>

ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ፣ኢጣሊያና የአድዋ ትውስታ - ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ፣ኢጣሊያና የአድዋ ትውስታ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


ኢትዮጵያ ጥንታውያን ከሚባሉት ሀገራት አንዷ እንደሆነች፣ከአምስት ሺህ አመት ያላነሰ ታሪክ እንዳላት፣ እንደ ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደኢየሱስ፣ ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ፣ ፕሮፌሰር ሀይሌ ላሬቦ ወዘተ ወዘተ በጥናት ወረቀቶቻቸው ያረጋገጡት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ ጥንታዊት ሀገር ስለመሆኗ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ በእነዚህ ዘመናት ቀደምት አባቶቻችን ሰርተው ፣ትተውልን ካለፉት ዕጹብ ድንቅ ሥራዎች መካከል የአክሱም ሐውልት፣የላሊበላ ቤተመቅደስ ሕንጻዎች፣የጎንደር ቤተመንግስቶችና የአጼ ፋሲል ግንብ፣የሀረር ጀጎል ግንብ፣ ለታሪክ ምስክርነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ታሪክ ፍንትው አድርጎ እንዳስቀመጠው በእነዚህ ዘመናት ሀገራችን ከርስበርስ ጦርነት ተለይታ አታውቅም፡፡ በብዙ የውጭ ወራሪዎች ደግሞ በጦርነት ተደቁሳለች፡፡ ጦርነት ተለይቷት የማታውቀው ሀገራችን መተኪያ የሌላቸውን ቅርሶቿ ወድመዋል፡፡ ለቁጥር የሚታክቱ ልጆቿ አልቀዋል፡፡ በውጭ ወራሪ ሀይላት የተዘረፉ ቅርሰቿ ዛሬም ድረስ የምእራቡን አለም ታላላቅ ሙዚዬሞች ( በተለይም በታላቋ ብሪታኒያና ፈረንሳይ የሚገኙትን ሙዚዬሞች) አበልጽገው ይገኛሉ፡፡ ከብዙ ዘመነ ፈተና በኋላ ደግሞ በዐስራ ስምንተኛውና ዐስራ ዘጠነኛው ምዕት ዓመት፣ ሀገራችን ዘመነ መሳፍንት ተብሎ ይታወቅ ወደ ነበረው የመከራ ዘመን ውስጥ ወደቀች፣ ያ ወቅት ደግሞ አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመከፋፈል ወስነው ዘመቻቸውን የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ ( የበርሊኑን የኢምፔሪያሊስቶች ኮንፍረንስ ያስታውሷል፡፡) 

በዚያ ወቅት፣ ይህች በዘመነ መሳፍንት አገዛዝ ሀይሏ የተዳከመችውን ሀገር መልሶ አንድ ለማድረግ የቋራው አንበሳ ካሳ ሀይሉ፣ በንግስና ስማቸው አጼ ቴዎድሮስ ተብለው ተነሱ፡፡ አጤ ቴዎድሮስም በእነዚህ መሳፍንት ላይ በመዝመት ድል አድርገው፣ ሀገራችን  ተመልሳ እንደቀድሞው አንድ እንድትሆን መንገዱን ከፈቱ፡፡ ባደረጉትም ዘመቻ አንድም ቀን ድል ሆነው የማያውቁት ንጉሠ ነገሥት፣ ከአውሮፓውያን ጋር በተፈጠረው ችግር፣ የእንግሊዝ ጦር እስረኞቹን ለማስፈታት በዘመተባቸው ጊዜ፣ እጃቸውን ለወራሪው ጦር መስጠትን እንደውርደት ቆጥረውት መቅደላ አፋፍ ላይ ሽጉጣቸውን ጠጥተው ፣የክብር ሞትን ጽዋ ተቀብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ አጼ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ የተነሱት ነገሥታት እሳቸው የጀመሩትን አለማ በመከተል ኢትዮጵያ አንድ እንድትሆን አድርገዋል፡፡ ከአጤ ቴዎድሮስ ቀጥለው የተነሱት ዐጤ ዮሃንስ 4ኛ ሲሆኑ፣ በእሳቸው ዘመን የሸዋው ንጉሥ ምኒሊክ እና የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ግዛቶቻቸውን እንደያዙ የዐጤ ዮሃንስን የበላይነት አሜን ብለው ተቀብለው ዕውቅና መስጠታቸውን ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ይሁን እንጂ በየበኩላቸው በቀጥታ ከውጭ ሀገር መንግስታት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያደርጉ እንደነበር ታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

አውሮፓውያን የአፍሪቃን ምድር፣ እንደ ቅርጫ ሥጋ በሚቀራመቱበት በዚያ ጊዜ፣ፋሺስት ኢጣሊያ በበኩሏ በጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ምድር የነበረችው የኢትዮጵያ አካልና ልጅ ባህረነጋሽ፣ አነርሱ ግን ( ጣሊያኖች) በኋላ ኤርትራ የሚል ስያሜ አውጥተውላታል፡፡ በነገራችን ላይ ጣሊያን በጥንቷ ባህረነጋሽ የቀይባህር ጠረፍ ላይ እግሯን ተክላ እንደነበር ከታሪክ ማህደር ላይ እንማራለን፡፡ እንደ ልቧ ለመስፋፋት ግን አጤ ዮሃንስ እንቅፋት ስለሆኑባት፣ የወሰደችው አማራጭ፣ ከሌሎቹ ነገሥታት ( ንጉሥ ምኒሊክ እና ንጉሥ ተክለሃይማኖት) ጋር ጥሩ የወዳኝነት ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ አንደሆነ በአንዳንድ የታሪክ መጻሕፍት ላይ ተጠቅሷል፡፡ ይህም ኢጣልያ ወደፊት ዐጼ ዮሃንስ ላይ ስትዘምት እንዲተባበሩዋት በማሰብ ነበር፡፡ ዋናው ሃሳብ ይህ ሆኖ ሳለ ፣ ነገር ግን በአሰብ ወደብ ስለሚገቡ ዕቃዎች ቀረጥና በሸዋ ስለሚኖሩ ኢጣሊያኖች ሁኔታ ለመነጋገርና ፔትሮ አንቶኔሊ መልእክተኛ ሆኖ ወደ ንጉሥ ምኒልክ በ21 ሜይ 1883 ዓመተ ምህረት በመምጣት ውል ተፈራረመ፡፡ ንጉሥ ምኒልክም ወደፊት በአጤ ዮሐንስ ላይ ለመዝመት እንዲያስችላቸው የጦር መሳሪያ እንዲገዙ ተስማሙ፡፡ ኢጣሊያኖችም በእውነት ንጉሥ ምኒልክ በዐጼ ዮሐንስ ይዘምታሉ ብለው ስላመኑ ተጫማሪ የጦር መሳሪያ በመስጠትና እንዲሁም ብዙ ብድር በመፍቀድ የንጉሥ ምኒሊክ ጦር ይበልጥ እንዲጠናከር አደረጉት፡፡ በዚህ መሃል ዐጤ ዮሐንስ፣ እንግሊዞች፣ በስምምነታቸው መሰረት፣ ምጽዋን ለኢትዮጵያ በማስረከብ ፈንታ ለኢጣሊያ መስጠታቸውን ንጉሥ ምኒሊክ እንዲያውቁ አደረጉ፡፡ ንጉሥ ምኒሊክ አንቶኒሌን በአስቸኳይ አስጠርተው (ጠርተው)፣ ሁኔታውን እንዲያስረዳ ለጠየቁት የሰጣቸው መልስ ስላላረካቸው፣ ከዚያን ግዜ ጀምሮ በጣሊያኖች ላይ ጥርጣሬ አደረባቸው፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር (እ.ኤ.አ.) 1889 ንጉሥ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ በቀድሞው አጠራር ወሎ ጠቅላይ ግዛት ላይ ልዩ ሥሙ ውጫሌ በሚባል ታሪካዊ ቦታ (ስፍራ) ሳሉ እያሉ ዐጤ ዮሐንስ ቤጌምድር ጠቅላይ ግዛት መተማ ላይ ለኢትዮጵያ ዳርድንበር መከበር እና ለክብሯ ሲሉ መሞታቸውን ሰሙ፡፡ በአጋጣሚ ሆኖ አንቶኔሊ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ይዞ ሲመጣ ንጉሥ ምኒሊክ እንጦጦ ሥላልነበሩ፣ ውጫሌ ሄዶ አገኛቸው፡፡ አንቶኔሊ ንጉሡ ወደ መናገሻ ከተማቸው እስኪመለሱ ድረስ መታገስ አቅቶት ነበር ወደ ውጫሌ የሄደው፡፡ ይህ እውነት በብዙ የታሪክ መጽሐፍት ላይ የተጠቀሰ አብነት ይመስለኛል፡፡( በተለይም በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በሚያተከሩ መጸሀፍት ላይ መመርመር ይቻላል፡፡) በነገራችን ላይ አንቶኔሊ ወደ ውጫሌ ያመራው በጌቶቹ በኢጣሊያኖች የተረቀቀውን ውል ለማስፈረም እንድነበር ለማወቅ የአሁኑ ትውልድ ታሪክን መመርመር፣ ማጥናት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረን ሃያ አንቀጽ ያለውን ይኀን ውል ንጉሥ ምኒሊክና እንዲሁም በንጉሥ ኡምቤርቶ ሥም አንቶኔሊ ሆኖ ፈረሙ፡፡ ይህ ውል በተፈረመበት ቦታ ስም ‹‹ የውጫሌ ውል ›› ተባለ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ውል ውስጥ አስራሰባተኛው (17ኛው) አማርኛው፣ ‹‹ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል ›› ሲል፡፡ የኢጣሊያንኛው ቋንቋ ደግሞ ‹‹ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ ነገሥታት ለሚፈልጉት ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት አማካይነት ማድረግ ይገባቸዋል ›› ይላል፡፡ ይህ አንቀጽ ውሎ አድሮ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የአድዋ ጦርነት ተብሎ ለሚታወቀው ምክንያት እንደሆነ ከታሪክ እንማራለን፡፡ ወይም ታላላቅ የታሪክ ሰዎች በምርምራቸው ያረጋገጡት አቢይ ጉዳይ ነው፡፡

ንጉሥ ምኒሊክ የውጫሌ ውል ሮም ላይ ሲጸድቅ በቦታው እንዲገኙ ራሥ መኮንን ወልደሚካኤልን ወደ ኢጣሊያ ላኳቸው፡፡ እሳቸውም ሮም ደርሰው በቬኒስያ ቤተመንግስት ተገኝተው፣ ውሉ ከመጽደቁ በፊት እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ኦክቶበር 1 ቀን፣ 1889 ‹‹ የኢጣሊያ ድንበር ግዛት የሚጸናው በዚያች ቀን የኢጣልያ ጦር  ባለበት ቦታ ላይ ነው፡፡›› የሚል ተጫመሪ ውል እንዲፈርሙ አደረጓቸው፡፡ የኢጣሊያን መንግሥት ይህን ያደረገውም በዚያ ወቅት በጦርነት ተዳክሞ የነበረው የራስ መንገሻ ሰራዊት አቅም እንደሌለው ዐውቆ፣ ወደ ትግራይ ግዛት ዘልቆ በመግባት፣ ብዙ ቦታዎችን ይዘው ስለነበር ነው፡፡ ውሉም እንደጸደቀ  ‹‹ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ሥር ናት ›› የሚል ጽሑፍ በየጋዜጦቹ ላይ ታትሞ ወጣ፡፡  ይህንኑ መልእክት የኢጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስፒ ፤ ኦክቶበር 11 ቀን 1889 ( እ.ኤ.አ.) ለአሜሪካና ለ12 አውሮፓ መንግስታት አስታወቀ፡፡

