>

ምርጫ በ‹ምራጮችና› በነባሩ መወቅር (ከይኄይስ እውነቱ)

ምርጫ በ‹ምራጮችና› በነባሩ መወቅር

ከይኄይስ እውነቱ


ተደጋግሞ እንደሚነገረው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነት በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ማኖር አይደለም፡፡ በነተበ ጨርቅ ላይ አዲስ እራፊ መጣፍም አይደለም፡፡ ይሄ ለውጥ ፈላጊ ኃይል አጥፊ በሆነው ነባር ኃይል መላወሻ ሲያጣ የሚከሰት ሁናቴን ነው የሚያመለክተው፡፡ ሥርዓታዊ ለውጥ ፈላጊው ሕዝብ እንጂ በሥልጣን የተቀመጠ ለውጥ ፈላጊ አዲስ ኃይል የለም፡፡ ‹ወይኑም እራፊውም› አዲስ አይደለም፡፡ ወይኑም አተላ÷ እራፊውም የነተበ ቡትቶ ነው፡፡ በቡትቶ ላይ ቡትቶ የመደራረቡን ውጤት ደግሞ አሁን ባለፉት ሦስት ዓመታት የወያኔን 27 ዓመታት በሚያስንቅ ሁናቴ እስኪታክተን አየነው፡፡

የቅርብ ጊዜ ወሬው ሁሉ ስለ ምርጫ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያለውን ጽድቅ በሚገባ ለሚያውቅና ለሚረዳ ሁሉ ጊዜው የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ምርጫ በጭራሽ አጀንዳችን አይደለም የሚል እምነት ካላቸው ወገኖች አንዱ ነኝ፡፡ ይህ እምነት ብቻ ሳይሆን እውነት መሆኑን አገራችን በ4ቱም ማዕዝናት በሰላም፣ በጸጥታ፣ ሥር በሰደደ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ውስብስብ ችግሮች ተተብትባ የምትገኝበትን ሁናቴ መመልከቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ 

ከሁሉም በላይ ወያኔ በኢትዮጵያ ምድር ሥርዓት አድርጎ የተከለብንን ጐሠኛነት፣ የጐሣ ፖለቲካ፣ ጐሣን መሠረት ያደረጉ የመንደር ‹ፓርቲዎች›፣ ‹ክልል› የተባለ አገር በታኝ መዋቅር፣ እነዚህ የአገርን ህልውናና የሕዝብን አብሮነት በቋፍ እንዲገኝ ያደረጉ በመዋቅር የተደገፉ አስተሳሰቦችን ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የተጫነብንን የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ይዘን እና አሁን ሥልጣን ላይ ያለው (ባንኩንና ታንኩን የተቈጣጠረው ኃይል) አገዛዝም ከቀደመውም በከፋ መልኩ የጐሣ ሥርዓቱን ለማስቀጠል እየማለና እየተገዘተ ባለበት ሁናቴ፣ ሌላዋ ዘረኛ ‹ዮዲት ጉዲት› የዳኝነቱን ሥርዓት በቀበረችበት (በነገራችን ላይ ሴትየዋ ለወያኔ አድራ የነበረች ግልብጥ ሎሌ መሆኗን መዘንጋት የለብንም)  ምርጫ የማድረጉ ፋይዳ የባርነት ምርጫ እንጂ ማንም ከአእምሮው ጋር ያለ ሰው ከጨለማ ወደ ብርሃን ሽግግር አድርጎ ሊመለከተው አይችልም፡፡ አንዳንድ ለሥልጣን የቋመጡና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ ማኅበረሰቦችን የጥቃት ዒላማ ያደረጉ ሰነፎች እንደሚሉት የአገርን ህልውና መታደጊያ ሊሆን አይችልም፡፡ ምርጫው የዛሬ ሦስት ዓመትም፣ ዐቢይ በወረርሽኙ አመካኝቶ በጉልበት የያዘውን ሥልጣን ሲያራዝምም፣ ለላቀ ምክንያት ደግሞ አሁን መካሄድ የለበትም የሚለው ጽኑ እምነቴ ነው፡፡ 

