>

ፖለቲካን እንደ ቆሼ ! (አሰፋ ሀይሉ)

ፖለቲካን እንደ ቆሼ !

አሰፋ ሀይሉ

*…. የእኛም ፖለቲካ ምንችክ ብሎ ነው የቆሸሸው፡፡ የእኛ ግን መቆሸሽ ብቻ አይደለም፡፡ የሚባላ ፖለቲካም ነው ያለን! ፖለቲካችን መቆሸሹ ብቻ አይደለም፡፡ የቆሸሸው ፖለቲካችን በደም ይነፃ ይመስል ካመት ዓመት ብዙ የደም ዋጋ ይገበርለታል፡፡ እስካሁን ግን ተቀናቃኞችን ሲያፀዳ እንጂ – የራሱ ጉድፍ ሲፀዳ አልታየም፡፡ የፖለቲካችን ቆሼ የብዙ ሳንካዎቻችን ምንጭ ነው፡፡ ገና ከሌሎች የሚጋቡብን ብዙ ሳንካዎች፣ ብዙ ቆሼዎች ይጠብቁናል፡፡ ፈጣሪ ፖለቲካችንን ያንጻልን!!!
 
ፖለቲካ የብዙዎች ሕልም ነው፡፡ ፖለቲካ የሃብት ምንጭ ነው፡፡ ፖለቲካ የበላይነትን ማሳያ ዓይነተኛ መንገድ ነው፡፡ ፖለቲከኝነት ብዙዎች በህልማቸው የሚመጣባቸውን ባለሥልጣን ኃያል፣ ተፈሪ፣ አድራጊ-ፈጣሪ፣ ታዋቂ፣ እና አዋቂ የመሆን ምኞት ያሳካል፡፡ ፖለቲካ ትልቅ ሰው የመሆኛ መንገድ ነው፡፡ ፖለቲካ በብዙ ሚሊዮን ሰዎች ህይወት፣ በብዙ ሚሊዮን ሰዎች ሃብትና ንብረት ላይ ለመወሰን የሚያስችል የሥልጣን ቁልፍን ያስጨብጣል፡፡ ታዲያ ብዙዎችን ምራቅ የሚያስውጠው ፖለቲካና ፖለቲከኝነት ስለምን እንደ ቆሻሻ ተቆጠረ?
ድሮ ሲጀመር ፖለቲካ ሕዝብን አፋቅሮ ለጋራ ፍላጎት የማስተባበሪያ ሁነኛ መሣሪያ ነበር፡፡ እየቆየ ሲመጣ ግን ፖለቲካ ሞሰነ፡፡ ተበላሸ፡፡ ከታሰበለት ታላቅ ግብ ይልቅ፣ ከሚያላብሰው ታላቅ ሥልጣን ጋር በፍቅር በወደቁ ‹‹ርካሽ›› ፖለቲከኞች እጅ ወደቀ፡፡ ርካሽ የተባሉት ሥጋቸውን ለጥቅም እንደሚቸረችሩ ዝሙት አዳሪዎች ሁሉ፣ ፖለቲከኞችም የከበረ ሰብዓዊ ማንነታቸውን ለጥቅምና ለሥልጣን ሲቸረችሩት ስለሚገኙ ነው፡፡ እና ፖለቲካ በሂደት እውነተኛ ሰብዓዊ ማንነትን አስረስቶ የዕድሜ ዘመን ተዋናይ አድርጎ ስለሚያስቀር ጭምር ነው፡፡
ፖለቲከኞች በብዙ ታዳሚዎች ፊት ቃለ-መነባንባቸውን የሚተውኑ የትያትር ተዋናዮች ሆነው ተገኙ፡፡ እዚህ ጋር አልቅሰው፣ እዚያ ጋር ይስቃሉ፣ እዚህ ጋር አድነው፣ እዚያ ጋር ይገድላሉ፡፡ ያውም በብዛት፡፡ እዚህ ጋር መፅውተው፣ እዚያ ጋር ይዘርፋሉ፡፡ ነገ በጀርባህ ዞሮ ሊወጋህ ሺህ ሰይፎችን እየሳለብህ ያለ ፖለቲከኛ፣ ዛሬ ሺህ የውዳሴ ስንኞችን እፊትህ እያዘነበ የፍቅር እንባውን በፊትህ ያዘራል፡፡ እውነተኛ የትያትር ተዋናዮች የሚተውኑት በጥበብ ፍቅር የተነሳ ነው፡፡ ፖለቲከኞች የሚተውኑት ግን ወደር በሌለው የሥልጣንና የጥቅም ፍቅር የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ ርካሽ ተባሉ፡፡ ሥራቸው ደግሞ ቆሻሻ፡፡