 

ንጉሥ ምኒሊክ ዐጤ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ ምንም ጊዜ ሳያጠፉ ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን በመላው ኢትዮጵያ ዐዋጅ አስነገሩ፡፡ ዐዋጁንም የየአውራጃው ገዢዎች ንጉሥ ተክለሃይማኖትን ጨምሮ ሁሉም አሜን ብለው ተቀበሉ፡፡ ሥርዓተ ንግስናቸውን አስመልክቶ ደብዳቤ ለኢጣሊያን፣ ለተላቋ ብሪታኒያ፣ ለጀርመንና ፈረንሳይ መንግሰታት ደብዳቤ ላኩ፡፡ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር፣ ኖቬምበር 1889 ዓ.ም. ንጉሥ ምኒሊክ በእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን በሊቀ በጳጳሱ በአቡነማቲዎስ እጅ ተቀብተው፣ ምኒሊክ ንጉሠ ነገሥታት ዘኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ፡፡

ከሥርዓተ ንግሣቸው በኋላ፣ በወሩ ራስ መንገሻንና ራስ አሉላን ለማሳመን ወደ ትግራይ ዘመቱ። እዚያም ሲደርሱ ኢጣሊያኖች በውጫሌ ውል ከተጠቀሰው ግዛት ዐልፈው ሌሎች ከተሞችን መያዛቸው አንሶ፣ በጃንዋሪ 29 ቀን 1990 ዓ.ም በጄኔራል ኦሬሮ የሚመራው ጦር አድዋንና አክሱምን ያዘ። ዐጤ ምኒልክም በፌብሩዋሪ 23 ቀን 1990 ዓ.ም በቀጥታ ወደ መቀሌ በመሄድ፣ ጄኔራል ኦሬሮ ለምን እነዚህን ከተሞች እንደያዘ አስጠየቁ። ጄኔራሉም ወደ እነዚህ ከተሞች የገባው፣ ግዛት ለማስፋፋት ሳይሆን፣ የተራቡትን ለመመገብ ነው በማለት የማይመስል ምክንያት ሰጠ።

ዐጤ ምኒልክም እዚያው መቀሌ እያሉ፣ የውጫሌን ውል ሲጸድቅ ለመገኘት ወደ ሮም ሄደው የነበሩት፣ ራስ መኮንን ብዙ የጦር መሣሪያ ይዘው ሲመለሱ እዚያው አግኝተው ድንበርን በተመለከተ ሌላ ተጨማሪ ውል እንደፈረሙና ኢጣሊያኖች ኦክቶበር 1 ቀን አሉበት ቦታ እንደሆነ አስረዱ። ዐጤ ምኒልክ ደግሞ ከሌሎች እንደተረዱት፣ ኢጣሊያኖች ከተባለው ቀን በፊት ቀደም ብሎ በውጫሌ ውል ከተጠቀሰው ድንበር ዐልፈው ገብተው መሬት እንደያዙ አስረዱ። ዐጤ ምኒልክም ኢጣሊያኖች ራስ መኮንንን እንዳታለሏቸው ቢገባቸውም፣ ኢጣሊያኖች ከያዟቸው ቦታዎች በቶሎ ለቀው እንዲወጡ አዘዟቸው። ኢጣሊያኖች ግን ከአድዋ ከአክሱም ለቅቀው ወጥተው በኦክቶበር 1 ከያዙበት ቦታ ላይ ቆሙ። ዐጤ ምኒልክም ወደ መናገሻ ከተማቸው ተመልሰው ድንበርን በተመለከተ ውይይቱን ቀጠሉ። ይህ በእንዲህ እያለ፣ ስለ ሥርዓተ ንግሣቸውን ደብዳቤ የጻፉላቸው እንግሊዝና ጀርመን፣ ለዐጤ ምኒልክ በጻፉት መልስ ላይ፣ በውጫሌ ውል መሠረት፣ ግንኙነታችን በቀጥታ ሳይሆን በኢጣሊያን በኩል ሊሆን እንደሚገባ አስረዱ። ይህ ደግሞ ዐጤ ምኒልክን ይበልጥ አስቆጣ። አንቶኔሊን የተካው ሳሊምቢኒም የ17ኛውን አንቀጽ እንዲያብራራ ሲጠየቅ በአማርኛውና በጣሊያንኛው መካከል የትርጉም ልዩነት እንዳለው ያወቀው ያነዬ ነበር። ዐጤ ምኒልክም ለሳሊምቢኒ ግልጥ ባለ አማርኛ፣ ይህች ሀገር እኮ የኔ ናት የማንም አይደለችም፣ ማንም ደግሞ ሊወስዳት አይችልም በማለት ተናግረው፣ በሴፕተምበር 1990 የውጫ ውል እንዲሻሻል በማለት ደብዳቤ ላኩ።

የኢጣሊያን መንግሥትም፣ ውሉ እየተበላሸ መሔዱን በመረዳት አንቶኔሊ መልሶ ላከው። አንቶኔሊኒም በዲሰምበር 17 ቀን 1890 እንጦጦ ደርሶ ‹<17ኛው አንቀጽ ከአሁን በኋላ ዋጋ የለውም ( ተበላሸ)> › ወይም ተሳስቷል የሚለውን ኢጣሊያ አትቀበልም፡፡ በዚህም ጉዳይ ማንም ሊያስገድዳት አይችልም፣ ምክንያቱም ክብሯን የምትጠብቅ ታላቅ ሀገር ናት በማለት የጣሊያንን አቋም አጠንክሮ ሲናገር እቴጌ ጣይቱ አቋርጠውት፣ < አንተ የምትለውን አንቀጽ በአማርኛ የተጻፈውን ምን እንደሚል ለመንግስታቱ አሳውቀናል፡፡ አንተ እንደምትለውም እኛም ክብራችንን እንጠብቃለን፡፡እናንተ የምትመኙት ኢትዮጵያ በእናንተ ሥልጣን ሥር እንድትሆን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለምንግዜውም የማይሆን ነገር ነው> አሉት። አንቶኔሊም፣ < የውጫሌ ውል ለአምሥት ዓመት ሲሆን፣ አሁን የቀረው ደግሞ 3 ዓመት ብቻ ስለሆነ፣ ለማንኛውም ይህ የቀረው ጊዜ እንዳለ ይለፍ> አለ። ዐጤ ምኒልክም < እነዲህ አይነቱ ውል እንኳን 3 ዓመት ሶስትም ቀን አያድርም  ይልቁንስ አሁኑ ይሻሻል ›› አሉት። (1)

አንቶኔሊም ደጋግሞ፣ <ለትንሽ ጊዜ አንጣላ፣ የውሉ ጊዜ ሲያልቅ ይህን አንቀጽ ልናሻሽለው እንችላለንና አሁን 17ኛው አንቀጽ አይነሳ ይቅር > አለ። አስተርጓሚው አቶ ዮሴፍ ቀበል አድርገው 17ኛው አንቀጽ አይነሣ ይቅር ብለው ተረጐሙ። ዐጤ ምኒልክም ትርጉሙን ሲሰሙ፣ <ድሮስ ቢሆን እኔ ያልኩት 17ኛው አንቀጽ እንዲቀር አልነበረምን?>። አሁንም እሺ ይቅር ይሰረዝ አሉ። በዚህ አባባል ሁለቱም ስለተደሰቱ ቃሉ እንደገና በአማርኛ <17ኛው አንቀጽ ተሰርዟል> የሚል በሁለት ወረቀት ላይ ተጽፎ አንዱ ለኮንት አንቶኔሊ ሲሰጥ ሌላው በቤተ መንግሥቱ እንዲቀመጥ ተደረገ። በማግሥቱም ያን ጽሑፍ ወደ ኢጣሊያንኛ ሲያስተረጉመው፣ <17ኛው አንቀጽ ተሰርዟል> > የሚል ሆኖ አገኘው። ወዲያውም ተደናግጦና ተናዶ ወደ ቤተ መንግሥት በመሄድ፣ <ለምን ተሠርዟል የሚል ቃል ተጻፈ > ብሎ ጠየቀ? ዐጤ ምኒልክም ሁለታችን ተነጋግረን፣ አንተው ወደህ የተጻፈ ነው እንጂ፣ እኛ የጨመርንበትም የቀነስንለትም ነገር የለም>> አሉ። ክርክሩ እየሰፋ ሲሄድም የውጫሌ ውል የተዋዋልነበት በፈረንሣይ ቋንቋ የተጻፈው ይታይልኝ አለ። እቴጌ ጣይቱ ግን <እኛ የምናውቀው በአማርኛ የተጣፈውን እንጂ ያንተን የፈረንጅ ቋንቋ እኛ አናውቅም አንተ ግን፣ የእኛን ቋንቋ ታውቃለህና በአማርኛ የተጻፈውን እየው አሉት>። በዚያን ጊዜ አንቶኔሊ ተናዶ፣ አዲሱን ውል ቀዳዶ ወዲያው ጣለና፣ ውሉን የኢጣሊያ መንግሥት በጦር ኃይል ያስከብረዋል በማለት እየተቆናጠረ ተናገረ። በዚህን ጊዜ፣ እቴጌ ሳቅ ብለው <የዛሬ ሳምንት አድርገው// አሉት። በዚህ ላንተ የሚደነግጥ ሰው የለም፡፡ ሂድ የፎከርክበትን አሁኑኑ አድርገው፡፡ እኛም የመጣውን እንመልሰዋለን፡፡ እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰው የሌለ እንዳይመስልህ፡፡ ደሙን አፍስሶ ለአገር መሞት ጌጥ ነው እንጂ መሞት አይባልም፡፡ አሁኑን ሂድ አይምሽብህ፣ የፎከርክበትን ባሻህ ጊዜ ታደርገዋለህ፡፡ እኛም እዚያ እንጠብቅሃለን፡፡ እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም፣ ግን እንዲህ ዓይነቱን ውል ከመቀበል ጦርነት እመርጣለሁ ›› አሉት፡፡

 ዐጤ ምኒልክ የውጫሌውን ውል በተዋዋሉ በ4ኛው ዓመት፣ ለአውሮጳ ኃያላን መንግሥታት የውጫሌን ውል ማፍረሳቸውን የካቲት 4 ቀን 1885 (ፌብሩዋሪ 1893)በደብዳቤ አስታወቁ። በዲሴምበር 1893 በጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ ላይ ተመልሶ የተቀመጠው ክሪስፒ፣ አንቶኔሊን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጸሐፊ፣ ጄኔራል ባራቲየሪን ደግሞ አዲሱ የኤርትራ ገዢ አድርጎ ሾማቸው። ጄኔራል ባራቲየሪ በ1894 መጨረሻ ላይ ጦሩን እየመራ ወደ ትግሬ ግዛት ዘልቆ በመግባት ከተማዎችን መያዝ ጀመረ። ጄኔራል ባራቲየሪ በ1895 በበጋው ወራት፣ ለዕረፍት ወደ ሮም በሄደ ጊዜ በጣሊያን ፓርላማ ተገኝቶ ንግግር ከማድረጉ በፊት፣ አባላቱ ከመቀመጫቸው ተነሥተው የደመቀ ጭብጨባ በመስጠት ተቀብለውታል። ንጉሡ ኡምቤርቶም ድል አድራጊው ጄኔራል ባራቲየሪ በማለትና በማድነቅ፣ የጣልያን ኀይልን “የሠለጠኑ የበላይነት ኋላ-ቀር በሆኑ ላይ” በማለት አወድሰውታል። ጄኔራል ባራቲየሪም በንግግሩ ላይ <በጥቅምት ወር ጦርነት ይኖራል > ሲል በኩራት ተናገረ። በቅኝ ግዛት መስፋፋት ምኞት ሕልም የሰከረው ፓርላማም፣ ንግግሩን ከሰማ በኋላ የጄኔራሉ ዓላማ እንዲሳካለት ለ1 ሺህ ተጨማሪ ወታደሮች መቅጠሪያ በጀት አፀደቀለት። ጄኔራል ባራቲየሪ በሴፕተምበር 26 ቀን 1895 ተመልሶ ምፅዋ ገባ።

