ከዴሞክራሲ ውጪ ያለውን መንገድ ደጋግመን ሄደንበት ደጋግመን ወድቀንበታል!
ዳንኤል ኪባሞ (ዶ/ር)
ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ብዙ ጥፋቶች ደርሰዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፡፡ በቅርቡ ደግሞ አገራችን እንደገና ተመልሳ ወደ ጦርነት ገብታ በትግራይ ክልል በርካታ ወገኖቻችን ሞተዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ መጠነ-ሰፊ የንብረት ውድመትም ደርሷል፡፡ በሕወሓት አክራሪ አመራር መሪነት በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የደረሰው የክህደት ተግባርም በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተቃጣ አደገኛ ድርጊት ነው፡፡ ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉት አገሪቱ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ ስንመለከትም፣ አሁን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቀውሱ ረገብ ያለ ቢመስልም ችግሩ ከስረ መሠረቱ ስላልተወገደ እንደገና ጊዜና ሁኔታ እየጠበቀ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡
የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በየደረጃው ችግሮቹን ሊቀርፉ የሚችሉ እርምጃዎችን እንወስዳለን ብለዋል፡፡ ይህም ሁልጊዜ የሚባል ነገር ነው፡፡ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ያሉ አመራሮች ስብሰባዎችን እያካሄዱ ነው፡፡ በእርግጥም ቁርጠኝነቱ ካለና ችግሮቹ ተለይተው እየተቀረፉ የሚሄዱ ከሆነ ቀውሱ ተመልሶ ላይመጣ ይችላል፡፡እንደተለመደው መዘናጋት የሚታይ ከሆነ ግን ቀውሱ ተመልሶ የማይከሰትበት ምክንያት የለም፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ትልቁ ስጋት እሱ ነው፡፡ በአገራችን የመንግሥት አመራሮች ስብሰባ ተቀመጡ፣ ግምገማ እየተደረገ ነው፣ የተሐድሶ እርምጃ እየተወሰደ ነው ወዘተ… ሲባል ሕዝቡ እምብዛም ተስፋ የማያደርገው በቂ ልምድ ስላለው ነው፡፡ ከስብሰባ፣ ግምገማና ተሐድሶ በኋላም ነገሮች ተመልሰው ባሉበት እየረገጡ፤ በሕዝቡና በመንግሥት መካከል ያለው መተማመን እየተበላሸና እየጠፋ መጥቷል፡፡
እንደሚታወቀው ችግሮቹ የተከማቹ ናቸው፡፡ በአንድ ጊዜ ሁሉም ችግሮች ከስር መሠረታቸው ይፈታሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ የይስሙላና የላይ ላዩን ብቻ አይቶ መሄዱ ዋጋ የለውም፡፡ ችግሮቹን ጊዜ ወስዶ ከመሠረታቸው መፍታት ከተቻለ ተስፋ ያሳድራል፡፡ ለአንድ ሰሞን ብቻ አውርቶ ቸልተኝነት ከታየ እንደገና ሊያገረሽ ይችላል፡፡ ይህም ተደጋግሞ የታየ ነገር ነው፡፡
ቅሬታ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች መካከል አሁንም የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቧል፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ያሉ አካላት የፖለቲካ ተሳትፎ ተገድቧል፣ የሲቪል ማኅበራት እንቅስቃሴ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በሚፈለገው ደረጃ መንቀሳቀስ አልቻሉም፣ የፍትሕ ሥርዓቱ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ሆኗል የሕግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ሰፍኗል፣ አሁንም አንድ ገዥ ፓርቲ የሁሉም ችግሮች መፍትሔ አመንጪ ነኝ ብሎ ራሱን ሰይሟል የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ በቁርጠኝነት ማስተካከል የሚገባው እነዚህን ሕዝብ ለዘመናት ሲጠይቃቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ነው፡፡ የመንግሥት አካላት በሕዝብ በኩል የሚቀርቡ ጥያቄዎችን አያውቋቸውም አይባልም፡፡ በሚገባ ያውቋቸዋል፡፡ ቁርጠኝነት ነው የጠፋው፡፡
ግልጽ መሆን ያለበት ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ አደገኛ ነው፡፡ የደረሱት ችግሮች ትምህርት ሊሆኑ ይገባል፡፡ የሚማር ከተገኘ የኢሕአዴግም ሆነ የሕወሓት አወዳደቅ ትልቅ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡
