>

“የቴዲ አፍሮዋ ኢትዮጵያ እና የፊድራሊስቶቹ ኢትዮጵያ ...!!!” (ዋጋዬ ለገሰ)

“የቴዲ አፍሮዋ ኢትዮጵያ እና የፊድራሊስቶቹ ኢትዮጵያ …!!!

ዋጋዬ ለገሰ


ከቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ላይ የተገኘ በራሪ ወረቀት እያየሁ ነው። የከንቲባውና የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ተማሪዎች ምስል ይታያል። “ከኮንሰርቱ የተወሰነ ገቢ ለዚሁ አገልግሎት እንዲሆን ድምጻዊው ፈቅዷል” አሉኝ። ይሄን ጥምረት “Feedralist” ብዬዋለሁ። አህዳዊና ፌዴራላዊ በሚል አጉል ብሽሽቅ ወስጥ ለተዘፈቀችው ስራ ፈት ሀገር፣ “federalism” የተሰኘ ፍልስፍና ይዞ መጥቷል። ይሄ ጥምረት ፖለቲካዊ ነው። በፌዴራላዊቷ ዋና ከተማ የተደረገ ፊዴራላዊ ጥምረት። በፌስ ቡክ የዜና አዘጋገብ፣ “አህዳዊው አርቲስት ከፌዴራሊስቱ ከንቲባ ጋር ተጣመረ!” ብለን እናስቀምጠዋ።

ወደ አዲሱ ጥምረት ከመግባታችን በፊት ግን፣ ስለከንቲባው ፌዴራላዊት ከተማና ስለ ድምጻዊው አህዳዊት ሀገር አንዳንድ ነገሮች እንጨዋወት።

የከንቲባው ከተማ”

ተዋወቃት፣ የፌዴራላዊው መንግስት መናገሻን፣

እህል ተነቅሎ ኮንዶሚኒየም የሚተከልባት፣ በ2009 ዳታ መሰረት ከ896 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 690ናው የግል የሆነባት፣ ከ1180 መዋእለ ህጻናት 216ቱ ብቻ የመንግስት የሆነባት፣ ወላጆች ለትምህርት ቤት ወጪ ከእለት ጉርስ ቀንሰው የሚቆጥቡባት፣ ቴክስት ቡክ በነጋዴ የሚቸበቸብባት፣ አከራይ ከብርሃኑ ጁላ በላይ የሚፈራባት፣ ጫት ቤት ከፋርማሲ የሚበዛባት፣ ከጫት ቀረጥ የማትሰበስብ፣ ወጣቱ ሞፈሩን ጥሎ ያለፍተሻ “ለስራ” ብሎ የሚሰደድባት፣ ሴትን የሚያህል ክቡር ፍጥረት ባሬላ ተሸክሞ የሚያድርባት፣ ደላላ የሚያሽከረክራት፣ የታክሲና የዳቦ ቤት ሰልፍ የሚያደናግርባት፣ ቡና እና ጤፍ እንደኢምፖርት ሸቀጥ ሰማይ የነኩባት፣ ባለስጋ ቤት ኮንትራክተር ሆኖ ኢንጂነሩን ቀጥሮ የሚያሰራባት፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በሚዘገንን ብር የግለሰብ ህንጻ የሚከራዩባት፣ ውልና ማስረጃ የግለሰብ ህንጻ ላይ ተከራይቶ ሲሰራ እያየህ ምኑን ውል ምኑን ማስረጃ አለኝ ልትል? ገቢዎች የሰበሰበውን ገንዘብ ለቢሮ አከራዮች የሚከፍልባት፣ ኤምባሲዎች የባለስልጣን ቪላ የሚከራዩባት፣ መከላከያ ሚኒስቴር አጠገብ ብላክ ማርኬት የደራባት፣ ከዩኒቨርሲቲና ከሆስፒታል በፊት ትምባሆ ፋብሪካ የገነባች፣ የከተማ እርሻን የምትጠየፍ፣ “የአፍሪካ ኩራት” ከምትለው አየር መንገዷ ስር ሰው በመኪና አደጋ እንደቅጠል የሚረግፍባት፣ ድህነት በሚንጎማለልባት መሃል ጨርቆስ ላይ ኳታርና ዱባይን የሚያጋጭ ግንባር መሬት ያላት (ከስሩ ውሃ ነው እሺ!)፣ እንቁላል ፋብሪካ የሚባል ሰፈር ውስጥ እንቁላል ፈልገህ የማታገኝባት፣፣ ለቦብ ማርሌይ ሀውልት ሰርታ ለጣይቱ ቦታ ያጣች፣ የካ፣ ለቡ፣ ኮልፌ፣ ጉለሌ፣ አባዶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ቀበና፣ ቁርጡሜ፣ ኮዬ ፈጬ፣ ጀሞ፣ ላፍቶ ወዘተ በሚሉ ስሞች ተጠራርታ እያደረች የታከለ ኡማን ኦሮሞነት ማጦዝ የሚያምራት፣ ቀላል ባቡር በሁለት ብረቶች ላይ በሚሄድበት ዘመን ይሄንን ሁሉ መሬትና ቁስ በባቡር ስም ያባከነች፣ ለንብም ለአይንም የማይሆን (በዚያ ላይ በበጋ የሚደርቅ) አበባ በዶላር ከውጪ አስገብታ የምትተክል፣ አረም በለው! ለም መሬቷን ለአደባባይና ለቆሻሻ ሰጥታ ነጭ ሽንኩርት በወርቅ ግራም የምትሸጥ፣ በሸዋ ሚልክ ሼዶች ተከብባ ወተት እንደ ጣዝማ ማር የተወደደባት፣ ቴአትር ቤቶቿን በፖለቲካ ቀፍድዳ በቴአትር ፈንታ የሰራተኞቹ ህይወት ወደ ቴአትር የተቀየረባት፣የአርብቶ አደሮችን ጉዳይ የሚመለከት መስሪያ ቤት አዲስ አበባ ላይ የሚቀመጥባት አዝናኝ ከተማ ናት፣