ዐጤ ምኒልክም፣ የውጫሌውን ውል ማፍረሳቸውን ለአውሮጳ ኃያላን መንግሥታት ካሳወቁ በኋላ፣ <የትግሬ ህዝብ እነዚህን ወራሪዎች ታጥቀህ ተነሳና አስወጣ> በማለት አዘዙ። ጄኔራል ባራቲየሪ 25 ሺህ የሚሆን ጦሩን ይዞ ወደ ትግራይ ግዛት ዘልቆ በመግባት፣ ወደፊት እየገፋ እያሸነፈ መቀሌን፣ አዲግራትን እና አድዋን በኦክቶበር 9 ቀን 1895 ዓም ያዘ። የኢጣሊያን ጦርም፣ ወዲያውኑ የአምባላጌን ተራራ ይዞ ምሽጉን መሥራት ቀጠለ። ሜጀር ቶዚሊም በዚያ የሠፈረው ጦር አዛዥ ሆነ። የተሸነፈውም የራስ መንገሻ ጦር እያፈገፈገ ከትግራይ ወጥቶ ወሎ ወደ ራስ ሚካኤል ዘንድ መጥቶ ሌላው የኢትዮጵያ ጦር እስኪመጣ በዚያ ተቀመጠ። ብልኁ ንጉሠ ነገሥት ዐጤ ምኒልክም የውጫሌውን ውል ሲያፈርሱ፣ ከኢጣሊያኖች ጋር ጦርነት የማይቀር መሆኑን ዐውቀውት ስለነበር፣ ወታደሮቻቸውን ማዘጋጀትና ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ከራሺያና ከፈረንሳይ በጅቡቲ በኩል ማስመጣት ቀጠሉ። በ1895 በአጠቃላይ ለዚህ ጦርነት ዝግጅት ዐጤ ምኒልክ ከ70 -100 ሺህ የሚደርስ ዘመናዊ ጠብመንጃ እና 5 ሚሊዮን ጥይት መግዛት ችለው ነበር።

ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት ( የክተት አዋጅ)

 ድንበር ጥሶ የመጣውን ወራሪውን የኢጣሊያ ጦር አስመክልቶ ለመነጋገር፣ በሴፕምተምበር 1895 ዐጤ ምኒልክ በየአውራጃው ያሉትን ሀገረ ገዥዎች ለምክር ወደ እንጦጦ እንዲመጡ አደረጉ። በምክክሩም ላይ ዐጤ ምኒልክ ይህን ከአውሮጳ የመጣ ወራሪ ጦር ከሀገር ለማስወጣት የሀገሪቷ ሀብት ለዚሁ እንደሚውል አስታውቁ።የየአውራጃው ገዥዎች፣ ሁሉም ሠራዊታቸውን ይዘው ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምቱ የክተት አዋጅ እንዲነገር አዘዙ። በሴፕተምበር 17 ቀን 1895 ዓም የክተት አዋጁን ነጋሪት ከንጋቱ አንስቶ እስከ ምሽቱ ድረስ በቤተ መንግሥቱ ግቢ ሲጐሸም (ሲመታ) ዋለ።

የዐዋጁም ቃል፣

 <እግዚአብሔር በቸርነቱ እስከአሁን ጠላት አጥፍቶ ሀገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስከአሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ፣ ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዜአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡ እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም ሀገር የሚያጠፋ ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት፣ እግዜአብሔር የወሰነልልን የባህር በር ዐልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስከአሁን ዝም ብለው፣ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል፣ መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን በእግዜአብሔር እረዳትነት  ሃገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሑ አይመስለኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልተውህም፡፡ ማርያምን ለዚህም አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እሰከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡

  1. በአዋጁ መሠረት ከ75 እስከ 120 ሺህ የሚደርስ የኢትዮጵያ ሠራዊት መሪዎቹን አጅቦ/ተከትሎ ጉዞ ወደ ጦርነቱ ስፍራ ቀጠለ። ዐጤ ምኒልክም፣ እቴጌ ጣይቱን እንዲሁም ሌሎቹ ጦራቸውን ይዘው በኦክቶበር 28 ቀን 1895 ከ18 ቀን ጉዞ በኋላ ወረኢሉ ከተማ ገቡ። ከደረቅ (ዋናው) ሌላ፣ በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ገበሬዎች፣ ሴቶችና ሕፃናት ወደ ጦሩ ግንባር አብረው ሄደዋል።

አምባላጌ የመጀመሪያው ጦርነት ( ዲሴምበር 7 ቀን 1895 )

ከንጉሠ ነገሥቱ አስቀድሞ ወደ ጦሩ ግንባር የዘመተው የራስ መኮንን፣ የራስ መንገሻ ሥዩም እና የራስ ወሌ ብጡል ጦር ነበር፡፡ጦሩም ወደ ትግራይ ግዛት በመግባት ጠላት ወደመሸገበት ወደ አምባላጌ አመራ፡፡ እነዚህ ብዙ ልምድ ያላቸው ራሶች፣ይህን የተጠናከረ ጦር የሰፈረበትን ተራራ ማጥቃት፣ ኢጣሊያኖቸን ስለሚያግዝና በቀላሉም ወታደሮቻችንን ስለሚያስጨርስ፣ ይህንን ትተን ዋናው የኢጣልያ ጦር ወደ ሰፈረበት ወደ አዲግራትና ወደ መቀሌ ሄደን እናጥቃ በማለት አልፈውት ሄዱ፡፡ ይሁን እንጂ ከራሶቹ በኋላ፣ በፊትአውራሪ ገበየሁ መሪነት ይከተል የነበረው 1200 ወታደር፣በአጋጣሚ፣ አካባቢውን ወጥቶ የሚቃኝ፣አንድ የኢጣሊያን ጦር ያገኙና ተኩስ ይከፍቱበታል፡፡ ኢጣሊያኖቹም ወደምሽጋቸው ሲያፈገፍጉ ኢትዮጵያውያኑ እየተከተሉ ሲያጠቁ ተኩሱ እየተፋፋመ መጣ፡፡ ራሶቹም ፊትአውራሪ ገበየሁ ውጊያውን አቁመው እንዲከተሏቸው ቢያዙም ሰሚ አልተገኘም፡፡

የፊትአውራሪ ገበየሁ ሰራዊትም ተራራውን እየቧጠጠ ወደላይ እየወጣ ጦርነቱን ቀጠለ፡፡ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ስለነበረ፣ራሶቹ ሳይፈልጉ ወደ ጦርነቱ ውሰጥ ገብተው መዋጋት ጀመሩ፡፡ ምንም እንኳ፣ ከላይ አመቺ የሆነ ቦታ ላይ ሆኖ ብዙ ጉዳት ቢያደርስም፣እንደ ማእበል ወደ ላይ የሚወጣው ጦር አሳሳቢ ስለሆነበት፣ የፋሺስት ጣሊያን የጦር መኮንን ቶዚሊ ተጨማሪ ጦር እንዲላክለት  ወደ አሪሞንዲ  አስቸኳይ መልእክት ላከ፡፡ አሪሞንዲም በተራው ተጨማሪ ጦር ለመላክ እንዲፈቀድለት ወደ ጄኔራል ባራቲየሪ መልእክት ላከ፡፡

ባራቲየሪ ግን ጦር እንዳይልክ ነገር ግን ቶዚሊ እየተከላከለ ቀስበቀስ ምሽጉን ለቆ እንዲወጣ እንዲነግረው አዘዘ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መልእክት ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ለቶዚሊ አልደረሰውም፡፡ ቶዚሊም ከአሁን አሁን ተጨማሪ ጦር ይደርስልኛል እያለ ባለ በሌለ ኀይሉ መዋጋት ቀጠለ፡፡ ከስድስት ሰዓታት ጦርነት በኋላ መሪውን ቶዚሊን ጨምሮ 2 ሺኅ የጣሊያን ወታደሮች ተገደሉ፡፡ ከሰዓት በኋላ ልክ በ10፡30 (4፡30PM) የኢትዮጵያ ባንዲራ በአምባላጌ ተራራ ላይ ተውለበለበች፡፡

ከዚያ የተረፉት የጣሊያን ወታደሮች እየሸሹ ሲሄዱ የኢትዮጵያ ጦር እየተከተለ ፈጃቸው፡፡ ትረፉ ያላቸው ጥቂቶች እንደምንም ብለው አምልጠው ከአሪሞንዲ ጦር ጋር ተቀላቀሉ፡፡ የኢትዮጵያ ጦር አሁንም ተከታትሎ ሥላጠቃቸው ወደ መቀሌ ሸሽተው፣ በማግስቱ ጠዋት ንጋት ላይ፣ ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ለመቀላቀል እንደበቁ ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ይህ ድንገተኛ ጦርነት በኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነት ቢጠናቀቅም፣በተለያዩ የታሪክ መጽሐፍት ላይ እንደተጠቀሰው፣ ለሀገራቸው ክብርና መከበር ሲሉ  ወደ 3ሺኅ የሚጠጉ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል፡፡

በዚህ በአምባላጌው ጦርነት በጀግንነት ስማቸው የተጠራው ፊታውራሪ ገበየሁ ናቸው። ከድሉ በኋላ፣ ሠራዊቱ <ጎበዝ አየኁ> እያለ ስማቸውን በማሞካሸት ከፍ ባለ ድምፅ ይጠራ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ራስ መኮንንና ራስ መንገሻ <ፊትአውራሪ ገበየሁ ያልተፈለገ ጦርነት አንዲነሳ አድርገው ለብዙ ሰው እልቂት ምክንያት ሆነዋል > በማለት ተበሳጭተው እንደነበር የሚያሳዩ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። ምንም እንኳ ዐጤ ምኒልክ በድሉ የተደሰቱ ቢሆንም፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ትእዛዝ ጥሰው ጦርነቱን ስለ ጀመሩ 3 ሳምንት በሰንሰለት እንዲታሰሩ ማዘዛቸውን  ታሪክ ተተቅሷል። የሆኖ ሆኖ ግን እምዬ ምኒልክ ዐልፎ ዐልፎ እንደ ሌሎቹ ሁሉ < ጎበዝ አየኁ> እያሉ የጀግናውን ስም በመጥራት ፈገግ ይሉላቸው ነበር። ዐጤ ምኒልክ በጦርነቱ ላይ የወደቁት ጀግኖች እንዲቀበሩ ትእዛዝ ሲሰጡ፣ የቶዚሊም ሬሣ ተነስቶ በክብር ይቀበር በማለታቸው፤ የባህታ ሐጐስ ወንድሞች፤ ወንድማቸው በ1894 በጣሊያኖች ላይ አምፀው በተገደሉ ጊዜ፣ ሬሳቸው እንዳይቀበር ጅብ እንዲበላው ያዘዘው ይህ ሰው ስለሆነ፤ እሱም በተመሳሳይ ይቀጣልን በማለት አቤት አሉ። ዐጤ ምኒልክ ግን፣ ‹<ጣሊያኖች ጨካኝ አረመኔ የሆኑ እንደሆነ እናንተም እንደነሱ ትሆናላችሁን ?>> በማለት እንዲቀበር አዘዙ።