ታዲያ አእላፍ ዜጎች ሕይወታቸውን ገብረውና አካላቸውን አጥተው፣ አገራችን አለኝ የምትለውንና ከድኆች ዜጎቿ አፍ ነጥቃና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማፍሰስ የገዛችውን የአገር መከላከያ መሣሪያ ያወደመ፣ የማይካድራውን የዘር ማጥፋት ያስከተለ፣ ሰላማዊ የትግራይ ወገኖቻችንን ለሞት፣ ለመፈናቀል፣ ለስደት፣ ለረሃብ፣ ለልዩ ልዩ ሰብአዊ ቀውስ/ስቃይ የዳረገ፣ አሁንም ያልተጠናቀቀ ጦርነት ከወያኔ ጋር ማድረጉ ከንቱ ሊሆን ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔን አምርሮ የሚጠላውና ጦርነቱንም ደግፎ መሥዋዕትነት የከፈለው በዋናነት ድርጅቱና በውስጡ የሚገኙት ሰዎች በሕግ በመዋቅር ደግፈው ሲያራምዱ የኖሩትንና ከሰው በታች አዋርዶ አገር ሊያሳጣው የተቃረበውን የጐሣ ሥርዓት እስከነ መርዘኛ አስተሳሰቡ ለማጥፋት እንጂ በተረኛ የኦሮሞ ጐሠኞች ለማስቀጠል ከሆነ ምርጫ ለምን ያስፈልጋል? መቼም የአገር ህልውና በጐሠኞች ይጠበቃል ብሎ የሚከራከር ባለአእምሮ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ምናልባትም ምርጫውን እጅግ በጉጉት እንጠብቀዋልን ያሉት ኃይሎች ሌሎች ጐሠኞችን በሎሌነት አስከትለው ኦሮሙማ የተሰኘውን አገር የማጥፋት ፕሮጀክታቸውን ከፍጻሜ ለማድረስ ዕርጥባን ለሚጥሉላቸው የውጭ ኃይሎች የውሸት ተቀባይነትን ያስገኝልናል በሚል እምነት ካልሆነ በቀር፡፡

የዚህ ክፉ ዘመን (ዘመኑን ያከፉት ጨካኝ ምናምንቴ ዘረኞች በመሠልጠናቸው ነው) የቅድሚያ አጀንዳ የአገርን ህልውና መታደግ ነው፡፡ ከባለ ወር ተራ ዘረኞችና ጨካኞች፡፡ የእምነት ካባ ለብሰው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አምርረው ከሚጠሉ ሥጋ ከለበሱ አጋንንቶች፡፡ አገርን ለባዕድ አሳልፈው ለመስጠት ወደ ኋላ ከማይሉ ከሃዲ ባንዳዎች፡፡ ሐሰትን፣ ቅጥፈትን፣ ሌብነትን፣ አረመኔነትን፣ እና ነውር የተባለን ሁሉ ገንዘባቸው ካደረጉ የበግ ለምድ ለባሽ ተኩላዎች፡፡ 