አንድ ብዙ ጊዜ የሚጠቀስ አባባል አለ፡፡ ፖለቲከኞች በሥልጣን በቆዩ ቁጥር ይሠየጥናሉ፡፡ በሥልጣን በቆዩ ቁጥር በሥልጣን ሙስና እየተጨማለቁ ይመጣሉ፡፡ ፖለቲከኞች ገደብ በሌለው ሥልጣን በተጨማለቁ ቁጥር፣ ንቅዘታቸውም ገደብ ያጣል፡፡ ይበልጥ እየቆሸሹ ይሄዳሉ፡፡ እና ቶሎ ቶሎ መቀያየር አለባቸው (ይባላል)፡፡ እንደ ህጻን ልጅ ሽንት ጨርቅ፡፡ “Politicians and diapers must be changed often, and for the same reason.” (‹‹ፖለቲከኛና የሽንት ጨርቅ ቶሎ ቶሎ መቀየር አለበት፣ ለተመሣሣይ ምክንያት ሲባል!››)፡፡ አንዳንዶች ግን እውነታው ከዚህም ይከፋል ይላሉ፡፡ ቢያንስ ሽንት ጨርቅ ታጥቦ ይነጻል፡፡ መልሶም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በሥልጣኑ የቆሸሸ ፖለቲከኛ መቼም ተመልሶ ሰው አይሆንም፡፡ ልብ ይባል፡፡ ይሄ ሁሉ የራሴ አባባል አይደለም፡፡
ስለ ፖለቲካና ፖለቲከኞች መቆሸሽ ይህን ያህል ‹‹በረከተ መርገም›› ካዘነብን – አሁን ወደዚህች የፔንስልቫንያ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ስኩል ኦፍ ኮሙኒኬሽን›› ዲን ወደሆነችውና የመጽሐፏን ርዕስ ‹‹ቆሻሻ ፖለቲካ›› ወይም ‹‹Dirty Politics›› ብላ ወደሰየመችው ፕሮፌሰር እንሸጋገርና ጥቂት ብለን እንሰነባበት፡፡
ፕሮፌሰር ኬትሊን ሆል ጄሚሰን ለመጽሐፏ ክብረ-ነክ የሚመስል ርዕስ ስለሰጠች ክብረ-ቢስ አድርገህ እንዳታሳባት፡፡ ፕሮፌሰሯ ከባድ ሚዛን አዕምሮን፣ ከብዙ ጊዜያቸውን ከተሻገሩ ምጡቅ አስተሳሰቦች ጋር የያዘች  ምሁር ነች፡፡ ከመጽሐፏ ይዘት  ልጀመርልህ፡፡ ከዚህ 335 ገጽ ካለው መጽሐፏ ውስጥ – 70ው ገጽ የዋለው ይህን የምርምር ውጤቷን ለመጻፍ የተጠቀመችባቸውን ዋቢ መጽሐፍና የመረጃ ምንጮች፣ ከተለያዩ ገላጭ ቻርቶችና ስዕሎች ጋር የደረደረችባቸው ናቸው፡፡
የእሷን ማጣቀሻ መጻሕፍት ዓይኔን እስኪደክመው ቆጠርኳቸው፡፡ ለ226 ገጽ የመጽሐፏ ይዘት – 389 ዋቢ ድርሳናትን ተጠቅማለች፡፡ ጉድ ነው ያሰኘችኝ፡፡ በተለይ የአካዳሚክ ሰዎች ትልቅ ሃብታቸው በአንድ ሥራ ውስጥ ይዘው የሚወጡት የዕውቀት ብዛት ነው፡፡ ብዙዎቹ ብዙ ነገር አጭቀው ነው የሚወጡት፡፡ እና ወደ ብዙ ተዛማጅ ንባቦችም ይመሩሃል፡፡ ከልቤ አከብራቸዋለሁ፡፡ ይህቺ ፕሮፌሰር አንዷ ነች፡፡