የመቀሌ ከበባ (ሁለተኛው ጦርነት 6 – 21 ጃንዋሪ 1896)

በመቀሌ የመሽገው ጦር በደንብ የተጠናከረ ቢሆንም፣ ከአምባለጌ ተርፈው የመጡት የኢጣሊያ ወታደሮች፣ እንደ ማዕበል እየጐረፈ የሚመጣውን ጦር ለማቆም ምሽጉን በደንብ አድርጎ መገንባትና ከምሽጉ ውጭ እስከ 30 ሜትር ርቀት ላይ ደግሞ፣ የሾሉ እንጨቶችን በመንገዱ ላይ አቀራርበው ተከሉ። ከዚያ አልፎ ደግሞ የእሾህ ሽቦ አነጠፉ። ይህም አልበቃቸውም ብሎ ብዙ የቪኖ ጠርሙሶችን ሰባብረው ከሽቦው ቀጥሎ ባለው መሬት ላይ በትነው ምሽጋቸውን አጠናከሩ። ኢጣሊያኖች ይኽንን ያደረጉበት ምክኒያት፣ ያለ ጫማ በባዶ እግሩ የሚጓዘው የኢትዮጵያ ጦር አንደለመደው እየሮጠ እንዳይመጣና ቀስ እያለ ለመራመድ ሲሞክር፣ ከምሽጋቸው ውስጥ ሆነው በጥይት ለመልቀም እንዲችሉ ነበር።

ይህ በእንዲህ እያለ፣ አምባላጌ ላይ የመጀመሪያውን ድል ያጣጣመው የኢትዮጵያ ጦር ጉዞውን ወደ መሐል ትግሬ ቀጠለ። ኢጣሊያኖችም የኢትዮጵያን ዘማች ሠራዊት መጥቶ ጦርነቱ እስኪጀመር በደንብ እየተደራጁ ሲጠባበቁ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት 5 ሺህ ጦራቸውን ይዘው በዲሴምበር 24 ቀን ከዐጤ ምኒልክ ጋር ተቀላቀሉ። ይህም ለጣሊያኖች ራስ ምታት ሆኖባቸው ነበር፤ ምክኒያቱም ጣሊያኖች ዐጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች, 28 Feb 2013 Page 8 ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጥሩ ግንኙነት ስለነበራቸውና ብዙ ስጦታም ይልኩላቸው ስለነበር ነው። ከሰላዮቻቸውም የደረሳቸው መረጃ፣ ንጉሡ ተ/ሃይማኖት በዐጤ ምኒልክ እና ትግሬዎቹ ላይ ቂም ስለቋጠሩ፤ በዚህ ጦርነት ገለልተኛ ሆነው ይቆያሉ፣ አልያም በዐጤ ምኒልክ ላይ ያምጻሉ የሚል ስለነበር ነው። እዚህ ላይ ኢጣሊያኖች ያልገባቸው ነገር ቢኖር፣ እነዚሁ ሰላዮች፣ ለንጉሡ በምስጢር የሚሠሩ፣ ነገር ግን ሆን ብለው የውሽት መረጃ የሚያቀብሉ መሆናቸውን አለማወቃቸው ነው። ከዚህም ሌላ ኢጣሊያኖች፣ ጦርነቱ ሲጀመር የኢትጵያን ጦር ከሌላ አቅጣጫ እንዲያጠቃ ቃል ገብቶ ባስታጠቁት በአውሳው ባላባት ላይ በራስ ወልደ ጊዮርጊስ፣ በራስ ተሰማ ናደውና በአዛዥ ወልደ ጻዲቅ የሚመራ ጦር ወደ አውሳ ዘምቶ ገና ሳይንቀሳቀስ ከበበው። በአውሳው መሪ የሚመራው ጦር እነዚህን ምርጥ ጀግኖች መቋቋም ስላልቻለ፣ አምልጦ ወደ በረሃ ገባ። ይሁን እንጂ ኢጣሊያኖች ይረዱናል ብለው ያሰቧቸው ባይመጡላቸውም፣ እንዲህ እንደነሱ በዘመናዊ የጦር መሣሪያ የተደራጀውን የአውሮጳን ጦር፣ ይህ ያልሠለጠነ ጥቁር ሕዝብ ያሸንፈዋል የሚል ጥርጣሬ ፈጽሞ አልነበራቸውም።

የመቀሌው ጦርነት የመጀመሪያው ግጭት በዲሴምበር 27 ቀን 1895 ተጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ እግረኛውና ፈረሰኛው ጦር ወደ ምሽጉ ሲጠጋ፣ በምሽጉ ውስጥ ያሉት የኢጣሊያን ወታደሮች ገና ሳይቀርቡ በሩቁ መትረየሳቸውን አንፈቀፈቁበት፡፡ ምሽጉ በቀላሉ የሚሰበር ስላልሆነም፣ በጀግንነት ፊትለፊት እየተጋፈጡ ብዙ የኢትዮጵያ ጀግኖች ወታደሮች ለሀገር ክብር ሲሉ እንደ ቅጠል ረገፉ፡፡ ስለዚህም ጦርነቱን ለግዜው እንዳቆሙ የሚያሳዩ መረጃዎች በታሪክ መጽሐፍት ላይ ተጠቅሷል፡፡

ለመቀሌ ቀረብ ብሎ የሰፈረው የራስ መኮንን፣ የራስ መንገሻ ሥዩምና የራስ ወሌ ብጡል ጦር፣ በሰላም ምሽጋቸውን ለቀው እንዲሄዱ ለኢጣሊያኖቹ መልእክት ላኩ፡፡ ከዚያም ራስ መኮንን በእንዳ ኢየሱስ ላይ ለሰፈረው ጦር አዛዥ ጋሊያኖ ጃንዋሪ 5 ቀን 1896 የሚከተለውን ደብዳቤ ጻፉ፡፡

‹‹ እኔ እዚህ አነስተኛ ምሽግ ላይ ጦርነት ለመክፈት አልመጣሁም፡፡ እኛ ብዛት አለን፡፡ የጦር መሣሪያችሁንም አንፈራም፡፡ አምባላጌንና የቶዚሊን መጨረሻ አስታውስ፡፡ አሁንም ምሽጉን  አስረክቡና በሰላም ወደ ምጽዋ ሂዱ፡፡ ›› (1)ነገር ግን ጣሊያኖቹ ምክሩን ከመቀበል ይልቅ፣ በምሽጋቸውና በመሣሪያቸው በመተማመን መቆየትን መረጡ፡፡

በማግስቱ በጃንዋሪ 6 ቀን 1896 ዐጤ ምኒሊክ ዋናውን የኢትዮጵያን ጦር ይዘው ከራሶቹ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ በነጋታውም ጃንዋሪ 7 ቀን (ታኅሣሥ 29) የኢትዮጵያ ገና በዓል ስለነበር እንዳ ኢየሱስ ላይ የሰፈረው የጣሊያን ጦር፣ በዚያ አካባቢ በሚያልፉ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ላይ ተኩስ ከፈቱ። የምሽጉን ጠንካራነት እና ለመያዝም አስቸጋሪ መሆኑን የተገነዘቡት ዐጤ ምኒልክ ግን ጦርነቱን መክፈት አልፈለጉም። ይሁን እንጂ፣ ተኲሱ እያየለ ሲመጣ ምሽጉን እንዲያጠቁ፣ ሊቀ መኳስ አባተንና በጅሮንድ ባልቻን አዘዙ። እነዚህ የጦር አበጋዞቹም ወታደሮቻቸውን ይዘው ቀኑን ሙሉ ሲታኮሱ ቢውሉም፣ ምሽጉን ግን መስበር አልቻሉም። እነርሱም ሌሊቱን ምሽግ ሲያሰናዱ አድረው በማግሥቱ ጧት በጃንዋሪ 8 ቀን የጣሊያንን ጦር ግራ ያጋቡት ጀመር። በተለይ ሊቀ መኳስ አባተ፣ የሚተኲሱት መድፍ በትክክል መሽገውበት የነበረውን የቤተ ክርስቲያኑን መስኮት ከመደብደቡም በላይ፣ በመድፋቸው አንዱን የጣሊያኖቹን መድፍ መስበር ችለው ነበር። 

እንዲሁም በራስ መኮንን የሚታዘዘው ወደ 60 ሺህ የሚጠጋው ጦር ከጃንዋሪ 8 እስከ 11 ምሽጉን ቢያጠቃም፣ ምሽጉን ሰብሮ መግባት አልቻለም ነበር፡፡ በእነዚህም ቀናት ውስጥ ወደ 500 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እንደሞቱ፣ከመሸጉት ኢጣሊያኖች፣የሞቱት 6፣ የቆሰሉት 9 ብቻ እንደነበሩ በታሪክ መጽሀፍት ላይ ተጠቅሷል፡፡

ይህንን ጠንካራ ምሽግ ለመስበር ሲባል፣ የሚሞተውን ወታደር ብዛት የተመለከቱት እቴጌ ጣይቱ፣ ኢጣሊያኖች የሚጠቀሙበትን የውሃ ጉድጓድ አቀማመጡን ካስጠኑ በኋላ ለመያዝ እንደሚቻል አረጋግጠው፣ ለዐጤ ምኒልክ ነገሯቸው። ንጉሠ ነገሥቱም ስለ ፈቀዱላቸው ውሃውን ሄደው እንዲይዙ ወታደሮቻቸውን አዘዙ። 900 የሚሆኑ ወታደሮችም ጨለማን ለብሰው ውሃውን በቀላሉ ያዙ። የውሃውንም መያዝ ጣሊያኖች ያወቁት በነጋታው ነበር፤ ለማስለቀቅም ደጋግመው ቢተኩሱም አልሆነላቸውም። ኢትዮጵያውያኑ በርትተው ተዋግተው መለሷቸው። እቴጌም በየቀኑ ምግብና መጠጥን ለወታደሮቹ ሌሊት ሌሊት ይልኩላቸው ነበር። በምሽጉ በጣም የተማመነው የጣሊያን ጦር አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ወደቀ፤ ከዚያች ዕለት ጀምሮ ውሃ የሚታደለው በራሽን ሆነ። የምሽጉ አዛዥ ጋሊያኖ፣ ወደ ባራቲየሪ ቶሎ እንዲደርስለት ደጋግሞ መልእክት ቢልክም መልስ ማግኘት አልቻለም። ባራቲየሪ መልስ ያልሰጠው አዲግራት ያለውን ምሽጉን ለቆ ከዐጤ ምኒልክ ጦር ለመዋጋት ፍላጎቱም ዐቅሙም ዐጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች, 28 Feb 2013 Page 10 አልነበረውም። ከዚያ ይልቅ ፒየትሮ ፊልተርን ወደ ዐጤ ምኒልክ ሄዶ የመቀሌን ምሽግ ለማስረከብ እንዲደራደር ላከው። 

