>

ከፍተኛ የጥንቃቄ መረጃ‼️ ወራሪው የሱዳን ጦር ወደ መተማ መስመር ታንክ አስጠጋ...!!! (ሙሉነህ ዮሐንስ)

ከፍተኛ የጥንቃቄ መረጃ‼️

ወራሪው የሱዳን ጦር ወደ መተማ መስመር ታንክ አስጠጋ…!!!
ሙሉነህ ዮሐንስ
*…ከምድረገነት ወደ መተማ የሚወስደው አስፓልት ደርሰዋል!
*…የወረሩት መሬት ላይ መንገድና ካምፕ እየሰሩ ነው!

ወራሪው የሱዳን ጦር አሁንም ተጨማሪ የኢትዮጵያን መሬት እየገፋ እየገባ ነው። በመተማ በኩል ያለው የደለሎ መሬት ቁጥር አምስት አካባቢ የሰሎሞን ካምፕ በሚባለው ሰፊ የእርሻ መሬት ላይ በትናንትናው እለት ሱዳኖች ተኩስ ከፍተዋል። በዚሁ ቁጥር አምስት በኩል የወራሪው ሃይል በከባድ መሳሪያ እና ፈጣን መኪኖች ላይ ታግዘው በከፈቱት ተኩስ ከምድረ ገነት (አብደራፊ) ከተማ ወደ መተማ መስመር የሚመጣውን የአስፓልት መንገድ ለመቆጣጠር ግማሽ ኪሎ ሜትር ያክል ብቻ ነው የሚቀራቸው።
ይህም ማለት ሱዳኖች በታችኛው አልፋሽካ ብለው በሚጠሩት ከእኛው የጓንግ ወንዝ ተሻግረው ወደ ሰላሳ ኪሎ ሜትር ያክል የኢትዮጵያን ግዛት ተቆጣጥረዋል። በላይኛው በኩል በምድረ ገነት ከተማ አቅጣጫ ደግሞ ሱዳኖች የእኛዋን ሰላም በር ከተማ ሲቆጣጠሩ በአማካኝ ከአርባ ኪሎ ሜትር በላይ የኢትዮጵያን ወሰን ገፍተው ወረዋል።
ሌላው ትኩረት የሚያሻው ከመተማ ማዶ ባለችው በሱዳኖቹ ገላባት ከተማ በኩል የሱዳን ሰራዊት ታንክ እያስጠጋ መሆኑ ታውቋል። ይህ እጅግ ትኩረት የሚሻ እና አፋጣኝ የመንግስትን ቅድመ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው።
ከአሁን ቀደም እንዳስጠነቀቅነው ወራሪው የሱዳን ሰራዊት በወረራቸው ይዞታችን ላይ ሁለት ትላልቅ አዲስ የመንገድ ስራ እና የወታደራዊ ካምፖች ምስረታ ላይ ይገኛሉ። ከምስሉ እንደሚታየው ስራውን በይፋ እያቀላጠፉ ነው።
ከሑመራ እስከ መተማ ከ400 ኪ.ሜ. በላይ እርዝመት ሲኖረው ከመተማ እስከ ቋራ ደግሞ ተጨማሪ ወደ 200 ኪ.ሜ. ይርቃል። በጥቅሉ ከሑመራ እስከ ቋራ ባለው የ600 ኪ.ሜ. እርዝመት ባለው ድንበራችን ላይ ሱዳን ከሃያ እስከ አርባ ኪ.ሜ. ወሰናችንን ጥሳ ገብታለች። ስላደረሱት ሰብአዊ፣ ቁሳዊ እና መሰል ጥቃቶች ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ ከዘገብናቸው መረጃውን ማግኘት ይቻላል። ይህንን መሰል መረጃ እየተከታተልን ለህዝብ ይፋ የምናደርገው እና የምናጋልጠው በቀጣይነት ለማይቀረው የሉአላዊነት ማስከበር እርምጃ ማስረጃው በሰነድነት እንዲያዝ ጭምር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት፣ ተቃዋሚ እና የሚዲያ አካላት እስከ አሁኑ ድረስ ድንበሩ ድረስ ዘልቀው ሄደው ተጎጅውን ሕዝባችንን አልጎበኙም ድጋፍም አላደረጉም።
ትኩረት ለድንበራችን!
የተደፈረው ሉአላዊነታችን ይከበር!
Filed in: Amharic