>
5:33 pm - Saturday December 5, 6189

እጅግ እየተደጋገመ ያለው የ«ኢትዮጵያ አትፈርስም!» መልእክት ምንድነው '?? ለማንስ ነው??? (ወንድወሰን ተክሉ)

እጅግ እየተደጋገመ ያለው የ«ኢትዮጵያ አትፈርስም!» መልእክት ምንድነው ‘?? ለማንስ ነው???

ወንድወሰን ተክሉ

 

* «ኢትዮጵያን ትናንሽ ሀገር እናደርጋለን ያሉ ኃይሎች ታጥቀው ተነስተዋል-ኢትዮጵያ ግን አትፈርስም» 
አቢይ አህመድ በቡሬ
 
* እነዚህ ኃይሎች እነማን ናቸው???
አስራ ስድስት ደቂቃ በፈጀው ንግግራቸው ጠምር አቢይ አህመድ ስምንት ጊዜ ያህል ስለኢትዮጵያን አፈራርሰው በምትኩ ትናንሽ በርካታ ሀገራትን ለመፍጠር ስለሚሹ -ግን- ያልተገለጹ ኃይሎች ትግልና ስለኢትዮጵያ መፈረስና ያለመፍረስን ቃል የተናገሩት በካድሬዎች ስብሰባ ላይ ሳይሆን ግንባታው ተጠናቆ ወደ ማምረት ስራ የገባውን ግዙፉን የቡሬ ዘይት ፋብሪካን መርቀው በከፈቱበት እለትና ስፍራ የመሆኑ ጉዳይ ልዩ አትኩሮትን እንድንቸረው ያደረገን ንግግር ሆኗል፡፡
«ዛሬ » አሉ ጠምሩ «ዛሬ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ዝናብ ማዝነብ፣አርቲፊሻል ንፋስ ማንፈስ፣አርቲፊሻል ጸሃይ ማውጣት የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ» በማለት ከሀገሪቱ ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታዎች ውስጥ በእጅጉ ያፈነገጠ አላማ፣ግብና አጀንዳን ሰንቀው እየታገሉ ስላሉ ያልገለጿቸው «ድብቅ» ኃይሎች ሁኔታ ከጠቀሱ በኃላ በማያያዝ «እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያን ትናንሽ ሀገር እናደርጋለን ብለው ታጥቀው ተነስተዋል…» ካሉ በኃላ የዚህ ሀሳባቸው መደምደሚያ አድርገው የተናገሩት ቃል የእነዚህን ስም የለሽ ድብቅ ኢትዮጵያን አፍራሽ ኃይሎች ማንነት ያመላክታል ብሎ ይህ ጸሃፊ ይረዳል፡፡ እናም ጠምሩ «በእርግጥ የትኛውም ሀሳብ አሸናፊ ገዢ ሀሳብ ሆኖ የሚወጣውን በጊዜው የምናየው ይሆናል » ሲሉ ነው የተደመጡት፡፡
ይህ ማለት በአጭሩ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ወይም የየራሳቸውን ነጻና ሉዓላዊ መንግስት ለመፍጠር አልመው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኃይሎች መኖራቸውን ይገልጽና የእነዚህ ኃይሎች ነጻ ሀገር የመፍጥር ምኞትና ራእይ የብዙሃኑን ሀሳብ አሸንፎ ገዢ ሀሳብ መሆን የመቻሉና ያለመቻሉ ጉዳይ በጊዜ ሂደት ውስጥ ይታያል ማለት የእነዚህን ኃይሎች ኢትዮጵያዊያነትን የሚያመላክት እንጂ ኢትዮጵያን ወደ ትናንሽ ሀገርነት ለመቀየር ያለሙ የውጭ ኃይሎችን ማንነት የሚያመላክት አባባል ሆኖ አናገኘውም፡፡  እነዚህ ኢትዮጵያን አፈራርሰው ትናንሽ ሀገራትን ለመፍጠር ያለሙ ኢትዮጵያዊያን የእናት ጡት ነካሾች እነማን ናቸው???