ሲጠቀለል፣ አዲስ አበባ ማለት፣ ሰገጤ፣ ከእውቀት ጽዱ፣ ክሉለስ፣ ግሪዲ፣ ሉዘር፣ ወዘተ ከተማ ናት ስልህ እንግሊዝኛ ቀልሎኝ አይደለም። አለ አይደል? የአፍሪካን መቀመጫ በአማርኛ ከመስደብ ቢያንስ በኢጋዲኛ ላጥረግርጋት ብዬ ነው። አሁንም ስጠቀልለው፣ እንደ ሪዮ ዲጄይኔሮ ሳኦፓውሎን ሰርቶላት የሚያሳርፋት አጥታ ነው እንጂ አዲስ አበባ ከተማ አይደለችም፣ ማክተሚያ እንጂ!

ቢሆንም ቢሆንም ይላሉ አለቃ ታከለ ኡማ ገብሩ

የአዲስ አበባን ቁልፍ እያሽከረከሩ

ቢሆንም ዋጋዬ ለገሰ ወሬ ቢያራቅቅም፣

“ቆሻሻ ነሽ” ብለው ሲንቋት አናውቅም።

“የቴዲ አፍሮዋ ኢትዮጵያ”

“የሚኒሊኳ”፣ “የሸዋዎቹ”፣ “የአማራው”፣ “የአማራውና የትግሬው”፣ “የኦርቶዶክሱ” ለሚሏት ሀገር አዲስ ስም አወጡላት። “ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ” ተባለች። በአዲሱ ስሟ የት ገባች? እዚያው ሚኒሊክ ቤተመንግስት። የት ከተማ? እዚያው አዲስ አበባ።

