>
5:13 pm - Saturday April 18, 1542

ያልተዘመረላቸው ጸረ ፋሽስቱ ጀግና — አለቃ መርሻ ወልደ ማርያም  (አቻምየለህ ታምሩ)

ያልተዘመረላቸው ጸረ ፋሽስቱ ጀግና — አለቃ መርሻ ወልደ ማርያም 

አቻምየለህ ታምሩ

በተለያዩ ዘመናት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡትን የባዕዳን ወረራዎች በመከላከል ረገድ  የኢትዮጵያ ጳጳሳትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ግንባር ቀደም ተሳትፎ ነበራቸው። የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል ከአርባ ዓመት በኋላ ፋሽስት ጣሊያን  የፈጸመብንን ወረራ ለመጋፈጥ  ቀድመው ከተነሱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መካከል  ሊቁ  አለቃ መርሻ ወልደ ማርያም ግንባር ቀደሙ ነበሩ።
አለቃ መርሻ ወልደ ማርያም  በ1862 ዓ.ም. ጎጃም ደብረ ወርቅ የተወለዱ ሲሆን በተማሪ ቤት ከኖሩ በኋላ በቤተ ክህነት ሹመት እየተዘዋወሩ በማገልገል ላይ ሳሉ የየካ ሚካኤል አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት በተወለዱ በሰባ ዘመናቸው ፋሽስት የአድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል  በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሲፈጽም በመጣ ጊዜ  ከአርበኞች ጋር አብረው ለመዝመት ፈልገው «ልዝመት» ብለው ቢጠይቁም የሰውነታቸው መሸምገል በግልጽ ይታይ ነበርና «አብሬ ልዝመት» የሚለው ጥያቄያቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ አዝነው ነበር ይባላል። ኋላ ላይ ፋሽስት ማይጨው ላይ ድል አድርጎ ሚያዚያ 27 ቀን አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ግን በጠላት መገዛትን በፍጹም መቀበል ስላልቻሉ ዱር ቤቴ ብለው ካርበኞች ጋር ፋሽስትን ለመፋለም ዝግጅት በማድረግ ላይ እንዳሉ ተደረሰባቸው።
በዚህ ጊዜ ማርሻል ባዶግሊዮ ሐምሌ 10 ቀን 1928 ዓ.ም. በሶስት የፋሽስት ሻለቆች  የሚመራ የጠላት ጦር ወደ ቤታቸው ልኮ አዛውንቱን አለቃ መርሻን «ትጠራለህ» ብለው አስረው እንዲያቀርቡለትና  እጅ አልሰጥም ብለው አሻፈረኝ ካሉ ግን ያለማመንታት አሰቃይተው እንዲገድሏቸው ትዕዛዝ ሰጠ።  በዚህ ጊዜ ወደ በርሀ ለመውረድ ዝግጅት ያደርጉ የነበሩት አለቃ መርሻ ጠላት ቤታቸውን  ከቦ «ትጠራለህ» ሲላቸው  አብረዋቸው ለነበሩት ተከታዮቻቸው ደብቀው ካስቀመጡት ሽጉጥ አንድ፣ አንድ አድለው እንዲከላከሉ ትዕዛዝ ሰጡ። ይህን ካደረጉ በኋላ በቤታቸው ዙሪያ ጦርነት ሲጀመር ግማሹ የሳቸው ሰው ሲሸሽና ግማሹ ደግሞ አደፈጠ።  በዚህ መሃል ጠላት ግቢያቸውን ሰብሮ ሊማርካቸው አልያም አሰቃይቶ ሊገድላቸው ሲገባ  አለቃ መርሻ  ግን በፋሽስት ከመማረክ እንዳባጉናና ማይጨው ላይ ቀድመዋቸው  እንደወደቁት  ጀግኖች ለመዋል  በመነሳት፤
ተምሮ ተምሮ፡ ካልሰበሰቡት፣
እንዴት ያሳዝናል ሲባክን እውቀት፤
ወግጅልኝ ድጓ፣ ወግጅልኝ ቅኔ፣
ወንዶች በዋሉበት እውላለሁ እኔ፤
ብለው ከፎከሩ  በኋላ  ሶስቱን የፋሽስት ሹማምንት ጥለው  ልክ እየሱስ ክርስቶስ በአሳዳጆቹ  እጅ በሞተባት ዓርብ ዕለት በብዙ ጥይት ተመተው የሞት ጽዋን ተቀብለዋል። ጀግናው አርበኛ አለቃ መርሻ በዚህ አኳኋን  ምድራዊ ሕይዎታቸውን ላገራቸው መስዕዋትነት አድርገው ቢቋጩትም  በሰባ ዘመናቸው ያደረጉት ተጋድሎ ግን በኢትዮጵያ ጀግኖች የታሪክ አምድ ላይ ጌጥ ሆኖ ለዘላለም ደምቆ ይኖራል።
ለጀግናው አርበኛ አለቃ መርሻ  በወቅቱ ከተገጠሙ የመታሰቢያ ግጥሞች መካከል  የሚከተሉት ይገኙበታል፤
አለቃ መርሻ አይፈራም እጁ፣
ጠላት ሲጋበዝ እንደወዳጁ፣
ገስግሰው ሄደው እንደጎመጁ፣
በሽጉጥ ጠርሙስ አንዳንዱን ፈጁ፤
መርሻ ቢያጠጣው የሽጉጥ ጠላን፣
ወዲያው ወደቀ ግብዙ ጣሊያን!
እነ አለቃ መርሻ የወደቁላት ኢትዮጵያ ሕዝብን ክደን ለሕዝብ ደኅንነት ጠላቶች መስገድና በሹመት መዋረድ አንሻም ብለው ከሚጠብቋቸው ተከያዮቻቸው በፊት የሕዝብ ደኅንነት ጠላቶችን ተፋልመው ለመውደቅ  የቆረጡ  የዘመኑ ዳግማዊ አለቃ መርሻዎች የት ይሆን ያሉት?  ስለምንስ  ይሆን የሚኖሩት?
Filed in: Amharic