ተደጋግሞ እንደሚነገረው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነት በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ማኖር አይደለም፡፡ በነተበ ጨርቅ ላይ አዲስ እራፊ መጣፍም አይደለም፡፡ ይሄ ለውጥ ፈላጊ ኃይል አጥፊ በሆነው ነባር ኃይል መላወሻ ሲያጣ የሚከሰት ሁናቴን ነው የሚያመለክተው፡፡ ሥርዓታዊ ለውጥ ፈላጊው ሕዝብ እንጂ በሥልጣን የተቀመጠ ለውጥ ፈላጊ አዲስ ኃይል የለም፡፡ ‹ወይኑም እራፊውም› አዲስ አይደለም፡፡ ወይኑም አተላ÷ እራፊውም የነተበ ቡትቶ ነው፡፡ በቡትቶ ላይ ቡትቶ የመደራረቡን ውጤት ደግሞ አሁን ባለፉት ሦስት ዓመታት የወያኔን 27 ዓመታት በሚያስንቅ ሁናቴ እስኪታክተን አየነው፡፡ ያለ ግብሩ ‹የለውጥ ኃይል› የሚል ስያሜ የያዘው ዘረኛ ቡድን፣ ወያኔ ጫካ ሳለ በመግለጫው፣ በጉልበት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ዘረኝነትን በተከለበት የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ› እና ይህንን ለማስፈጸም በዘረጋቸው መዋቅሮች አማካይነት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖቱና በአምሐራነቱ ለይቶ ከኢትዮጵያ ምድር እንዲጠፋ በፈረደበት ሕዝብ የጅምላ ፍጅት መፈጸሙና ዘር ማጥፋቱ፤ ክቡሩ የሰው ልጅ ወገናችን ዘመዳችን የአገር ዜጋ ሐዘንና የክብር መቃብር ተነፍጎት በጠራራ ፀሐይ በስለት፣ በቀስት እና በጦር መሣሪያ ተጨፍጭፎ እንደ አልባሌ በግሬደር ታፍሶ በጉድጓድ ውስጥ የሚጣልባት ኢትዮጵያን ማየቱ፤ በጉልበትም ቢሆን ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ አገር ያለው ይመስል እንደ ባዕድ ኃይል ሁሉ የኔ ነው በሚል ለከት የሌለው ስግብግብነት በመላው አገሪቱ የመሬት ወረራ በማድረግ ሚሊዮኖችን ማፈናቀሉ፤ በጥበባዊ አመራርና በጊዜው በሚወሰድ ርምጃ ሊቀር የሚችል አውዳሚ ጦርነት ማድረጉ፤ በባዕዳን የተደገሰልን ጦርነት ያንዣበበት ሁናቴ መኖሩ፤ የአገር መከላከያ ኃይልን ኢትዮጵያዊ ቁመና በማሳጣት በጐሣ አደራጅቶና ከጥቅም ውጭ አድርጎ ኢትዮጵያን ለሥጋት መዳረጉ፤ ጐሣን መሠረት ያደረገና ሕዝብን ለማሸብር የተዘጋጀ ‹ልዩ ኃይል› የተባለ ሕገ ወጥ ‹ጦር› በሕዝብ ገንዘብ በየመንደሩ መገንባቱ፤ ሚሊዮኖች የዕለት ጉርስ አጥተው የአገር ሀብትና ገንዘብ የሚዘረፍበት፣ ለጥቂት ተረኞች ተድላ ደስታና የማይረባ ዝና ‹ኬክ› (መናፈሻ ወዘተ.) የሚዘጋጅበት ሁናቴ፤ በታቀደና በተጠና ሁናቴ ነባርና ብሔራዊ ምልክት የሆኑ ተቋማትን ማፍረስና ለባዕዳን አሳልፎ ለመስጠት መዘጋጀቱ፤ በጥላቻና በድንቁርና መንፈስ ታሪክን፣ ብሔራዊ ቋንቋንና ብሔራዊ ቅርሶችን የማጥፋት ዘመቻ፤ ስንቱን እንዘርዝረው፡፡ እነዚህ ሁሉ በቡትቶ ላይ ቡትቶ የመደራረቡ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ባለፉት 3 ዓመታት ይህንን የፈጸመውና ያስፈጸመው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስሙን ‹ብልጽግና› ብሎ ለመሸፈን የሚታገለው፣ ቡቱቷሙ የወያኔ ውሉድና ወራሽ የሆነው ኦሕዴድ የሚባለው ኢሕአዴግ ነው፡፡ ይሄ የጥፋት ኃይል ከወያኔ ሕወሓት ጋር ልዩነት አለው ከተባለ የጐሣ ተረኝነት፣ ከፍርሃት የመነጨው ጭካኔው፣ ‹እምነትን› ለነውረኛ ተግባሩ ሽፋንና መሣሪያ ማድረጉ፣ ከወያኔ እንዳለ የቀዳውን የነውረኛነት መንገድ በብዙ እጥፍ አሳድጎ የጥፋት ሬከርዱን በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ መስበሩ ነው፡፡ ዛሬ ኦሕዴድ የሚመራው ኢሕአዴግ ወያኔ የተከለለትን የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት›፣ ሌሎች አፋኝ ሕጎችን፣ እስከ ገጠር ገበሬ ማኅበር የዘረጋለትን የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅር፣ በግልብጥ አሽከሮቹ (ብአዴን፣ ደሕዴን እና ‹አጋር› የተባሉትን የጐሣ ፓርቲዎች) ታጅቦ፣ አፍና ሆድ ብቻ ያላቸውን ደናቁርትና ወንጀለኛ ካድሬዎቹን ይዞ፣ የመንግሥት ሀብትና ንብረት እንዲሁም ሜዲያውን በዘረኝነት ለተበከለው ‹ፓርቲው› ጥቅም ተቈጣጥሮ፣ አዲስ አበባን ሕገ ወጥ በሆነው ልዩ ኃይሉና ከከተማው አስተዳደር እስከ ወረዳ ባሰማራቸው ካድሬዎቹ ተቈጣጥሮና አፍኖ፣ እንኳን በየክፍላተ ሀገሩ ሄዶ ለመቀስቀስ ከደብረ ዘይት አልፎ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ሁናቴ ስለ ‹ምርጫ› ያውም ‹ወያኔያዊ ምርጫ› ማንሣት ዕብደት የሚለውም ቃል በቅጡ የሚገልጸው አይመስለኝም፡፡ 