ፒየትሮ ፊልተርም፣ ዐጤ ምኒሊክ ፊት ቀርቦ፣ የመጣበትን አስረድቶ፣ውይይት ሲካሄድ ቆይቶ በጃንዋሪ 17 ቀን 1896 ዐጤ ምኒሊክ፣ የኢጣሊያ መንግሥት በውጫሌ ውል መሰረዝ ከተስማማ፣ የተከበቡት የጣሊያን ወታደሮች መሔድ እንደሚችሉ ነገሩት፡፡ በመጨረሻም በጃንዋሪ 19 ፒየትሮ ፊልተር የውጫሌ ውልና ድንበርን ግጭቱን አስመልክቶ እንደገና እንደሚታይና፣ጋሊያኖም ምሽጉን አስረክቦ እንዲወጣ፣ ከጄኔራል ባራቲዬሪ መልእክት ይዞ መጥቶ ለዐጤ ምንሊክም  አስረከበ፡፡ ዐጤ ምንሊክም ለመልእክተኛው እኛ አረመኔዎች አይደለንም፡፡ ክርስቲያኖች ነን እንጂ፡፡ እምነታችን ደግሞ ጠላቶቻችንን እንድንወድ ያዘናል፡፡ አሁንም እነዚህ ክርስቲያኖች አይሞቱም ይሂዱ፡፡ ነገር ግን አሁንም ልትወጉን የምትፈልጉ ከሆነ፣ በአንድነት ሆናችሁ ጠብቁኝ በማለት አሰናበቱት፡፡ በማግስቱ በጃንዋሪ 20 ቀን ኢጣሊያኖቹ ምሽጉም ካስረከቡ በኋላ ውሃ እንዲቀዱ ፈቀዱላቸው፡፡ በጅሮንድ ባልቻም በምሽጉ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሰቀሉ፡፡ ጃንዋሪ 21 ቀን ጋሊያኖና ሠራዊቱ ዳርና ዳር ቆሞ በተሰለፈው ወታደር መኃል ዐልፈው ወደ ዐጤ ምኒሊክ ፊት ቀርበው፣ አጅ ከነሱ በኋላ ፣ ከዚያ ወደ አዲግራት ሄዱ፡፡ ይሁን እንጂ የሚደራደር ሰው ከጣሊያኖቹ እስኪመጣ ድረስ 10 ወታደሮች በመያዣነት ታግተው እንዲቆዩ አደረጉ፡፡

ጦሩ አዲግራት ከገባ በኋላ፣ ባራቲዬሪ ሜጀር ሳልሳ ስለ ስምምነቱ ለመነጋገር ለመሄድ ሲነሳ፣ ዐጤ ምንሊክ ዘንድ በመያዣነት የታገቱ ወታደሮች መኖራቸውን ሰማና እንዳይሄድ ከለከለው፡፡ ዐጤ ምንሊክም ስምምነቱን የሚደራደረው የኢጣሊያን ተወካይ እስኪመጣ ድረስ ለ10 ቀናት ከጠበቁ በኋላ፣ ኢጣሊያኖች እንዲህ የዘገዩት ተጨማሪ ጦር ከሀገራቸው እስኪመጣላቸው ጊዜ ለመስጠት ነው የሚል ጥርጣሬ ስለገባቸው ተናደዱ፡፡ በመያዣነት የታገቱት የጣሊያን ወታደሮችም፣ ተደራዳሪው ስለዘገየ፣ካሁን አሁን ገደሉን በማለት በሚጨነቁበት ሰዓት ወደ ራስ መኮንን ተጠሩ፡፡ ራስ መኮንንም ‹‹ በስምምነቱ መሰረት ሜጀር ሳልሳ ስላልመጣ እንድትገደሉ ተፈርዶባችሁ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዐጤ ምንሊክ በአንዱ ጥፋት ሌላው ሊቀጣ አይገባም ብለው የሚያምኑ ንጉሠ ነገሥት በመሆናቸው፣ ወደ ወገኖቻችሁ በሰላም እንድትሄዱ ተፈቅዶላችኋል››

በማለት አሰናበቷቸው፡፡ ለጄኔራል ባራቲየሪ ግን፣ ሜጀር ሳልሳን መላክ ካልፈለገ ፊልተርንም ቢሆን መላክ እንደሚችል፣ ነገር ግን አንዳቸውም ካልመጡ የክርስቲያን ደም መፍሰሱ አይቀርም ብላችሁ ንገሩት ብለው አሰናበቷቸው፡፡

በፌብሩዋሪ 11 ቀን ሜጀር ሳልሳ ከዚህ ሁሉ ሽንፈት በኋላ የማይሆን ጥያቄ ይዞ መጣ። ይኽውም የውጫሌ ውል እንደገና እንዲታደስና የተወሰዱት ቦታዎች ሁሉ እንዲመለሱ የሚል ነበር። ዐጤ ምኒልክም በነገሩ ተገርመው ሜጀር ሳልሳን በመጣበት እግሩ ተመልሶ በአስቸኳይ እንዲሄድ አዘዙት። ባራቲየሪ ልቡ በትዕቢት ተወጥሮ ‹<ካሁን በኋላ ድርድር ብሎ ነገር የለም፡፡ አስፈላጊ መስሎ የታየንን ሁሉ እናደርጋለን ›> ሲል በዛቻ ተናገረ። ይኽን ካለ ከ2 ቀን በኋላ፣ ከራስ መንገሻ ጋር ተጣልተው ወደ ጣሊያን ገብተው የነበሩት ራስ ስብሐት አረጋዊና ደጃዝማች ሐጎስ ተፈሪ 500 ጦራቸው ይዘው ከኢጣሊያ በመክዳት ወደ ዐጤ ምኒልክም መጥተው ተደባለቁ። እነዚህ የጣሊያንን እንቅስቃሴና ምሽግ በሚገባ የሚያውቁ ወታደሮች፣ ከእንጢቾ ወደ አዲግራት ሲጓዝ የነበረውን የጣሊያን ጦር ደመሰሱ። በተጨማሪም የቴሌግራፍ መስመሮችን በመበጣጠስ ሌላም ጥቃት አደረሱ። ቀጥሎም የሀማሴን ገዢ የነበሩት ራስ ወልደ ሚካኤል ሰሎሞን ወደ ዐጤ ምኒልክ በመምጣት ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ተሰለፉ። በፌብሩዋሪ 23 ቀን 1886 የኢትዮጵያ ጦር ወደ ፊት በመጓዝ ወደ አድዋ አካባቢ መጥቶ ሰፈረ። ዐጤ ምኒልክም፣ ጣሊያኖቹ ያሉበት ምሽግ በጣም የተጠናከረና በቀላሉ ሊሰበር እንደማይቻል ስለተረዱ፤ ጣሊያኖቹ ከምሽግ ወጥተው ይገጥሙኛል በማለት መቆየቱን መረጡ።

የዐድዋ ጦርነት (ሦስተኛው ጦርነት ማርች 1 ቀን 1896 )

የኢትዮጵያ ሠራዊት በአድዋ አካባቢ ከሰፈረበት ከፌብሩዋሪ 23 እስከ 28 ጀምሮ፣ ምሽጋቸውን አጠናክረው ሲሠሩ ለጦርነት ዝግጁ ሆኑ። ኢጣሊያኖችን ከምሽጋቸው እንዲወጡ ለማድረግም የፕሮፓጋንዳውን ሥራ ተያያዙት። ይህንን ያደረጉት የኢትዮጵያ ሠራዊት ምግብና አንዳንድ ነገሮችን ፍለጋ ኢጣሊያኖቹ ወደ አሉበት መንደር አካባቢ ሲሄዱ፤ የኢጣሊያኖቹ ሰላዮች በምስጢር ግን የዐጤ ምኒልክ የሆኑት ለጣሊያኑ ጦር አዛዥ ለባራቴየሪ፤ ብዙ ወታደሮች ጦርነቱ ገና ብዙ ጊዜ ይወስዳል እንዲሁም የጣሊያንን ትልልቅ መድፍ ለመቋቋም አንችልም ብለው ፈርተው እየከዱ ወደመጡበት ሀገራቸው እየተመለሱ ነው። የጐጃሙ ንጉሥ ከዐጤ ምኒልክ ተቃቅረዋል ስለዚህ ጦራቸውን ይዘው ወደ ጐጃም ሊመለሱ ነው። እንዲሁም ራስ መኮንን ለማመጽ እየተዘጋጁ ነው። አብዛኛው ሠራዊት አክሱም ጽዮን ለመሳለም ሄዷል የሚል የፈጠራ ወሬ ሪፖርት አቀረቡ። በፌብሩዋሪ 28፤ ጄኔራል ባራቴየሪ፣ ሌሎቹን የጦር ሹማምንቶች ጄኔራሎች፣ አልቤርቶኒን፣ አሪሞንዲን፣ ዳቦርሚዳንና ኤሌናን ስብሰባ ጠራ። ጄኔራል ባራቴየሪም ያላቸው ስንቅ ለ4 ቀን ብቻ የሚበቃ መሆኑን ገልጾ፣ ያለውም አማራጭ ወደ አስመራ ማፈግፈግ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያን ጦር ማጥቃት ነው ሲል ስብሰባውን ጀመረ። አራቱም ጄኔራሎች ወደ አስመራ ማፈግፈግ የሚለውን በአንድ ድምፅ ተቃውመው፣ በኢትዮጵያ ጦር ላይ ዘምተው ጥቃት በመፈጸም፣ አምባላጌና መቀሌ ላይ ዐጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች, 28 Feb 2013 Page 12 የደረሰባቸውን ውርደት ማስወገድ እንዳለባቸው በቁጭት ተናገሩ። ጦርነቱም በማግሥቱ በፌብሩዋሪ 29 ሊያደርጉ ወሰኑ። በአድዋ የኢትዮጵያ ሠራዊት አሰላለፍ እንደሚከተለው ታቀደ። ዐጤ ምኒልክ፣ በአባ ገሪማ ኮረብታ ከቤተ መንግሥቱ የጥበቃ ሠራዊት ጋር ሲሰፍሩ፤ እቴጌ ጣይቱ ደግሞ እዚያው አጠገብ 5 ሺህ የሚሆን ጦራቸውን ከመድፋቸው ጋራ ይዘው ሰፈሩ። ከእቴጌ ጋራ ወ/ሮ ዘውዲቱ ምንሊክና ሌሎች የቤተ መንግሥቱ ሴቶች ነበሩ። እነዚህ በጦርነቱ ሰዓት ውሃ፣ ጥይት በማቀበልና ቁስለኞችን በመንከባከብ የሚረዱ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት 12 ሺህ ጦራቸውን ይዘው በመሄድ፣ በስተቀኝ በኩል አጥቂ ሆነው ተሰለፉ። ራስ መንገሻና ራስ አሉላ፣ 13 ሺህ ጦራቸውን ይዘው ኪዳነ ምሕረት ላይ ሰፈሩ። የራስ መኮንን፣ የራስ ሚካኤል እና የራስ ወሌ ጦር ደግሞ የመኻከሉን ቦታ ያዘ።

