>

ሀገር የሚከፈልለት የክብር ዋጋ አለ፤ እሱን የክብር ዋጋ እስክትከፍል ሀገር አይኖርህም...!!! (ሸንቁጥ አየለ)

ሀገር የሚከፈልለት የክብር ዋጋ አለ፤ እሱን የክብር ዋጋ እስክትከፍል ሀገር አይኖርህም…!!!

ሸንቁጥ አየለ

ኢትዮጵያዉያን ሀገር እንዲኖራቸዉ ተባብረዉ ለመስራት ፈቃደኛ እስካልሆኑ ድረስ በጎሳ ስም የተደራጁ አክራሪ ሀይሎች የጎሳችን ነዉ ከሚሉት መሬት/ክልል/አካባቢ ላይ ሲያባርሯቸዉ በደስታ መቀበል አለባቸዉ::የሀገር ባለቤትነት ዝም ብሎ አይገኝም::
አክራሪ ጎሰኛ ሀይሎች ሲደራጁ መነሻቸዉም ሆነ መድረሻቸዉ ግቡ አንድ ብቻ ነዉ::የነሱን ጎሳ ጠቅመዉ ሌላዉን ማህበረሰብ ማጥፋት/መግፋት ነዉ::
 አዲስ አበባ ላይ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊም የሚጠብቀዉ ይሄዉ ነዉ::በመላ ሀገሪቱ እጅግ ብዙ ሚሊዮን ህዝብ  በጎሰኞች ሲባረር እና ሀገር አልባ ሲደረግ ቆሞ ከመዋጋት ይልቅ እሮሮ እያሰማ በመሸሽ ጎዳና ላይ ወድቆ በበሽታ አልቋል::
በመሸሽ የትም መድረስ አይቻልም::ባልህበት ቆመህ ለህልዉናህ መዋጋት የመጀመሪያዉ እርምጃ ነዉ:: በሁለተኛ ደረጃ ግን ኢትዮጵያዉያን ሀገር እንዲኖራቸዉ ከፈለጉ ለሀገር የሚገባዉን ክብር መክፈል አለባቸዉ::
አክራሪ ጎሰኞችን በማባበልም ሆነ በመካደም ወደ ሰዉነት ደርጃ ማሳደግ አይቻልም::አክራሪ ጎሰኞች የሚያስቡት እንደ ጎሳ እንጂ እንደ ሰዉ ልጅ አይደለም::ታሪክ በመተንተን እና በማጣቀስ: ወንድማማችነት በመስበክ: ሳይንሳዊ ያጋራ እድገትን በመተንተን ለአክራሪ ጎሰኞች ማስረዳት ታላቅ ጅልነት ነዉ::ተዋልደናል ተጋብተናል አንድ ህዝብ ነን የሚለዉ ትረካ ሁሉ ያስቃቸዋል እንጅ ከቶም አያሳምናቸዉም::
የቀደሙት ሀገር የሰሩ አባቶች በዘመናቸዉ አክራሪ ጎሰኞች/ብሄረተኞች አልነበሩም ማለት አይደለም:: በዚህ በእኛ ዘመን ከተነሱት. ህዉሃታዉያን/ኦህዸዳዉያን/ኦነጋዉያን/ብልጽግናዉያን/ከጀዋራዉያን/መለሳዉያን የከፉ በርካታ አክራሪ ጎሰኞች በየዘመኑ ነበሩ::ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዳትቆም ብዙ ያደሙዋት እና ያቆሰሏት ብሎም የሀገር መስራች አባቶቻችችን በጅጉ ያወኩ በርካታ መርዘኛ እና ጉልበታም ጎሰኞች ነበሩ::
የሀገር ባለቤትነት ዝም ብሎ አይገኝም:: ሀገር የሚከፈልለት የክብር ዋጋ አለ::እሱን የክብር ዋጋ እስክትከፍል ሀገር አይኖርህም::
Filed in: Amharic