>

«በአክሱም  በኤርትራ ወታደሮች የተፈጸመው የጅምላ ግድያ በሰብአዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን ይችላል» (አምነስቲ)

«በአክሱም  በኤርትራ ወታደሮች የተፈጸመው የጅምላ ግድያ በሰብአዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን ይችላል»
 
አምነስቲ

በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች በኅዳር ወር በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ገድለዋል ሲል ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዉ ድርጅት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ይፋ ባደረገዉ መግለጫ አስታወቀ። አክሱም ከተማ በኅዳር 10  እና 20፤ 2013 ዓ.ም መካከል የተፈጸመው የጅምላ ግድያ በሰብአዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል። ድርጅቱ በመግጫዉ በአክሱም ከተማ በደረሰዉ ጥቃት በህይወት የተረፉ 41 የዓይን ምስክሮችን ማነጋገሩን እንዲሁም በከተማዉ የታየዉን ግጭት  ሸሽተዉ ወደ  ምስራቅ ሱዳን የገቡ ስደተኞችን በአካል አግኝቶ ማነጋገሩን  ብሎም ስለጉዳዩ በአክሱም ከተማ ካሉ ሌሎች 20 ሰዎች ጋር የስልክ ቃለመጠይቆችን ማድረጉን  አመልክቶአል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች ኅዳር ወር አጋማሽ ላይ ከተማዋን ለመቆጣጠር ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ / ህወሃት / ጋር ዉግያ  ከገጠሙ በኋላ በከተማዋ ግድያ ተፈጽመዋል፤ ፍንዳታዋች ደርሰዋል፤  ሰፊ ዝርፊያዎች ተፈጽመዋል ማለታቸዉን የከተማዋን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ አምነስቲ በመግለጫዉ አመልክቶአል። አምነስቲ እንዳለዉ በድርጅቱ የሳተላይት ምስል ትንተና የጅምላ ግድያ እና ዘረፋ መካሄዱን ዘግቦአል። ትንተናዉ በከተማዋ በሚገኙ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት አቅራቢያ አዳዲስ የጅምላ መቃብር ምልክቶች እንደታዩ ምልክቶችን እንደሚያሳይ ገልጾአል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮዘ ሙቼና «ማስረጃው ዘግናኝ ሁኔታ ስለመከሰቱ አሳማኝ  መሆኑን ያያመላክታል » ማለታቸዉ በመግለጫዉ ተካቶዋል።  የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች አክሱምን ለመቆጣጠር በተካሄደዉ  ጥቃት በርካታ የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል ፡፡ ከዚያ በላይ የኤርትራ ወታደሮች በአመጽ በመሄድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በግፍ መግደላቸዉ በሰብአዊነት ላይ ወንጀል የተፈፀመ  ይመስላል ”ሲሉ  መናገራቸዉን መግለጫዉ አመልክቶአል። ዳይሬክተር ዴፕሮዘ ሙቼና «በአክሱም የታየዉ ሁኔታ እስካሁን በትግራይ ዉስጥ በነበረዉ  ግጭት  ከተመዘገቡት እጅግ የከፋ ነዉ። እየጨመረ ከሚሄደው የሟቾች ቁጥር በተጨማሪ የአክሱም ነዋሪዎች በሁከት ፣ በሐዘንና ስሜት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል»  ብለዋል። በአክሱም ከተማ የታየዉ ይህ የጅምላ ግድያ የተከሰተዉ በአክሱም ጽዮን ማርያም ዓመታዊ በዓል ኅዳር 21 ከመከበሩ ከጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ መሆኑም የአምነስቲ መግለጫ ያመለክታል።
Filed in: Amharic