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ፌቡሩዋሪ 29 ቀን 1896- የጦርነቱ ዋዜማ

3:00 (9:00 pm) ቅዳሜ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ ጄኔራል ባራቲየሪ ጨለማን ተገን በማድረግ ቁጥሩ 17 ሺህ (10,600 ኢጣሊያኖች እና 7000 ተወላጆችን(አስካሪስ) የሆነውን አራት ብርጌድ ጦር ይዞ፣ አድዋ ላይ የሰፈረውን የኢትዮጵያን ጦር ለመውጋት ጉዞ ጀመረ። የጉዞውም ዕቅድ፣ አራቱ ብርጌዶች በተለያየ አቅጣጫ ተጉዞው፣ እተመደበላቸው ቦታ ላይ ከመንጋቱ በፊት እንዲደርሱና፣ የኢትዮጵያን ጦር ከከፍታ ቦታ ላይ ሆነው ከበው እንዲያጠቁ ነበር። ይሁን እንጂ፣ በዚያ ጭለማ የያዙት ካርታ ትክክል ስላልነበር፣ በተጨማሪም ጦሩን የሚመሩት በርካታ ኤርትራውያን ( የአውአሎም ገድል እዚች ላይ አንጸባራቂ ኮከብ ሆኖ ዝንተዓለም ኖራል፡፤)በምሥጢር የሚሠሩት ለዐጤ ምኒልክ ስለነበር፣ ጉዞአቸው አስቸጋሪ ነበር። 8:30 (2:30 am) በጄኔራል ባራቲየሪና በጄኔራል ጁሴፔ ኤሌና የሚመሩት ብርጌዶች በ8:30 ሰዓት ላይ እሻሾ ተራራ ደረሰ። ሁለቱ ብርጌዶች በታዘዙት መሠረት በጄኔራል አልቤርቶኒ የሚመራው ጦር በስተግራ ታጥፎ፣ ወደ ኪዳነ ምሕረት ሲሄድ፤ የጄኔራል ዳቦርሚዳ ብርጌድ ጦር በቀኝ በኩል አልፎ ከፍ ያለውን ገዥ መሬት (ኮረብታ) ለመያዝ ጉዞውን ሲቀጥል፣ ጄኔራል አሪሞንዲ መሐሉን ይዞ ተጓዘ። 10:00 (4:00 am) ጄኔራል አልቤርቶኒ እንደታዘዘው፣ ጦሩን እየመራ ኪዳነ ምሕረት ደረስኩ ብሎ ሲያስብ፣ አሳሳች መንገድ መሪዎቹ ኤርትራውያን (ለዐጤ ምኒልክ በምስጢር የሚሠሩ)፣ ኪዳነ ምሕረት ገና አልደረስንም ገና ብዙ መንገድ ይቀረናል በማለት ሌላ 4.5 ማይልስ ጉዞ ወደፊት ቀጠሉ። 2.5 ማይልስ እንደተጓዙ፣ በራስ አሉላ ከሚመራው ጦር ጋር ተገናኙ። እንግዲህ የመጀመሪያው ተኩስ ልውውጥ በዚህ ቦታ ላይ ተጀመረ። ሌሎቹም ብርጌዶች በየታዘዙበት አቅጣጫ ቢጓዙም፣ በዚያ ባልለመዱት ምድር የተጓዙት ጊዜው ያለፈበት ካርታ በመጠቀማቸውና፣ የአሳሳች መሪዎቻቸውን ኤርትራውያን ቃል አምነው፣ እንደታሰበው ተቀራርበው ሳይሆን የሠፈሩት፤ በጣም ተራርቅው ነበር። ዐጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች, 28 Feb 2013 Page 13 በዚያች ሌሊት፣ ኢጣሊያኖችቹ ወጣ ገባውን መንገድ በድቅድቅ ጨለማ ሲጓዙ፣ ዐጤ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ንጉሥ ተ/ሃይማኖት እንዲሁም ሌሎች ራሶች፣ አድዋ በሚገኘው በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ነበሩ። አንዳንድ ጸሐፊዎች፣ ዐጤ ምኒልክ በዚያች ሰዓት ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን በድንኳናቸው ውስጥ ነበሩ ብለው ጽፈዋል። የሆኖ ሆኖ መልእክተኛ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ ጠላት መምጣቱንና ጦርነት መጀመሩን ተናገረ። አቡኑም ከቤተ መቅደሱ ወጥተው፣ <ልጆቼ ሆይ፣ ዛሬ የእግዜአብሔር ፍርድ የሚገለጥበት ቀን ነው > ብለው አሳረጉ። መኳንንቱም እየቀረበ መስቀል እየተሳለመ ወደ ጦር ግንባር ሄደ። 11:30 (5:30 am) የሸዋ ፈረሰኛ ጦር ወደ ንጉሠ ነገሥቱ መጥቶ፣ የፈረንጅ ጦር፣ አባ ገሪማ፣ ላይ መታየቱን አስታወቀ። ከዚያም ዐጤ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ እና ፈረሰኛው ጦር ወደ አባ ገሪማ ሄዱ። 12:00 (6:00 am) የዐጤ ምኒልክ ቃፊሮች(ወታደሮች)፣የጠላትን እንቅስቃሴ በየአቅጣጫው እየተከታተሉ ለዐጤ ምኒልክ እያሳወቁ፣ ቦታቸው ላይ በተጠንቀቅ ሆነው የጠላትን ጦር ይጠብቁ ነበር። አልቤርቶኒም 4500 ጦሩን እየመራ ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ኪዳነ ምሕረት ደረሰ። 12:10 (6:10 am) አልቤርቶኒ ከሚመራው ጦር፣ የተወሰነው አቅጣጫውን ለውጦ ሲጓዝ፣ በቀጥታ በንጉሥ ተ/ሃይማኖት የሚመራው ጦር እሰፈረበትና፣ ከባድ መሣሪያ ጠምደው እሚጠብቁበት ቦታ ገቡ። ያን ጊዜ ከባዱ ጦርነት ፈነዳ። 12:15 (6:15 am) በእሻሾ ተራራ ላይ ተጠባባቂ ጦሩን የያዘው ዋናው አዛዥ ጄኔራል ባራቲየሪ፣ የአልቤርቶኒ ጦር የት እንዳለ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከ። 1:45 (7:15 am) ባራቲየሪ ካገኘው መረጃ በመነሳት፣ በአልቤርቶኒ እና በአሪሞንዲ ብርጌዶች መኻከል ያለው ቦታ ሩቅ መሆኑን ለማወቅ ቻለ። በዚህ ጊዜ ባራቲየሪም፣ ዳቦርሚዳ ወደ ግራ ታጥፎ፣ መኻል ያላውን ጦር በስተግራው ሆኖ እንዲረዳው አዘዘ። ይሁን እንጂ፣ ዳቦርሚዳ ባልታወቀ ምክንያት፣ የታዘዘውን ትቶ ፣ በተቃራኒው ወደ ቀኝ ታጥፎ ወደ ማርያም ሸዊቶ በማቅናት፣ ከሌላው ተለይቶ በጣም ርቆ ሄደ። (ምናልባት መልእክተኛው የንጉሡ ድርብ ሰላይ ይሆን?) በዚህ ጊዜ፣ የራስ መኮንንና የራስ አሉላ ጥምር ጦር፣ አጋጣሚውን በመጠቀም፣ ይህን ተነጥሎ ለብቻው የመጣውን ጦር፣ በገላጣው ሜዳ ላይ ሊወጋው ወጣ። ዐጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች, 28 Feb 2013 Page 14 ከንጉሥ ተ/ሃይማኖት ሠራዊት ጋር ጦርነት የገጠመው አልቤርቶኒ፣ ጠንክሮ መዋጋቱን ያዩት እቴጌ ጣይቱና ራስ መንገሻ፣ ዐጤ ምኒልክን፣ ምርጥና ጠንካራ የሆነውን 25 ሺህ የቤተ መንግሥቱን ጦር እንዲልኩና ኢጣሊያኖቹን እንዲወጉ አሳሰብዋቸው። 2:15 (8:15 am) አልቤርቶኒ በአስቸኳይ ተጨማሪ ጦር እንዲላክለት፣ መልእክተኛ ወደ ባራቲየሪ ላከ። 2:30 (8:30 am) በዐጤ ምኒልክ 25 ሺህ ጦር ላይ፣ እቴጌ ጣይቱ 3 ሺህ ተጨምሮበት በድምሩ 28ሺህ፣ አልቤርቶኒን እንዲያጠቃ ተላከ። 3:00 (9:00 am) የቤተ መንግሥቱ ምርጥ ወታደሮች፣ ከመላው የኢትዮጵያ ሠራዊት በጀግንነት የታወቁና የተፈሩ ነበሩ። አልቤርቶኒን ማጥቃት በጀመሩ በግማሽ ሰዓት ውስጥ፣ ምሽጉን ሰብረው ገብተው፣ ጄኔራሉን ራሱን ማረኩት። የተረፈውም ጦር ወደ ኋላ እግሬ አውጭኝ ብሎ ሸመጠጠ። 2 ማይልስ ላይ ርቀት ላይ እየተዋጋ ወዳለው ወደ አሪሞንዲ ተፈተለከ። አሪሞንዲ ጠንክሮ በውጊያ ላይ እያለ፣ ከተደመሰሰው የአልቤርቶኒ ጦር ተርፈው የሚሸሹትን ወታደሮች የሚከታተለው የዐጤ ምኒልክ ምርጥ ጦር ደርሶ ማጥቃት ሲጀምር፤ አሪሞንዲ ሊቋቋመው አልቻለም። 3:15 (9:15 am) እንደ ማዕበል እየጐረፈ የመጣው የኢትዮጵያ ጦር፣ በመጨረሻ የአርሞንዲን የሰፈረበት ቦታ ላይ ወጥቶ በጨበጣ ውጊያ ተያያዘው። ባራቲየሪ ተጠባባቂ ጦሩን ይዞ ወደ ጦርነቱ ቦታ ሲደርስ፣ ከአሪሞንዲ በስተቀረ ሌላ የሚዋጋ ጦር አልነበረም። በርቀት የአልቤርቶኒ ወታደሮች ሬሳ ምድሩን ሞልቶታል። እንዲሁም ቅጥረኛ ወታደሮቹ ወደ ታች ሲሮጡ ተመለከተ። ዳቦርሚዳ ግን የት እንደገባ ማወቅ አልቻለም። 4:00 (10:00 am) የራስ መንገሻና የራስ ሚካኤል ጦር፣ ከሌላ አቅጣጫ ሆኖ፣ የአርሞንዲን ጦር ማጥቃት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ የአርሞንዲ ወታደሮች ከነመሪያቸው ጭምር ተገደሉ። በስተግራም በኩል፣ ኮሎኔል ጋሊያኖ የሚመራው ጦር፣ የዐጤ ምኒልክ ልዩ ጦር ከደረሰበት በኋላ፣ በትንሽ ደቂቃ ውስጥ ብትንትኑ ወጣ። ጋሊያኖም ከነወታደሩ እንዳለ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ፤ ለወሬ ነጋሪ እንኳ የተረፈ ሰው አልነበረም። ዐጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች, 28 Feb 2013 Page 15 5:30 (11:30 am) ባራቲየሪ ይዟቸው የመጣው ተጠባባቂ ብርጌዶች፣ ከጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ጋር ጦርነቱን ቀጠሉ። ይሁን እንጂ፣ ቆራጦቹን የኢትዮጵያ ጀግኖች መቋቋም አልቻለም፤ ብዙ ኢጣሊያኖች ክፉኛ እየተመቱ መውደቅ ጀመሩ። ባራቲየሪም ሽንፈቱን ስላወቀ፣ የቀረውን ወታደር ማስጨረስ አልፈለገም። የተረፈውን ጦር ይዞ ወደ አዲግራት ፈረጠጠ። አንዳንዶቹማ ጠረፍ እስኪደርሱ ድረስ ለዐፍታ እንኳ አልቆሙም ነበር። 8:00 (2:00 pm) በዚህ ጊዜ የዳቦርሚዳ ጦር ማርያም ሸዊቶ ላይ፣ ባለፈው 4 ሰዓት፣ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር በጦርነት እንደተጠመደ ነው። እስካሁን ከባራቲየሪ ምንም ነገር ስላልሰማ፣ተጨማሪም ጦር ስላልመጣለት፣ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩን ተገነዘበ። ስለዚህ፣ ቀስ በቀስ እየተዋጋ ወደ ሰሜን ለማፈግፈግ ወሰነ። 9:00 (3:00 pm) ይህ ሁሉ ሲሆን ጠቅላላ የጦርነቱን ዜና ዐጤ ምኒልክ ይደርሳቸዋል። ዐጤ ምኒልክ፣ ሌሎቹ ብርጌዶች ድምጥማጣቸው መጥፋቱን እንዳወቁ፣ መጨረሻ ላይ ብቻውን የቀረውን የዳቦርሚዳ ጦር፣ አንድም እንዳያመልጥ፣ የራስ ሚካኤልና በግራ ክንፍ በኩል የሚዋጋው 20 ሺህ ጦርና 8ሺህ ፈረሰኛ ወደዚያ ሄዶ እንዲወጋ አዘዙ። ዳቦርሚዳም ጦሩን ይዞ በጠባቡ ሸለቆ ውስጥ ማፈግፈግ ሲጀምር፤ ፈረሰኛው ጦር ደርሶ እያራወጠ ይወጋው ጀመር። ግማሽ ሰዓት ባላሞላ ጊዜ ውስጥ ዳቦርሚዳም ከ4500 ጦሩ ጋራ በዚያ ቦታ ወደቁ። እስከ ምሽቱም ድረስ የቀሩትን የኢጣሊያ ወታደሮች እያሳደዱ፣ እየገደሉና እየማረኩ ቆዩ። ሲመሻሽም ፣ዐጤ ምኒልክ ከአምባ ገሪማ ወደ አድዋ ተመለሱ። ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ውጊያ እንዲቆም፤ ጠላትንም መማረክ እንጂ እንዳይገደል ሲሉ አዘዙ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሽለላ፣ፉከራ፣የድል ዘፈን፣እልልታ ማስተጋባት ጀመረ፡፡ ዐጤ ምንሊክም፣ በዛሬው ቀን፣በዚህ ጦር ሜዳ ተዋግተው የወደቁት ሰዎች ናቸውና፣ ዘፈኑ ሆነ ሽለላውን ወዲያው እንዲቆም አዘዙ፡፡ ዐጤ ምንሊክም፣ ለክብራቸው ተዘርግቶ የነበረውን ቀይ ዣንጥላ ታጥፎ በምትኩ ጥቁር ዣንጥላ እንዲዘረጋ አዘዙ፡፡ ከባድ ዝናብም ጣለ፡፡ እቴጌም ለሀገራቸው ክብር የወደቁትን ጀግኖች ስም ሲነገራቸው እንባቸውን ያፈሱ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነት ቢጠናቀቅም መኳንንቱና ሠራዊቱ በዚያች ቀን ጀንበር ሳትጠልቅ በጦርነቱ ላይ የወደቁትን፣ በሺኅ የሚቆጠሩ ወገኖቻቸውን እያሰቡ በኀዘን ተውጠው ነበር፡፡