በፓርቲዎች መካከል ክርክሮች፣ ፍትጊያዎች እና ፉክክሮች መኖራቸው በራሱ መጥፎ ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ ነገሮች መልካም ነገሮች ሊወጡ የሚችሉበት ሁኔታ አለና ነው፡፡ የፓርቲዎች ፉክክር ውጤት ሊያመጣ የሚችለው ግን በሰለጠነ መንገድ እና በእኩልነት መንፈስ የተካሄደ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተደጋግሞ እንደሚባለውና እውነትም እንደሆነው ባለ ብዙ ዘውግና ሃይማኖት አገር ናት፡፡ ሰፊ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶችም አሉ፡፡ ስለሆነም እነዚህን ሁሉ ልዩነቶች በአግባቡ ማስተናገድ የሚቻለው በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ መሆኑን ከምር መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ከዴሞክራሲ ውጪ ያለው መንገድ ለኢትዮጵያ የጥፋት መንገድ ነው፤ ከዚህ ቀደም የመጣንበት ሁኔታ በግልጽ የሚያስተምረንም እሱን ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሁሉንም በእኩል ዐይን እስካየ ድረስ አምባገነን መሪ ቢኖር መልካም ነው ሲሉ ይደመጣል፡፡ ቻይናና ሩሲያም እንደምሳሌ ሲቀርቡ እናያለን፡፡ በአገራችን የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ብዙ አድናቂዎች ያሏቸው ይመስላል፡፡ የቻይናና የሩሲያ ፈለግ ግን ለኢትዮጵያ ፈፅሞ የማይሆን ነገር ነው፡፡ ያለው የዘውግ፣ የሃይማኖትና የሐሳብ/ትርክት ልዩነት ዴሞክራሲን የግድ የሚል ነው፡፡ የሚያዋጣው ጠንካራና ዘመናዊ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መገንባት ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ፉክክር መጠላት የለበትም፡፡ ዋናው ነገር ፉክክሩ ሕግ እና ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ መካሄድ መቻሉ ነው፡፡
ብሔራዊ መግባባት
በአገራችን ስለ ብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት ብዙ ተብሏል፡፡ እውነትም ብሔራዊ መግባባት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ እንኳን በአገር ደረጃ በቤተሰብም ደረጃ በሁሉም ነገር አንድ ዓይነት መግባባት ላይኖር ይችላል፤ የሚቻልም አስፈላጊም አይደለም፡፡ ነገር ግን በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገርና በመመካከር መሥራት ይቻላል፡፡ ብሔራዊ መግባባት ስባል ልዩነቶችን ቀስ በቀስ እየፈቱ አብሮ ለመሥራት ወደፊት ለመራመድ የሚያስችል ሒደት ነው፤ ብዙ ውይይች፣ ክርክሮችና ሰጥቶ መቀበሎችን የሚጠይቅ ሒደት፡፡ ብሔራዊ መግባባት በእያንዳንዷ ጉዳይ ላይ ምንም ሳይቀር ሙሉ ስምምነት ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ የሚታየው ትልቁ ስህተት እሱ ነው፡፡ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ያለው ውይይት እና ንግግር እያደረጉ የጋራ ወይም ተቀራራቢ አቋም መያዝ ያስፈልጋል፡፡
መንግሥት በሕገ መንግሥት የተፈቀዱ/የተረጋገጡ የሕዝብ መብቶችን ሥራ ላይ የማዋል ኀላፊነት አለበት፡፡ ዜጎችም እንደ ዜጋ ሥርዓት እንዲከበር የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ይገባናል፡፡ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ሐሳብን መግለጽ፣ ሰልፍ ማድረግና ጥያቄ ማቅረብ ሕገ መንግሥቱ ይፈቅዳል፡፡ ይህንን በየሰበብ አስባቡ መከልከል የሕግ የበላይነትን መሸርሸር ማለት ነው፤ ሕገ መንግሥታዊነት እናዳያብብ እንቅፋት መፍጠር ነው፡፡ ፓርቲዎችም መንግሥትም ለዚህ ኀላፊነት አለባቸው፡፡ በመርህ አንድ ነገር እየተነገረ በተግባር ግን ሌላ ነገር መፈፀም ያስከተለውን ውጤት እያየነው ነው፡፡ ይህ ነገር ካተሻሻለ ቀውሱ እንደገና ተባብሶ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መብቶችን ለመከልከል የሚነሱ የመንግሥት ኀላፊዎችን የመገሰጽ እና የእርማት እርምጃ የመውሰድ አሠራር መኖር መቻል አለበት፡፡ ተጠያቂነት መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የተረጋገጠ በመሆኑ እሱ ይከበር ማለት “ሕገ መንግሥቱ ችግር አለበት፣ ይሻሻል ወይም ይለወጥ” ብሎ ሐሳብን በነጻነት መግለጽን ይጨምራል፡፡ ስለ ሕገ መንግሥት መለወጥ ወይም መሻሻል አስፈላጊነት መከራከር መብት መሆኑን የመንግሥት አካላት በሚገባ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ እንደ ወንጀል ሲታይ እንታዘባለን፡፡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ራሱን በሚመለከት በነጻነት ሐሳብን መግልጽ በሕገ መንግሥት የተረጋገጠ መብት ነው፡፡
በጥቅሉ ማለት የሚቻለው፣ የኢትዮጵያ መድህን ዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ከዴሞክራሲ ውጪ ያለው አማራጭ ለጊዜው መፍትሔ ቢመስልም ለአገሪቱ ህልውና እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሲባል ከሕግ ውጪ የሆነ፣ ማንም እንደ ፈለገ የዜጎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥልበት ነገር ነው ማለት እንዳልሆነ ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የሚካሄድ ነገር ነው፡፡ ሕጉ ደግሞ ለሁሉም እኩል የሚሠራ መሆን ይገባዋል፡፡
ለዴሞክራሲ መድረስ?