ገዥውም ተገዥውም፣ አህዳዊ ፍቅሬ የሚለውም፣ ፌዴራሊዝሜን ባዩም በእሷ አይጨክንም። የአዲስ አበባ ወንበር ዋጋው ውድ ነው። በእጅ አዙርም ሆነ በቀጥታ ሸገርን መዘወር የፖለቲካ ስልጣኑን መቆጣጠሪያ ቁልፍ ነው። ስለዚህ መንገስ ቢያቅት፣ ለአንጋሽነት ይፋለሙባታል። ከነጋሹም ከአነጋሹም ጋር ለመንጦልጦልም የመጀመሪያ ምርጫ ናት። ያልረባ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ትስስር ሳይዘረጋላቸው በፌዴራሊዝም ስም “ራሳችሁን አስተዳድሩ” ተብለው የተነጠሉት ክልሎችም፣ ወይ እሷን ለመምሰል አሊያም የእሷ ቁራኛና ብክነት ማራገፊያ ከመሆን ውጪ ያየንባቸው መልክ የለም። ሙስጠፌ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ግዴታ ቦሌ ይመጣል። በከርካሳ ፎከር ጅግጅጋን ተሰናብቶ፣ በድሪም ላይነሩ አዲስ አበባን ይለቃል። ይህቺ ቀላል ምሳሌ፣ “አህዳዊ ጠላቴ” የሚሉትንም ሆነ “ፌዴራሊዝሙ ሰው አደረገን” ባዮቹን የምታፈርጥ ድጥ ናት። ያልተማከለ ባዩን ሁሉ እዚህችው አሳዛኝ ከተማ ላይ ተማክሎ ታገኘዋለህ።

“የትግራይ ነጻ አውጪ” በሚል ስም ትግልህን ብታቀጣጥልም ድልህን ለማብሰር ግን መቀሌን ሳይሆን አዲስ አበባን እንድትመርጥ በስውር ታዝዘሃል። “ረስተነው ነበር ህዝባችንን” ብለህ በታላቅ ስላቅና ድርቅና ከ27 አመታት በኋላ ለመመለስ እስክትገደድ ድረስ በሸዋ ዳቦ ሱስ ተጠልፈህ ታረጃለህ። ኰንክሪታዊውንም ሆነ ሶፍትዌራዊውን እውቀት እዚህች ከተማ ላይ አከማችተሃልና ከጉና ተራራ መመለስ ሃርድ ይሆናል። ፖለቲካዊ ክንድህን ያለ አራት ኪሎ አታፈረጥምም።

ኮሚኒስቱን ተወልደ ወልደማርያምን በሸበጥ ሸኝተህ፣ በካፒታሊስቱ ተወልደ አየር መንገድህን ይዘህ ትቀጥላለህ። ሚኒሊክን ብትጠየፈውም ወንበርህን ግን እሱ በሰራው ቤት ለመትከል ትገደዳለህ።

“ህዳር 29 የልዩነታችንን በአንድነት” ትልና ለሱርማው አዲስ አበባ ላይ ራቁት መደነሻ ቦታ ትሰጣለህ። ጂንካ ላይ ሱፍ አልብሰህ ስብሰባ ለመጥራት ትጋጋጣለህ። ሲጀመር አንድ ሱፍ የለበሰ የሱርማ ካድሬ ነፍ ራቁት የመንደሩን ህጻናት ሰብስቦ “በባህሌ አልደራደርም” ሲለኝ ጋድ መስት ቢ ክሬዚ በለው!! ራቁት ገላውን አስጎብኝተህ ዶላር ለማግኘት ትፋለጣለህ፣ ሰው እንዴት ሰውን እንደእቃ ለፈረንጅ እያሳየ ቱሪዝም ተስፋፋ ይላል? የቦዲውን ጎረምሳ ኒው ዩርክ ብትወስደው እኮ ቱሪስት ነው፣ ልብስ በለበሰ ሰው የሚደነቁና ልብስ ባልለበሰ ሰው የሚደነቁ የሁለት አለም ሰዎችን እያገናኘህ “ገቢ አገኘሁ” ትለኛለህ? ሁለቱም ለተደነቁት ለተሳቀቁት ለተገረሙት እንዴት አንደኛው ገንዘብ ይከፍላል? ለማነው የሚከፈለው? ላንተ? ላስጎብኚው? ምን ስላደረገ? ስለሰራሀቸው? ሰዎቹን እንደህንጻ ስለገነባሀቸው? የሀመር ህጻናትን ሆዳቸው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተቆዝሮ እያሳየህ ቱሪዝም ነው ትለኛለህ? የእዝን ነው እንዴ የምትቀበለው?

