“ከሰባት ወራት ትዕግስት በኋላ ዛሬ ዝምታዬን እሰብራለሁ…!!!”
የፋናው ጋዜጠኛ አዳነ አረጋ
*”…አዳነ ለግዜዉ ሁሉም ነገር የፖለቲካ ዉሳኔ ነዉ፤ ስለዚህ እዚህ እኛ ጋር የምታገኙት የተለየ ነገር ስለሌለህ ከላይ የምታዉቃቸዉ ሃላፊዎች ካሉ እዉነቱን ለማስረዳት ሞክር!!!”
ችሎቱ ላይ በአንደኝነት የተሰየመ ዳኛ
ለርካሽ ፖለቲካቸው ሰለባ ስላደረጓት እህቴ በአጭሩ:-
ሽብሬ አረጋ ትባላለች። የቤታችን ሶስተኛ ልጅ ናት። ያለፉትን ሰባት ወራት ሙሉ በማታዉቀዉ እና ባልተፈፀመ ወንጀል በእስር እየማቀቀች ትገኛለች ።
እዉነቱ ይህን ይመስላል :-
ነሃሴ 07/2012 ዓ.ም ከለሊቱ 11:00 ላይ ከመኖሪያ ቤቷ የሻሸመኔ ከተማ ፖሊሶች ፤ የሰዉ ቤት በማቃጠል ወንጀል ተከሰሻል ሲሉ ወደ እስር ቤት ወሰዷት።
ነገሩ ለኛ ለቤተሰቦችዋ ብቻ ሳይሆን ከተማ ዉስጥ ለሚያወቁን ሁሉ ግራ የገባ ነበር። ምክንያቱ
በወቅቱ ፤ የአንድ አጎታችን ሆቴል ተቋጥሏል አጎታችንም በፌሮ ተደብድቦ ከሞት አፋፍ በተዓምር ተርፏል። የሌላኛዉ አጎታችን መኖሪያ ቤት ሙሉ በሙሉ ወድሟል ፤ የሌላኛዉ አጎታችን ልጅ ቤት ሲቃጠል አራስ ላይ ከምትገኝ ሚስቱ ጋር ህይወቱ በፈጣሪ ፍቃድ ተርፏል።
የታላቅ ወንድማችን ቤት በድንጋይ ስብርብሩ ወጥቶ በጋዝ ሊያነዱት ሲሉ ሌሎች ቤተሰቦቻችን እና የአካባቢዉ ሰዉ ደርሶ አትርፎታል።
ታዲያ በዚህ ሁሉ ህመም ዉስጥ የከረመ ፤ የፍትህ ያለህ እያለ የመንግስትን ዉስኔ የሚጠባበቀዉ ቤተሰብ አባል ግድ የለም ቤት አቃጥለሻል ተብላ ታሰረች።
በወቅቱ አሳሪዉም ታሳሪዉም ስለማይታወቅ ለማን አቤት ማለት እንኳን እንዳለብን ግራ ገብቶን ነበር። ምክንያቱም ሁሉም እርስ በርስ የተፈራራበት ወቅት ነበር፤ ከዛም ባለፈ የፍትህ ያለ ስንል አይደለም እናንተ እነንትናም ታስረዋል የሚል አስቂኝ መልሶች ይመለሱልን ነበር።
ከፍርድ ቤት ዉጭ የተከሳሽ እህታችን ጠበቃ ቤቱን ለማስረጃነት ፎቶ ሊያነሳ በሄደበት ወቅት የከሳሽ ባለቤት ፤ እኛ ማንንም ቤት አቃጠሉብን ብለን አልከሰስንም እኛ ያልነዉ ሰድባናለች ብቻ ነዉ የሚል አስቂል ምላሽ ሰጠችዉ።
እኔ እንደ አንድ ወንድም ሁሉን አናግሪያለሁ ፤
ከሳሽ አቃቤ ህግን ፤ ለምን ባልተቃጠለ ቤት አቃጥለሻል ብላችሁ ንፁህ ሴት ታስራላችሁ?
አቃቤ ህግን ፤ ምክንያቱም ምስክር አለባት
እኔ ፤ ሰዉ ገድለሃል ተብሎ የተመሰከረበት ሰዉ ፤በድንገት ተግሏል የተባለዉ ሰዉዬ ፍርድ ቤት በህይወት ቢመጣ እና አልሞትኩም ቢል የተመሰከረበት ሰዉ ገዳይ ተብሎ ያለ ጥፋቱ ይፈረድበታል?
አቃቤ ህግ ፤ እሱን ፍርድ ቤቱ ነዉ የሚወስነዉ (ወይኔ ሀገሬ)
በመጀመሪያዉ ችሎት የተሰየመዉን ዳኛ ጋዜጠኝነቴን ተጠቅሜ ቢሮዉ ድረስ ገብቼ ጉዳዩን ሙሉ አስረዳዉት። ልብ ዝቅ የሚያደርግ ምላሽ ሰጠኝ።
“አዳነ ለግዜዉ ሁሉም ነገር የፖለቲካ ዉሳኔ ነዉ፤ ስለዚህ እዚህ እኛ ጋር የምታገኙት የተለየ ነገር ስለሌለህ ከላይ የምታዉቃቸዉ ሃላፊዎች ካሉ እዉነቱን ለማስረዳት ሞክር” አለኝ።
(ይህ ምላሽ ሀገሬ ከፍ ወዳለ የፍትህ ስርዓት ላይ ለመድረሷ ማሳያ ሆነኝ )
ሚገርመዉ እህቴ ሰዎች ቤት ሲያቃጥሉ በር ላይ ቆመሽ ” አቃጥሉ !” ብለሻል በተባለችበት እለት የአካባቢዉ ፖሊሶች በወቅቱ በነበረዉ ግርግር መሸሻ ሲያጡ እና ሲርባቸዉ እህቴ ቤት ገብተዉ ምግብ በልተዉ እንደወጡ በወቅቱም በእህቴ እና በልጆችዋ ፊት ላይ እኛም ጋር ይመጡ ይሆን የሚል ፍርሃት እንደነበር ነግረዉኛል ፤
ይህን ለፍርድ ቤት መናገር ግን በወቅታዊዉ ሁኔታ ምክንያት እንደሚያስፈራቸዉ አጫዉተዉኛል።
እና ዛሬም እህቴ ዳግም ለየካቲት 16 ተቀጥራለች።
ከቤተሰቤ መሃል ባጣት ሆድ ቢብሰኝ ከማዉቀዉ እና ከሆነዉ ሁሉ ሩቡን ብቻ ፃፍኩት።