ዛሬ ፖለቲካን በጐሣ አደራጅተው  አገርን ለማፍረስ ላይ ታች የሚሉት ‹ፖለቲከኞች› ብቻ ሳይሆኑ በኢትዮጵያ አገራዊ ህልውናና አንድነት ላይ አንደራደርም፣ የዜግነት ፖለቲካ እናራምዳለን የሚሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች የብሔራዊ (ኢትዮጵያዊ) ማንነት መሠረትና ጉልላቱ ምን እንደሆነ ጥርት ባለ መልኩ ሠፍረው ቈጥረው ለክተው አልነገሩንም፡፡ ለጊዜው ኢትዮጵያዊነት ከነ ታሪኩ፣ ከነ ቀደመ እውነቱ፣ ክብሩ፣ ጥቅሙ፣ ኩራቱ ወዘተ ያለው በአብዛኛው ሕዝባችን ልብ ውስጥ ታትሞ ነው፡፡ 

በነገራችን ላይ በበርካታ አገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባት በሌለበት፣ አንኳር በሚባሉ ጉዳዮች ጠርዝ የረገጠ አስተሳሰብ ባላቸው የ‹ፖለቲካ ድርጅቶች› እና የኅብረተሰብ ክፍል ባለበት አገር ተፎካካሪ የሚባል ፓርቲ የለም፡፡ እንኳን በጐሣ በተደራጁና የዜግነት ፖለቲካ በሚያራምዱ ኃይሎች መካከል ይቅርና በጐሣ ድርጅቶች መካከል የተፎካካሪነት ሳይሆን የተቃውሞ መንፈስ ነው ያለው፡፡ የጐሣ ድርጅት ለማስመሰልም ቢሆን ጥብቅናው ላገር/ለዜጎች ሳይሆነ ማኅበራዊ መሠረቴ ነው ለሚለው ጐሣ ነውና፡፡ የጐሣን ፖለቲካና ፓርቲ እየተቃወምን ‹ተፎካካሪ› እያልን ለማለዘብ የምንሞክረውን ግብዝነት ብንተወው ይሻላል፡፡ ለማንኛውም እውነተኛ ተቃዋሚ የምንላቸውን የፖለቲካ ማኅበራት አንድ ሁለት ብለን መሠለስ የምንችል አይመስለኝም፡፡

ወደ ምርጫው ስንመለስ ዜጎች በእምነታቸውና በማንነታቸው በሚጨፈጨፉበት፣ በሚሊዮኖች ተፈናቅለው የመንግሥት ያለህ የወገን ያለህ በሚሉበት አገር አንገብጋቢው ጉዳይ ተአማኒ፣ ነፃ፣ ግልጽና ፍትሐዊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የማካሄድ አይደለም፡፡ አዲሶቹ ‹ወያኔዎች› የፈጠሩት ምስቅልቅል ምርጫውን እውን ሊያደርገው አይችልም፡፡ ሰውየው እንደሚቀጥፈው ‹ምርጫው› ሸፍጥ ለመሥራት ላደፈጡት የኦሮሙማ ፕሮጀክት ፈጻሚና አስፈጻሚዎች እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያጓጓና የሚጠበቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ይካሄዳል የሚባለው ‹ምርጫ› ምናልባት የሚካሄድ ከሆነ የተበላ ዕቁብ እንደሚባለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ለዚህ አገር አጥፊ ‹ተውኔት› መድረኩም መመቻቸት የለበትም ባይ ነኝ፡፡ ወረርሽኙን ምክንያት አድርጎ የተራዘመው ምርጫ አሁን ይበልጥ ተስፋፍቶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል በሚባልበት ጊዜ (ምስክርነቱን የሰጡት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕዝብ ጤና ተቋም ናቸው) እንዴት ነው ሊካሄድ የሚችለው? ስለ ወረርሽኙ የሚነገረን ውሸት ካልሆነ በቀር፡፡ በርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወረርሽኙ የበለጠ ሥጋቱ በገዛ አገሩ ባይተዋር ያደረገውና የሚያሳድደው አገዛዝና አገዛዝ-ወለድ የሆነው የኑሮ ውድነቱ ነው፡፡  እግዜሩ ደግ ሆኖ በወረርሽኙ አልጨከነብንም እንጂ በዚህ የሰላም እጦትና ችጋር ላይ ምን እንሆን ነበር? ይህ የውሸት ምርጫ እልቂትን እንደሚያስከትል ሥጋት አለኝ፡፡ በኃይል የበላይነት እቈጣጠራለሁ ቢባል እንኳን ለጊዜው ነው እንጂ ውሎ አድሮ ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ ዓመፃ እንደሚኖር ከግምት በዘለለ መናገር ይቻላል፡፡ ብዙዎች እናከብራት የነበረችው ወ/ት ብርቱካን ፈቅዳም ይሁን በማናውቀው ምክንያት የዚህ ‹ተውኔት› አካል በመሆኗ በእጅጉ አዝናለሁ፡፡ 

