>
5:29 pm - Sunday October 10, 0894

"አሥርቱ ትእዛዛት - ለኢትዮጵያውያን"  (መስፍን ማሞ)

“አሥርቱ ትእዛዛት – ለኢትዮጵያውያን”

 መስፍን ማሞ

 

ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ከሰባ  ዓመት በፊት “ታሪክና ምሳሌ”  የተሰኙትን ተከታታይ መፃህፎቻቸውን ሲፅፉ እዛ ዘመን ላይ ሆነው ለዛሬው ትውልድ ያሰቀመጡትን ክቡር፤ ታላቅና  ቅዱስ የሆኑትን የኢትዮጵያዊነት /የትውልድ/ መርሆዎች እነሆ እንዳለ ያለ ማብራሪያ እናወርዳለን።የትውልድ መምህሩና ረቂቁ  የጥበብ ሰው ከበደ ሚካኤል እንዲህ  ይላሉ፤
እኛ ኢትዮጵያውያን ባሁኑ ጊዜ በግድ ልንከተለውና ልንፈፅመው  የሚገባን ዐሳብ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው።
አንደኛ ፤- ኢትዮጵያዊ የሆንህ ሁሉ ሰንደቅ ዓላማህ አገርህና ነፃነትህ የሚጠቁበትን መንገድ ለማስወገድ፤ወይም ደግሞ እነሱ የሚጠቀሙበትን ሥራ ለመፈፀም ብለህ  በሞትህ ጊዜ በሰማይና በምድር  ስምህ በወርቅ ቀለም የሚፃፍበትን የሰማዕትነት ሥራ መስራትህን ልብህ ተረድቶ ደስ ይበለው።
ሁለተኛ ፤- አገርን መውደድ ማለት አገርህ የምትጠቀምበትንና የምትከብርበትን ሥራ መሥራት ማለት ነው።
ሶስተኛ ፤- አገርህንና ወገንህን  የሚያስንቅ ወይም የሚጎዳ ሥራ ከመሥራት መሞት ይሻልኻል።
አራተኛ ፤- እኛ ኢትዮጵያውያን የምንሠራው ሥራ መልካም ቢሆን አገራችን ኢትዮጵያ እንደምትከብር፤  የምንሠራው ሥራ መጥፎ ቢሆን  ግን እንደምትዋረድ አትርሳ።
አምስተኛ ፤- ኢትዮጵያ አገርህ  ከሌሎቹ ከማንኛዎቹም አገሮች ሁሉይልቅ የምትበልጥብህ መሆንዋ  ቀንም ሆነ ሌሊት በዐሳብህ ውስጥ ሳይረሳና ሳይዘነጋ ተፅፎ ይኑር።
ስድስተኛ ፤- ማንኛውም የውጪ  አገር ሰው ለተወለደባት አገሩ የሚያስብላት መልካም ዐሳብ ወይም  የሠራላት መልካም ሥራ ሲነገር በሰማህ ወይም ተፅፎ ባየህጊዜ አንተም ደግሞ እንደዚሁ ይህንኑ  ያህል ላገርህ ለኢትዮጵያ  ልታስብላትና ልትሠራላት የሚገባህ መሆኑን  ዕወቀው።
ሰባተኛ ፤- አንድ ኢትዮጵያዊ  ሲበደልና ሲጠቃ ባየህ ጊዜ የተበደለችውና የተጠቃችው እናትህ  ኢትዮጵያ መሆንዋን ተረዳው።
ስምንተኛ ፤-  ኢትዮጵያ አገርህ በዕውነት ትልቅ ሳትሆንና ወንድሞችህምኢትዮጵያውያን ሁሉ ሳይደላቸው አንተ ብቻህን የምታገኘው ደስታ ገንዘብና ተድላበህልም እንደተገኘ  ወርቅ መና ባዶ ሆኖ የሚቀር  መሆኑን ልብህ አይዘንጋው።
ዘጠነኛ ፤- ብዙ ገንዘብና ብዙ ርስት ከማግኘት ይልቅ ለአገሩ ትልቅ ሥራ የሠራላትሰው ስሙ ለዘለዓለም
በታሪክ ሲጠራ ይኖራል።
አስረኛ ፤- ሌሎቹ የዓለም ነገሥታት ከደረሱበት የሥልጣኔ ደረጃ አገራችን ኢትዮጵያ በቶሎ እንድትደርስ እኛ  ኢትዮጵያውያን ሁሉ ማሰብና መጣጣር ይገባናል።ድካማችንምና ትጋታችንም በተለይ ለዚሁ ዐሳብ ብቻ እንዲሆን ያስፈልጋል።…በማለት ፅፈዋል ቀደምቱ የኢትዮጵያሊቅ ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል።
****
አንተ ወጣት ትውልድ ሆይ! እነሆ ቀደምቶችህ ያስቀመጡልህ አሥርቱ የኢትዮጵያዊነትህ  ትዕዛዛት እኒህ ናቸው። በእዝነ  ልቡናህ አኑራቸው፤ ማተብህ  ናቸውና። በመንገድህ ሁሉ ተከተላቸው፤ መብራትህ ናቸውና። ከዘመነ ፍዳ መገላገያህ ናቸውና  ተግብራቸው።  አገርህንና ወገንህን መታደጊያ ናቸውና ተመራባቸው።  የነፃነትህ አብሳሪ ናቸውና ከፍ  አርገህ ያዛቸው። ኢትዮጵያና  ህዝቧ ባንት መስዋዕትነትና መራራ ትግል ከወራሪዎችና ዘረኞች፤  ከመዝባሪዎችና ነፍሰ ገዳዮች ነፃ  ይሆናሉ፤ ድል ያለመሥዋዕትነት እንዳይኖር ታውቃለህና!! [መስፍን ማሞ ተሰማ – ፎቶ፥ ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል]
Filed in: Amharic