ሃጂ አባስ ገነሞ የሚባል አርሲ ፍሪክ ስኮላር አለልህ፤ ሲጽፍ እነ መኩሪያ ቡልቻን እነ አሰፋ ጃለታን መጥቀስ ያበዛል። ስለዚህ በጎሪጥ አንብበው። እነ አለቃ አጽሜን እነ አባ ባህሪን የምታነብበትን መነጽር ሳታወልቅ ማለቴ ነው። ሁሉም የየራሱ ኢትኖሴንትሪክ ማማ አለው። ከዚህች ማማ እስክንወርድ ድረስ እንዲችው አመዳችንን ለብሰን እንዘልቃታለን። “Islam, the Orthodox Church and Oromo Nationalism (Ethiopia)” በሚለው ከ18 አመታት በፊት የቀረበ መጣጥፉ “ኢትኒክ ኮር” ይላቸዋል፣ ትግሬና አማራን። ላለፉት 100 አመታት በሁለቱ ቁጥጥር ስር ወድቀናል ይላል።

በAndrew KORYBKO “Oromia Is Ethiopia’s Achilles’ Heel” መጣጥፍ ውስጥ ደግሞ “Triply Colonized” የምትል ትርክት ትመጣለች። ኦሮሞ ለሶስተኛ ቅኝ ግዢ ተዳርጓል እያለ ነው። ሶስተኛ ገዥ ሆኖ የመጣው ሶማሌ ነው። በርግጥ፣ የዚህኛው ጸሃፊ ጭብጥም ወደ ሀጂው “ኢትኒክ ኮር” የሚወስድ ነው። “ኦሮሞን ለማዳከም ሌላው እንዲጠናከር እየተደረገ ነው” እንደማለት ነው። ግቡም ለሁለቱ ኮሮች ስልጣን ማደላደል ነው።

“Ethnicity, Democratisation and Decentral­ization in Ethiopia: The Case of Oromia” የሚለው የመረራ ጽሁፍ ነው፡፡ ከ13 አመታት በፊት ነው ያቀረበው፤ ሲጨመቅ የስልጣንና የሀብት (ፓወር ኤንድ ሪሶርስ) ድርሻችን አልተከበረም ነው። “ኦሮሞ እንደብዛቱ የስልጣንና የሀብት ድርሻ ይኑረው” ይላል። ስልጣን ምንድነው? ሀብትስ? በአናሳው ህወሓት ተጠቅልለናል ባይ ነው። የስልጣን ድርሻ እንዴት ነው የሚሰላው? ወጥ ፎርሙላ አለው? የኢኮኖሚ ድርሻስ? አይብራራም፤ በአሲሚሌሽን አማርኛና ኦርቶዶክስ ሀይማኖት ወርሮናል ይልሃል። እዚህም ጋ ኮሩ ይመጣል።

ሁሉም ስለኮሩ ነው የሚያወሩት። ኮሩስ ምን ይላል? ስብሃት ነጋ “አማራው ነው የበዘበዘኝ” ሲል፣ አማራውም “ትግሬው በዘበዘኝ” ይላል።

ወዳጄ ፌዴራሊዝም ተብዬውም ሆነ አህዳዊ ምናምኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በብላክ ማርኬት ነው የተዘረዘሩት። እርስ በርስ የሚገበያዩ ቢዝነስ ፓርትነርስ ናቸው። ሁለቱም ትምህርት ቤት ውስጥ እንጂ መሬቱ ላይ የሉም። አንዳቸውም “ሳታማክል የምትመራ ሀገር” ሊያቀርቡልን አይችሉም። ሀገር ስትሆን ትማከላለህ፤ በቃ! ቀበሌ እንኳን ሳታማክል አትመራም። “ለምሳሌ የአሜሪካንን አወቃቀር፣ የህንድ፣ የቤልጂየም” ይሉሃል፣ ያለፔንታገን ፊርማ የኔቫዳ ከንቲባ ሲንቀሳቀስ የሚያሳየን ግን የለም። በትራምፕ ቁጣ ሽሮ ሜዳ ሲተራመስ እያየህ ዲሴንትራላይዜሽን ምን እንደሆነ ይምታታብሃል።