ፕሮፌሰር ኬትሊን በአሜሪካ የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት በተደረጉ የምረጡኝ ውድድሮች ዙሪያ ነው ጥናቷን ያደረገችው፡፡ ከሮናልድ ሬገን ምርጫ እስከ ጆርጅ ቡሽ፣ የነጭ አክራሪዎች ምሥጢራዊ ማኅበር ከኩክሉክስ ክላኑ ግራንድ ዊዛርድ ዴቪድ ዱክ፣ እስከ ጆ ባይደን ድረስ ያሉ የሚታወቁ ሰብዕናዎችንና የምርጫ ወቅት የተከተሏቸውን ቆሻሻ ስትራቴጂዎች፣ ወይም ደግሞ በተወዳዳሪዎቻቸው በዘነበባቸው የፖለቲካ ቆሻሻ የተነሳ እንዴት ያሉ አሳዛኝ ሰለባዎች ሆነው እንደተሸኙ ትነግርሃለች፡፡ የእሷ ትልቁ ትኩረት በፖለቲካል ኢቬንቶቹ ላይ አይለም፡፡ ክስተቶችንና ታሪኮችን ሌሎች ሊናገሯቸው ይችላሉ፡፡ የእኔ ሥራ ‹ፕሮሰሱን›› የዚያን ሁሉ ሂደት በጥልቀት መመርመር ነው – ትላለች፡፡
በተለይ በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1980ዎቹ የሬገን ፕሬዚደንታዊ ውድድሮች ጀምሮ ‹‹Attack Politics›› እና ‹‹Attack Campaigning›› ዋነኛ የአሜሪካ የፖለቲካ ሜዳ መገለጫ መሆን እንደጀመረ ትናገራለች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌቪዥንን የምስልና የድምጽ ድራማዊ ጥበብ እውነትን ለመደበቅ፣ እውነቱን ለማስቀየስ፣ እና ባላንጣዎቹን ለማንጓጠጥ ዓላማ የተጠቀመበት የፖለቲካ ተወዳዳሪ ሮናልድ ሬገን ነው ትለናለች፡፡
በእርግጥ ሬገንን ‹‹እውነትን በትያትር የቀየረ›› የቆሻሻው ፖለቲካ አስጀማሪ ትለዋለች እንጂ፣ በዋነኝነት የምትከሰው ግን ሬገንን ራሱን አይደለም፡፡ የሬገንን የምርጫ ዘመቻ ለማድረግ በቅጥርና በፓርቲ ተመልምለው ከጀርባው የተሰለፉትን ‹‹ቲንክ ታንኮች›› ወይም ‹‹የምርጫ ስትራቴጂስቶች›› ነው፡፡ ለፕሮፌሰር ኬትሊን የብዙው ፖለቲካ ብልሽት ምንጮች እነዚህ ከየመሪው ጀርባ ያለ ይሉኝታ ባላንጣን የማዳፋትና አፈር የማስበላት ‹‹ሥራቸውን›› ሌት ተቀን የሚያከናውኑ የምርጫ አማካሪዎችና የፖለቲካ ቴክኒሺያኖች ናቸው፡፡