ለምንስ ነው ጠምሩ ይህንን መሰል አስጊ የሆነን ጸረ ህዝብና ጸረ ሀገር ኃይሎችን ማንነት ፍርጥርጥ አድርገው በመናገር -ማለትም የሀገር ውስጥም የሆኑትንና የውጭ ኃይሎች የሆኑትን – ለኢትዮጵያ ህዝብ በማሳወቅ ህዝቡ አምርሮ እንዲታገላቸውና ሀገሩን ከእነዚህ መሰሪ ኃይሎች ድብቅ ሴራና እንቅስቃሴ እንዲጠብቅ እማያደርጉት??
ጠምሩ «ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልጉ…» የሚሉትን አባባላቸውን ላለፉት ሶስት ዓመታት በእርግጥ አዘወትረው የሚናገሩት ቃል ቢሆንም ብዙዎን ግዜ ግን ይህንን አባባል መዠረጥ እያደረጉ ሲጠቀሙ የታየው እንደ የሀጫሉ ግድያና በእሱ አሳብቦ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ወቅት ቢሆንም ዛሬ ግን በአማራዊቷ ጎጃም ቡሬ ከተማ የተገነባውን ግዙፉን የአቶ በላይነህ ክንዴንና የአቶ ሙላት መንገሻን የዘይት ፋብሪካን ለመመረቅ በተገኙበት ስፍራ የመግለጻቸው ጉዳይ ይህ ኢትዮጵያን አፈራርሶ ትናንሽ ሀገራትን የመፍጠርን አጀንዳ የሚያራምዱ ውስጣዊና ውጫዊ ኃይሎች እንቅስቃሴ በእጅጉ ገፍቶ ያለበት ሁኔታ ላይ ስለደረሰ ነው ብሎ ይህ ጸሃፊ ይረዳል፡፡
በዚህ አስራ ስድስት ደቂቃ በፈጀው ንግግራቸው ጠምሩ ስለቡሬ ዳሞት ታሪካዊ ዳራና እምቅና ቅምጥ ሀብት የአድማጭ ተመልካቹን የጋለ ጭብጭባን ማፍለቅ ባስቻለ መልኩ በተናገሩበት ሁኔታ ከስምንተኛው ደቂቃ ንግግራቸው በኃላ ግን «ኢትዮጵያ አትፈርስም…ሊበትኑን የሚፈልጉ…ጥቃቅን ትንሽ መንግስታት ሊያደርጉን የፈለጉ…መፍረሷን የሚጠብቁ…ኢትዮጵያን ማፍረስ…ኢትዮጵያን መናድ…ኢትዮጵያን ማዋረድ…መፍረሷን የሚሹ…»እና መሰል ሀገራዊ አደጋዎችን እያከታተሉ የገለጹትን ያህል አንዴም አምልጧቸውም ይሁን ደፈር ብለው የእነዚህን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሹትን ኃይሎች ሙሉ ስምም ሆነ በጨረፍታ እንኳን ለመግለጽ ሳይፈልጉ ንግግራቸውን ደምድመዋል፡፡
በጣም በሚገርም ሁኔታ በዚሁ ሳምንት በእለተ ማክሰኞ እሳቸው በሚመሩት የኦሮሚያው ኦህዴድብልጽግና አዘጋጅነት በኦሮሚያ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ እጅግ ሀገር ወዳድ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ግዴታቸውንም ያወቁ በመሆን የመከላከያ ሰራዊቱ ሰሜን እዝ ክፍለ ጦር ላይ በትህነግ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘውና ብሎም የተካሄደውን ጦርነት ደግፈው መግለጫ ያወጡትንና የመንግስትን «የህግ የበላይነትን የማስከበር ወታደራዊ ዘመቻን» የደገፉትን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብንን «ጽንፈኛ አሸባሪ ናቸው፣የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው…» በማለት ከጁንታውና ከኦነግ ሸኔ ጋር አዳብለው ስማቸውን ላብጠለጠሉ ሰልፈኞች የምስጋና እና የአድናቆት መልእክታቸውን የገለጹ ሰውዬ ምነው አሁን ሀገር አፍርሶ ጥቃቅን መንግስታትን ለመፍጠር የሚፈለግ ኃይል ታጥቆ ተነስተዋል ያሉትን ወገን ማንነት ለመግለጽ ከበዳቸው ብሎ መጠየቅ ተገቢና አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል፡፡