አለም አቀፍ ስታንዳርዱን የጠበቀ “እንትን” ከመስራት ሌላ ግብ ያለው አለ? ማነው አለማቀፍ ስታንዳርድ? ምንድነው? ሰው ነው? ቀርከሃ ነው? ቻይና ናት? አሜሪካ? ማን ነው ጣሪያ ያበጀለት? የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስን በኦሮሚኛ ነው የሚያስተምረው ባላልከኝ? የአዲግራቱማ ባዮሜዲሲኑን በትግሪኛ እየፈለጠው ነው እያልኸኝ ነው? የዳንግላው ኢንስትራክተር ጂኦግራፊን በአዊኛ እየከተከተው ነው በለኛ፤ የእኔ የፌዴራሊስት ሃይል፣ አርማህን በአሜሪካ ዴስክቶፕና ሶፍት ዌር ስታሰማምር እየዋልክ መግለጫህን “በጃፓን ቲቪ” ለማስተላለፍ በኮሪያ ካሜራ እየቀረጽክ “ራሴን በራሴ ለማስተዳደር” ስትይኝ ሳቄ ይመጣል። ቀለብ መግዣ ብድርህን በእንግሊዝኛ እየተፈራረምክ፣ ዳቦህን በሶማሊኛ ለመጉረስ ትፋለጣለህ እንዴ? ኦነግ ሆንክ ደህሚት፣ ኢህዴን ሆንክ ብአዴን ብትሸፍት በኢንተርናሽናል ጠብ መንጃ፣ ብትነግስም የአውሮፓ ሱፍህን ገጭ አድርገህ ነው፣ ፕሬዝዳንታዊ ጠቅላይ ሚኒስቴራዊ ብትለኝ ሲያደርጉ አይተህ ነው። እስቲ ፕሬዝዳንት በአማርኛ ምንድን ነው የሚባለው? በኦሮሚኛስ? የትግራይን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር ስትለኝስ? አለም አቀፍ ስታንዳርዱን የጠበቀ ሆስፒታል እንዲኖረው አይደል? ነጻነቱን በአጥንቴ በደሜ አስከብሬለት ስትለኝስ? ክላሺንኮቩን ለምን ረሳኸው? ወኔውን ከራሴ ብትለኝ መሳሪያውን ሰርቼ እንደማትለኝ እርግጠኛ ነኝ፤ ትጥቅ ትግሉ ስትለኝ ትጥቁን ራስህ እንደሰራህ አክት አታድርጋ፤ ትግሉ ነው ያንተ (እከራከራለሁ ብትል፤ ትግሉም ያንተ እንዳልሆነ ማሳመን አይከብደኝም። ወዳጄ እንኳን ለ“Castle in the Sky” ዋናውንም አፈራረሰነው የለ እንዴ?)፣ ጠብመንጃውን ተወው፤ ርእዮተአለሜ የምትለውንስ የራሴ ነው ልትል? እረፋ! ሲያድ ባሬ “ሳይንቲፊክ ሶሻሊዝም” መንጌ “ኢትዮጵያዊ ሶሻሊዝም” ሲሉህ የእኔ የእኔ ልትጫወት አማረሃ?

የፊድራሊስቶቹ ከተማ

ወዳጄ! በዚህ ሁሉ መካካል ያልከሰርነውን ጠይቀኝ። ስለዚህ ወደ እነ ታለከና ቴዲ አፍሮዋ ፊድራሊስት ከተማ እንገስግስ። ይህቺኛዋ ከተማ ኮምፓሽኔት ናት። ከሁለቱም አይዲዮሎጂስቶች ጋር አትጣጣምም። ፖለቲካውን ራቁቱን አስቀርታዋለች። ምን መቅደም አንዳለበት ያወቁ ሁለት አስተሳሰቦች የገጠሙባት ከተማ ናት። እንዲህ ሲሆን ብዙ ረብሻ አይኖርም። ተማሪ እየራበው በሚማርባት ሀገር ላይ ፖለቲካ እህል እንጂ ባንዲራ መትከል እንደሌለበት ትነግረናለች። ሀገሪቱ የሚያስፈልጋት መግቦ አሳዳሪ ነው። ለምግብ ያልዋለ ፖለቲካ በጥጋብ ይሞታል። “food is an ultimate power” ይልሃል የገባው። “የራበው ህዝብ መሪውን ይበላል” ያለው መረራ ይኸው እስከዛሬ ዱቅ ብሏል። ማንም አልነካው።

