እምዬ ምኒልክ ጦሩን ሲያሰልፍ…!!!
(ጸጋዬ ገብረ መድኅን በ”ምኒልክ” ተውኔት እንደጻፈው)
ዳንኤል በቀል
…ምኒልክ ድምጹን ከፍ አርጎ በቆፈጠነ ልሣን ትእዛዝ መስጠት ጀመሩ፤ “ገበየሁ! አንተ ከኔ በስተቀኝ ከከሰም ወንዝ ማዶ ሜዳ ጓጉአን በር አርገህ፣ ከስድስቱ ሺህ ዋና የጦር አበጋዝ ሠራዊትህ ጋር፣ እስካሁን ባሳየኸኝ ጀግንነትህ ላይ ተጨማሪ ጀግንነት እንድታሳየኝ! ሒድ! እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን!
“እቴ ጣይቱ! አንቺ ከሦስት ሺህ ጦርሽ ጋር፣ እዚሁ አዲ ማህልያ ግንባር፣ ከኔው ከሠላሳ ሺህ ሠራዊት በቀኝ ደጀን ቁሚ፡፡የኢትዮጵያ አምላክ ካንቺ ጋር ይቁም እቴ፡፡
“መኰንን! አንተ በአድዋ ግንባር ግራ ጎን፣ ከስምንቱ ሺህ ሠራዊትህ ጋር፣ አዲ አቡንና ዳአሮ ተክሌን በራፍ እድርገህ፣ በነበርክበት ቀጥል፡፡ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን፡፡
“ልጄ ዘውዲቱ! አንቺ ከእቴ ጣይቱ ጦር ጋር ከኔ በስተቀኝ ቁሚ፡፡ ከእሷ ጋር ሆነሽ ለቁስለኛው ካለው መድኃኒት፣ ለጥማተኛው ካለው ውሃ ለግሺ፡፡ ጦር ዘልቆ ለሚቀድመው ጎበዛዝ ማበረታቻ፣ ጦር ሸሽቶ ፈርቶ ለሚሸሸው መገሰጫ ቃል ስጪ፡፡ ሒጂ በክብር ቁሚ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ካንቺ ጋር ይሁን ልጄ ወዳጄ፡፡
“ሀብተጊዮርጊስ፣ አንተ እዚሁ ከኔ ጎን ከሠላሳው ሺህ ሠራዊቴ ጋር አብረኸኝ ግንባር ቁም፡፡ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን፡፡
“ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ አብረኸኝ እንደቆምክ ወደፊትም አብሮ ያቆየን፡፡ አንተ ሦስት ሺህ ጦርክን ይዘህ፣ ከዋና ጦር አበጋዝ ከገበየሁ ግራ ጎን፣ ከከሰም ወንዝ ማዶ ማይ ጓጉአን በር እጠር፡፡ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን፡፡
“ብፁዕ አባታችን ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ማቴዎስ፣ እርስዎ የእግዝእትነ ማርያምን ፅላት ይዘው ከኔ ሠራዊት ጀርባ ለውጊያ ይሰለፉ፡፡ ይሒዱ፡፡ እመብርሃን ከርስዎ ጋር ትሁን፡፡
“ሚካኤል፣ አንተ ከስምንቱ ሺህ ጦርህ ጋር ማዶ በሰናይ ፀባኦና በእንዳ ሚካኤል በር ግባ፡፡ ወሌ፣ አንተ ከሦስት ሺህ ጦርህ ጋር፣ ከኔ ሠራዊት ግራ ክንፍ ዳር፣ በማይ ደላንታ በር ተቋቋም፡፡
መንገሻ፣ አንተ ከሦስት ሺህ ጦርህ ጋር፣ በእንዳ ማርያም ሸዋቶ ደጀን ግባልኝ፡፡ ጓንጉል፣ አንተ ከሰባት ሺህ ሠራዊትህ ጋር፣ የመንገሻን ደጀን በተደራቢ አጠናክርልኝ፡፡ እሱ መንገድ ጥንትም ክፉ የፈተና በር ነው፡፡ አድዋ ድረስ አብሮን የዘመተው የጊዮርጊስ ፅላት ይታደጋችሁ ወንድሞቼ፡፡
“መንገሻ፣ አሉላ፣ እናንተ ሁለታችሁ ከሦስት ሺህ ሠራዊታችሁ ጋራ በእንዳ ማርያም ሸዊቶ ግንባር ጠንክራችሁ ቁሙልኝ፡፡ አደራችሁን ወንድሞቼ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ከናንተ ጋር ይሁን፡፡”
* * *
ዳግማዊ ምኒልክ በአዋጅ ወረኢሉ እንዲከት ያደረጉትን ብሔራዊ ጦር እየመሩ ወደ አድዋ ሲዘምቱ የሚያሳይ ታሪካዊ ፎቶ። ዳግማዊ ምኒልክ ከሠራዊቱ ፊት ጥንግ ድርብ ካባቸውን ለብሰው በፈረሳቸው በዳኘው ላይ ሆነው የሚጓዙት ናቸው!
ምንጭ ፡-
FONTAINE Hugues (2020). Ménélik. Une Abyssinie des photographes (1868-1916), Page 101.
ክብር ለአድዋ ጀግኖች!!!