/ይቺ ደራሲ አንድም ቦታ ይህን አትለውም እንጂ – ግን ሬገን ፖለቲከኛ ከመሆኑ በፊት – የፊልም ተዋናይ እንደነበር ሳስበው በጣም ነበር ያሳቀኝ፡፡ በትወና ከፈለግክ ታለቅሳለህ፣ ታስለቅሳለህ፣ ትስቃለህ፣ ታሰቅቃለህ – የተሰጠህን ስክሪፕት እየተከተልክ፡፡ እና የትወና ዲሴፕሽኑን ወደ ፖለቲካቸው ያመጣባቸው ሬገን ነበር ማለት ነው? ገረመኝ! የትወና ፖለቲካው ጅማሮ፡፡ ምናልባት የዚህች ተመራማሪ ሥራ አድማስ የጊዜ ገደብ ስለተቀመጠለት እንጂ – ኋላ የጥንታዊ ሮማውያን ገዢዎች ለመሆን የበቁት እነ ጁልየስ ቄሳር በአደባባይ ሕዝብን የሚያዝናኑ የሠርከስ ተጫዋቾች እንደነበሩ ማን በነገራት? ይህን አታውቅ ይሆን? ብዬ አሰብኩ፡፡ እና በራሴ ተሳቀቅኩ፡፡ እኮ ማን? ይህቺ የመጠቀች የፔንስልቫንያ ፕሮፌሰር ነች ይሄን የማታውቀው?! ድጋሚ ብዙ መሳቀቅ!/
ፕሮፌሰር ኬትሊን በምሳሌ ስታስረዳ ሬገን ከጂሚ ካርተር ጋር ሲፎካከር – ወይም ከማይክል ሞንዴል ጋር ሲወዳደር – ብዙ ጊዜ ባላንጣዎቹ የሰነዘሩበትን በትክክልም እውነት የሆኑ የክርክር ነጥቦች ፊት ለፊት ሞግቶ የእርሱ ፖሊሲ እነዚያን የተባሉትን ዓይነት እንዳልሆኑ በተጨባጭ ምክንያት አስደግፎ አስረድቶ አያውቅም፡፡ ወይ በደምሳሳው ተከራካሪውን ተችቶ ያልፋል፣ ወይ ደሞ ከማግስቱ ጀምሮ ያን ነጥብ ለማካካስ ታልመው የተሰሩ ተከታታይ የቴሌቪዥን ትዕይንቶችን ለህዝብ ያሰራጫል፡፡
ለምሳሌ ‹‹የሬገን ፖሊሲ ለአረጋውያን ተገቢውን ትኩረት አይሰጥም›› በማለት የቀረበበት ክርክር ነበር፡፡ እውነት ነበረ፡፡ ግን በማግስቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሬገን ከተለያዩ አረጋውያን ዜጎች ጋር ያደረጋቸውን ግንኙነቶች፣ ጉብኝቶች፣ ልገሳዎች፣ ውይይቶች፣ ምርቃቶች፣ አድናቆቶችና ሽልማቶች እያቀናበረ ለህዝብ ማሰራጨት ይጀምራሉ፡፡ ከዚያ የአሜሪካ ህዝብ እውነቱን የመመርመርና የማወቅ ዕድል ሳይኖረው በዓይኑ ላይ የሚሽከረከረውን በዜና መልክ ቅርጹን እየቀያየረ የሚሰጠውን የምረጡኝ ቆሎ ከክቶ ይጨርሰዋል፡፡ እና ለአረጋውያን ተቆርቋሪ ከሬገን በላይ ማን ይምጣ? ይልሃል የምታናግረው ሰው በቁጣ ተሞልቶ፡፡
ሬገን በ1988 ምክትል የነበረው የሪፐብሊካኑ ጆርጅ ቡሽ ሲወዳደር – በግልጽ አደባባይ ወጥቶ ነበር ተመሳሳይ የቴሌቪዥን ሽፋን ድጋፉን ሲያበረክት የነበረው፡፡ የቡሽንና የማይክል ዱካኪስን ነገሮች በዝርዝር እያነሳችም ታስረዳለች ፕ/ር ኬትሊን፡፡ ዱካኪስ በዚያ ምርጫ ቢሸነፍም በምርጫው ካነሳቸው ከ90 በመቶው በላይ አጀንዳዎች ትክክለኛ (በማስረጃና ትንተና የሚረጋገጡ) ነጥቦች ነበሩ፡፡
