዮሐንስ ዘ-ጎንደር)

አሳረኛዋ ጎንደር…

ሙሉነህ ዮሐንስ ዘ-ጎንደር

ድሮ በ1993 የአራተኛ አመት የስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ከስድስት ኪሎው አንበሳ ጊቢ አቅራቢያ ወደ ነበረው ወደ ዝነኛዋ ጦቢያ መፅሄት እና ጋዜጣ ቢሮ አቀናሁ። እናንተየ ጊዜው ነጉዶ ዘንድሮ ልክ ሃያ አመት ሞላው። በጦብያ ሽፋን ከሰጡ ብየ አንድ የቁጭት ፅሁፍ ይዤ ነበር። የቤት ስሜ በሆነው ብእር ስም “አምበይ” ብየ ነበር ያዘጋጀሁት። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ስለ ጎንደር ልዩ ትኩረት እንዳደርግ ካስገደዱኝ ምክንያቶች አንዱ ነበር።
የፅሁፏ አርእስት “ጎንደር ምን አደረገች?” የምትል ነበረች። የጦቢያ አዘጋጆች ወረቀቷን ተቀብለው ወዲያው አነበቧት። ስማቸውን የዘነጋሁት የህግ ባለሞያ የነበሩ ሰው መሰሉኝ ዝርዝር ጉዳይ አናገሩኝ (ስማቸውን የምታውቁ አስታውሱኝ)። እኒሁ ሰውየ ትኩር ብለው አይተው ስለምን ፃፍከው አሉኝ። የጎንደር ተገልሎ መጎዳት ቢቆረቁረኝ አልኳቸው። ፅሁፉን እንደሚሆን እናያለን ብለው አሰናበቱኝ። ይዘቷን አመኑባትና በጋዜጣም ወጣ። ኮፒውን አያይዤዋለሁ ገብታችሁ አንብቡት። ፍሬ ነገሩ ከወሎ ወደ ትግራይ የተዘረጋው የአሁኑ የባቡር መስመር የመጀመሪያ እቅዱ እና እሳቤው በወሎ አድርጎ፣ ጎንደር ከተማን ተመርኩዞ ወደ መተማ እንዲያልፍ ነበር። በወያኔ ፍርደ ገምድልነት ያ ግዙፍ ፕሮጀክት ከጎንደር ሕዝብ ጉሮሮ ተነጠቀ። የጎንደርን በኢኮኖሚ መጨፍለቁ አንዱ ግዙፍ ማሳያ ነው።
ከሃያ አመታት በኋላ በመላ ኢትዮጵያ በነበረው የሕዝብ ትግል ወያኔ ተወገደ። ለዚህ ድል የጎንደር ሕዝብ በተለየ የከፈለውን ህልቆ መሳፍርት መስዋእትነት መዘርዘር ለቀባሪ ማርዳት ነው። ይህን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አይኖርም። በወያኔ ዘመን ጎንደር ላይ የነበራቸው የማድቀቅ ፖሊሲ ውጤት ወደ ቦታው ስትሄዱ አፍጥጦ ይጋፈጣቹሃል።
ምንም አይነት ፋብሪካ አልተገነባም፣ ኢንደስትሪያል ፓርክ ለምልክት የለም፣ የአዘዞ ኤርፓርት ማኮብኮቢያ ናት ብትባል ይቀላል፣ ከአየር ማረፊያው ወደ ጎንደር ከተማ ለመድረስ ወገባችሁን የሚያላቅቅ ኮረኮንች መንገድ ማለፍ አለባችሁ፣ ምናልባት ከዲያስፖራ የሞከራችሁ ካላችሁ ትልቅ ፋብሪካ በባለሃብትነት ልክፈት ብትሉ የሚመጥን የመብራት ሃይል ጣብያ የላትም፣ ቀሃ እና አንገረብ ወንዞሽ የሚከቧት ከተማ አሁንም የውሃ ጥም ላይ ትገኛለች፣ ከኢትዮጵያም ከአማራ ክልልም በዳስ ትምህርት ቤቶች ጎንደር ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ ናት፣ ጎንደር ከተማ ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች (ዋናውን ባንክና ቴሌ መስሪያቤት፣ መዘጋጄ ቤቱን ጨምሮ) በጣሊያን ጊዜ የተሰሩ ናቸው ስላችሁ ትደነግጡ ይሆናል።  ስንቱን ዘርዝሬ እዘልቀዋለሁ። ይህ ሁሉ ሲሆን የጎንደር ሕዝብ ቅድሚያ ለነፃነቱ ሰጠና በልማት ተጎዳሁ ሲል ሰምታችሁ አታውቁም። “የአማራ ክልልን” ግማሹን የቆዳ ስፋት እና የሕዝብ ብዛት የያዘው ጎንደር አሁንም ከኢኮኖሚ ሸፍጥ ያመለጠ አይመስልም።
ትናንትና የመንገዶች ባለስልጣን በክልሉ ሊሰራ ያወጣውን የመንገድ ዝርዝር ብታዩት ማሳያ ይሆናል። ጎንደር ከመንገድ ስራ ውጭ መደረጓን ብቻ አይደለም እንድታስተውሉ የምፈልገው። ይልቅስ ልክ ከላይ ከመንደርደሪያው እንዳነሳሁት ጎንደር ከተማን ከታሪካዊ፣ ከተፈጥሯዊ፣ መብቷ ከሆነው የመተማ የወደብ መስመር ጥቅም የሚገፋ መሰሪ እቅድ ይፋ ሆኗል። ባጭሩ መንገዱ ከመተማ ጎንደር ከተማ የነበረውን ጥንታዊ የንግድ መስመር ወደ ሌላ አቅጣጫ አዙሮ መውሰድ ነው።
የጎንደር ከተማ ትልቁ የኢኮኖሚ መስመር መተማ ነው። ያንን የሰሊጥ፣ የጥጥ፣ የሙጫ፣ የማሽላ እና የከብት ሃብት መስመር ከጎንደር ከተማ ጠምዝዞ ወደ ሌላ መውሰድ ሸፍጥ ብቻ ሳይሆን ንቀትም ነው። የጎንደር ሕዝብ ወጥመዱን ቀድመህ አክሽፍ። የጎንደር ሕዝብ አይደለም ጎረቤቱ ለሆነው ሕዝብ ይቅርና ለሁሉም ኢትዮጵያ ቀና ነው። ይህንን በጎ ግንኙነት ለመጉዳት እና በመሃሉ እርካሽ ሃብት በማካበት ከወያኔ ጓሮ ያደጉ አለቅቶች ግን በቃችሁ ሊባሉ ይገባል። የጎንደር ወጣት እኛ ድሮ ያነሳነውን “ጎንደር ምን አደረገች?” የሚለውን ጥያቄ መርምር እና መፍትሄህን ፈልግ።
እንደ መነሻ ቅሬታችሁን ለመንገዶች ባለስልጣን መስሪያ ቤት በሚከተለው ኢሜል ላኩላቸው።  admin@motcouncil.org.et
Filed in: Amharic