የአድዋ ጦርነት በታላቁ ዐጤ ምኒልክ መሪነት፣ ኢትዮጵያውያኑ አንድ የሰለጠነን የአውሮጳ ጦር ዐጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች, 28 Feb 2013 Page 16 በማሸነፍ ተጠናቀቀ። በዚህ ጦርነት 13,300 ኢጣሊያኖች ሲሞቱ 700 ተማርከዋል። ከእነዚህም ውስጥ ጦርነቱን የመሩት 2 ጄኔራሎች አሪሞንዲና ዳቦርሚዳ ሲገደሉ፤ ጄኔራል አልቤርቶኒ ደግሞ ተማርኳል። በኢትዮጵያውያን በኩል 20,000 ሲወድቁ ፣ 7000 ደግሞ ቆስለዋል።

ዐጤ ምኒልክም ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ የሞቱትን ጀግኖች ሬሣ ሲያስቀብሩ፣ ሀገር እያረጋጉ ሰነበቱ። ቀጥሎም፣ ለአውሮጳ መንግሥታት፣ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ራሷን የቻለች ነፃ ሀገር መሆኗን ገልጠው፣ ለአድዋ ጦርነት መነሻ የሆነውን ምክንያት በመዘርዘርና፣ ከዚያም ኢጣሊያ በጦር ኀይል አስገብራለው ብላ የብዙ ክርስቲያኖች ደም እንዲፈስ ማድረጓን፤ ነገር ግን ከጥንት ጀምሮ ሀገራችንን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ስላልተለየን ድል ማድረጋቸውን የሚገልጥ ደብዳቤ፣ በኤፕሪል 2 ቀን 1896 ዓም ላኩላቸው። እንዲሁም በዚያው በተመሳሳይ ወቅት፣ ለሙሴ ሽፍኔ እንዲህ ሲሉ ጻፉለት፣ << በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ። እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኋቸው ብዬ ደስ አይለኝም >>። ከአድዋ ድል በኋላ በጄኔራል ባልዲሴራ የሚመራ አዲስ 15 ሺህ ጦር ከኢጣሊያ ተነስቶ ምፅዋ ገባ። ከዚያም ለዐጤ ምኒልክ ዕርቅ እንፈጽም፣ እስረኞቹም ይለቀቁ ብሎ ደጋግሞ ጠይቆ ነበር። ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ ከመቀሌ ምሽግ በሰላም እንዲወጡ ሲደረግ፣ ዋናው ምክኒያቱ የውጫሌን ውል ይሻሻላል በሚል እምነትና ተስፋ ነበር። ነገር ግን ነፃ ከወጡ በኋላ፣ ኢጣሊያኖቹ ቃላቸውን አጥፈው ለብዙ ሰው ሕይወት መጥፋት ምክኒያት መሆናቸውን የታወቀ ነበር። አሁንም የኢጣሊያኖቹ ዓላማ፣ እስረኞቹን አስፈትቶ፣ እንደገና አዲስ በመጣው ጦር ለመውረር እንዳሰቡ ዐጤ ምኒልክ ዐውቀዋል። ስለዚህ ኢጣሊያኖቹም በቃላቸው የሚታመኑ ስላልሆኑ፣ የውጫሌ ውል መፍረሱን ለዓለም መንግሥታት ካላሳወቃችሁ፣ እስረኞቹን አልፈታም በማለት ዐጤ ምኒልክ እምቢ አሉ።

በመጨረሻም የተማረኩትን የኢጣሊያን ምርኮኞች እና ብዙ መሣሪያዎች ይዞ ወደ መናገሻ ከተማቸው ለመሔድ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቀቀ፡፡

ዐጤ ምንሊክ አዲስ አበባ ስለመግባታቸው

ዐጤ ምኒልክም መናገሻ ከተማቸውን በለቀቁ፤ በስምንተኛ ወር በጁን 12 ቀን 1896፤ በድል አድራጊነት ጦራቸውንና፣ የተማረኩትን የኢጣሊያ ወታደሮች እየመሩ፤ እንጦጦ ገቡ። ሕዝቡም፣ ንጉሡ እና ሠራዊቱ በደህና መመለሳቸውን፣ በእልልታ፣ በጭፈራ፣ በጭብጨባ እና በሽለላ ወጥቶ ሲቀበላቸው፤ ካህናቱ ደግሞ ዝማሬያቸውን ያሰሙ ነበር። የኢጣሊያ መንግሥት፣ የኢትዮጵያን ጦር እንዲወጋበት ተልኮ አድዋ ላይ የተማረኩት መድፎችም፣ በዕለቱ፣ ለበዓሉ ክብር መቶ ጊዜ እንዲተኩሱ ተደርገዋል። ከበዓሉም ፍጻሜ በኋላ፣ ተማርከው የመጡት የኢጣሊያ ወታደሮች፣ በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መንግሥት መካከል ስምምነት ተደርሶ እስኪመለሱ ድረስ፣ የተለያዩ ባላባቶች በኃላፊነት እንዲጠብቋቸው ተሰጡ። እነዚህንም እስረኞች ለማስፈታት የኢጣሊያ መንግሥት መልእክተኞች ደጋግሞ ቢልክም፤ ቀደም ብለው ለጄኔራል ባልዲሴራ የሰጡትን መልስ ሰጡ። በዚህ መኻል የሮማው ፖፕ ሊዎን 13ኛ፣ በጁን 11 ቀን 1896፣ እስረኞቹ እንዲፈቱ የሚማፀን ደብዳቤ ለዐጤ ምኒልክም ላኩ። ዐጤ ምኒልክና ኢጣሊያኖች, 28 Feb 2013 Page 17 ዐጤ ምኒልክም በኦክቶበር 3 ቀን 1896፣ ለሮማው ፖፕ፣ የጻፉት ደብዳቤ እንደደረሳቸውና፣ ስለክብራቸው ሲሉ እስረኞቹን ሊፈቱ አስበው እንደነበር፤ ነገር ግን እነዚያ በጦር ሜዳ የወደቁትን የኢትዮጵያ ልጆች ሲያስቡ፤ እስረኞቹን መልቀቅ የማይቻላቸው እንደሆነ ገለጹ። ይሁን እንጂ እስረኞቹ እዚህ በሚቆዩበት ጊዜ ምንም ሳይጓደልባቸው ተንከባክቤ ይዛቸዋለው በማለት መልስ ሰጡ። ነገር ግን አንድ ተራ ምርኮኛ ወታደር እናቱ የጻፈችለትን ደብዳቤ አንብቦ፣ በጣም እያለቀሰ ማስቸገሩን ምኒልክ ሰምተው፣ እስረኛው እንዲመጣ አድርገው ደብዳቤው እንዲነበብ አደረጉ። የእስረኛው እናትም በደብዳቤዋ ላይ <‹ ልጄ ሞተሃል ብለውኝ ተስፋ ብቆርጥ እንደ ሌሎች እናቶች ሁሉ አልቀሼ ይወጣልኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ቀንም ለሊትም ላንተ ለልጄ እንዳለቀስሁ ነኝ፡፡ ምንም ቦታ ወድቀህ እንደሆነ አላይህም፡፡ ከአፌ እየነጠልሁ ያለችኝን ደህና ምግብ እያበላሁ ያሳደግሁህ ልጄ ዛሬ የምትበላውን አላውቅም…….ልጄ እንደምወድህ ታውቃለህ፡፡ የማምነው አምላክ በሰላም ያገናኘናል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡ ልጄ በሕይወት መጥተህልኝ ዓይንህን እስካይ ድረስም ውሎዬ ከቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነው። … ለቤተ ክርስቲያኗም በየቀኑ አንዳንድ ሻማ ስለት ተስዬ በየቀኑ እያበራሁ ላንተ ለልጄ እየተንበረከክሁ እፀልያለሁ። … በጸሎቴ ብርታት ተለቀህ እንደምትመጣ ተስፋ አለኝና፤ አንተም ባለህበት ጸልይ። … የምወድህ ልጄ፤ አይዞህ በርትተህ ኑር … አንተም እንደምትናፍቀኝ አውቃለሁ። ለቅሶዬ ባክኖ አይቀርምና እንገናኛለን >> የሚል ነበር።

ርኁሩኅ እምዬ ምንሊክም ደብዳቤውን ካዳመጡ በኋላ፣አዝነውና አልቅሰው ‹‹ ሂድ በነጻ አሰናብቸሃለሁ፣ የእናትህ እንባ አማለደህ ›› ብለው በበቅሎ አድርገው አስመራ ድረስ አሸኝተው ሰደዱት፡፡(1)