ለምሳሌ በወታደራዊ ፖሊሲ፣ በዓለማቀፍ ዲፕሎማሲ፣ በሀገር ውስጥ የጤና ፖሊሲ፣ በታክስ መጠንና አሰባሰብ፣ በአሜሪካ የፍትህ ሥርዓትና በሌሎችም ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ዱካኪስ ያነሳቸው ከቡሽ ጋር የተቃረኑ ነገሮች ሁሉ እውነት የነበሩና – በምርጫው በተለያዩ የውሸት ማስታወቂያዎችና በቴሌቪዥን ፕሮፓጋንዳዎች ተዳፍነው እንዲቀሩ የተደረጉ – በኋላ ግን ቡሽ ከተመረጠ በኋላ ዱካኪስ ባስቀመጣቸው መልኩ አንድ በአንድ የተተገበሩ መሆናቸውን በሚገርም መልክ እየነቀሰች ታሳየናለች፡፡
ወደ መጨረሻ የዱካኪስ አማካሪዎችም በአዲሱ ቆሻሻ የፖለቲካ መንገድ (በቲቪ ፕሮፓጋንዳና የሚዲያ ዘመቻ) ገቡበት፡፡ ምርጫው የፖሊሲዎችና የሃሳብ ፍልሚያ መሆኑ ቀርቶ፣ በሚዲያዎች አማካይነት የሚካሄድ ያለማቋረጥ በባላንጣ ተፎካካሪ ላይ የመሳለቅና ሰብዕናውን የማዋረድ፣ እና የራስን ምስል ከፍ የማድረግ ዘመቻነት ተቀየረ፡፡ እና ውጤቱ አስገራሚ ነበር፡፡ ዱካኪስ በአራት እጥፍ ድምጽ ተበልጦ በቡሽ ተሸነፈ፡፡ ያም ቆሻሻው ፖለቲካ፣ በሃቅ ላይ ተመሥርቶ ከሚደረገው ፖለቲካ ይበልጥ አዋጪ መሆኑን ለአሜሪካና ለዓለም በማያወላዳ አኳኋን አበሰረ፡፡
አሁን ፖለቲካው ከመቆሸሹ የተነሳ የመመረጥ ዕጣ ፈንታ በእውነት እና ትክክለኛውን ነገር ይዞ በመገኘት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ቀርቶ – ማን የማንን ቅሌት ሠርሥሮ ስሙን የበለጠ ማጥፋት ይችላል – በሚለው ላይ የተመሠረተ ሆኗል፡፡ አሁን በዘመነ ቴክኖሎጂ የህዝቡን አስተያየትና ፍላጎት ለማወቅ – በኢንተርኔትና በሌሎች መንገዶች የሰው አስተያየት በመሰብሰብና በመተንተን ሥራ ላይ የተሰማሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ባለዲግሪ የመረጃ አልቅቶች 24 ሰዓት ጠምደው በየሰዉ ስሜት መጠን የተመጠኑ የምርጫ ፕሮፓጋንዳዎችን ሲያዘንቡ ይከርማሉ፡፡ የምርጫ ተወዳዳሪውን እንዲህ ሁን፣ እንዲያ ተናገር፣ በዚህ ውጣ፣ በዚህ ግባ፣ ይሄን ልበስ፣ ያን ተላበስ.. ብለው የሚያዙት እነዚያ የምርጫ አማካሪዎቹ ናቸው፡፡
የፖለቲካ ተቀናቃኙን የጀርባ ታሪክ ከአያት ቅድመ አያቱ ጀምሮ እስከ ተጸነሰበትና እስከ ተወለደባት ቀን ድረስ፣ ከእናቱ እስከ ሚስቱ፣ ከልጆቹ እስከ አብሮአደጎቹ፣ እያንዳንዷን የረገጣትን መሬትና የቀመሳትን እህል ውሃ ሳይቀር መዓት ዘማቾች ተሰልፈው ሲያጠኑት ይከርማሉ፡፡ እና ምርጫው የህዝቡን የማወቅ አምሮት የሚያረኩ ተከታታይ ጉዶች የሚዘከዘኩበት መድረክ ሆኖ ይጠናቀቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት በባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ራሳቸውን እውነታን እየተከታተሉ ለህዝብ በገለልተኝነት ከሚዘግብ የዜና ማሰራጫነት – እልም ወዳለ የዚህ ወይም የዚያ ወገን የድጋፍ ማሰባሰቢያ አስተዋዋቂነት ደረጃ ራሳቸውን ዝቅ አድርገውታል፡፡ ሚዲያዎች ከዜና አሠራጪነት ወደ ፈራጅነት ተሸጋግረዋል፡፡
በፖለቲካው መድረክ ላይ ‹‹የትኛው የፖለቲካ ተወዳዳሪ ነው የትኛውን ለሀገር የሚበጅ ሃሳብ ያቀረበው?›› የሚለው ዋና ጥያቄ ከተረሳ ቆይቷል፡፡ ዋናው ነጥብ ሚዲያዎቹ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ቀጥረው በሚያሰሯው ‹‹የህዝብ አስተያየት መለኪያ አሃዞች›› ማን ማንን እየመራ ነው፣ ማን ነው በዚህ አካባቢ ከፍተኛ ድጋፍ እያገኘ የመጣው? ማነው ተወዳጅ የሆነ ድራማን በብቃት እየተወነ ያለው – ወደሚል አስገራሚ ግን በእውን እየሆነ ወዳለ የመንጋ ውጤት ዕለት በዕለት እየተገለጸ መሪ የሚመረጥበትና የሚሰናበትበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
እንደ ፕሮፌር ኬትሊን ላሉ ምሁራንና ዘመናዊ ፖለቲካና ዲሞክራሲ ከየት ወደየት እየሄደ ነው ብለው ለሚጨነቁ ዜጎች ይህ ሁሉ በየሀገሩ እየተዳረሰ ያለ ሂደት – የዲሞክራሲ ተሳልቆ ብቻ ሳይሆን – የሰውን ልጅ ወደተሻለ የጋራ ግብ ማሻገሪያ መዋል የነበረበትን ፖለቲካችንንና ሂደቶቹን ሁሉ ያቆሸሸ ዓይነተኛ ስንክሳራችንም ሆኗል፡፡ የሃሳብ መንሸራሸርን ገድቧል፡፡ የውይይት ባህልን አጥፍቷል፡፡ ፖለቲካን በደቦ ወደሚከወን የውንብድና ሥራነት ዝቅ አድርጎታል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ በሂደት ስንት ዘመን የሰበክንለትንና የቆምንለትን ዲሞክራሲያችንን በቁሙ ቀብሮ፣ የፖለቲካ ሞታችንን ያረዳናል፡፡
በሃሳብ ክርክር ረቺነት፣ በምክንያትና በሰው ልጅ ከፍ ባለ የኃላፊነት ስሜት፣ በዕውቀትና በሰብዕና ታላቅነት፣ በጥበብና በሎጂክ አሸናፊነት፣ በሚዛናዊ መረጃና ማስረጃ ተዓማኒነት አምነው – ስለ ፖለቲካችን ህይወታቸውን የሰጡ – የዓለማችን እልፍ ፈላስፎችና የዲሞክራሲ አባቶች – ዛሬ በተግባር እያደረግን ያለነውን ነገር ቢያዩ – ሃፍረትና ብስጭት ይገድላቸዋል፡፡ የምትል መሠለኝ፡፡ በብዙ ቦታዎች ላይ፡፡ ፕሮፌሰር