የመንግስትን ዘመቻ የሀገርን ሉዓላዊነትና ሀገራዊ ህልውናን ለመታደግ የተደረገ ዘመቻ ነው ብለው ድጋፋቸውን በይፋ የሰጡ ድርጅቶችን እሳቸው በሚመሩት ፓርቲ በሀሰትና በውሸት «ጽንፈኛ አሸባሪ…የኢትዮጵያ ጠላቶች …» የሚል የስም ማጥፊያ ታፔላን በግል አደባባይ አስለጥፈው ማስነገር ያልቸገራቸው ሰውዬ ዛሬ ሀገር አፍራሽ ብለው በውስጠ ወይራ አገላለጽ ሾላ በደፈናው አድርገው ከማቅረብ ይልቅ ድርጅታዊ ህልውናውንና ማንነቱን ይፋ በማድረግ ህዝቡ ሀገሩን ለመጠበቅ እንዲታገላቸው መግለጽ አልቻሉም???
ለእነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛና ተገቢውን መልስ ሊሰጠን የሚችል ሰው አለሁ ሊለን ይቻለው ይሆን???
ስለጠምሩ ንግግር እሳካወራሁ ዘንዳ ሳልጠቅስ እማላልፈው ሰውዬው ሲነጋሩ በእያንዳንዷ አረፍተ ነገር  መገባደጃ ቃል ላይ ሲስተጋባ የተሰማው የጋለ ጭብጨባን በተመለከተ ይሆናል፡፡ አጨብጫቢዎቹ አንድ ለባለሀብቱ ካላቸው ፍቅርና ድጋፍ ሊመርቁ ለመጡት ታላቁ የክብር እንግዳ የሆዴን በሆዴ ይዤ አስደስቼ ልመልስ በሚል እሳቤና እምነት ሲያጨብጭቡ የዋሉ መሆናቸውን ፣ሁለተኛ – አጨብጫቢው በየአረፍተ ነገር መጨረሻ ላይ እንዲያጨበጭብ በባለስልጣናቱ ታዞና ተገዶ ለማጨብጨብ የተገኘ ካድሬ ይሆናል ብዬ ተውኩት እንጂ እንደሰማሁት ጭብጨባ ሁኔታ ሰውዬው ከቀናት በፊት በመላ ኦሮሚያ ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ ላይ «ነፍጠኛ ከኦሮሚያ ይውጣ..» እያሉ ሲያስተጋቡ የዋሉ መልእክቶችን በደስታ ተቀብለው ያመሰገኑ መሪ መሆናቸውን እና በእሳቸው እንዝህላላዊ አመራርና መንግስታዊ አሻጥረኝነት በመተከል በሚኖሩ የጎጃም ክፍለሀገር አካል አማራ-አገው ተወላጅነታቸው ብቻ በሺህ የሚቆጠሩት በግፍ ተጨፍጭፈው የተሰውበትና ከ440ሺህ በላይ ደግሞ ተፈናቅለው በሜዳ ላይ የተሰጡበት ክስተት የተፈጠረም አይመስልም ነበር ጋል ባለሁኔታ ሲስተጋባ የነበረውን ጭብጨባ ለሰማ ሰው፡፡
👉 የኢትዮጵያ መሪዎችና ስለሀገር መፍረስ የገለጹበት ሁኔታ-