የኢጣሊያ መንግሥትም፣ ዐጤ ምኒልክ አዲስ ውል ተፈርሞ የውጫሌ ውል እስካልተሻረ ድረስ፣ እስረኞቹን እንደማይፈቱ ስላወቁ፣ በመጨረሻ በኦገስት 23 ቀን 1896 የውጫሌ ውል መፍረሱንና ኢትዮጵያ ራሷን የቻለች ነፃ ሀገር መሆኗን አረጋግጣለሁ አለ። በኦክቶበር 26 ቀን 1896 ዘጠኝ ክፍል ያለው ሰነድ፤ ዐጤ ምኒልክ በፈለጉት ዓይነት ተዘጋጅቶ፣ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ተፈረመ። በተጨማሪም ኢጣሊያኖች 10 ሚሊዮን ሊራ ካሳ ለኢትዮጵያ እንዲከፍል ተደረገ።

 የአድዋ ድል አርአያነት አንድ የጥቁር ሀገር፣ በዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀን የአውሮጳን ጦር ማሸነፉ ዓለምን ያስገረመና የኢትዮጵያን ዝና ከፍ ያደረገ፣ ነገር ግን ኢጣሊያንን ያሳፈረ ነበር። ይህ የአድዋ ድል በተለይ ደግሞ በባርነት ሥርዓት ሲገዙና ሲጨቆኑ የነበሩ ሕዝቦች፣ እነሱም ከተባበሩና ከተደራጁ፣ ወራሪዎችንም ማሸነፍ እንደሚችሉ የተስፋ ጭላንጭል በሕሊናቸው እንዲፈነጥቅ ምክንያት ሆነ። ከዚህ ባሻግር ምንሊክ ለሰብዓዊ መብት መከበር፣ ስለ ዜግነት ክብር ያስተማሩ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ሌሎች የጥቁር ህዝቦች የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር እንደሚችሉ ፋና ወጊ ንጉስ ነበሩ፡፡

 በርከክ በርከክ አሉ አውሬ መስያቸው፤

ከሰው መፈጠሬን ማን በነገራቸው፡፡

በማለት የኢትዮጵያ ህዝብ የሰውነት ክብር በፋሺስት ጣሊያኖች እንዳይደፈር፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በማስተባበር ወርቃማ ታሪክ ያጻፉ ታላቅ ንጉስ ነበሩ፡፡ አጼ ምንሊክ፡፡

እንደ መደምደሚያ

ምኒልክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ፣ እንዲሉ ዳግማዊ ንጉሠ ነገሥት ምንሊክ የሚከበሩ መሪ እንጂ የሚወቀሱ አይደሉም፡፡ ይህ ማለት ግን ምሉሄ በክሉሄ ፍጹም ነበሩ ማለቴ አይደለም፡፡ ጋሪባልዲ በጣሊያን፣ ቢስማርክ በጀርመን፣ የታሪክ የክብር ስፍራ እንዳላቸው ሁሉ፣ እምዬ ምንሊክ በኢትዮጵያ ታሪክ ያላቸውን የክብር ስፍራ ማንም አይነጥቃቸውም፡፡ የኔልሶን ማንደላን ለቅሶና ቀብር ሳይ በጣም ተገረምሁ ብቻ ሳይሆን እፍሪቃዊ መሆኑ ራሱ አኰራኝ። ከዚህም ተነሥቼ፣ታሪክን ወደኋላ መለስ ብዬ በኅሊናዬ መስተዋት ቃኝቼ ሳበቃ፣ ጊዜው እንደዛሬ ሁኖ ቢያመችለት ኖሮ፣ እንደሳቸው ሊለቀስ የሚገባ ሰው በአፍሪቃ ምድር ከዚህ በፊት ታይቶ አይታወቅምን ብዬ ራሴን በራሴ ደጋግሜ ጠየቅሁ። ማንዴላ የሚደነቁት፣ በቀለሙ በመጀነንና፥ በዘመናዊ መሣርያው በመተማመን፣ በበላይነት ረግጬው ልግዛው ብሎ፣ ለብዙ ዘመናት በሥልጣን ላይ ሁኖ ያሠቃይ የነበረውን ጨቋኙን የነጮች ግዛት ከነሥርዐቱ አሸንፈው፣ ለሀገራቸው ጥቊር ሕዝብ የድል ዋንጫ አጐናፅፈው፣ ነፃነቱንና ክብሩን ስለመለሱለት ነው። ግፈኞቹን የድሮ ጠላቶቻቸውንም እንደመበቀል ፈንታ በፍቅር ያዟቸው። ሁሉም የደቡብ አፍሪቃ ዜጋ በጐሣና በዘር፤ በሃይማኖትና በቀለም ሳይለያይና ሳይከፋፈል፣ ታዲያ በመቻቻል፣ ባንድነትና በፍቅር ተቀራርቦ እንዳንድ ሀገር ሕዝብ እንዲኖር አደረጉ። ለኻያ ሰባት ዓመታት በእስራት ራሳቸውን በመሠዋት፣ ጠላታቸውን በማሸነፍ፣ ራሳቸውንና ሀገራቸውን ያኰሩ ደግና ብልህ መሪ፣ ሰውን በማንነቱና በእምነቱ ሳይሆን በሙያውና በችሎታው የሚፈርጁ፤ ጠላትን እንኳ የሚራሩና የሚወዱ ሰው ነበሩ። ይኸንን በዐይነ ኅሊናዬ መላልሼ ካሰላሰልሁ በኋላ፣ የዓለምን ታሪክ ደግሞ ቃኝቼ ሳበቃ አንድ እጅግ በጣም ታላቅ ሰው አገኘሁ። አፄ ምኒልክ። አፄ ምኒልክ በሠሩት ሥራ፣ ባሳዩት ብልሃትና ደግነት፣ ከኔልሶን ማንዴላ በምንም መልክና ሚዛን ይበልጣሉ እንጂ፣ ያንሳሉ ብዬ አልገምትም። በኔ ብቻ ሳይሆን በብዙ አፍሪቃውያንና የዓለም ምሁራን አስተያየት በጣም ይበልጧቸዋል። ኔልሶን የጥቊሮችን እኩልነት በአገራቸው ከማስከበር ውጭ በሌላው ዘርፍ ብዙ አልገፉበትም። የደቡብ አፍሪቃ ጥቁር ሕዝብ በነጮች የተወረሰውን ሀብት በፍጹም መልሶ አላገኘም። ነጮቹ አሁንም እንደድሮው በቊጥራቸው የአገሩ ሕዝብ ከመቶ ዐሥሩ እጅ እያሉ፣ ግን ከመቶው ሰማንያ እጅ በላይ የሚሆነዉን የሀገሩን ሀብት እየተቈጣጠሩ ናቸው። ይኸ የማይካድ ሐቅ ነው። ከሁሉም የባሰ ደግሞ ያገራቸው ጥቁሮች በመጨረሻ ላይ ድል-ቢያደርጉም፣ በነጭ ተሸንፈው መገዛታቸው ራሱ በመንፈሳቸዉና በታሪካቸው ውስጥ የማይሽር አሳዛኝ ጠባሳ Page 2 of 47 ትቶባቸዋል። ስለዚህም እንደሌሎቹ ለአውሮጳውያን ቅኝ አገዛዝ እንደተዳረጉ ሕዝቦች ሁሉ የዝቅተኝነትና የውርደት ስሜት በየሄዱበት እንደማይለያቸው ግልጥ ነው። የአፄ ምኒልክ ሥራ ይኸንን ሁሉ ለኢትዮጵያውያን አስወግዶላቸው፣ ከፍተኛ በራስ የመተማመንና ከማንም (ፈረንጅም ጭምር) አላንስ ባይነትን፣ የልዕልናንና የኩራትን ስሜት እመንፈሳቸው ውስጥ ቀርጿል። ጆን ቦየስ የተባለ ጸሓፊ፣ የምሥራቅ አፍሪቃን የእንግሊዝ ግዛቶች ዙሮ ካየ በኋላ፣ ከኢጣልያን ወረራ በፊት ወደአዲስ አበባ ሲደርስ እጅግ የገረመው ነገር ቢኖር፣ ለመጀመርያ ጊዜ “አንድ አፍሪቃዊ ነጮችን እያዘዘ ቤት ማሠራቱን ማየቱና”፣ ኢትዮጵያውያን ፈረንጆችን “ባሮች እያሉ ሲጠሩዋቸው” መስማቱ ነበር። እንዲሁም ኢጣልያ ሀገሩን ለሁለተኛ ጊዜ ሲትወርር ወደኬንያ የሸሹትን የኢትዮጵያን ሰደተኞች፣ ቅኝ ገዢዎቹ እንግሊዞች፣ በተለመደው በዘር ተፋሰስ ድርድራቸው መሠረት፣ ከዕርከኑ ሥር ከነበሩት ከሌሎቹ አፍሪቃዉያን ቢያስቀምጧቸው፣ ከፍተኛ ትርምስ ፈጠሩ። እንግሊዞች “ኢትዮጵያዉያን” የሚል ሌላ ከሌሎቹ አፍሪቃዉያን ከፍ ያለ ዕርከን ሲፈጥሩ ብቻ ነው ሰላምና ሥርዐት የሰፈነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቢያውቅም ባያውቅም በገዛ ራሱ የመተማመንና የመንፈሳዊ ኩራት አለው ብል አልሳሳትም። ይኸም የአፄ ምኒልክ የሥራ ውጤት ነውና ሁሌዬ ልመሰገኑ ይገባቸዋል። ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ለሳቸው ተከፍሎ የማይዘለቅ ከፍተኛ ውለታ አለበት። አፄ ምኒልክ ኔልሶን ማንዴላን ይብለጡ እንጂ በብዙ መልክ ግን እንደሳቸው የታደሉ አልነበሩም። ማንዴላ የወረሱት በዘመናዊ መልኩ የተዋቀረ፣ አንድነቱ የጠነከረ፣ በሥልጣኔ የዳበረ፣ በዓለም መንግሥታት የታወቀ፤ ዳሩና ድንበሩ የማይደፈር መንግሥት ነው። ምኒልክ ግን ይኸ ዕድል አልገጠማቸውም ብቻ ሳይሆን፣ መልሰው ያዋሀዱት የኢትዮጵያ መንግሥት ጥንታዊነትና አስደናቂ ታሪክ ቢኖረውም፣ ፈርሶ በመገነባት ላይ ያለ ነበር። ለግንባታው አፄ ቴዎድሮስ መሠረቱን ጣሉ። አፄ ዮሐንስ ደግሞ ተመልሶ ከመፍረስ አዳኑት እንጂ ለግንባታው ጊዜና ዕድል ግን አላገኙለትም። እንግዴ አሁን የምንኖርባት  በዘመናዊ መልኩ የተዋሀደችው የኢትዮጵያ ጥንታዊና አኲሪ ታሪኳ እንደተጠበቀ ሁኖ፣ በአብዛኛው የአፄ ምኒልክ እጅ ፍጡር ናት ማለት ይቻላል።

    ምንሊክ ተነስቶ ባያነሳ ጋሻ፤

    ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ግዜ አበሻ፡፡

  ዋቢ ጽሁፍ

     1.ጳውሎስ ኞኞ ( ዐጤ ምኒሊክ)

  1. ተክለጻድቅ መኩሪያ ( ምንሊክ እና የኢትዮጵያ አንድነት፣ አጼ ዮሃንስና የኢትዮጵያ አንድነት)
  2. አቶ በሪሁን ( የአጼ ሐይለሥላሴ ታሪክ)
  3. የፕሮፌሰር ሐይሌ ላሬቦ ጥናታዊ ጽሁፍ
Filed in: Amharic