ለማጠቃለል ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ (for all practical purposes the so-called Prosperity Party is nothing but the disguised form of EPRDF) የሚባል ወንጀለኛ ድርጅት እስከነ ሕጉ፣ መዋቅሩና በሸፍጥ የተሞላ ድርጅታዊ አሠራሩ ባለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሊኖር አይችልም፡፡ ከወያኔ ኢሕአዴግ ወደ ኦነጋዊው-ኦሕዴድ ኢሕአዴግ የሚለው በትክክል የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡ መለስ በ1997 ዓ.ም. በጀብደኝነትና በተሳሳተ የራስ መተማመን የፈጸመውን ስህተት ደቀመዝሙሩ ዐቢይ ዳግም ይፈጽማል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ነባራዊ ሁናቴውም ይህንን አያሳይም፡፡ አምባገነንና እና ጨካኝ ገዢዎች ተንኮልን ለመማር የፈጠኑ በጎውን ለመከተል የዘገዩ ናቸውና፡፡ ምራጮቹ ኦሕዴድ/ኢሕአዴጋውያን እንደ ግብር አባታቸው ወያኔ እስከነ ቡትቷቸው ለኢትዮጵያውያን የምንጊዜም ዕዳና ጠንቅ ናቸው፡፡ ምራጭን (ዘረኞችን ባጠቃላይ) የሚመርጥ ደግሞ በዘረኝነት የተለከፈና ሆድ አደር ብቻ ነው፡፡

እንኳን የብሔራዊ በዓላት ሁሉ በኵር ለሆነው የኢትዮጵያና የመላ ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ቀን፣ የኢትዮጵያውያን ድል በዓድዋ እውን ለሆነበት መታሰቢያ በዓል 125ኛ ዓመት በጤና በሕይወት አደረሰን÷ አደረሳችሁ

ኢትዮጵያ÷ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ሲኖራት አገዛዞች በሕዝብ ላይ የባርነት ቀንበር የሚጭኑበት ቀን ሳይሆን፣ በዓድዋ የተመዘገበው የኢትዮጵያና የመላው ጥቁር ሕዝብ የድል ቀን የብሔራዊ በዓላት ሁሉ በኵር ሆኖ እንደሚከበር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ነፃነትን የምናውቅና ለነፃነት ታላቅ ዋጋ የምንሰጥ ሕዝብ ከሆንን እምቢ አሻፈረኝ ማለት ያለብን የውጭ ወራሪዎችን ብቻ ሳይሆን በገዛ አገራችን ባርነት የሚያጸኑብንን አገዛዞችንም ሊሆን ይገባል፡፡

በትግራይ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ በኮንሶና በሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ባስቸኳይ ይቁሙ!!! በሁሉም አካባቢ አደጋ የደረሰባቸው ወገኖቻችንን ፈጥነን እንርዳ!!! 

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!! 

ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡

ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡ (የምርጫ ቦርድ የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነትን መሠረዙ አንድ የሚያበረታታ ጉዳይ ሆኖ፣ በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባዋል፤ ትጥቅ ይዞ አገርንና ሕዝብን እያሸበረ ያለው ኦነግም ላይ ባስቸኳይ ሕጋዊ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡)

Filed in: Amharic