“ኢትዮጵያዊያን ለዴሞክራሲ አልደረስንም” የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እነ መንግሥቱ ኀይለ ማርያምን የሚናፍቁ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም አምባገነን መሪ ቢሆኑ እንደሚመርጡ የሚናገሩ እና የሚጽፉ ሰዎችም አሉ፡፡ ከለውጡ ማግስት የመንግሥት ቀንደኛ ደጋፊና ሹመኛ የነበሩት እና በኋላ ተመልሰው ሥርዓቱን አምርረው የሚተቹት እነ ብርሃነ መስቀል ሰኚ እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮ/ል መንግሥቱም የሚበልጡ አምባገነን ቢሆኑ እንደሚመርጡ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በበኩላቸው ከአገሪቱ ሕዝብ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው በገጠር የሚኖር፣ ድሃ እና እምብዛም ያልተማረ በመሆኑ በእንዲህ ዓይነት ኅብረተሰብ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስር ሊሰድድ አይችልም፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ዕውን ለማድረግ ኢኮኖሚው የግድ ማደግና መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ አለበት ሲሉ ይደመጣል፡፡ ይህ እንግዲህ በፖለቲካል ሳይንስ አስተምህሮ የዘመናዊነት ንድፈ ሐሳብ (modernization theory) የሚባለው ነው፡፡
ሆኖም ይህን ንድፈ ሐሳብ እነ ሕንድ ፉርሽ አድርገውታል፡፡ ሕንድ ያን ሁሉ ሕዝብ (አሁን በሕዝብ ብዛት ቻይናንም እየቀደመች ነው) እና ያን ሁሉ ልዩነት ይዛ፤ ግን ደግሞ ታዳጊ ኢኮኖሚ ይዛ “የዓለማችን ትልቋ ዴሞክራሲያዊት አገር” ለመባል በቅታለች፡፡ የሕንድን ህልውና የጠበቀው ዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ሕንድ እንደ ቻይና ኢዴሞክራሲያዊ መሆን እንደማይቻላት እና ኢዴሞክራሲያዊ ሆና ያን ሁሉ ልዩነት ማስተናገድ እንደማትችል የሕንድ ልኂቃን አምነው ዴሞክራሲያዊት አገር በመገንባታቸው፤ ዛሬ ሕንድ ብዙ የቤት ሥራዋን ያጠናቀቀች ምሳሌ ልትሆን የምትችል አገር ሆናለች፡፡
በዚህ ወቅት በፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ዘንድ ማዕከላዊ ቦታ የያዘው አመለካከት ከፍ ያለ የፖለቲካ፣ ዘውግና የሃይማኖት ልዩነት ባላቸው አገሮች (highly divided societies) ውስጥ የተሻለው ጎዳና ልዩነትን በአግባቡ ሊያስተናግድ የሚችል እና በየጊዜው ራሱን እያረመ ሊሄድ የሚችለው ዴሞክራሲያዊ አማራጭ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ውጪ መሆን አትችልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ አልደረሰም የሚሉት ሰዎች አንድም ከነጻነት ይልቅ ሰላምና መረጋጋት ይሻለናል የሚሉ ነገር ግን ደግሞ አምባገነናዊ አገዛዝ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሊያረጋግጥ እንደማይችል በቂ ግንዛቤ የሌላቸው፤ አልያም አምባገነናዊ አገዛዝ ሰፍኖ እነሱ ከሥርዓቱ በጊዜያዊነት ተጠቅመውና ፍርፋሪ ይዘው መሸሽ የሚፈልጉ በላተኞች ናቸው፡፡ ኅሊናው በአግባቡ የሚሠራ ኢትዮጵያዊ አምባገነንነትን እንደ አማራጭ ሊያቀርብ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል ከተፈለገ ያላት ብቸኛ አማራጭ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ ነው፡፡