የጠምር አቢይ አህመድ የእለተ እሁዱ የቡሬ ጎጃም አማራ ንግግር ላይ ስለሀገር መፍረስና ስለሀገሪቱን ለማፍረስ ስለሚፈልጉ ኃይሎች ሲናገሩ ፈጥኖ የታወሰኝ በ1983 መጋቢት ወር ላይ የተደረገውን የኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያምን ንግግር ሲሆን የሁለቱ መሪዎች ንግግር አንድነት ሀገሪቱ ስለተጋፈጠችው የህልውና አደጋ የሚገልጽ ይሆንና ልዩነቱ ግን -አንደኛ- የኮ/ል መንግስቱ ኢትዮጵያ ስለህልውናዊ አደጋዋ የተናገሩላት በሻእቢያ፣በህወሃት/ኢህአዴግ፣በኦነግ፣በኦብነግና መሰል ተገንጣይና አስገንጣይ ኃይሎች ጋር እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ ላይ ያለች ሀገር የነበረችና ያም ፍልሚያ በሚያሰጋ ሁኔታ በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ተጧጡፎ ውጊያው ወደ መሀል ሀገር እየገሰገሰ ያለበት ሁኔታ ላይ ሆነው የተነገረ የመፍረስ አደጋ ሆኖ ሳለ የአቢይ ኢትዮጵያ ግን በግልጽና በይፋ ሀገሪቱን ለመገነጣጠል ብሎ የተነሳና እየተዋጋ ያለ ሀይል የሌላባት የመሆኑ ጉዳይ የሁለቱን መሪዎች የሀገር መፍረስን አደጋ ንግግር አንድነትና ልዪነት ያሳያል፡፡
በእርግጥ ኮ/ል መንግስቱ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ህልውና ለመበታተን እየተዋጉ የነበሩትን ኢትዮጵያዊያን ኃይሎችን ስምና ከበስተጀርባቸው ሆነው የሚያግዟቸውን የውጭ ኃይሎችን ስም በይፋ ለኢትዮጵያ ህዝብ የገለጹበትና በአንጻሩም ጠምር አቢይ አህመድ ስለኢትዮጵያ ሀገራዊ መፍረስ ጉዳይ አስጊ ኃይሎች ብለው በደፈናው ከመግለጽ በስተቀር ስም ያለመጥቀሳቸውም ጉዳይ ሌላው የሚለዩበት ነጥብ ቢሆንም አቢይ አህመድ ልክ በጦርነት ውስጥ እንደተዘፈቀችው የኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም ዘመኗ ኢትዮጵያ – ሀገራዊ ህልውናዋን አፈራርሰው ትናንሽ መንግስታትን ለመፍጠር ያሰቡ ኃይሎች ቆርጠው ተነስተዋልን በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያን የመፍረስ አደጋን ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ጠምሩ በተቆናጠጡት መንግስታዊ ስልጣንና ቢሮክራሲያዊ ተቋም በመጠቀም ይህንን የሀገራችንን ሀገራዊ ህልውናን ለከፍተኛ አደጋ ላይ የጣለ ውስጣዊና ውጫዊ ኃይልን ማንነት ለማወቅ የሚያስችል የመረጃ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ያለሆኖ ሳለና ምናልባትም በዚሁ መንግስታዊ የመረጃ ተቃም በኩል በሚደርሳቸው ሪፖርት መሰረት ይህንን ውስጣዊና ውጫዊ የሆነን የሀገር ጠንቅ ጠላት ጠንቅቀው እያወቁ ሳለ ለምንድነው ለኢትዮጵያ ህዝብ ማንነቱን በይፋ በመግለጽ ህዝቡ እንዲታገለው እማያደርጉት በሚለው ጥያቄ መልስ ውስጥ የጠምሩ የተደጋገመው ኢትዮጵያ አትፈርስም መፈክር  ምንጭና መንስኤን እንዲሁም የዚህ ማንነቱን ሊገልጹልን ያልፈለጉትን ሀገር አፍራሽ ኃይል ማንነትን የምናገኝበት መልስ ነውና ሁላችንም ወደ መልሱን ፍለጋ እንሰማራ እያልኩ በእኔ በኩል ያገኘሁትንና የማገኘውን በቀጣይ እንደምመለስበት እየገለጽኩ መጣጥፌን እቋጫለሁ-ቸር እንሰንብት!!!
Filed in: Amharic