Jason Hickel “እድገት ከዚህ በኋላ መኖር የለበትም። ምክንያቱም አለም ከሚበቃት በላይ አድጋለች” ይላል። “Forget ‘developing’ poor countries, it’s time to ‘de-develop’ rich countries” በሚለው መጣጥፉ። ደሀ ሀገሮች ሀብታሞቹ ላይ ለመድረስ መጋጋጥ የለባቸውም። ሀብታሞቹ ናቸው ማቀዝቀዝ ያለባቸው ይልሃል። አካፍል አግዝ ስጥ እያለ ነው። ለባለመጋዘኑ የተላለፈ መልእክት ነው። መጋዘኑ ፖለቲkኛው ጋ ይበዛል። ባታርስም ገዝተህ አብላ። ሁሌ መሸጥህን ተው።

ከንቲባው አርሶ ማብላት እስኪችል ገዝቶ ማብላቱን አውቆበታል። መስቀል አደባባይ ላይ ከተካሄደ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ለፕሮጀክቶቹ ገቢ መጋራት የሚችልን ከንቲባ አለማድነቅ አልችልም። ያው በለመድነው የብሄር ፖለቲካ ስንመታው ደግሞ ከንቲባው የዋዛ ፖለቲከኛ እንዳልሆነ መገመት አይከብድም። ሲያዩት ቀላል ግን ብዙ አይነት ብቃቶች የሚፈልግ ስራ ነው። ከአዲስ አበባ ከንቲባ የሚጠበቅም ነው።

“የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ” እንዲቋቋም በማድረጉ ከንቲባውን አደንቃለሁ። ጉዳዩ ከተራ የምርጫ ቅስቀሳም፣ ከተለመደው የፖፑሊስትነት ወቀሳም የሚያድን ከፍ ያለ ስራ እንደሆነ አሳይቶናል። በእርግጥ ማንም ከዚህ በላይ ምርጫ መቀስቀሻ ማቅረብ አይችልም። ከሰሩም እንዲህ ልዩነት ካመጡም እንዲህ ነው። በፌዴራሊስቱ ፓርቲህ ፊድራሊስት ሆነህ መምጣት ነው።

ኤጀንሲው ቦርድም አቋቁሟል፣ “ህጻናትና ወጣት ተማሪዎች በምግብና በትምህርት ግብአት አቅርቦት ችግር ከትምሀርት ገበታ ውጪ እንዳይሆኑ የማስተባበርን የመከታተል ሀላፊነት እንደሚኖረው” ከጽ/ቤቱ የፌስቡክ ገጽ የተገኘው መረጃ ይናገራል።

ይሄ ከዘፍጥረት ጀምሮ የመንግስት ግዴታ የነበረ ግን ከመልመዳችን የተነሳ ወደ በጎ አድራጎት የተቀየረ ስራ ነው።’ እንደነገርኩህ፣ ፌዴራሊዝሙ ወይስ አህዳዊዝሙ በሚለው ክርክር ስንቋሰል እየራባቸው የሚማሩ ተማሪዎችን ታቅፈን ቀረን። የአስተማሪውስ ባይብስ ነው?

ኢትዮጵያ አሳዛኝ ሀገር ናት። ቴዲ አፍሮ ሲዘፍናት ብታስደንስም፣ ታከለ ኡማ ሲጠራት ብታስጨበጭብም ኢትዮጵያ እንባ የማይበቃት አሳዛኝ ሀገር ናት። ቱሪዝም ተብሎ በሚኒስቴር ደረጃ ከተመሰረተ ግማሽ ምእተ አመት በኋላ “የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ” የሚቋቋምባት ሀገር ነች። ለቀይ ቀበሮ ተጨንቀው ለሰው ግድ በሌላቸው ፖለቲከኞች የተሞላች ሀገር ናት። ህዝብ በንቀት ፖለቲካ የሚተዳደርባት ሀገር ናት።

ትምህርት የአንዲት ሀገር ትልቁ ሀብት ነው። ትምህርት ቤት ደግሞ ገበያው ነው። ትምህርት ቤትን ከያዝክ የማትይዘው አይኖርም። ረሀብ ትምህርት ቤት ውስጥ ምን ይሰራል? መንግስት ልኮት ካልሆነ። ብራቮ ከንቲባው በርታ! ከፊድራሊስት ሀይሉ ጋር ወደፊት!!

Filed in: Amharic