ኬትሊን ሆል ጄሚሰን፡፡ መፍትሄዎቿም በሚዲያና ምርጫ ስነምግባሮች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡ ያው ያወገዘቻቸውን ነገሮች ሁሉ የማቃናት ዓላማ እንድንሰንቅ፣ ነቄ እንድንሆን፣ ስለ ሀገርና ስለመጪ ትውልዶች አስበን በእውነት አርበኝነት የቆሸሸ ፖለቲካችንን ለማጽዳት በጋራ እንድንሰለፍ ነው፡፡ መልዕክቷ፡፡
ለመደምደም ራሱን የቻለ ጥልቅ ጥናት ቢጠይቅም – ስናየውና ስንጋተው የኖርነውን በጥቅሉ ብንመዝነው ግን – የኛን ፖለቲካ ጠቅልሎ በሚዘውረው በጣዩ መንግሥታችን ደረጃ – ፖለቲካው – በአሜሪካና ሌሎች ምዕራባዊ ዲሞክራሲዎች በሚነገርለት መልኩ – ከፍተኛ አንጡረሃብት በፈሰሰባቸው ባለሙያዎችና የሚዲያ አውታሮች አዝማችነት እየታገዘ ህዝብን እንዳሻው ወደሚያታልልበትና ወደሚያወናብድበት ግዙፍ የብቃት ደረጃ ተሸጋግሯል ለማለት ቢከብድም – በእኛም ሀገር ግን የመንግሥት አንጡረሃብቶችና ሚዲያው በአጠቃላይ በሥልጣን ላይ ላሉ ተረኞች የ24 ሰዓት የፕሮፓጋንዳ አውታር ሆኖ እያገለገለና – ብዙዎችንም ምርኮኛው አድርጎ እንዳስቀረ ግን ብዙ ምርምር የሚያሻው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡
የእኛም ፖለቲካ ድብን ብሎ ነው የቆሸሸው፡፡ እኛ ጋር ግን መቆሸሽ ብቻ አይደለም፡፡ የሚባላ ፖለቲካም ነው ያለን፡፡ “African politics is not only dirty it is a politics that kills!” ብሏል አንዱ አህጉራችንን በአንድ ቅርጫት ከትቶ ሲደመድመን፡፡ ያናድደኛል እንዲህ ያለው ተናጋሪ፡፡ በጋራ መሰደብ ቢያስከፋም ከእውነታው ብዙ በመራቅ ግን የሚታማ አይመስለኝም፡፡ ፖለቲካችን መቆሸሹ ብቻ አይደለም፡፡ የቆሸሸው ፖለቲካችን በደም ይነፃ ይመስል ካመት ዓመት ብዙ የደም ዋጋ ይገበርለታል፡፡ እስካሁን ግን ተቀናቃኞችን ሲያፀዳ እንጂ – የራሱ ጉድፍ ሲፀዳ አልታየም፡፡ የፖለቲካችን ቆሼ የብዙ ሳንካዎቻችን ምንጭ ነው፡፡ ገና ከሌሎች የሚጋቡብን ብዙ ሳንካዎች፣ ብዙ ቆሼዎች ይጠብቁናል፡፡ ፈጣሪ ፖለቲካችንን ያንጻልን፡፡ እንድናነጻ ልቦናችንን ያንጻልን፡፡ ለእውነት፡፡ ለፍትህ፡፡ ለእኩልነት፡፡ ለማሰብ፡፡ ለመተሳሰብ፡፡ ለትውልድ ለመመልከት፡፡ ያነሳሳን የኢትዮጵያ አምላክ፡፡
ደራሲዋን ከልብ አመስግኜ አበቃሁ፡፡ መልካም ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic